Friday 5 December 2014

የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ምዕራፍ ሁለት ክፍል አራት



የቤተክርስቲያን ተልዕኮ


ምዕራፍ ሁለት



ክፍል አራት



ከሐሰተኛ ነቢያት ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ራስንና መንጋውን መጠበቅ



ከንቱ ራዕይ



ኖን፦ ነቢያቶችሽ ከንቱና ሐሰተኛ ራእይ አይተውልሻል ምርኮሽንም
      ይመልሱ ዘንድ በደልሽን አልገለጡም ከንቱና የማይረባ ነገርንም
      አይተውልሻል

            ሰቆቃወ ኤርምያስ 2 14







የከንቱ ራዕይ መነሻው ምንድነው ? ከንቱና ሐሰተኛ  ራዕይስ ከምን ይመጣል ? ብለን ይህንን ሁኔታ በጥልቀት ስናጠና ወደ ኋላ መለስ ብለን በክፍል አንድ ፣ በክፍል ሁለትና በክፍል ሦስት ላይ ያነሳናቸውን ዋና ሃሳቦች አትኩረን እንድንመለከት ግድ ይለናል በክፍሎቹም እንዳየነው እነዚህ ከንቱና ሃሰተኛ ራዕይ የሚያዩ ሰዎች ወደዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸው ትልቁና ዋናው ነገር ትምክህትና እኔ እበልጣለሁ ከሌላው ይልቅ እኔ እሻላለሁ ባይነት ነው ለምን እንዲህ ሊሉ ቻሉ ? በውኑ እነዚህ ሰዎች ከሌላው ሰው የተሻሉ ሆነው ነው ወይ ? ስንል መልሱ በአጭሩ አይደለም ነው የምናገለግለው በብልጫ ጉዳይ ውስጥ ገብተን በእበልጣለሁና በእሻላለሁ ባይነት ተይዘን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል  እንደ እግዚአብሔር ቃል በመናገር ነው የምናገለግለው ለዚህ ነው በሉቃስ ወንጌል 1 1 _ 4 ላይ የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን፥ በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ፥ እኔ ደግሞ ስለ ተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ ሲል የተናገረን በ1ኛ ጴጥሮስ 4 11 ላይ ደግሞ ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን ይለናል አገልጋይ በመሆናችን ደግሞ አገልጋይ እንኳ ሳይቀር የሆነው ከሌላው ስለበለጥንና ስለተሻልን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽመን ለመስበክ ስለተጠራንና ስለተመረጥን ነው በቆላስያስ 1 25 ላይ ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ ይለናል ሰሚዎችም ደግሞ  ከእግዚአብሔር ባሮች የተነገረውን ቃል እንደ እግዚአብሔር ቃል አድርገው እንዲቀበሉ ፣ ቃሉን እንዲሰሙ እና እንዲፈጽሙትም የታዘዙ ናቸው በ1ኛ ተሰሎንቄ 2 13 ላይ ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን አለ በመዝሙር 102 ( 103 ) 20 ላይ ደግሞ ቃሉን የምትፈጽሙ፥ ብርቱዎችና ኃያላን፥ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ባርኩ አለን ስለዚህ ክርስትና የእግዚአብሔርን ቃል የማሰማትና የመስማት ሰምቶም የመፈጸም ጉዳይ እንጂ የውዽድርና የእበልጣለሁ ባይነት ጉዳይ አይደለም ድርሻችን የእግዚአብሔርን ቃል ማሰማት ከሆነ ድርሻችንን ለመወጣት ቃሉን ማሰማት ነው መስማት ከሆነ ደግሞ ድርሻችን ቃሉን በትሕትናና በትዕግስት ሆኖ መስማት ነው በዚህ ጉዳይ ላይ ሳሙኤል የእግዚአብሔርን ቃል የማሰማት ሃላፊነት የተቀበለ በመሆኑ ሳኦልን በመጨረሻ ሁሉን ከፈጸመ በኋላ የእግዚአብሔርን ቃል አሰማህ ዘንድ በዚህ ቁም አለው 1 ሳሙኤል 9 27 ንጉስ ሳኦልም የእግዚአብሔርን ቃል የመስማት ግዴታ ስለነበረበት የእግዚአብሔርን ቃል ሰማ ይህ ነው ክርስትና እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል የማሰማት ፣ የመስማትና ሰምቶም የማድረግ ጉዳይ ነው ነገር ግን ከዚህ ውጪ ሲሆን መልኩን ይቀይራል ውዽድር ፣ ፉክክርና እልከኝነትንም የተላበሰ አገልግሎት ይሆንና የኔ አገልግሎት ፣ የእኔ ቤተክርስቲያን ይበልጣል ለምን እኔ ጋር አትመጡም  ? እነርሱ እኮ እንዲህ እና እንዲያ ናቸው መባል ይጀመራል በዚህ ነገርም አገልጋዮችሞ ሆነ ተገልጋዮች ሲያሰናክሉ በደጅ ያለው ሕዝብ ደግሞ የሞተለትን ጌታ አይቶ መዳን ሲገባው በዚህ ክፉ ወሬ ሲሰናከልና በብዙ ሲደነቃቀፍ ይስተዋላል በእርግጥም ሰዎቹ ሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች ሆነው ለሕዝቡ ጤናማ ያልሆነ ትምህርት የማይሰጡ ከሆነ ወደዛ ቦታ አትሂዱ ማለት ተገቢ ስለሆነ የእውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ሃላፊነትና አደራም ጭምር ነው  የሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች አገልግሎት  ሁኔታ ሳይገታ ቀርቶ ቀጣይነት ያለው ከሆነ  ሐሰተኛና ከንቱ ራዕይን ይወልድና ሕዝብን ለመያዝ ሰዎችንም ስቦ የራስ ለማድረግ ሲባል የውሸት ትንቢትና የራስ ጥቅምን ለማስከበር ሲባል የእግዚአብሔርን ቃል Twist ( ትዊስት ) በማድረግ ማለት የእግዚአብሔርን ቃል በመጠምዘዝ የሐሰት ትምህርትና መልዕክት ሲነገር ይታያል ለዚህ ነው በሰቆቃው መጽሐፍ ላይ  ነቢያቶችሽ ከንቱና ሐሰተኛ ራእይ አይተውልሻል ምርኮሽንም ይመልሱ ዘንድ በደልሽን አልገለጡም ከንቱና የማይረባ ነገርንም አይተውልሻል በማለት በእግዚአብሔር ቃል የተነገረው በሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች ዘንድ በደልን መግለጥ ሰዎችንም ምን እናድርግ ? አስብሎ ለንስሐ ማዘጋጀት የተግሳጽ መልዕክትም ተናግሮ ሰዎችን ከጥፉት መመለስ ፈጽሞ የሚታሰብ ነገር አይደለም  ለምን ሲባል ተመለሱ የሚል የተግሳጽ መልዕክት የምንናገር ከሆነ ሕዝብ ይሸሸናል ሕዝብ ከሸሸ ደግሞ መባ ፣ አስራትና በኩራቱ ፣ ጥቅማ ጥቅሙ ይቀራል ፣ መከበር ይጠፋል ተብሎ ስለሚታሰብ ትንፍሽ የሚል ሰው የለም በዚህ ጉዳይ ላይ እግዚአብሔርን ደስ ላሰኝ ፣ ለእግዚአብሔር ልታዘዝ ብሎ እግዚአብሔር የሰጠውን ቃል ሳይሸፍን የሚናገር መልዕክተኛ ከተገኘ ደግሞ መልዕክተኛ ምን አይተህ ? ምን ሰምተህ ተናገርክ ? ተብሎ ይጠየቃል ይጎነተላል ፣ ይገፋል ፣ ይጠላል ፣ ትልቅ ጥቃትም ይደርስበታል ሁለተኛም መድረክ አካባቢ ድርሽ እንዳይል ተደርጎ ይባረራል ይህ ግን ፍጹም ስሕተትና እግዚአብሔርም የማይቀበለው ነገር ነው ለምን ? ስንል በትንቢተ ኢሳይያስ 58 1 ላይ በኃይልህ ጩኽ፥ አትቈጥብ፥ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፥ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር ይለናል የሰዎችን መተላለፍና ኃጢአት ስንናገር ደግሞ ተቆጥበንና ፈርተን ሳይሆን በኃይል ጮኸንና ድምጻችንንም እንደ መለከት አንስተን ነው የእግዚአብሔር ቃል የሚለን እንግዲህ ይህንን ነው ምክንያቱም በትንቢተ ሕዝቅኤል 18  20 ላይ ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች ልጅ የአባቱን ኃጢአት አይሸከምም፥ አባትም የልጁን ኃጢአት አይሸከምም የጻድቁ ጽድቅ በራሱ ላይ ይሆናል፥ የኃጢአተኛውም ኃጢአት በራሱ ላይ ይሆናል ስለሚለን ማንም የማንንም ኃጢአት አይሸከምምና እያንዳንዱ በኃጢአቱ ጸንቶ ንስሐ ካልገባ  የሚሞት በመሆኑ ሕዝብን በኃጢአት ምክንያት ከሚመጣበት ሞት ለማዳን መተላለፉንና ኃጢአቱን የግድ መናገር ይኖርብናል ዮሐንስ መጥምቁ ሳይፈራ ፣ ሳይሳቀቅ እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ ?  እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ በልባችሁም አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል በማለት ተናገረ የማቴዎስ ወንጌል 3 7 _ 10 ኢየሱስ ደግሞ እንግዲህ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤ እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና አላቸው ዮሐንስ ወንጌል 8 24 እንደገናም በዮሐንስ ወንጌል 8 21 ላይ  ኢየሱስም ደግሞ እኔ እሄዳለሁ ትፈልጉኛላችሁም በኃጢአታችሁም ትሞታላችሁ እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አላቸው ይለናል ወደ ሐዋርያት ትምህርት ስንመጣ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ አላቸው 1 ቆሮንቶስ 15 17 ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ደግሞ በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው ሲላቸው እናያለን ኤፌሶን 2 1 _ 2 ሐዋርያው ያዕቆብም ደግሞ እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች አለን ያዕቆብ 5 16 በነቢያቱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በሐዋርያቱ ያለ እውነተኛው ትምህርት እንግዲህ ይሄ ነው ኃጢአትን ሸፋፍኖና ደብቆ እሹሩሩ አይልም ገልጦ በመናገር ሰዎች እንዲፈወሱ ያደርጋል ጳውሎስ ሐዋርያው ከዚህ የተነሳ ነው የብሉይ ኪዳኑን ጥቅስ ድጋፍ አድርጎ በመነሳት የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም ያለን ኤፌሶን 4 28 ዘጸአት 22 3 እና 4 እኛም እንዲህ ልንል ይገባል ንስሐ ግቡ ከኃጢአታችሁ ተመለሱ ብቻ ሳይሆን የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ ማለት ይገባናል መጽሐፍቅዱሳችን ስለ ሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች ሲናገር ከንቱ ራዕይ አይተውልሻል በደልን አይገልጡም በማለት ብቻ አያበቃም ካህናቶችዋም ሕጌን በድለዋል ቅድሳቴንም አርክሰዋል ቅዱስ በሆነና ቅዱስ ባልሆነ መካከልም አልለዩም፥ በንጹሕና በርኩስ መካከል ያለውን ልዩነት አላስታወቁም ዓይናቸውንም ከሰንበታቴ ሰወሩ እኔም በመካከላቸው ረከስሁ በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ የስስትን ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ነፍሶችንም ያጠፉ ዘንድ እንደሚናጠቁ ተኵላዎች ናቸው እግዚአብሔርም ሳይናገር ነቢያቶችዋ  ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እያሉ ከንቱን ራእይ በማየት የሐሰትንም ምዋርት ለእነርሱ በማምዋረት ያለ ገለባ በጭቃ ይመርጓቸዋል የምድርን ሕዝብ ግፍ አደረጉ ቅሚያም ሠሩ ድሆችንና ችግረኞችን አስጨነቁ፥ መጻተኛውንም በደሉ ቅጥርን የሚጠግንን፥ ምድሪቱንም እንዳላጠፋት በፈረሰበት በኩል በፊቴ የሚቆምላትን ሰው በመካከላቸው ፈለግሁ፥ ነገር ግን አላገኘሁም አለ ትንቢተ ሕዝቅኤል 22 26 _ ፍጻሜ እንመልከት በትንቢተ ኢሳይያስ 5 20 ላይ ደግሞ ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፥ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፥ ጣፋጩን መራራ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው በማለት ይናገራል የእግዚአብሔር ቃል የሌለውና እንደ እግዚአብሔር ቃል የማይናገር የማይተነብይም ሐሰተኛ ነቢይና አስተማሪ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚበድል ቅዱስ በሆነና ቅዱስ ባልሆነ መካከል የማይለይ በንጹሕና በርኩስ መካከል ያለውን ልዩነት ማስታወቅ የማይችል በመሆኑ የስስትን ትርፍ ለማግኘት ሲል ደምን ለማፍሰስና ነፍስንም ለማጥፋት እንደሚናጠቅ ተኩላ ነው እንደገናም ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑን ጨለማ ጣፋጩን መራራ መራራውን ጣፋጭ የሚያደርግ የጥቅም አገልጋይ ነው ሐሰተኛ አስተማሪዎችና ሐሰተኛ ነቢያት ግፍና ቅሚያ መሥራት ድሆችንና ችግረኞችን ማስጨነቅ የተለመደ ባሕርይ ሲሆን ቅጥርን ለመጠገን ሲባል በፈረሰበት በኩል መቆም ግን ፈጽሞ የሚታሰብ ነገር አይደለም እግዚአብሔር ከዚህ ዓይነቱ አሳፋሪ የተኩላነትና የወስላታነት ሕይወት በቸርነቱ ይጠብቀን  የአንድ እውነተኛና ታማኝ አገልጋይ ኳሊቲው ግን ቅጥርን ለመጠገን በፈረሰበት በኩል መቆም ነው እንጂ ቅሚያና ዝርፍያ በማካሄድ ችግረኞችንና ድሆችን ማስጨነቅ አይደለም ይህን ማድረግ ደግሞ የሌባውንና የክፉውን ተግባር መፈጸም ስለሆነ ከእውነተኛ አገልጋዮች የምንጠብቀው አይሆንም በሐዲስ ኪዳንም ሆነ በብሉይ ኪዳን ያሉ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ያደረጉት ነገር ቢኖር ቅጥርን ለመጠገን በፈረሰበት በኩል መቆም ነው እግዚአብሔርም ይሄ ዓይነት ልብ ኖሮን እንድናገለግል ይፈልጋል ከዛ ውጪ ያለውን ከጥቅም ጋር የተገናኘ አገልግሎትን እግዚአብሔር ተኩላነት ነው ከሚለው ውጪ አያውቀውም   አይደግፈውም ደግሞም አይቀበለውም  በትንቢተ ኢሳይያስ 28 7 ላይ እነዚህም ደግሞ ከወይን ጠጅ የተነሣ ይስታሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ ካህኑና ነቢዩ ከሚያሰክር መጠጥ የተነሣ ይስታሉ፥ በወይን ጠጅም ይዋጣሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ በራእይ ይስታሉ፥ በፍርድም ይሰናከላሉ ይለናል ከሰከረና ከፋነነ በራዕይ ከሳተ በፍርድም ከተሰናከለ ካህንና ነቢይ በዛሬው አነጋገር በቤቱ ያለን አገልጋዮችንና መሪዎችን ሳይቀር የሚጠቀልል ነገር ነውና በእንዲህ ሁኔታ ካለን ከእኛ የሚጠበቅ ምንም ነገር የለም ሕግን ስንበድል ቅድሳቱንም ስናረክስ የሚፈጠረው ነገር እንግዲህ ይሄ ነው ለዚህ ነው በማቴዎስ ወንጌል 5 19 ላይ እንግዲህ ከነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል፤ የሚያደርግ ግን የሚያስተምርም ማንም ቢሆን እርሱ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል ያለን ስለዚህ እግዚአብሔር በሰጠን ሃላፊነትና በሰጠን ቦታ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽመን ልንሰብክ ልናስተምር  እንጂ ቃሉን ልንሽር እግዚአብሔር አላስቀመጠንም ይህንንም ሥልጣን አልሰጠንም  ከንቱ ራዕይ ያላቸው ሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች ግን ሃሳባቸው ከዚህ የእግዚአብሔር ቃል እውነት የተለየ ነው በማቴዎስ ወንጌል 15 9 በተጻፈው ቃል መሠረት የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ ስለሚለን  የሚያስተምሩት የእግዚአብሔርን ቃል ሳይሆን ለጥቅም የሆነ የሰው ሥርዓት ነው እንደገናም በሮሜ 16 17 እና 18 ላይ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ ስለሚለን ቃሉ ሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች ሁልጊዜ  የተማርነውን ትምህርት በመቃወም መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉ ናቸው ይሄ ነው መገለጫቸው ከዚህም ሌላ ለጥቅማቸውና ለገዛ ሆዳቸው ሲሉም የፍቅር ሰው በመምሰል ሰውን ያቆላምጣሉ ስለዚህ እንዲህ ካሉት ፈቀቅ ማለት አስፈላጊያችን ነው እንደገናም እንደነዚህ ያሉ ሰዎች   የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል ይለናል  2 ቆሮንቶስ 11 13 _ 15 ስለዚህ በወንጌል እውነት በእግዚአብሔር ቃል ጸንተን እንድንቆም የገላያ ክርስቲያኖችን ብቻ ሳይሆን ዛሬ ላይ ያለነውን እኛንም የተለየ ነገር ከቶ እንዳታስቡ እኔ በጌታ ስለ እናንተ ታምኜአለሁ፤ የሚያናውጣችሁ ማንም ቢኖር ግን ፍርዱን ሊሸከም ነው በማለት በሃሳባችን ሳይቀር ሳንናወጥ ጸንተን በመቆም ለመንግሥቱ ክብር እንድንበቃ በጌታ ወንድማችን የሆነው ጳውሎስ ወንድማዊና በክርስቶስ የሆነ ሐዋርያዊ ምክሩን አስተላለፈልን ጌታ እግዚአብሔር በምናነበው ቃል ይባርከን በእምነታችንም ያጽናን በቀጣዩ የትምህርት ክፍለ ጊዜ እስከምንገናኝ ሰላም ሁኑልኝ እያልኩ የምሰናበታችሁ


ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ


ተባረኩልኝ ለዘላለም




     

No comments:

Post a Comment