Friday 5 December 2014

የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ምዕራፍ ሁለት ክፍል አምስት



የቤተክርስቲያን ተልዕኮ


ምዕራፍ ሁለት



ክፍል አምስት



ከሐሰተኛ ነቢያት ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ራስንና መንጋውን መጠበቅ




የራዕይ መጥፋት



እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስ አፍስሶባችኋል ዓይኖቻችሁን ነቢያትንም
ጨፍኖባችኋል ራሶቻችሁን ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል ራእዩም ሁሉ እንደ
ታተመ መጽሐፍ ቃል ሆኖባችኋል ማንበብንም ለሚያውቅ ይህን አንብብ
ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ ታትሞአልና አልችልም ይላቸዋል ደግሞም
መጽሐፉን ማንበብን ለማያውቅ ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ
ማንበብ አላውቅም ይላቸዋል
      
         
 ትንቢተ ኢሳይያስ 29 10 _ 12

ባለፈው በክፍል አራት ትምህርታችን ላይ ከንቱ ራዕይ የሚያዩ ሰዎች ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ የማይረባን ነገር ከሚያዩ በስተቀር በደልን የማይገልጡ ማለት እውነትን እውነት ብለው በመናገር የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ የሚሉ አለመሆናቸው ከዚህ ይልቅ እውነተኛውን ትምህርት በመቃወም መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉ ለገዛ ሆዳቸውም የሚኖሩ መሆናቸውን ከዚህም ሌላ ውሸተኞች ነቢያትና ሐሰተኛ አስተማሪዎች በመሆናቸው ሰዎች  በተማሩት እውነት እርግጠኞች ሆነው ጥንቃቄ ካላደረጉ የተለየ ነገር እንዲያስቡ  በማድረግ የሚያናውጡ መሆናቸውንና ሌሎችንም ጉዳዮች አንስተን በሰፊው ተማምረናል ዛሬ ደግሞ የራዕይ መጥፋት በሚል ንዑስ አርዕስት የራዕይ መጥፋት መዘዙ ምን እንደሆነ  ፣ ራዕይ ሲጠፋ ምን ዓይነት ነገር እንደሚከሰት  ፣ ራዕዩም የጠፋው ከምን የተነሳ እንደሆነና የመሣሠሉትን አንስተን በሰፊው እንማማራለን እግዚአብሔር በዚህ ትምህርት ይባርከን ራዕይን የምናገኘው በእግዚአብሔር ቃል አማካኝነት ነው ራዕይን የሚሰጥ የእግዚአብሔር ቃል ነው በዘኁልቊ 24 ፥ 4  እንደገናም በዘኁልቊ 24 16 ላይ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለን የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥  ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል ይለናል በዚሁ ምዕራፍ በቊጥር 16 ላይ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ የልዑልንም እውቀት የሚያውቅ፥  ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል በማለት ተመሣሣይ ሃሳብ ይናገራል የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት የልዑልን እውቀት ማግኘት የአምላክንም ራዕይ ማየትና የዓይን መከፈት ይመጣል ውሸተኛ ራዕይ ወይም ከንቱ ራዕይን የሚያዩ ሰዎች እውነተኛውን የእግዚአብሔር ቃል በትክክል ያልሰሙ ሰምተውም ከሆነ ደግሞ እንደሚገባ ያልተረዱ በመሆናቸው ከዚህ በፊት የማይረባ ነገር ተናግረዋል ዛሬም የማይረባ ነገር ይናገራሉ የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል ሰምተው የተረዱ ግን የልዑሉ እውቀት ያላቸው በመሆኑ የአምላክን ራዕይ ለማየት የውስጥ ዓይናቸው የተከፈተ ነው ከአንደበታቸው የሚወጣው ቃልም በዚያው ልክ የማይረባ ነው ተብሎ የሚጣል ሳይሆን እንደዚሁ የሰዎችን ዓይን የሚከፍት ነው ከላይ በጠቀስኩት መነሻ ጥቅሴ ላይ የመጽሐፉ ቃል የታተመባቸው ወይም የታሸገባቸው ሰዎች እግዚአብሔር የእንቅልፍን መንፈስ ያፈሰሰባቸው ዓይኖቻቸው የተያዙ ራዕዮቻቸው የተሸፈኑ ነቢያትና ባለራዕዮች ናቸው በዛሬው በሐዲስ ኪዳኑ አነጋገር ወንጌል ሰባኪዎች አስተማሪዎች መጋቢዎችና ሌሎችንም የቃሉ አገልጋዮች ሊያካትት የሚችል ነገር ነው ለምን ይሄ ሆነ ? ስንል የዓይን መጨፈንም ሆነ የራዕይ መሸፈን ብዙ ጊዜ ኃጢአትን ከመለማመድና በኃጢአትም ሳይወቀሱ ሳይናዘዙና ምሕረትን ሳይጠይቁ ጸንቶ በመቆየት የሚመጣ ነገር ነው ሌላው ደግሞ እውነተኛውን የእግዚአብሔር ቃል በትክክል ለመረዳት ካለመፈለግ የተነሳም የዓይን መጨፈንና የራዕይ መሸፈን ይመጣል ለዚህም ነው በ2ኛ ቆሮንቶስ 3 13 _ 16 ላይ የዚያንም ይሻር የነበረውን መጨረሻ ትኵር ብለው የእስራኤል ልጆች እንዳይመለከቱ፥ በፊቱ መጋረጃ እንዳደረገ እንደ ሙሴ አይደለንም ነገር ግን አሳባቸው ደነዘዘ ብሉይ ኪዳን ሲነበብ መጋረጃ ሳይወሰድ እስከ ዛሬ ድረስ ይኖራልና፤ በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ የሙሴ መጻሕፍት በተነበቡ ጊዜ ሁሉ መጋረጃ በልባቸው ይኖራል ወደ ጌታ ግን ዘወር ባለ ጊዜ ሁሉ መጋረጃው ይወሰዳል የሚለን መጋረጃዎች ማለትም የዕይታ ሽፋኖች ሁልጊዜ ከእኛ የሚወሰዱት ሙሉ በሆነ መረዳት ወደ ጌታ ዘወር ባልን ጊዜ ነው ያኔ የታተመ የሚመስለውም መጽሐፉ  ሳይቀር ይገለጥልናል ሌላው ግን ዕይታን ለማግኘትና ከሽፋኖቻችንም ለመውጣት የኃጢአት ሰንኮፋችንን በንስሐ ከልባችን አውጥተን መጣል ነው በ1ኛ ሳሙኤል 3 1 እና 2 ላይ ብላቴናውም ሳሙኤል በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ ራእይም አይገለጥም ነበር በዚያም ዘመን እንዲህ ሆነ የዔሊ ዓይኖች ማየት እስኪሳናቸው ድረስ መፍዘዝ ጀምረው ነበር ይለናል የዓይን መፍዘዝ ባለበት ቦታ ምንጊዜም ቢሆን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነው ራዕይ ደግሞ የሚገለጠው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ስለሆነ የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ በሆነበት ቦታ ሁሉ ራዕይ አይገለጥም ራዕይ አልተገለጠም ማለትደግሞ ራዕይ የለም ማለት ነው ለዚህም ነው በመጽሐፈ ምሳሌ 29 18 ላይ ራዕይ ባይኖር ሕዝብ መረን ይሆናል ሕግን የሚጠብቅ ግን የተመሰገነ ነው በማለት የነገረን ስለዚህ በዔሊ ዘመን የነበረው የክህነት አገልግሎትም ሆነ የሕዝቡ ሁኔታ መረን የወጣ ነበር በዚህ ጉዳይ ላይ የዔሊ ዓይኖች ማየት እስኪሳናቸው ድረስ መፍዘዝ መጀመራቸው ከምንም የተነሳ ሳይሆን ዔሊ  ልጆቹ የእርግማን ነገር እንዳደረጉ አውቆ አልከለከላቸውምና ስለ ኃጢአቱ በቤት ለዘላለም እንድፈርድ አስታውቄዋለሁ ስለዚህም የዔሊ ቤት ኃጢአት በመሥዋዕትና በቍርባን ለዘላለም እንዳይሰረይለት ለዔሊ ቤት ምያለሁ በማለት እግዚአብሔር ለሳሙኤል የዔሊን ነገር ሲናገር እንመለከታለን ሳሙኤልም እስኪነጋ ተኛ፥ ማልዶም ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት ደጅ ከፈተ ሳሙኤልም ራእዩን ለዔሊ መንገር ፈራ ይለናል 1 ሳሙኤል 3 13 _ 15 እግዚአብሔርም በዚያም ቀን በቤቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ በዔሊ አወርዳለሁ እኔም ጀምሬ እፈጽምበታለሁ አለው 1 ሳሙኤል 3 12 እግዚአብሔር ማንኛውንም ነገር አይጀምር እንጂ ከጀመረ ይፈጽማል እግዚአብሔር ጋር ጀምሮ መተው ወይም ማቋረጥ የሚባል ታሪክ የለም ለዚህ ነው ተናግሬያለሁ እፈጽምማለሁ አስቤያለሁ አደርግማለሁ ያለን ኢሳይያስ 46 8 _ 13 ታድያ ለብዙዎች ዛሬም የእግዚአብሔርን አደራረግ ስንናገር ማስፈራራቱን የተያያዝነው አድርገው ይገምቱና ማናናቅ ይጀምራሉ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሃሳብ ውሎ ሳያድር በሕይወታቸው ይፈጸማል ዔሊም ሳሙኤልን ጠርቶ ልጄ ሳሙኤል ሆይ፥ አለ እርሱም፦ እነሆኝ አለ እርሱም፦ እግዚአብሔር የነገረህ ነገር ምንድር ነው፧ ከእኔ አትሸሽግ ከነገረህ ነገር ሁሉ የሸሸግኸኝ እንደ ሆነ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብህ፥ እንዲህም ይጨምርብህ አለው ሳሙኤልም ነገሩን ሁሉ ነገረው፥ አንዳችም አልሸሸገውም ዔሊም እርሱ እግዚአብሔር ነው ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ የእግዚአብሔር ሃሳብ በዔሊም ውሎ ሳያድር ተፈጸመ በመሆኑም ይህንን መልዕክት የምትከታተሉ ቅዱሳን እግዚአብሔር በተናገረው ነገር ጻድቅ ስለሆነ አይደርስም የሚመጣም ነገር የለም ብለን እንደ ዔሊ በግድየለሽነት እርሱ እግዚአብሔር ነው ደስ ያሰኘውን ያድርግ ብንል በእርግጥም እርሱ እግዚአብሔር ስለሆነ ደስ ያሰኘውን ሳይሆን ያለውንና በእኛም ላይ የተናገረውን ሁሉ አንድም ሳያስቀር ያደርጋልና ከእንዲህ ዓይነቱ ማስተዋል ከጎደለው የስንፍና ንግግር እግዚአብሔር ይጠብቀን ቅዱሳን ወገኖች ይህንን ትምህርት ለማንበብ እንዲመቻችሁ ስል በአጭር በአጭሩ ላድርገው ብዬ ነው ተከታታይነት ያለው በመሆኑ እቀጥለዋለሁ እስከዚያው ተባረኩልኝ የምላችሁ

ወንድማችሁ ቀሲስ ዮናስ ጌታነህ ነኝ ( አባ ዮናስ )



No comments:

Post a Comment