Thursday 4 December 2014

ቤተክርስቲያን ክፍል ሃያ ሦስት



ቤተክርስቲያን




ክፍል ሃያ ሦስት


በክርስቶስ የመሆን ጥቅሙን አጽንታ ታስተምራለች



ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው
አሮጌው ነገር አልፎአል እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል
         
      
     
           2 ቆሮንቶስ 5 17



በክርስቶስ የመሆን ጥቅሙ ምን እንደሆነ ከመጽሐፍቅዱስ ማስረጃዎች ጋር በተከታታይ  ባቀረብናቸው ሃሳቦች በብዙ እንደተጠቀማችሁ እንደተጽናናችሁበትም ተስፋ አደርጋለሁ የዛሬው መልዕክት ግን ይህንን ርዕስ በተመለከተ የማጠቃለያ የመደምደምያና የመጨረሻ ሃሳብ ነው ለትምህርታችን መጠቅለያ ሃሳብ እንደ  መነሻ የምናደርገው በ2ኛ ቆሮንቶስ 5 17 ላይ የተጻፈውን ክፍል ነው የክፍሉም  ሃሳብ እንዲህ ይላል ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው አሮጌው ነገር አልፎአል እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል በማለት ይናገራል በክርስቶስ የመሆናችን ዋናው ጥቅም ይሄ ነው «አዲስ ፍጥረት መሆን»  የክርስትናችንም አንኳሩ ሃሳብ ይህ ሲሆን ወደቅድስቲቱ ከተማም የምንገባበት መግቢያ በር በክርስቶስ በመሆናችን በምናገኘው አዲስ ፍጥረት የመሆን ማንነት ነው  በዚህ በክርስቶስ በተገኘው አዲስ ፍጥረት የመሆን ማንነት ውስጥ የዚህ ሃይማኖት የዛ ሃይማኖት ተብለን ጎራ ለይተንና ተከፋፍለን ለመኖር  አዲስ ፍጥረት አልሆንም መጽሐፍቅዱሳችንም ከዚህ ሃይማኖት የመጣ ከዛ ሃይማኖት የወጣ አዲስ ፍጥረት ነው አላለንም ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው አሮጌው ነገር አልፎአል እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል ነው ያለን ስለዚህ አዲስ ፍጥረት ለመሆን የሚያስፈልገው በክርስቶስ መሆን ነው ይህ ትምህርት በክርስቶስ የመሆን ጥቅሙ በሚል ሃሳብ በተከታታይ ያቀረብናቸውን ትምህርቶች የሚጠቀልል ነው ይህንን ልል የቻልኩበት ምክንያት በክርስቶስ የመሆን ጥቅሙ ገብቶን በተጻፉልን የእግዚአብሔር የቃሉ እውነቶች ውስጥ ገብተን ክክርስቶስ ጋር ልንተባበርና  በክርስቶስም ነን ልንል የምንችለው በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት መሆን ስንችል ነው  በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ያልሆነ ሰው በክርስቶስ የመሆን ጥቅሙ አይገባውም በክርስቶስ ነኝ ቢልም ከክርስቶስ ጋር አይተባበርም አንድ የጌታ አማኝ ጌታን ተቀብሎ ማለት ጌታ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኙ አድርጎ እና ተቀብሎ በጌታ ነው መባል ቀላል ነገር አይደለም እገሌ እገሊት እነእገሌ  በጌታ ናቸው መባል ጌታን ለሕይወታቸው ወስነው በመቀበል አዲስ ፍጥረት ሆነዋል ማለት ስለሆነ ሁሉ ነገር የሚጀምረው ከዚህ ነውና በጣም ትልቅ ነገር ነው ሰው ለሕይወቱ አዳኝ የሆነውን ጌታ አምኖና ወስኖ ሳይቀበል የጌታ መሆን አይችልም በጌታም መሆን አይችልም እንደገናም አዲስ ፍጥረት የሆነ ማንነትም የለውም በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ካልሆነ ደግሞ ባለፈው መጽሐፍቅዱሳዊ ማስረጃ በመስጠት በተከታታይ ባቀረብነው በክርስቶስ የመሆን ጥቅሙ ምን እንደሆነ አይገባውም ስለዚህ ወደዚህ በክርስቶስ የመሆን ጥቅም ውስጥ ለመግባት ጌታን ተቀብሎ አዲስ ፍጥረት መሆን የግድ ነው በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ስንሆን አሮጌው ነገር ያልፋል እነሆ ሁሉም አዲስ ይሆናል አዲስ ፍጥረትነት የሚጀምረው ክርስቶስን ከመቀበል ነው ክርስቶስን ስንቀበል አዲስ ፍጥረት እንሆናለን ከእግዚአብሔርም እንወለዳለን ለዚህም ነው በዮሐንስ ወንጌል 1 11 _ 13 ላይ የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም ሲል የተናገረን ከእግዚአብሔር የምንወለደው ደግሞ በሕያው በእግዚአብሔር ቃል  ነው ስለዚህ ከእግዚአብሔር ለመወለድ የግድ የእግዚአብሔር ቃል ያስፈልገናል የእግዚአብሔር ቃል ደግሞ ሕያውና ለዘላለም የሚኖር የማይጠፋ ዘር ነው ስለዚህ  የማይጠፋውን ሕያውና ለዘላለምም የሚኖረውን የእግዚአብሔርንም ቃል አምነን መቀበል አለብን ለዚህም እውነታ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ይናገራል ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ 1 ጴጥሮስ 1 23 ሁለት ዓይነት መወለድ አለ ከእግዚአብሔር የሆነ መወለድ ግን ክርስቶስን በመቀበል የሚመጣ በእግዚአብሔር ቃል የሆነ ዳግመኛ መወለድ ነው ለዚህም ነው የጌታ ደቀመዝሙር ለመሆን በሌሊት እየመጣ ለሚማረው የአይሁድ አለቃ የእስራኤል መምህር ለሆነው ኒቆዲሞስ ጌታ ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው ሲል የተናገረው ኒቆዲሞስም መልሶ፦ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ? አለው ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን ? እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም ሲል መለሰለት ዳግመኛ መወለድ ከመንፈስ የሆነ መወለድ በመሆኑ ኢየሱስን ጌታዬና አዳኜ ብለን ቃሉንም በእምነት ተቀብለን የምናገኘው የመንፈስ  መወለድ ካልሆነ በስተቀር እንዲሁ በሥጋዊ አዕምሮ የአይሁድ መምህር ኒቆዲሞስ ያነሳውንም ጥያቄ መልሶ በማንሳት ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል ? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን ? ብለን ስለጠየቅን የሚሆን ነገር አይደለም በዳግመኛ መወለድ መካከልና ከሥጋና ከደም ፈቃድ በሆነ መወለድ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ ከሥጋና ከደም ፈቃድ መወለድ እገሌ እገሌን ወለደ እንደሚለው በተቃራኒ ፆታ መካከል ባለ ግንኙነት  የሚመጣ ሲሆን ዳግመኛ መወለድ ግን ከመንፈስ የሆነ መወለድ በመሆኑ የእግዚአብሔርን ቃል በማመንና ኢየሱስን በመቀበል የሚመጣ ነው መምህሩ እና የአይሁድ አለቃው ኒቆዲሞስ እንግዲህ ያልተረዳው ይህንን ነበረ ስለዚህ ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል ? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን ? በማለት ጠየቀ ጌታችንም ሲመልስለት እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው በማለት አስረዳው ክርስቶስን በመቀበል ውስጥ የሚሆነውን ነገር ሊነግረን ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 8 ከቁጥር 9 ጀምሮ እንዲህ አለ የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፥ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው በማለት ተናገረን ስለዚህ ክርስቶስን በመቀበላችን የእግዚአብሔር ወገን ሆነናል ሰውነታችን በኃጢአት ምክንያት የሞተ ቢሆንም መንፈሳችን ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ሆኗል ስለዚህም ነው አሁንም ጳውሎስ አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል በማለት የተናገረው ሮሜ 8 15 አያይዞም ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን ሲል አስረዳ ሮሜ 8 16 እና 17 በመሆኑም ይህ ሁሉ እንግዲህ ከሥጋና ከደም በሆነ መወለድ የመጣ ሳይሆን በዳግመኛ ከእግዚአብሔር መወለድ የመጣ ነው በመሆኑም ይህንን ላደረገ በዳግመኛም ልደት ወራሾች ልንሆን ልጁን ኢየሱስን ጌታና የግል አዳኛችንም አድርገን እንድንቀበለው ለሰጠን ለሠራዊቱ ጌታ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁንለት በክርስቶስ መስቀል ላይ 1 ኃጢአት ተሽሮአል 2 የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን ስለሚል ቃሉ ይኸው አሮጌው ሰዋችን ከጌታችን ከኢየሱስ ጋር አብሮ ተሰቅሏል ለዚህም ነው በዕብራውያን 9 26 ላይ እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል ያለን እንደገናም በሮሜ 6 6 ላይ ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን፤ የሞተስ ከኃጢአቱ ጸድቋልና በማለት የተናገረን ከዚህም የተነሳ ነው ስለዚህ አሮጌው ነገር አልፎአል  ያለው እንግዲህ አሮጌው ነገር አልፎአል  የተባለው  ተሽሮአል በተባለው ኃጢአትና  የኃጢአት ሥጋ በተሰኘው አሮጌው ሰዋችን ውስጥ ነው በመሆኑም ኢየሱስ እነዚህን ሁለቱን ነገሮች ፣ በሞቱና በትንሳኤው አሸነፋቸው ማለትም ኃጢአትን ሻረው አሮጌውን ሰው ሰቀለው ታድያ ዛሬ ኃጢአት ስለተሻረ ኃጢአት የለም እኛም ኃጢአትን አንሰራም ማለት አይደለም እንደገናም የተሰቀለው አሮጌው ሰዋችን ተሰቅሏልና አያስቸግረንም ማለትም አንችልም እኛ ወደ ጌታ እስክንሄድ ወይንም ጌታ ወደእኛ እስከሚመጣና እስከሚወስደን ፣ በምድርም ላይ እስካለን ድረስ እነዚህ ነገሮች ወደ ሕይወታችንን እየመጡ እንደሚፈትኑን የታወቀ ነገር ነው ነገር ግን ኢየሱስ ኃጢአትን የሻረው በመሆኑና እኛንም አንድ ጊዜ በማቅረብና በመቀደስ የዘላለም ፍጹማን ስላደረገን ዕብራውያን 10 10 14 _ 18 ይኸው ወደ ሕይወታችን የሚመጣው ኃጢአት ደህንነታችንን የሚነጥቅ አይሆንም እንደገናም ይህንኑ ኃጢአት እኛም አቅፈንና ተስማምቶን እንኖራለን ማለት አይደለም ኃጢአታችንን ይቅር ሊል ወደሚችል በደሙም ወደሚያጥበን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስና ወደ ደሙ እየቀረብን ለጌታችን በመናዘዝ ከኃጢአታችን እንነጻለን 1 ዮሐንስ 1 7 _ 10 ለዚህም ነው በ1ኛ ዮሐንስ 2 1 ላይ ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ የሚል ቃል የተጻፈልን ቃሉን ስንመለከት መጽሐፉ ኃጢአት እንድናደርግ አያበረታታንም 1 ዮሐንስ 3 9 ነገር ግን ኃጢአትን ብናደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ እንዳለን ግን በእርግጥ ይነግረናል ይሄ ጠበቃችን ደግሞ ኃጢአትን የሻረልን የኃጢአትንም ሥርየት የሰጠን ኃጢአትንም በመተው ጽድቁን ያሳየን ጠበቃ ነው ሮሜ 3 25 እና 26 የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ የተሰቀለውን አሮጌውን ሰው በተመለከተ ደግሞ መጽሐፉ ይኸው አሮጌው ሰው እንደተሰቀለ እናውቃለን ይለናል ስለዚህ በእኛ በኩል ያልተቤዠ ሰውነት ነውና ያለን ይህ አሮጌው ሰው ምንም እንኳ የተሰቀለ ቢሆንም እኛም  አምነንና ፈቅደን የሰቀልነው እንኳ ቢሆን እንደ መንፈስ ፈቃድ በማንመላለስበት አንዳንድ ጊዜ ብቅ እያለ ያስቸግረናል ፣ በሥጋም እንድንመላለስና  የሥጋ ፈቃዳችንንም እንድንፈጽም ያደርገናል ታድያ ለዚህ መፍትሔው ጳውሎስ እንደተሰቀለ እናውቃለን ያለውን ይህንን አሮጌውን ሰው በኃጢአቱ እንዲገፋበት ማሽሞንሞን ሳይሆን እኛም መልሰን መስቀል ነው የሚያስፈልገን መጽሐፍ ሲናገር የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ ይለናል ገላትያ 5 24 እንግዲህ ይህንን ክፉ መሻትና ምኞቱ ጋር ያለውን አሮጌውን ሰው ለመስቀል የኢየሱስ መሆን ያስፈልጋል የኢየሱስ ያልሆኑቱ በዚህ በአሮጌው ሰው መሻት ሲሰቃዩና ሲቃጠሉ ይኖራሉ እንጂ ከኢየሱስ ጋር ሊሰቅሉት አይችሉም አንዳንዶቹም ይህንን ክፉ የሆነውን  የሥጋ መሻት ከመፍራት የተነሳ ነው መንነውና ዓለም በቃኝ ብለው ሰው ወደሌለበት ገዳምና ዱር ውስጥ ገብተው የሚደበቁት ይህንን ሁኔታ እኔም በክርስቶስ ከመሆኔ በፊት በብዙ የማውቀውና ያሳለፍኩትም ታሪክ በመሆኑ  ስለማውቀው መናገር እችላለሁ አንዳንዶች ደግሞ ከራስ ጸጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው ድረስ ተሸፋፍነውና ተጀቡነው ከተማ ለከተማ ሲዘዋወሩ የምናያቸው ይህንኑ ክፉ የሆነ የሥጋ መሻት ለመከላከልና ለእግዚአብሔርም ለመቀደስ ከሚል ፍላጎት ተነስተው ነው ነገር ግን በልብስም ይጀቦኑ ገዳምም ይግቡ ይሄ ክፉ የሆነ የሥጋ መሻትና ምኞት ግን የሚወገድ አይሆንም ፣ ሊወገድም አይችልም ለዚህም ነው አንዳንድ ድብቅ የሚመስሉ ነገር ግን ጸሐይ የሞቃቸውና ሰዎችም ሁሉ የሚያውቋቸውን  የኃጢአት ወሬዎችን በአብዛኛው የምንሰማው አሁንም ግን ከዚህ ክፉ የሆነ የሥጋ መሻትና ምኞት ለመላቀቅ ብቸኛ መፍትሔው ኢየሱስን እንደግል አዳኝ አድርጎ መቀበልና የኢየሱስም መሆን ነው የኢየሱስ ሲኮን የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዌ ከእርሱ ጋር እንደተሰቀለ አውቃለሁ ማለትና ለዚህም ለአሮጌው ሰው ዕድል ላለመስጠት ፣ የኃጢአትንም በር ላለመክፈት አሮጌው ሰዌ የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ከኢየሱስ ጋር ተሰቀለ በማለት ፕሮክሌም ማድረግ ፣ ማወጅ ይቻላል ሐዋርያው ጳውሎስ በገላትያ ምዕራፍ 2 20 ላይ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው ሲል በራሱ ላይ አወጀ በዚህ ብቻ አላበቃም ስለ ዓለምም ሲናገር ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ አለ ገላትያ 6 ፥ 14 ስለዚህ የጳውሎስ ትምክህቱ ክርስቶስና በክርስቶስም የሆነለት ነገር ነበር የእኛም እንዲሁ ሊሆን ይገባል ከዚህም ሌላ የኢየሱስ የሆነ ሰው ሥጋን ከክፉ መሻቱና ምኞቱ ጋር የሚሰቅል ስለሆነ የኢየሱስ ከሆኑ የራስንም ክፉ የሆነ የሥጋ መሻትን ከምኞቱ ጋር መስቀል ይቻላል ይህ በሚሆንበት ጊዜ ገዳምና ዱር ገብተን ሳንንከራተት እንደገናም በረጃጅም ጨርቆች ሳንከናነብና ሳንጀቧቦን በተጨማሪም ከዚሁ ለማምለጥ ስንል ልዩ ልዩ የሃይማኖት ሥርዓቶችና ወጎችን ሳንፈጽም  በዚሁ ጌታ ድልን ማግኘት ነጻነትም መውጣት ይሆንልናል የዮሐንስ ወንጌል 8 31 _ 33 ገላትያ 5 13   ቆላስያስ 2 16 _ 20 የማቴዎስ ወንጌል 15 1 _ 6  ወገኖች እነዚህ ጥቅሶች የሚጠቅሙዋችሁ ስለሆኑ ከመጽሐፍቅዱሳችሁ አውጥታችሁ አንብቧቸው ይህንን ትምህርት አሁንም በዚሁ እንጠቀልላለን ብዬ አስቤ ነበር ነገር ግን አሁንም ትምህርቱ እየሰፋ በመምጣቱ ምክንያት በሚቀጥለው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ልናጠቃልለው ተገድደናል  እስከዚያው ጌታ ይባርካችሁ ደህና ሁኑ እያልኩ የምሰናበታችሁ


ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ

Bless you all People of God

No comments:

Post a Comment