Friday 5 December 2014

የአዋልድ መጻሕፍት በእግዚአብሔር ቃል ሲፈተሽ ምጽዋት ከሞት ታድናለችና ከኃጢአትም ሁሉ ታነጻለችና መጽሐፈ ጦቢት 12 ፥ 9

የአዋልድ መጻሕፍት በእግዚአብሔር ቃል ሲፈተሽ

ምጽዋት ከሞት ታድናለችና ከኃጢአትም ሁሉ ታነጻለችና 

መጽሐፈ ጦቢት 12 ፥ 9

ኃጢአትን መናዘዝ መልካምና ተገቢም እንደሆነ የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል ምሣሌ 28 ፥ 13 ፤ 1ኛ ዮሐንስ 1 ፥ 7 _ 10 ፤ ያዕቆብ 5 ፥ 16 ታድያ እርስ በእርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለሌላው ይጸልይ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች ቢለንም እኔ ግን አናዛዥ ነኝ እንጂ ተናዛዥ አይደለሁም የሚል እንዳይኖር ኢፈለጠ ወኢሌለየ እስመ ኩሎሙ አበሱ ወጌገዩ ወኀደጉ ስብሐተ እግዚአብሔር ትርጉም ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል አለን ሮሜ 3 ፥ 23 እንደገናም ወእመሰ ንብል አልብነ ኃጢአት ንጌጊ ለርእስነ ወአልቦ ርትዕ ኀቤነ ወእመሰ ነገርነ ወአመነ ኃጢአተነ ምዕመን ውእቱ ወጻድቅ ከመ ይኅድግ ለነ ኃጣውኢነ ወያነጽሐነ እምኩሉ አበሳነ ትርጉም ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን እውነትም በእኛ ውስጥ የለም በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው ይለናል 1ኛ ዮሐንስ 1 ፥ 8 እና 9 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር መጥቶ ደሙን በማፍሰስ ለሰው ልጆች ሁሉ የኃጢአትን ሥርየት እስኪሰጥ ድረስ በሰው ልጆች መካከል ልዩነት ሳይኖር ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ነበር እንደገናም በዚህ ጌታ በኩል የኃጢአትን ሥርየት ሳይቀበሉ ኃጢአት የለብኝም ማለት ደግሞ ራስን ማሳት ነውና አይገባም በመሆኑም ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው ስለሚለን ቃሉ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1 ፥ 15 የሰው ልጅ በዚህ ጌታ ከዳነ በኋላ እርስ በእርሱ ባለ ግንኙነት ኃጢአቱን ከመናዘዙ በፊት እንደገናም ለመፈወስ አንዱ ለሌላው ከመጸለዩ በፊት በቅድሚያ የኃጢአትን ሥርየት ለመቀበል ሰው ሁሉ ወደ ኢየሱስ መምጣትና ኃጢአቱንም ለኢየሱስ ክርስቶስ መናዘዝ አለበት የተወደዳችሁ ወገኖች ይህንን የኃጢአትን መናዘዝ ያነሳንበት ምክንያት አለን ከላይ በመግቢያ ጥቅሳችን ላይ ባነሳነው ሃሳብ መሠረት በአዋልድ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው የጦቢት መጽሐፍ ምጽዋት ከሞት ታድናለችና ከኃጢአትም ሁሉ ታነጻለችና ስለሚል ብዙዎች በዚህ በጦቢት መጽሐፍ ሃሳብ ላይ ተመሥርተው ከኃጢአታቸው ለመንጻትና ከሞትም ለመዳን ምጽዋት የሚመጸውቱ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ናቸው ይህ ማለት ደግሞ ለእያንዳንዱ የኃጢአት ዓይነት በቀኖና መጽሐፍና በሌሎችም ተመሳሳይ መጽሐፎች ቅጣት መወሰኑ ነው ተናዛዡ ኃጢአቱ ሊያስከፍለው የሚችለውን ቅጣት በመጽሐፈ ቀኖና እንደታዘዘው ራሱ በመቀጣት እንዲከፍል የሚደረግበት ሥርዓት በመሆኑ የጦቢትም መጽሐፍ ከነዚህ የቀኖና መጻሕፍት ጋር የሚስማማና ይህንኑ የሚደግፍ በመሆኑ ፍጹም የተሳሳተ ነው የኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል በመስቀል ላይ መሰቃየቱና መሞቱ ሰው ሁሉ የየራሱን ኃጢአት እየተሸከመ ኃጢአት ሊያስከፍለው የሚችለውንም ዋጋ በገንዘቡ ልዋጭ እየተመነና እየከፈለ የኃጢአቱን ይቅርታ እንዲቀበል አይደለም እንዲህ ብሎ ማሰብና የጦቢትንም መጽሐፍ እንደማስረጃ ማቅረብ ደግሞ ኢየሱስ ለእኛ ሲል ያፈሰሰውን ደም ማክፋፋትና በራስ ላይም እንደመቀለድ ነውና የባሰ ፍርድ እንዳንቀበል ቢቀርብን ይሻላል ዕብራውያን 10 ፥ 29 _ 31 ከዚህም ሌላ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር የእውነት ቃል ላይ አምኖ መራመድ ካልቻለ የጊዜውንና የዘላለሙን ፍርድ ከእግዚአብሔር ይቀበላል እንጂ በተገለጠው የእግዚአብሔር እውነት ላይ ግን መቀለድ አይችልም ዳንኤል 12 ፥ 2 ፤ ማቴዎስ 25 ፥ 46 ፤ ዮሐንስ ወንጌል 5 ፥ 29 በተጨማሪም ከጮራ መጽሔት ቁጥር 8 ላይ እንዳገኘሁት የመጽሔቱ አዘጋጅ በገንዘብ መቀጫ የኃጢአት ዕዳ አይከፈልም ካሉ በኋላ ለመሆኑ ሥርየትን ይቸረችር ዘንድ በጅምላ የገዛ ነጋዴ ማነው ? በማለት ነገሩን ሲያስቡት የእግዚአብሔርን ጸጋ ሊያክፋፋ የተነሳ የመናፍስት አሠራር ተልዕኮ መሆኑን ስለተገነዘቡት እግዚአብሔር ይገስጽህ በክርስቶስ ደም አትቀልድ አንተ ሰይጣን በማለት ገስጸውታል (ምንጭ ጮራ መጽሔት ቁጥር 8 ገጽ 18 )ታድያ ይህ በጌታችንና በሐዋርያትም የተደረገና ተገቢም የሆነ ተግሣጽ ነው ማቴዎስ 4 ፥ 1 _ 11 ፤ የሐዋርያት ሥራ 8 ፥ 14 _ 23 ፣ የሐዋርያት ሥራ 13 ፥ 8 _ 12 ፣ የሐዋርያት ሥራ 5 ፥ 3 _ 11 ወገኖቼ እኛም እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል በተገቢው መንገድ ባለማወቅ በምናደርገው ለነፍስ መዳኛና ለኃጢአት ይቅርታም ስንል በምንሰጠው ሳንቲም በደሙ መቀለዳችን ነውና ተገስጸን በፍጻሜው ለሰይጣን ተላልፈን እንዳንሰጥ ከውዲሁ ልናስብበት ልንጠነቀቅ ይገባል እንደ እግዚአብሔር ቃልም እራሳችንን ልናስተካክልና ወደ እውነቱም መጥተን በዚህ ጌታ ልንድንና የኃጢአታችንንም ሥርየት ልንቀበል ያስፈልጋል እግዚአብሔር ለዚህ ይርዳን ትምህርቱ በዚህ የተጠቃለለ ሳይሆን የሚቀጥል ነውና በጌታ ፍቅር እንድትከታተሉ አሳስባለሁ ተባረኩ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment