Thursday 11 December 2014

የመናኙ ሰው ዕድል ፈንታው ክርስቶስ ሆነ Part Two



የመናኙ ሰው ዕድል ፈንታው ክርስቶስ ሆነ

Part  Two




የተወደዳችሁ ወገኖች የአባ ዘውዱ ኪዳኑን ምስክርነት ክፍል አንድ ማቅረቤ ይታወሳል ክፍል ሁለትን ደግሞ እንደሚከተለው አቀርበዋለሁና ተከታተሉ አባ ዘውዱ ኪዳኑ ለከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ መጽሔት አዘጋጅ ስለተነሳበት መንፈሳዊ ይዘት ሲያጫውት በደብረ ብርሃን ጊዮርጊስ እንደነበረና ከዚያም በዝዋይ አቡነ ጎርጎርዮስ ዘንድ ሄዶ ከሳቸው  ሰፊ የሆነ መንፈሳዊ ትምህርት እንደቀሰመ ከዚያም የአውራጃ ሰባኪ እንዲሆን ጥርጊያ መንገዱን ጳጳሱ ያመቻቹለት እንደነበር ተርኳል ነገር ግን ስብከቱን አጥብቆ ቢወደውም ለነፍሱ እረፍት ባለማግኘቱ ምክንያት ወደ ገዳም እንዳመራ ይናገራል

ከሣቴ ብርሃን ፦በገዳም የነበርዎት ቆይታ ምን እንደሚመስል ቢነግሩን ?

አባ ዘውዱ፦  በገዳም ሕይወቴ በመጀመርያ ለመናንያኑ ውሃ እየቀዳሁና እግዚአብሔርን በጽሞና ሆኜ በመፈለግ ተጠምጄ ሳለሁ ውስጤ « ይህ ያንተ ቦታ አይደለም አንተ ወንጌል ሰባኪ እንጂ ባህታዊነት አይደለም » ሲለኝ ተመልሼ ወደ ከተማ እመጣለሁ ከተማ ሦስትና አራት ወር የቆየሁ እንደሆነ ደግሞ « አንተ ብሎ ክርስቲያን አንተ እዚህ ዘኬህን እየበላህና ጠላህን እየጠጣህ ጽድቅን ትመኛለህ ? መነኮሳቱ ግን አንጀታቸውን አስረው ራሳቸውን እያሰቃዩ ይኖራሉ » ሲለኝ ጓዜን ሸክፌ ስሜቴ ሂድ ወዳለኝ አቀናለሁ ዝቋላ አቦ ፣ አሰቦት ሥላሴ ፣ ዋልድባ ያልሄድኩበት ገዳም የለም አስራ ሰባት ዓመታት ያሳለፍኩትም በዚህ ሁኔታ ነው በመጀመርያ ግን የሄድኩበት ገዳም ዝቋላ አቦ ነው በወቅቱ ከተማ ቀመስ ስለነበርኩ በሬ ጠምጄ ማረስ ባልችልም በዶማ እቆፍር ነበር መሬቱን የምቆፍረው እጆቼ እስከሚደሙና እስከሚላላጡ ድረስ ነው ከከሳሼ ሰይጣን ጋር እልህ ተጋብቼ  ስለነበር ሥጋዬ ያሻውን ቢሆን ግድ አልነበረኝም ሃሳቤ ሁሉ ከእርሱ መዳፍ በማምለጥ ጉዳይ ላይ የተያዝኩ ስለሆንኩ የማደርገው ሁሉ አይታወቀኝም ነበር በገዳሙ ውስጥ ለመነኮሳቱ የሚዘጋጀውን እህል በማስፈጨትና ዳቦ በመጋገርም ተሳታፊ ነበርኩ መንነው ያልመነኮሱትን አራሽ መናንያንን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ለመርዳት ሞፈር ቤት እቀመጥ ነበር

ከሣቴ ብርሃን የመነኑ ግን ያልመነኮሱ የሚባሉት ሰዎች ሞፈር ጠምዶ የማረስ ዓላማ ምንድነው ?

አባ ዘውዱ ፦የእነርሱ ዓላማ ምንኩስና ነው አመጣጣቸው ለዚያ ነው ይሄ የአራሽነት ተግባርም ወደ ምንኩስና ለሚያደርጉት ጉዞ እንደ መፈተኛ መስክ ነው እዚያ አበ ምኔት አርድእት እና ሊቀ አርድእት የሚባሉ ለምንኩስና መብቃትህን የሚያጸድቁልህ ሃላፊዎችና መጋቢዎች ናቸው

ከሣቴ ብርሃን እነዚህ መጋቢዎች መናኙን አልፈሃል ወድቀሃል የሚሉበት መመዘኛው ምንድነው ?  

አባ ዘውዱ በተሰጠህ የሥራ ድርሻ ያሳየኸውን ትዕግሥትና ያከናወንካቸውን በጎ ምግባራት ይገመግማሉ ጠባይህም መልካም መሆኑንና አለመሆኑን ያጣራሉ በዚያም በስሜት ተነሳስቶ የመጣውን በዓላማ ከመጣው ይለያሉ

ከሣቴ ብርሃን አንድ መናኝ ፈተናውን ለማለፍና ምንኩስናን ለማግኘት ምን ያህል ዓመት መቆየት ይጠበቅበታል ?

አባ ዘውዱ ሰባት ዓመት ይፈጃል

ከሣቴ ብርሃን እርስዎ ይህንን ያህል ዓመት በመቆየትና በዚያ የሚሰጠውን ፈተና አልፈው ነው ምንኩስናን የተቀበሉት ?

አባ ዘውዱ አዎን

ከሣቴ ብርሃን ከየትኛው ገዳም ነው እርስዎ ይህንን ምስክርነት ያገኙትና የመነኮሱት ? የምንኩስናውን ማዕረግ የመስጠቱ ሥነስርዓት የሚከናወንበት የተለየ ሁኔታ አለ ወይ ?

አባ ዘውዱ እኔን እንግዲህ የብዙ ገዳማት አበምኔቶች ያውቁኛል ሆኖም ግን የመነኮስኩት ደብረ ሊባኖስ ነው ዋናውን የምንኩስና ምስክርነቱን የሚሰጡት የገዳሙ አበምኔቶች ቢሆኑም የቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች እና ባለሥልጣናቱም በዚህ ውስጥ ይሳተፋሉ አስቀድመህ ለዚሁ ጉዳይ ወደ ገዳም ስትሄድም ከአጥቢያ ቤተክርስቲያንህ የሚጻፍልህን ወረቀት ካልያዝክ የሚያስገባህ የለም ፈተናህን ስትጨርስ ደግሞ ከገዳሙ የምታገኘው ማረጋገጫ ከዚያ ጋር ተያይዞ ነው የምንኩስናው ሥርዓት የሚፈጸመው

ከሣቴ ብርሃን አንድ መናኝ መነኩሴ ከመባሉ አስቀድሞ ምን እየተባለ ነው የሚጠራው ?

አባ ዘውዱ ፦« አዬዋ እገሌ » ነው የሚባለው

ከሣቴ ብርሃን ፦« አዬዋ ዘውዱ » የምንኩስናውን ፈተና ማለፋቸው ሲረጋገጥ ደግሞ « አባ »ወደ መባል ተሸጋገሩ ማለት ነው ?

አባ ዘውዱ የክርስትና ስሜ ጥበበ ጊዮርጊስ ስለሆነ ከመመንኮሴ በፊት አዬዋ ጥበቡ በመባል ነው የምጠራው በማለት አባ ዘውዱ ኪዳኑ ምንኩስናን የተቀበልኩት በ1980 ዓመተ ምህረት መሆኑን ይናገራል አያይዞም በገዳም ውስጥ በሚኖርበት ጊዜ  ስለሚበላው መብልና ስለሚለብሰው ልብስ ይዘረዝራል የምለብሰው ወይባ ነው ቢጫ ቀለም ያለውና አብዛኛው ባሕታዊ የሚለብሰው ጨርቅ ነው ሆኖም እኔ ባሕታዊ ብቻ ሳልሆን ወንጌል ሰባኪም ስለነበርኩ ጥቁሩንም ልብስ እለብስ ነበር በማለት ይገልጻል አያይዞም ስለ ዋልድባ ገዳም ይተርካል በነገራችን ላይ የዋልድባ ገዳም ዋናውና የመጨረሻው የመናኞች ማጠቃለያና ማብቂያ ገዳም ነው የተወደዳችሁ የመልዕክቴ አንባቢዎች አባ ዘውዱ ኪዳኑ በዚሁ በዋልድባ ገዳምም ነበረና እስቲ ስለዚህ ገዳም የሚያጫውተንንና የሚያወጋንን ደግሞ እንስማ

ከሣቴ ብርሃን ከሌሎች ገዳማት ይልቅ የዋልድባ ገዳም ዓይነተኛ ልዩነት ምንድነው ይላሉ ?

አባ ዘውዱ በዚያ ያለው አኗኗር ከበድ ይላል ራስን ያለልክ ማጎሳቆልም ይበዛል ዓለምን ጨርሶ ለመርሳትና የሥጋን መሻት ለመግደል የሚደረገው ትግልም ብርቱ ነው በዚያ የላመና የጣመ ምግብ አይበላም የሁልጊዜም ምግብህ ቋርፍ ነው

ከሣቴ ብርሃን ቋርፍ ምንድነው ?

አባ ዘውዱ ቋርፍ ከደረቅ ጥሬ ሙዝ የሚዘጋጅ ነው በዚህ ገዳም ውስጥ የሚኖሩ መነኮሳት እስከ 16 ክፍለ ዘመን ድረስ ቋፍሌ የሚባል ከመሬት ውስጥ ተቆፍሮ የሚወጣ መራራ ተክል ይመገቡ ነበር ተፈጥሮው የጅብ ሽንኩርት እየተባለ የሚጠራውን ተክል ይመስላል ቆይቶ ግን አንዳንድ ባሕታውያን በገዳሙ አካባቢ ሙዝ መትከል እንደጀመሩ ይነገራል ሆኖም ሙዙን የምትመገበው የተፈጥሮ ወዙን ጣዕሙን ካጠፋህ በኋላ ነው አዘገጃጀቱም በካራ የተቆራረጠው ጥሬ ሙዝ ጸሐይ ላይ ክው  ብሎ ይደርቃል በጨውና በሚጥሚጣ ተደቁሶ ጎላ ውስጥ ገብቶ ይቀቀላል በስሎ ከቀዘቀዘ በኋላ በምግብ ሰዓታችን በልክ በልካችን በጭልፋ እየተጨለፈ ለእያንዳንዳችን ይሰጠናል

ከሣቴ ብርሃን ይህ ምግብ የሚዘጋጀው በማን ነው ?

አባ ዘውዱ ገዳሙ ውስጥ ከባሕታውያኑ በስተቀር ማንም ስለማይገባ ምግቡ የሚዘጋጀው መነኮሳቱን በሚያገለግሉት አርድእት ነው ቅድም እንደነገርኩህ ለምናኔ ወደ ገዳሙ የገቡ መናንያን ወደ ምንኩስና ከመድረሳቸው አስቀድሞ እንዲህ ያለውን አገልግሎት መስጠት አለባቸው

ከሣቴ ብርሃን የዚህ ምግብ አዘገጃጀት አላማ ጣዕም የሌለውን ምግብ መፍጠር ነው ?

አባ ዘውዱ   አዎና የመናኝ ሕጉ እራሱ የላመ የጣመ አይብላ የሚል ነው ዓላማው ግን ጣዕሙን ብቻ ሳይሆን የምግብነት ጠቀሜታውንም ማሳጣት ነው ለሰውነትህ የሚስማማ ሆኖ ዝሙትን እንዳይጠራብህም ለመከላከል ማለት ነው

ከሣቴ ብርሃን የገዳሙ የጠዋትና የማታ የምግብ አቅርቦት ይኸው ብቻ ነው ?

አባ ዘውዱ የምን ጠዋትና ማታ አመጣህ ? በዚያ የምግብ ጊዜ ሁሌም ዘጠኝ ሰዓት ላይ ብቻ ነው ዘጠኝ ሰዓት ላይ መጥቅዕ ( ደወል ) ሲደወል ሁሉም ከያለበት እየመጣ ከእንጨት ተፈልፍሎ በተሠራው ሰሃኑ ድርሻው እየተመጠነ ይሰጠዋል በዋልድባ ሥጋን የመጉዳት ደረጃው እጅግ ከፍ ያለ በመሆኑ በዚያ ሁኔታ ብዙ ዘመን ካሳለፉ ሰዎች አንዳንዶቹ ተመስጦ ውስጥ ገብተው ትንቢት ይናገራሉ ሌሎችም እንደ እብድ ብቻቸውን ይለፈልፋሉ

ከሣቴ ብርሃን ትንቢትና መገለጡ ከእግዚአብሔር እንደሆነና እንዳልሆነ መፈተኛው ምንድነው

አባ ዘውዱ መገለጡ ከእግዚአብሔር ነው ለማለት በጣም ይቸግረኛል ትንቢቱና መገለጡ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ለመመስከር አልችልም ነገር ነገር ግን  መንገዱ ባይሆንም ለጽድቅ ብለው እየከፈሉ ያሉትን እጅግ ከባድ ዋጋ እያሰብኩ ከአንጀቴ ስለምራራላቸው ስለ እነርሱ ክፉ ከመናገር እቆጠባለሁ ምኞቴና ጸሎቴ ግን ሁሉም እኔ ወዳገኙሁት እረፍት እንዲመጡ ጌታ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሠራላቸው ሥራ ዕርፍ እንዲሉ ነው አባ ዘውዱ ኪዳኑ ምስክርነታቸው በዚህ አላበቃም በክፍል ሦስትም ቀጥለው የሚሉን ነገር አለ ለዛሬ ግን የክፍል ሁለት ምስክርነቱን በዚህ እናጠቃልላለን እስከዚያው ሰላም ሁኑ ስል የምሰናበታችሁ

ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ


ተባረኩልኝ ለዘላለም 

No comments:

Post a Comment