Sunday 7 December 2014

የግጥሙ ርዕስ እግዚአብሔር በተቀደሰ መቅደሱ አለ

የግጥሙ ርዕስ

እግዚአብሔር በተቀደሰ መቅደሱ አለ


እግዚአብሔር በተቀደሰው መቅደሱ ነው
እግዚአብሔር ዙፋኑ በሰማይ ነው
ዓይኖቹ ወደ ድሃ ይመለከታሉ
ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራሉ

መዝሙር (11) ፥ 4

እግዚአብሔር ከተቀደሰ መቅደሱ ነቅቶአልና
ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሆይ በፊቱ ዝም በል

ዘካርያስ 2 ፥ 13

ስለ ክርክሬ ለምን አልሰማኝም
በማለት አምላኬን ስጨቀጭቅ በጣም
ግፍና አመጻው ገኖና ተስፋፍቶ
የሰዎች አካሄድ ፍጹም ተበላሽቶ
ሁኔታው በሙሉ የከፋ ቢመስልም
የእኛ እግዚአብሔር ግን ከቶ አልተለወጠም
እርሱ ለዘላለም የሚኖር ጌታ ነው
ሃሳቡንም ደግሞ ማንም አይለውጠው
ይህንን ሳውቅና ያንንም ስረዳ
በሥፍራዬ ሆኜ ፍጹም ሳልጎዳ
ጌታዬን በእምነት መጠበቅ ጀመርኩኝ
ጸንቼና አምኜ ማማዬ ላይ ቆምኩኝ
እግዚአብሔር በሥፍራው በመቅደሱ አለ
መቀየር መለወጥ በእርሱ ዘንድ የሌለ
ነገርን ሊፈጽም ቸኩሎ ይወጣል
ማንም ሳያግደው ሁሉንም ያሳካል
ያንተ ጉዳይ ከቶ የተረሳ አይደለም
ክፋትና አመጽ ነገር ቢሸረብም
ጌታ በፍጻሜው ሲሰራው ሁሉንም
ለበጎ ይሆናል ክፉው ተለውጦ
ሠራተኛው ጌታ በላዩ ተገልጦ
ስለዚህ ቅዱሳን ተጽናኑ በጌታ
በማደርያው ሆኖ ሁሉንም በአንድ አፍታ
ውበት ይሰጠዋል ፍጹም አሳምሮ
ሃዘንና ልቅሶን ምሬትን ቀይሮ
ስለዚህ ይህን ጌታ ተመስገን በሉት
ምስጋናን ውዳሴን እልልታን ስጡት
ጌታ አምላካችን ምስጋና ይገባዋል
ኤልሻዳይ ነውና ሁሉንም ይችላል
ተመስገን ተመስገን ተመስገን ጌታዬ
አንተ ነህ መድኅኔ ባለ ውለታዬ
ሥራዬን በሙሉ ሰርተህ ያሳረፍከኝ
ከምስጋና ሌላ ምሰጥህ ምን አለኝ
ሥራዬን በሙሉ ሰርተህ ያሳረፍከኝ
ከምስጋና ሌላ ምሰጥህ ምን አለኝ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment