Sunday 7 December 2014

የባልና የሚስት የግንኙነት ምስጢር ክፍል ሦስት



የባልና የሚስት የግንኙነት ምስጢር

ክፍል ሦስት

ሰዎች ከእጮኝነት ዘመናቸው አንስተው ባልና ሚስት እስከሚሆኑበት ጊዜ ድረስ በተለያየ መንገድ ውስጥ አልፈው የተገናኙ ቢሆኑም እንኳ መጽሐፍቅዱሳችን እንደሚያስተምረን ስንመለከት የጋብቻ መሥራች ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ ከተለያዩ የመጽሐፍቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ሄደን አውጥተን መመልከት እንችላለን በዘፍጥረት 2 18 ላይ የተጻፈውን የእግዚአብሔርን ቃል ስንመለከት እግዚአብሔር አምላክም አለ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት ይለናል ስለዚህ ብቸኛ መሆን የማይፈልግና የሚመች ረዳት የሚፈልግ ሰው ዓይኑን ወደ እግዚአብሔር ማንሳት አለበት ያኔ እግዚአብሔር የምትመቸውን ረዳት ያዘጋጅለታል ነገር ግን ዓይናችንን ከእግዚአብሔር ላይ በመንቀል በሁኔታዎችና በራሳችንም ኃይል የምትመቸውን ረዳት እናዘጋጅ ብንል ረዳት ሆና የመጣችው የምትመች ረዳት መሆኗ ቀርቶ የምትቆረቁር የምትቆጠቁጥ የምታቃጥልና የምታስለቅስ ትሆንብናለች በመሆኑም ታድያ ብዙዎች የምትመቸውን ረዳት ከእግዚአብሔር ተቀብለው ማረፍ ሲገባቸው የምትመቸውን ረዳት ከሁኔታዎችና ከነገሮች ተቀብለው ይኸው ዕድሜ ዘመናቸውን ሲቃጠሉ ሲያሩና ሲተክኑ ይኖራሉ አንዳንዶችም ይህንን ሁኔታ መቋቋም አቅቷቸው ለፍቺ የበቁ ከቁጥር በላይ ናቸው ይህንን ስል የእግዚአብሔር ፈቃድም ሆኖ የምትመች ረዳትም ተገኝታ ግጭት የለም ማለቴ አይደለም ግጭቱ አንዳንዴም የባሰ ሊሆን ይችላል ነገር ግን እግዚአብሔር ወደ በጎ ይለውጠዋል ግጭታችንንም ተጠቅሞ የምንማርበት የምንሰራበትና የምንቀረጽበት የምንበጅበት የሕይወት ትምሕርት ቤት ኮሌጅ ወይም ዩንቨርስቲ ያደርገዋል ትዳር ቤተሰብ የምናፈራበት ልጆች የምንወልድበትና ወግ ማዕረግም የምናይበት ብቻ ሳይሆን የምንማርበትም ነው የትም ተምረን የማናውቀውን ወላጆቻችንም የላስተማሩንን የምንማረው በትዳራችን ማለት እግዚአብሔር በሰጠን ባላችን ወይም ሚስታችን አንዳንዴም በልጆቻችን ይሆናል ስለዚህ ወደ ትዳር ዓለም ስንመጣና ለማግባትም ስንወስን በሰዎች ፊት ለሠርጋችን የምንለብሳቸው ቬሎዎችና እስቶኪንጎች የምንኳኳላቸው ኩሎችና የተዋቡ ጫማዎች በወንዶችም በኩል ያማሩ የሀገራችን ሱፎች ወይም በውጪው ዓለም ሳይቀር የሚመጡልን የተዋቡ የእንግሊዝና የጣሊያን ሱቶች ብቻ ሊሆኑ አይገባም ከዚያ መልስም በጋብቻ የኑሮ ዘይቤ ውስጥ ያለውን ሂደትና አስተምህሮትም ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን አለበለዚያ ግን ሱፍና ቬሎ ብቻ ሆነን እንቀራለን ለዚህ ነው መጽሐፍቅዱስ ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደምያ የሚያበቃ ያለው እንደሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ከሳራውን የማይቆጥር ማነው ? የሚለን ያለዚያ መሠረቱን ቢመሠርት ሊደመድመውም ቢያቅተው ያዩት ሁሉ ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው ብለው ሊዘብቱበት ይጀምራሉ ወይም ሌላውን ንጉሥ በጦርነት ሊጋጠም የሚሄድ ከሁለት እልፍ ጋር የሚመጣበት በአንድ ዕልፍ ሊገናኝ የሚችል እንደሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ የማያስብ ንጉሥ ማን ነው ? ባይሆንስ ሌላው ገና ሩቅ ሳለ መልዕክተኞች ልኮ ዕርቅ ይለምናል የሚለን የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 14 28 _ 35 ስለዚህ በዚህ ነገራችን ውስጥ የትዳር ጀማሪው እግዚአብሔር አንድ ብሎ ሊያስጀምረን ሲገባ እኛ ግን እግዚአብሔርን ቀድመን ያለ እግዚአብሔር በነገሮችና በሁኔታዎች የጀመርነው ትዳር እልባትና መቋጫ ያጣና ሳይደመደምም መሐል ላይ በመቅረት ለብዙዎች መዘበቻ እንዳይሆን ያገባንም ለትዳራችን ያላገባንም ወደፊት ስለምናገባው ትዳራችን በብርቱ ልናስብ ልንጸልይ ጌታንም ልንማጸነው የእግዚአብሔር ፈቃድ በሆነው ነገር ውስጥም ተስማምተንና ተረዳድተን ተጋግዘንም ልንኖር ይገባል ሊፈቱ ባልቻሉ ነገሮች ላይ ደግሞ ስሜታዊ ሳንሆንና ሳንቸኩል በትዕግስት ሆነን ጊዜ በመውሰድ ነገሮችን ማስተካከል ነው ከዚህ በተጨማሪም በትዳር ውስጥ ያለና ወደፊትም ሊኖር የሚፈልግ ጣልቃ ገብነት ካለ ቶሎ ብሎ ማስወገድ የተጋቢዎች ማለት የባልና ሚስቱ ፈንታ ነው ጌታ እግዚአብሔር ለአዳም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት ብሎ ዝም አላለም እንፍጠር ያለ እግዚአብሔር መፍጠር ጀመረ ከየት ? ስንል በአዳም ከባድ ዕንቅልፍ ጥሎ ከአዳም ከጎኑ አንዲት አጥንት ወስዶ ሠራ ያቺ የተሠራችው አጥንት ሔዋን ትባላለች ከዚያ በኋላ ነው የተሠራችውን ሴት ወደ አዳምም ያመጣትን ሴት ይህቺ አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል ሲል አዳም የተናገረው አዳም ያልተሰጠውን ሴት ለራሱ ወስዶ ይህቺ አጥንት ከአጥንቴ ሥጋም ከሥጋዬ ናት አላለም እግዚአብሔር ሠርቶ የሰጠውን ሰው ነው አጥንቴና ሥጋዬ ናት ሲል የተናገረው እግዚአብሔር ሠርቶ እስኪሰጠው ድረስ ግን በከባድ እንቅልፍ ውስጥ ነበር ይህም እንቅልፍ እርሱ በራሱ ያመጣው ሳይሆን ከእግዚአብሔር ከባለቤቱ የተሰጠው ነው ዘፍጥረት 2 21 _ 25 ከዚህ የምንማረው የእግዚአብሔር እውነት እግዚአብሔር ወደ እኛ የሚያመጣቸው ረዳቶች አጥንቴና ሥጋዬ ብለን አምነን የምንቀበላቸው ተሠርተው ወደ እኛ የመጡ ማለት እግዚአብሔር ያመጣልን እህቶች ናቸው እነዚህ እህቶች ታድያ ለእኛ በልካችን የተሠሩ ስለሆኑ ከራሱ ከእግዚአብሔር ውጪ ሌሎች ነገሮች የሚያመጧቸው አይሆኑም እስኪሆን ድረስ እኛ ወንድሞች ለትዳር በሆነው ጉዳይ በቅልጥፍና በሥልጣኔና በንቃት የሚመጣ ነገር የለምና አወኩ፣ ነቃሁ፣ ሰለጠንኩ ተቀላጠፍኩ ብለን ወዲያ ወዲህ ከምንል ይልቅ አጥንታችንና ሥጋችን የሆነችዋን እህታችንን ለመቀበል የሚያስችለውን እንቅልፍ ያውም እግዚአብሔር የሰጠንን ከባዱን እንቅልፍ በጸጥታ ሆነን እናንቀላፋ እንተኛ ይሄ እንቅልፍ ካልተሰጠን ደግሞ እግዚአብሔር ጊዜውን ጠብቆ እስኪሰጠን ድረስ አርፈን እንቀመጥ ከዛ ውጪ ግን በቅልጥፍናና በንቃት የሚመጣ ረዳት የለም ካለም በትምህርቴ መጀመርያ ላይ እንደጠቀስኩት ምን ጉድ ውስጥ ገባሁ ? ያኔ ምነው በቀረብኝ ኖሮ ? አስብሎ በፍጻሜያችን መራራና ልቅሶ የተሞላበት ሕይወት ውስጥ እንድንገባ የሚያደርግ ነው ስለዚህ እግዚአብሔር ከዚህ ካልታሰበው የሮሮና የልቅሶ ሕይወት ይጠብቀን ጌታ እግዚአብሔር ይህንን ከባድ እንቅልፍ ለአዳም እንደሰጠው ለእኛም የሚሰጠን ምክንያት እርሱ ለእኛ ረዳት አዘጋጅቶ በሚሰጠን ሥራ ውስጥ ጣልቃ እንዳንገባበት ነው አንዳንዴ ወንድም በወንድሙ እህት በእህቱ ዘመድ በዘመዱ ጓደኛ በጓደኛው ጎረቤት በጎረቤቱ ነገር ውስጥ ጣልቃ እንደሚገባ እንዲሁ በእግዚአብሔር ነገር ውስጥም ጣልቃ እንገባለን ነገር ግን የምንጨምረውም ሆነ የምንቀንሰው አንዳች ነገር የለም እርሱ እግዚአብሔር ስለሆነ ተናግሬአለሁ እፈጽማለሁ አስቤአለሁ አደርግማለሁ ይላል ኢሳይያስ 46 8 _ 11 ስለዚህም ተናግሮ የሚፈጽም አስቦም የሚያደርግ ትልቁ አምላካችን ዛሬም አለ ከእኛም ጋር ነውና የተናገረውን እስኪፈጽም ያሰበውን እስኪያደርግ ድረስ እኛም በጸጥታ ውስጥ ሆነን እግዚአብሔር የሰጠንን የእንቅልፍ ኤክሰርሳይስ እንለማመድ ነገር ግን እግዚአብሔር የሰጠንን ከባዱን የእንቅልፍ ኤክሰርሳይስ ትተን የየራሳችንንና የበኩላችንን ትዳር የማግኘት ኤክሰርሳይስ የምንሰራ ከሆነ እግዚአብሔርን ተናግረህ አትፈጽምም አስበህ አታደርግም እያልነው እንደሆነ ሁላችንም ልናውቀው ይገባል እግዚአብሔር ደግሞ ለእናንተ የማስባትን ሃሳብ እኔ አውቃለሁ ፍጻሜና ተስፋ እስጣችሁ ዘንድ የሰላም ሃሳብ ነው እንጂ የክፉ አይደለም ብሎናል ኤርምያስ 29 11 _ 14 እግዚአብሔር በምናነበው ቃል ወደ ሕይወታችን ይምጣ ይባርከን ይለውጠን አሜን

ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment