Sunday 7 December 2014

የግጥሙ ርዕስ በራእዩ መንገድ ባለ ራእዩ

የግጥሙ ርዕስ

 



በራእዩ መንገድ ባለ ራእዩ

 




በሰዎች ተከሶ በሰው ተወንጅሎ
ባለ ዕዳ ሆኖ ነገር ተመሳቅሎ
ዘመኑን ጨረሰ ዮሴፍ በስደት 
መኖርያው ሆኖለት የግብጽ ወህኒ ቤት
እግሮቹም ደከሙ በእግር ብረት
የተሸጠው ዮሴፍ ለዚያ ለባርነት
ነገር ግን እግዚአብሔር ከላይ ከጸባኦት
ለዕብራዊው ዮሴፍ አበዛለት ምሕረት
የእግዚአብሔር አሠራር ከሰዎች ይለያል
እንዳየሁ አልፈርድም አልበይንም ይላል
የሰዎችን ኑሮ ለውጦ የሚያቀና 
ልዑል እግዚአብሔር በሰማይ አለና
ዮሴፍ በእስር ቤት ፈጽሞ ተጽናና
ደግሞም ሕልም ፈቺ አደረገውና 
በታሪክ ማኅደር በሕይወት ጎዳና
የተተበተበው ተቋጥሮ በእስር 
በላይኛው ጥበብ በልዑል እግዚአብሔር
ይፈታ ጀመረ ምስጢር ሆኖ ላይቀር
ዘመኑ በእስር ቤት ያላበቃው ዮሴፍ 
ለክብር ለሹመት በንጉሡ ደጃፍ 
ይፈለግ ጀመረ ሳይውል ሳያድር
ሕልም ፈቺ ሆኖ ሊገለጥ በክብር
ሕልሞቹም ተፈቱ በተራ በተራ
ዮሴፍ ተቀመጠ በነገሥታት ጎራ
ይህንንም ሥልጣን ዮሴፍ ተቀበለ
አስተዳዳሪና መሪ ነህ ተባለ
ለግብጽ ሀገር ሁሉ በረከት የሆነ
ሕልሞችን በመፍታት እየተነተነ
ድንገት ሳያስበው ወንድሞቹን አየ
ዮሴፍም አወቀ ላፍታም አልዘገየ 
ነገር ግን አሁንም ያላወቀ መስሎ
የባዕድ ሀገር ሹም ሆኖ አድሮ ውሎ
በወንድሞቹ ፊት ራሱን ከልሎ
ይመረምር ጀመር እያጠያየቀ
በተለይ ወንድሙን ቢንያምን ናፈቀ
ልቅሶ እየመጣ ቢያጨናንቀው
በወንድሞቹ ፊት ዮሴፍን ሊገልጠው
ዮሴፍ ፈጥኖ ሄደ ወደ እልፍኙ ገባ
ፍጹም አለቀሰ አፈሰሰ እንባ
ከዚያም በመቀጠል ዮሴፍ ነኝ ለማለት
ራሱን ለመግለጥ በወንድሞቹ ፊት
እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ ቢላቸው
ምሕረትን ለመኑ ከእግሮቹ ሥር ወድቀው
ታሪኩ አብቅቷል ሞቷል የተባለው 
ንቀት የጠገበ ተሰኝቶ ሕልመኛው 
ሕልሙም ሆነ ግቡ ሕልም ሆኖ አልቀረም
ፍጻሜን አግኝቶ ተሰማ ለሁሉም 
ዛሬም ለቅዱሳን እግዚአብሔር የሰጠን
በውስጣችን ያለው ራዕይ እውን ሊሆን
ጌታ መንፈስቅዱስ በእኛ ውስጥ ይተጋል
የተሰጠን ሥራ በእርሱ ይጠናቀቃል

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment