Friday 5 December 2014

የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ምዕራፍ ሁለት ክፍል ዘጠኝ



የቤተክርስቲያን ተልዕኮ


ምዕራፍ ሁለት



ክፍል ዘጠኝ



እረኞች ሰንፈዋል


እረኞች ሰንፈዋልና፥ እግዚአብሔርን አልጠየቁትምና አልተከናወነላቸውም፥ መንጎቻቸውም ሁሉ ተበትነዋል
                      
                            ትንቢተ ኤርምያስ 10 21





ባለፈው ትምህርታችን ላይ ባነሳናቸው አርዕስቶች የሕዝብ መሳሳት የራዕይ መጥፋት የሕዝብ እውነተኛን ነገር መጥላትና የመሳሰሉትን በማንሳት በጉዳዩ ላይ ሕዝባችን ሰፊ ግንዛቤና እውነተኛ የሆነ የእግዚአብሔር ቃል መረዳት አግኝቶ ከሳተበት ተመልሶ እንደገናም ከራሱ አልፎ በዚህ ጉዳይ ላይ ላሳሳቱትና ከእግዚአብሔርም መንገድ ላወጡት ሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች ሳይቀር መልስ ሊሰጥ የሚችልበትን የእውቀት መንገድ ማሳየታችን ይታወሳል ይህንን ያነበባችሁም ቅዱሳን በብዙ እንደተጠቀማችሁ ተስፋ አደርጋለሁ ይሁን እንጂ አሁንም ለዚህ  የሕዝብ መሳሳት የራዕይ መጥፋት የሕዝብ እውነተኛን ነገር መጥላትና ለመሳሰሉት ጉዳዮች በዋናነት ተጠያቂዎች እረኞች ናቸውና  ለዚህ ደግሞ ትልቁ ምክንያት የእረኞች ስንፍና ስለሆነ ዛሬ እንግዲህ በክፍል ስምንት ትምህርታችን ላይ የምንመለከተው በዚሁ አርዕስት ላይ ተንተርሰን እረኞች ከስንፍናቸው የሚወጡበትን ሰፊ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ሃሳብ  በመተንተን ከዚህ እንደሚከተለው ልናቀርብ እንወዳለን ስለዚህ በየትኛውም ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት  ሀገር ያላችሁ የየትኛውም አጥቢያ ቤተክርስቲያን መጋቢዎች ወይም እረኞች የሆናችሁ ወገኖቼ በፍጹም ትሕትናና በተዋረደ ልብ ይህን የተጻፈውን የእግዚአብሔርን ሃሳብ የምትጠቀሙበት እንድትሆኑ ስል በጌታ ፍቅር ሆኜ ላሳስባችሁና ላበረታታችሁ እወዳለሁ እግዚአብሔር የሌለበት እግዚአብሔር የማይጠየቅበት እረኝነት ሁልጊዜም በፊት ለፊቱ ያለው ነገር ጥፋትና መበተን ነው እረኛ ደግሞ ብዙ የሆኑ ኃላፊነቶችን ከጌታ የተቀበለና የጌታ የእግዚአብሔርም ባለ አደራ ስለሆነ ስንፍና ከእርሱ አይጠበቅም እረኛ በጎችን ጠቦቶችንና ግልገሎችን የሚጠብቅ ነው ጌታ ጴጥሮስን ለመንጋው ባለ አደራና እረኛም ሲያደርገው ግልገሎቼን አሰማራ ጠቦቶቼን ጠብቅ በጎቼን አሰማራ ነበር ያለው ዮሐንስ ወንጌል 21 15 _ 19 በዚህ ውስጥ ታድያ የሚሰማራ አለ የሚጠበቅ ደግሞ አለ ነገር ግን የሚሰማራውን ስንጠብቅ የሚጠበቀውን ደግሞ ስናሰማራ እንዳንገኝ እንድንጠብቃቸው በኃላፊነት የተሰጡንን በጎች ተጠግተንና ጠንቅቀን ልናውቃቸው ይገባል እንደገናም በጎቹን ለማሰማራትም ሆነ ለመጠበቅ የሚያስችል አቅም እንዳለው ከጴጥሮስ ይልቅ በጴጥሮስ ሕይወት ውስጥ ጌታ ስለተመለከተ ይህንን ሃላፊነትና አደራ ሰጠው እረኞች የምንሆነው የእረኝነት ችሎታው አለን ስላልን ቦታውም ለእኛ የተሰጠን ሆኖ  እረኞች ነን ስላልንና እረኞችም ስለሆንን ሳይሆን  ጌታ እረኛ ስላደረገንና ስለሚያደርገንም  ነው ጌታ ዓሣ  አጥማጁን ጴጥሮስን ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ ብሎት ነበር አሁን ደግሞ የመንጋው ጠባቂና  እረኛ አደረገው የሉቃስ ወንጌል 5 1 _ 11 ዳዊትን ከበግ ጥበቃ ወስዶ በእስራኤል ላይ አለቃና ንጉሥ እንዲሁም የእስራኤል ሁሉ እረኛ አደረገው 2 ነገሥት 7 9 ሳኦልንም አህያ ከመፈለግ አውጥቶ የእስራኤል ንጉሥ አደረገው 1 ሳሙኤል ምዕራፍ 9 እና 10 በሙሉ እናንብብ ሌሎችንም ከመጽሐፍቅዱሳችን አውጥተን ልናነሳ እንችላለን እንግዲህ እረኞች ስንሆን ከዚሁ ጋራ ለመንጋው የምንሰጠው ምግብ ተያይዞ መቅረብ አለበት አለበለዚያ ከዚህ ውጪ እረኝነት ብቻውን ሲሆን ኤርምያስ እንደተናገረው አለመከናወን ይሆናል መንጎችም በጊዜው ሊቀርብላቸው የሚገባውን ምግብ አላገኙምና ቀስ በቀስ በረታቸውን እየለቀቁ እየመነመኑና እየተበተኑ ይሄዳሉ በመሆኑም ተገቢ የሆነውን የጊዜውን ምግብ ለማምጣትም ሆነ መንጋውን በአግባብ ለመምራት እግዚአብሔርን መጠየቅ አማራጭ የሌለው ነገር መሆኑን አውቀን መንጋውን በእኩልነት ለመምራትና ተገቢ የሆነውንም ምግብ ለመስጠት  በጓዳችን እግዚአብሔርን በብዙ ልንማጸነውና ልንጠይቀው ይገባል ለዚህም ነው ጌታም ሲናገር እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ልባም መጋቢ ማን ነው ? በሚል ጥያቄ ወደ ወደ ሐዋርያቱ ብቻ ሳይሆን ወደ እያንዳንዳችንም ጭምር መምጣት የወደደው አያይዞም  ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ባሪያ ብፁዕ ነው እውነት እላችኋለሁ፥ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል ካለን በኋላ ባሪያ ግን ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ ሎሌዎችንና ገረዶችንም ይመታ ይበላም ይጠጣም ይሰክርም ዘንድ ቢጀምር የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል እድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርጋል የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ባሪያ እጅግ ይገረፋል ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል በማለት ተናገረን የሉቃስ ወንጌል 12 42 _ 48 የተጻፈውን እንመልከት ወገኖቼ አገልጋይ መጋቢዎች ታድያ ዛሬ እኛ ምን እያደረግን ይሆን ? እንደዚያ እንደ ልባሙ መጋቢ ምግብን በጊዜ ለመስጠት በመንጋውም ይሁን በእግዚአብሔር ፊት ተፍ ተፍ እያልን ይሆን ? ወይስ ጌታ ይዘገያል ብለን በተለያየ የሃላፊነት ቦታና አገልግሎት አካሉን ለመጥቀም እግዚአብሔር ካስቀመጣቸው የእግዚአብሔር ሎሌዎችና ገረዶች ጋር ባለመስማማት እየተጣላን እየተነታረክንና እየተማታን የራሳችንንም ምቾት በመጠበቅ ለብቻችን እየበላን እየጠጣንና እየሰከርን ይሆን ? መልሱን ለእናንተ ለአንባቢዎች እተዋለሁ ነገር ግን መጣላትን በተመለከተ ደግሞ የጌታም ባሪያ ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም ደግሞም፦ ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሐን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው፥ ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ ነው የሚለን 2 ጢሞቴዎስ 2 24 _ ፍፃሜ የልባም መጋቢነትና ሞያተኝነት ጠፍቶብን እንደ ሰነፉ መጋቢ በየገዛ ምክንያቶቻችን ተይዘንና ጌታም ይዘገያል ብለን እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ደግሞ ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይምና 2 ጴጥሮስ 3 9 እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ያለው ጌታ በድንገት መጥቶብን ጉድ ሊያፈላብን የሚችል ጌታ ስለሆነ  ከወዲሁ ልናስብበት ተጠንቅቀንም ሥራችንን ልንሰራ ይገባል  የሰው ግርፋትስ ይሽራል የእግዚአብሔር ግርፋት ግን ጠባሳው የማይሽርና እጅግም የከፋ ነው የምንታመን አደራም የተጣለብን ሆነን ሳለን ዕድል ፈንታችን ከሁለት መሰንጠቅ ሆኖ ከዚህም ሌላ ከማይታመኑ ሰዎች ጋር መሆኑ ደግሞ ሌላው ትልቁ  የእግር እሳት ሲሆን ነገራችንንም ይበልጥ እየከፋ የሚሄድ ያደርገዋል  ጴጥሮስም ለዚህ ነው እንግዲህ እንደ አሁኑ ዘመን የይወቁልኝ ዓይነት አነጋገር እኔ እኮ በቃ ከዚህ በኋላ እረኛና መጋቢ ነኝ ማለት ሲችል ይህንን የእረኝነት አገልግሎት ጌታ በሃላፊነት ሰጥቶት ሳለ ጴጥሮስ ግን ከዚያ ይልቅ ጌታን ለመውደዱ እንኳን እርግጠኛ መሆኑን የሚያውቅለት ጌታ ብቻ መሆኑን ስለተረዳ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ በማለት ለዚሁ ጌታ  የትሕትናን መልስ ሰጠ እዚህ ላይ አሁንም አንድ በምሳሌ የቀረበ ሃሳብ ላጫውታችሁ እወዳለሁና ተከታተሉ ለብዙ ዓመታት ከእናቱ ጋር የሚኖር አንድ ሰው ነበረ ከዕለታት አንድ ቀን ከእናቱ ተለይቶ እንዲሁ ለብዙ ዘመን ለብቻው ከኖረ በኋላ አንድ ቀን ለእናቱ እንዲህ የሚል መልዕክት ላከ እናቴ ሆይ  ጳጳስ ሆኜልሻለሁ ደስ ይበልሽ ከዚህ በኋላ ታሪክ ተለውጦአልና የሚያሰጋሽ ነገር የለም ሲል መልዕክቱን ለላካቸው ሰዎች በአደራ ለእናቴ እንዲህ ስትሉ ንገሩልኝ በማለት አስተላለፈ መልዕክቱን የሰማችው እናቱ ግን እርሱ ትደሰታለች ብሎ በጠበቀው መንገድ ሳትደሰት ትቀርና  በምትኩ የለቅሶና የዋይታ ሮሮዋን አስተጋባች ይሄን የሰማ ልጇም በጣም ይደነግጥና ምነው እናቴ ጳጳስ ሆኜ በመሾሜ ደስ ሊልሽና ሐሴትም ልታደርጊ ሲገባ ይሄ ሁሉ ሮሮ ተገቢ ነው እንዴ ? በማለት ደግሞ ቢልክባት እርሷም ስትመልስ አዎ ድሮ እዚህ ነገር ውስጥ ሳትገባና ሳትሾም በፊት በራስህ  ኃጢአት ነበር የምትጠየቀው አሁን ግን በብዙዎች ኃጢአት ተጠያቂው አንተ ስለሆንክ ይህ ነገር ስለከበደኝ ነው እንዲህ ምርር ብዬ ያለቀስኩት ገናም አለቅሳለሁ አለችው ይባላል እንግዲህ  ጴጥሮስ አሁንም በዚህ አላበቃምና እንደዚህች እናት ልቅሶና ሮሮ ውስጥ ባይገባም ነገር ግን እያዘነ  አንተ ሁሉን ታውቃለህ ሲል ለጌታ መልስ የሰጠው  ከዚህ የተነሳ ነው ጌታም ያለምንም ማንገራገር ሙሉ የሆነውን የእረኝነት ሃላፊነት ለጴጥሮስ በአደራ አሳልፎ ሰጠው  ወገኖቼ ጌታ በሃላፊነት የሰጠን ሹመት ብናውቅበትና ቢገባን ከሌላው ለይቶ ጮቤ እንድንረግጥ የሚያደርገን በቃ እንግዲህ አስብሎም በሌሎች ወገኖቻችን ላይ እንድንኩራራ የሚያደርገንና የሚያዘልለን ደረታችንንም እንድንነፋ የሚያደርገን አይደለም እንደገናም ከሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጋራ በሰላምና በፍቅር በስምምነትም መኖር ሲገባን አብሮም በመቀባበልና በመያያዝ ማገልገል ሲጠበቅብን እራስን ከመውደድ የተነሳ  እኔ ብቻ ስንል የምንጣላበትና የምንበጣበጥበት ሊሆንም  አይገባም በእርግጠኝነት ካሰብንበት ደግሞ እኛም እንደዚያች እናት ግድ ብሎን ሃላፊነቱንና አደራውንም በአግባቡ ካልተወጣነው በብዙ የሚያስጠይቀን የሚያስቀጣንም ነውና ይህንኑ እውነት ተረድተን  በብዙ ጸሎትና ምልጃ ከብዙ እንባም ጋራ የጌታን ፊት እንድንፈልግ የሚያደርገን ሊሆን ይገባል የጴጥሮስ ሃዘንም እንግዲህ የሚያስታውሰን በጥቅሉ ይህንን ነው ከጌታ የተሰጠን ሃላፊነት በቀላሉ ልንወጣው የማንችል በመሆኑ ምን ያህል ከባድና የሚያስጠይቅ መሆኑን ጭምር ያመለክተናል ከአንድ መንፈሳዊ አገልጋይና መጋቢም የሚጠበቀው ይሄ ነው መጋቢዎች ዋኖች ብቻ ሳይሆኑ ስለብዙዎች ነፍስ የሚተጉ በመሆናቸው በዕብራውያን 13 17 ላይ ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፥ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፥ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፥ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ የሚል ቃል ተጻፈልን ታድያ ቅዱሳኑ እንዲታዘዙልንና እንዲገዙልን የምንፈልግ ደጋግ መጋቢዎች ከቅዱሳኑ መገዛትና መታዘዝ በፊት ቀድመን የነርሱን መገዛትና መታዘዝ ሳንጠብቅ እረኞች እንደመሆናችን መጠን ለነፍሳቸው መትጋታችንን በእግዚአብሔርና በቅዱሳኑም ፊት በእርግጠኝነት ማሳየት አለብን  ሌላውን የመታዘዙንና የመገዛቱን ነገር ግን እኛ ሳንፈልገውና ተገዛ ታዘዝ እያልንም  በመድረኮቻችን ላይ ሳናውጅ  ሳንጨቃጨቅም እራሳቸው ቅዱሳኑ ለነፍሳቸው ግድ ብሎን ያደረግነውን ትጋትና ታማኝነት አይተው በፈቃዳቸው ሲገዙልንና ሲታዘዙንም እናያቸዋለን በዚህ ጉዳይ አንድ ስንኳ ልታደርጉ እንዳይቻላችሁ ታያላችሁን ? እነሆ፥ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል የተባለው ኢየሱስ ትልቁ ምሳሌያችን ነው የዮሐንስ ወንጌል 12 19 እንደገና አሁንም በዚህ ጉዳይ ከመንጋውም ጋር ብዙ ግጭቶችን ፈጥረን በመንጋው መካከል መበታተን መለያየትና መከፋፈልም እንዳይመጣ ሐዋርያው ጴጥሮስ በ1ኛ ጴጥሮስ 5 2 _ 4 ላይ በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ ያለንን ልናስታውስ ይገባል  እዚህ ላይ አሁንም አንድ ወንድም በሕይወቱ ባለፈበት ነገር ያጫወተኝን አንድ ምሳሌ ላወጋችሁ እፈልጋለሁ ይህ ወንድም ዛሬ የጌታ አገልጋይ ነው ነገር ግን የትላንት ሕይወቱ እጅግ አሳፋሪና ዱርይነት የተሞላበት ነበረ በዚህ ላይ ደግሞ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት እምነት ተከታይ ነው ነፍስ አባትም አለው ስለዚህ እርሱ እንዳጫወተኝ ከጓደኞቼ ጋር በርጫ ልልና ጫት ልቅም ጫቴን ከመርካቶ ገዝቼ በግራና በቀኝ ክንዴም ሸጉጬ ሲጋራዬን እያንቧለልኩና ከተለያዩ ኮረዶች ሴቶች ጋር እየተሳሳቅሁ ስሄድ ያዩኝ ነፍስ አባቴ እኔ አይቻቸው ብሳቀቅም እንኳን እርሳቸው ግን ምንም ሳይላቸውና ሳይሳቀቁ ልጄ እግዚአብሔር ይባርክህ እያሉ መስቀላቸውን ያሳልሙኛል አለ አንድ ቀን ግን ጌታ ደረሰልኝና ያን ሁሉ ጉዴን አስጣለኝ በአፌ ውስጥ ገብቶ በሚንቧለለው የሲጋራ ጢስ ፋንታ ዝማሬን በአፌ ጨመረ  በግራና በቀኝ ጎኔ ከወዳጆቼ ጋር በመሆን ልቅማቸው በያዝኳቸው ጫቶች ፈንታ መጽሐፍቅዱሴን ሸጉጬና ሁሉም ነገር ቀርቶብኝ ኢየሱስን ብቸኛ ወዳጄ በማድረግ ከኢየሱስ ጋር ሆኜ  ስዘምር ዳግመኛ ያገኙኝ ነፍስ አባቴ አቅላቸውን ጥለው አበስ ገበርኩ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ አንተም ጴንጤ ሆንክ ? ሲሉ የድሮ ፈገግታቸው ጠፍቶ ገፍትረውኝና አቃለውኝ የሄዱትን አልረሳውም ያለኝን እኔም አልረሳውም ይህ ወንድም አሁንም አያይዞ ሲነግረኝ ነገሩ ግር አለኝና እኚህ ቄስ ምን ነካቸው ? አልኩኝ አለ ጥንት ጫቴን ይዤ ሲጋራዬን እያንቧለልኩ ከሴት ኮረዳዎች ጋር  ስሽካካ ምንም ሳይሉኝ መስቀል ያሳለሙኝ ዛሬ መጽሐፍቅዱሴን ይዤ የጌታዬን መዝሙር  ስዘምር እንዲህ የጠሉኝ አለ ምክንያት አይደለም ስለዚህ እኚህ ቄስ ድሮም ቢሆን ለነፍሴ የሚተጉ አልነበሩምና ካዛሬ ጀምሮ ነፍስ አባትነታቸውን ከላዬ አንስቻለሁ በማለት ሙሉ ለሙሉ ጌታን መከተል ጀመርኩኝ ብሎ አጫወተኝ ስለዚህ ዛሬም የእኛ የመጋቢዎች ታሪክ ከዚህ የተለየ ታሪክ አይሆንም ምዕመኖቻችንን ለነፍሳቸው ሳንተጋላቸው ሳንመክራቸው ሳንጎበኛቸው ሳንጸልይላቸው የችግራቸውም ተካፋይ ሳንሆን እገሌ እገሊት አልተገዛም አልተገዛችም አልታዘዘም አልታዘዙም ብንል ይህ እኛኑ በብዙ የሚያስገምተን ከሚሆን ውጪ ሌላ ትርጉም አያሰጠንምና  ልክ አይሆንም ይህ እንዲሆን ከወደድን ደግሞ ከእኛ ከአገልጋዮች የሚጠበቀውን ሁሉ ያለማቋረጥ ማድረግ ነው በመጨረሻም በመልዕክታችን በዋናነት ወዳነሳነው የጴጥሮስ ሃሳብ ስንመጣ  ጴጥሮስ በፍጻሜው ሰዓት ለጌታ የሰጠው  መልሶቹ ሁሉ ትክክለኛና እውነተኝነት ያላቸው ናቸው እኛ ስለእኛ እንዲህና እንዲያ ከምንል ይልቅ እርሱ ከእኛ በላይ የእኛን ሁሉንም ነገር በእርግጠኛነት ጠንቅቆ ያውቃል ደግሞም የሚወድ ነው መንጋውን መጠበቅና ማሰማራት የሚችለው ከሚወድ እረኛ የተወደደ ነገር ይወጣል እንደገናም ጥበቃውና ስምሪቱ ጸጥ ያለና የማያሰጋ ስለሆነ ከጀርባው ሌላ ነገር ይመጣል ተብሎ የሚታሰብ አይሆንም ከዚህም የተነሳ በጥያቄውና በመልሱ ጴጥሮስና ጌታ ተግባብተዋልና  ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ሁሉንም ነገር ለጴጥሮስ በአደራ ተወለት በጌታ የተወደዳችሁ መጋቢዎች መንፈሳውያን መሪዎችና የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በሙሉ በዚህ በምናነበው ቃል ጌታ እግዚአብሔር በብዙ ይባርከን ትምህርቱ ይቀጥላል በተከታዩ የትምህርት ክፍለ ጊዜ እስከምንገናኝ ሁላችሁንም ጌታ ይባርካችሁ ለማለት እወዳለሁ


ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ

No comments:

Post a Comment