Thursday 4 December 2014

ቤተክርስቲያን ክፍል አስራ አራት



ቤተክርስቲያን



ክፍል አስራ አራት



ቤተክርስቲያን የበኩራት ማኅበር ስብስብ ሆና ቃሉን የምትታዘዝና የምታደርግ ናት



ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥
ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት
በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ
እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች የአዲስም ኪዳን
መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር
ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል

              ዕብራውያን 12 23


የክርስቶስ አካል ልትሆን ክርስቶስን ራስ ያደረገች ቤተክርስቲያን ወደዚህ ወደ በኩራት ማኅበር የደረሰች መሆን ይጠበቅባታል ይህ የበኩራት ማኅበር ደግሞ የክርስትና እና  ክርስቶስንም የመምሰል መጨረሻ ሳይሆን መጀመርያና መግቢያ በርም  ነው በ2ኛ  ጴጥሮስ 1 3  ላይ የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ ስላለን ቃሉ  የጠራንን በማወቅ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል በተሰጠን በሚሆነው ነገር ሁሉ  እርሱን እግዚአብሔርን ልንመስል ተጠርተናል እርሱን የምንመስለው ደግሞ የበኩራት ማኅበር ልንሆን ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈሳዊ ልደት አግኝተን ማለት ልጆች ሆነን ተወልደን ራስ ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ ተጠግተን አካል የመሆን ምሥጢር ገብቶን ምግብንም ለመቀበል ከአካሉ ጋር ተገጣጥመን በምንያያዝበት ጊዜ በመገጣጠምና በመያያዝ ውስጥ ከተቀበልነው ምግብ የተነሣ እግዚአብሔር በሚሰጠን ማደግ ውስጥ ራሱን እግዚአብሔርን እንመስላለን ቆላስያስ 2 19 እና 20 1ኛ ጢሞቴዎስ 4 6 _ 10 1 ጢሞቴዎስ 6 3 _ 10  ወደዚህ እግዚአብሔርን የመምሰል መጨረሻ የምንመጣው ግን ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈሳዊ ልደት በማግኘት ወደ በኩራት ማኅበር ውስጥ ገብተን ተጨምረንና በዚህ በበኩራት ማኅበር ውስጥ አልፈን መጥተን ነው ማደግና እግዚአብሔርን መምሰል ያለው በመወለድ ውስጥ ነው እግዚአብሔርን መምሰል የሚችል ሰው የተወለደ ነው ያልተወለደ ሰው ማደግም ሆነ እግዚአብሔርን መምሰል አይችልም ለዚህም ነው በያዕቆብ መልእክት ላይ ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን በማለት የነገረን ያዕቆብ 1 18 የተወለደ ሰው ማደግ አለበትና ጴጥሮስ ደግሞ እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ አለን 1 ጴጥሮስ 2 1 _ 3  አሁንም ተወልዶ ለማደግ የቃሉን ወተት መመኘት ብቻ በቂ አይደለም በያዕቆብ መጽሐፍ ላይ እንደተነገረው ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል ራሱን አይቶ ይሄዳልና፥ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፥ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፥ በሥራው የተባረከ ይሆናል ይለናልና ያዕቆብ 1 22 _ 25 ነፍሳችንን ማዳን የሚችለውን በውስጣችን የተተከለውን ቃል በየዋኅነት መቀበል ለቃሉ መታዘዝና ቃሉን ማድረግ ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክተን በእርሱ መጽናት ስንጀምር አንደኛ በሥራችን የተባረክን እንሆናለን ሁለተኛ እግዚአብሔርን የመምሰል ሙላቱ በእኛ ይገለጣል 2 ጴጥሮስ 1 2 _ 11 እንግዲህ ይህንን ሁሉ የገለጽኩበት ምክንያት ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ቃል መንፈሳዊ ልደትን አግኝታ የበኩራት ማኅበር እንድትሆን ከተጠራችበት ጀምሮ ለእግዚአብሔር ቃል ራሷን ሰጥታ የቃሉን ወተት ተመኝታና ቃሉንም በየዋሃት መንፈስ ተቀብላ ስታድግ በቃሉም በመጽናት ቃሉንም ወደ መስማትና ወደ ማድረግ ሕይወት ስትመጣ የሚሆነውን ነገር  ለማሳየት ወድጄ ነው የበኩራት ማኅበር የመሆንን ጉዳይ  ስናስብ ይህንን ሁኔታ ከእስራኤል ጋር እንድናያይዝ ያደርገናል ክርስቶስ ራስ በሆነባት ቤተክርስቲያንና በብሉይ ኪዳን በነበሩት እስራኤል መካከል በትይዩነት የምንመለከታቸው ብዙ ሃሳቦች አሉ ክርስቶስ ራስ የሆነባት ቤተክርስቲያን የበኩራት ማኅበር እንደተባለች ሁሉ በብሉይ ኪዳን የነበሩት እስራኤልም በኩር ተብለዋል በዘጸአት 4 22 እና 23  ላይ ፈርዖንንም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦እስራኤል የበኵር ልጄ ነው ይገዛልኝ ዘንድ ልጄን ልቀቅ አልሁህ አንተም ትለቅቀው ዘንድ እንቢ አልህ እነሆ እኔ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ ትለዋለህ ይለናል ልዩነቱ በሐዲስ ኪዳን ባለችው ክርስቶስን ራስ ባደረገች ቤተክርስቲያን ያለ የበኩራት ማኅበር አጠቃላይ ስብስብ ያለበት የበኩራት ማኅበር ነው ስኩቲስ  የግሪክ ሰው ባርያ ጨዋ ወንድ ሴት አይሁዳዊ አሕዛባዊ ሳንል በክርስቶስ በሆነልን ሥራም ልዩነት ሳናደርግ አንድ ቤተሰብ ስለሆንን የበኩራት ማኅበርነቱ ሰማያዊ የሆነና ነገድ ጎሳ ቋንቋ  ሳይለይ ሁሉን ያጠቃለለ ነው በብሉይ ኪዳን ያለ የእስራኤል በኩርነት ግን ለእስራኤል ብቻ የሆነ በኩርነት ነው ነገር ግን እስራኤል የእግዚአብሔር በኩር ሆነውና ከፈርኦንም ባርነት ተላቀው በበኩርነታቸው ለእግዚአብሔር እንደሚገባ አልሆኑም ለቃሉ ሳይታዘዙ ቀሩ ለነውርም የተለዩ ሆኑ ረከሱ በትንቢተ ሆሴዕ 9 10 ላይ እስራኤልን በምድረ በዳ እንዳለ ወይን ሆኖ አገኘሁት አባቶቻችሁንም ከመጀመሪያዋ ዓመት እንደ በለስ በኵራት ሆነው አየኋቸው እነርሱ ግን ወደ ብዔልፌጎር መጡ፥ ለነውርም ተለዩ፥ እንደ ወደዱትም ርኩስ ሆኑ ይለናል በሐዋርያት ሥራ 7 38 ላይ ደግሞ ይህ ሰው በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በማኅበሩ ውስጥ የነበረው ነው፤ ይሰጠንም ዘንድ ሕይወት ያላቸውን ቃላት ተቀበለ ለእርሱም አባቶቻችን ሊታዘዙት አልወደዱም፤ ነገር ግን ገፉት በልባቸውም ወደ ግብፅ ተመለሱ አሮንንም በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና አሉት በዚያም ወራት ጥጃ አደረጉ ለጣዖቱም መሥዋዕት አቀረቡ፥ በእጃቸውም ሥራ ደስ አላቸው እግዚአብሔር ግን ዘወር አለ የሰማይንም ጭፍራ ያመልኩ ዘንድ አሳልፎ ሰጣቸው፥ በነቢያትም መጽሐፍ እናንተ የእስራኤል ቤት፥ አርባ ዓመት በምድረ በዳ የታረደውን ከብትና መሥዋዕትን አቀረባችሁልኝን፧ ትሰግዱላቸውም ዘንድ የሠራችኋቸውን ምስሎች እነርሱንም የሞሎክን ድንኳንና ሬምፉም የሚሉትን የአምላካችሁን ኮከብ አነሣችሁ፤ እኔም ከባቢሎን ወዲያ እሰዳችኋለሁ ተብሎ እንዲህ ተጽፎአል በማለት ተናገረ ዘጸአት 7 38 _ 43  እነዚህ የእግዚአብሔር በኩር የሆኑት እግዚአብሔርም በኩሬ ብሎ ተማምኖ ከግብጽ የባርነት ቤት ያላቀቃቸው እስራኤል ያልተጠበቀ አሳፋሪ የሆነ ተግባር መፈጸም ጀመሩ ወደ ብዔልፌጎር መምጣታቸው ለነውር መለየታቸው መርከሳቸው አሮንንም በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን በማለት ጥጃ ማቆማቸው መሥዋዕት ማቅረባቸው ብቻ ሳይሆን ለዓመታት አብሯቸው ሲመራቸው የነበረውን የእግዚአብሔር ሰው ሙሴን ሳይቀር ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅም ማለታቸውና ሙሴንም ገፍተዉት በልባቸው ወደ ግብጽ መመለሳቸው እጅግ የሚደቅ አሳዛኝ የሆነም ድርጊት ነበር ታድያ የዚህ ሁሉ ችግር መንስዔው ምንድነው ስንል ሙሴ ሊሰጣቸው ለተቀበለው ሕይወት ላላቸው ቃላት እስራኤል ያለመታዘዛቸው ነው  እንግዲህ በዚህ ጉዳይ ላይ እስራኤል ብቻ ሳይሆኑ እኛም የሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የበኩራት ማኅበር የሆንን ቅዱሳን የጽዮን ሀገር ተጓዦች ሊሰጡን ላሉ ሕይወት ላላቸው  ለእግዚአብሔር ቃሎች በማንታዘዝበት ጊዜ የምንሆነው እንዲህ ነው ባልታዘዝን ቁጥር ለነውር እንለያለን የእግዚአብሔርም ሥዕል ከፊታችን ይጠፋና በምትኩም ጣኦት የሆነን ነገር በፊታችን እናኖራለን ለእርሱም እንሰግዳለን የሕይወትን ቃል ያመጡልንንና የሚያመጡልንንም ባሮች እንገፋለን አናውቃቸውምም ብለን ሽምጥጥ አድርገን እንክዳቸዋለን ይህ ልንታዘዝ እንቢ ያልነው ቃል እኮ ከባርነት ቤት አውጥቶ ብኩርናን የሰጠን ያሳደገንና ለራሱ ለእግዚአብሔር እንድንሆን ያደረገን ቃል  ነው የእስራኤል ሕዝብ የተለየ ዕቃ የተለየ  መዝገብ ነበር በእንግሊዘኛው እንዲህ ይለዋል  The nation was to be a " special treasure " to God " a kingdom of priests and a holy nation "  የመንግሥቱ ካህንና ቅዱስ ሕዝብ ነበር ዘጸአት 19 :  5 _ 6  ነገር ግን ለነውር ተለየ ረከሰ እኛም በሐዲስ ኪዳን ያለን ሕዝቦች የተመረጥን የንጉሥ ካህናትና  ቅዱስ ሕዝብ ነን እንግሊዘኛው አሁንም  The Church is now to him a chosen generation a rayol priesthood a holy nation . His own special people  ይለዋል 1ኛ ጴጥሮስ 2 9 ነገር ግን አሁንም እስራኤልን ያነወረ ነገር እኛንም አነወረን ለቃሉ ያለመታዘዝን ነገር ሐዋርያው በሮሜ መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ላይ በአጭሩ እንዲህ ብሎ ያስቀምጠዋል እንግዲህ ምንድር ነው ?  እስራኤል የሚፈልጉትን አላገኙትም ፤ የተመረጡት ግን አገኙት ሌሎቹም ደነዘዙ፤ እንዲሁም ዓይኖቻቸው እንዳያዩ ጆሮቻቸውም እንዳይሰሙ እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስን እስከ ዛሬ ድረስ ሰጣቸው ተብሎ ተጽፎአል ዳዊትም፦ማዕዳቸው ወጥመድና አሽክላ ማሰናከያም ፍዳም ይሁንባቸው ዓይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፥ ጀርባቸውንም ዘወትር አጉብጥ ብሎአል እንግዲህ የተሰናከሉ እስኪወድቁ ድረስ ነውን ?  እላለሁ አይደለም ፤ ነገር ግን እነርሱን ያስቀናቸው ዘንድ በእነርሱ በደል መዳን ለአሕዛብ ሆነ ይለናል ወገኖቼ በእግዚአብሔር ቤት ተቀምጠን እግዚአብሔርን ከመበደል እግዚአብሔር ይጠብቀን በእኛ የበደል ብዛት ለብዙዎች መዳን ቢሆንም በእኛ ሕይወት ላይ ግን የሚያመጣውና እያመጣም ያለ አስከፊ ነገር አለ የዓይን መጨለም እስከ ዛሬ የሆነ የእንቅልፍ መንፈስ መደንዘዝና መጉበጥ ከበደል ብዛት የሚመጣ ነው ይሄ ነገር እየገፋ ከመጣ ደግሞ የሕይወት መቆረጥንና ያለጊዜም መወገድን ሁሉ ሊያስከትል ስለሚችል እጅግ አስፈሪ ነው በዚህ ክፍል በጣም የሚያስፈራ ቃል ለእስራኤል እንዲህ ሲል ተጽፎአል እግዚአብሔር ግን ዘወር አለ የሰማይንም ጭፍራ ያመልኩ ዘንድ አሳልፎ ሰጣቸው በዚህ ብቻ አላበቃም ከባቢሎን ወዲያ እሰዳችኋለሁ አላቸው ወገኖቼ የእግዚአብሔር ዘወር ማለት ለእሥራኤል ብቻ ሳይሆን ካልተመለስን ለእኛም ነው በብሉይ ኪዳን ብቻ ሳይሆን በሐዲስ ኪዳንም ተላልፎ መሰጠት አለ እግዚአብሔር ይህን አደረገ ማለት ደግሞ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ለሁላችንም ግልጽ ነው ስለዚህ ይህ በሕይወታችን እንዳይሆን ዛሬውኑ ከተኛንበት የእንቅልፍ መንፈስ እንድንነቃና ጌታን ከምንበድልበት ነገር እንድንወጣ ንስሐም እንድንገባ ያስፈልገናል  ክርስቶስ የሚፈልጋት የሚፈልጋት ቤተክርስቲያን ደግሞ ከነውር የጸዳችና የፊት መጨማደድ የሌለባትን ነው እግዚአብሔር በዚህ እውነት ያግዘን ይርዳን አሜን


ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን

ኤፌሶን 1 ፥ 4




እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ

ኤፌሶን 5 27




ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነ

No comments:

Post a Comment