Friday 5 December 2014

የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ምዕራፍ ሁለት ክፍል ስድስት



የቤተክርስቲያን ተልዕኮ


ምዕራፍ ሁለት



ክፍል ስድስት



ከሐሰተኛ ነቢያት ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ራስንና መንጋውን መጠበቅ




የራዕይ መጥፋት





የተወደዳችሁ ወገኖች በክፍል አምስት ትምህርታችን ራዕይ የማይገለጥበትን ምክንያቶች ዘርዝረን ነበር እነዚህም ምክንያቶች አንደኛው የእግዚአብሔርን ቃል ለማወቅ ለማጥናት እና ለመረዳት ያለመፈለግ ሁኔታ ሲሆን ሁለተኛው ሃሳብ ደግሞ በልብ ላይ ያለን የኃጢአት ሰንኮፍ በንስሐ ከውስጥ አውጥቶ ያለመጣል ጉዳይ ራዕይን እንዳይገለጥ ያደርገዋል ብለናል ይህም ሁኔታ የነቢያቱንም ሆነ የካህናቱን ዓይን የሚይዝና ራዕዮቻቸውንም ጭምር የሚሸፍን በመሆኑ የካህኑ የዔሊ ዓይኖች ሳይቀር  ምን ያህል የፈዘዙ እንደሆነ ከተመለከትን በኋላ በዚህም ምክንያት ዔሊ በግድየለሽነት እርሱ እግዚአብሔር ነው ደስ ያሰኘውን ያድርግ በማለቱ እግዚአብሔርም የወሰደውን እርምጃ አስመልክተን በሰፊው ተማምረናል ዛሬም ከዚሁ እንቀጥላለን ዕይታን የሚያስተካክል ራዕይን የሚሰጥ የእግዚአብሔር ቃል ነው የእግዚአብሔር ቃል እንደሚገባ በማይገለጥበት ቦታ ሁሉ ብዙ ዓይነት ችግሮች ይመጣሉ የእግዚአብሔር ቃል የተገለጠበት ራዕይ በነቢዩ ናታን በኩል ለዳዊት መጣለት ሃሳቡንም እንዲህ ብሎ ይጀምረዋል በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ እንዲህም አለው ሂድ፥ ለባሪያዬ ለዳዊት ንገረው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ በቤት አልተቀመጥሁምና አንተ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም ከእስራኤል ልጆች ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉን ስለ ምን ቤትን ከዝግባ እንጨት አልሠራችሁልኝም ? ብዬ ሕዝቤን እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ላዘዝሁት ለአንዱ በውኑ ተናግሬአለሁን ?  አሁንም ዳዊትን ባሪያዬን እንዲህ በለው የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ መንጋውን ስትከተል በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ ወሰድሁህ በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆቹ ስም ታላቅ ስም አደርግልሃለሁ በማለት ይቀጥልና እንደዚህ ቃል ሁሉ እንደዚህም ራእይ ሁሉ ናታን ለዳዊት ነገረው በማለት ያጠናቅቃል 2 ሳሙኤል 7 1 _ 17 1 ዜና መዋዕል 17 1 _ 15 ነቢዩ ናታን በመጀመርያ ለንጉሥ ለዳዊት ያየው ራዕይ ትክክል አልነበረም ዕይታው በእግዚአብሔር ቃል በድጋሜ ከጠራና ከተስተካከለ በኋላ ግን ለንጉሥ ዳዊት ይዞት የሄደውና የነገረው ራዕይ በእግዚአብሔር ቃል ተመዝኖ ያለፈ ራዕይና የእግዚአብሔርም ቃል የተገለጠበት ራዕይ ነበር ለዚህም ነው ገና ሲጀምር በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ እንዲህም አለው በማለት የነገረን ታድያ አሁንም በእኛ ዘመን የራሳቸውንና  የብዙዎችን  የዘመን ታሪክ ለመለወጥ እግዚአብሔር ለአንዳንዶች ራዕይ ሊሰጥ ሲፈልግ ዛሬም የሚመጣው በቃል ነው ቃል የሌለበት ራዕይ በሥራ ብዛት የታየ ሕልም አለበለዚያም እውን ያልሆነና የማይፈጸም የሌሊት ቅዠት ነው የመክብብ መጽሐፍ ሲናገር ሕልም በሥራ ብዛት ይታያል እንዲሁም የሰነፍ ድምፅ በቃሉ ብዛት ይሰማል ይለናል መጽሐፈ መክብብ 5 3 ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ይህንን ሁኔታ በጥልቀት ካለመረዳትም ይሁን በስሜት አይታወቅም ብቻ እንዲሁ ከመሬት ተነስተውና ብድግ ብለው ራዕይ አለን በማለት አንድን  ነገር ይጀምራሉ ነገር ግን ራዕያቸው ፍጻሜ ላይ ሳይደርስ ይቀርና ራዕይ ወይንም ሕልም ብቻ ሆኖ ይቀራል ችግሩ ምንድነው ? ስንል እነዚህ ሰዎች ራዕይ አለን ብለው የተነሱበትን ነገር አስቀድመው በእግዚአብሔር ቃል አላስፈተሹም ወይም በሌላ አነጋገር ራዕያቸው የእግዚአብሔርን ቃል ምስክር ያደረገ የእግዚአብሔርም ቃል የሚገለጥበት ባለመሆኑ እነዚህ ሰዎች በጀመሩት ራዕይ ፍጻሜ ላይ ሳይደርሱ ይቀራሉ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የጀመርነው ራዕይ ትክክል ነው ያዋጣናል ያዛልቀናል ብለው ገፍተው ሄደው ብዙ ነገር ካደረጉ በኋላ በራዕያቸው ፍጻሜ ላይ ሳይደርሱ ቀርተው የጀመሩት ነገር መቋጫ አጥቶ ይበተናል እንደ ሰናዖር ግንብም ይናዳል ወይም ሳያልቅ ይቀራል ይህ እንግዲህ የሚያሳየን እነዚህ ሰዎች ራዕይ አለን ብለው ሲጀምሩ ራዕያቸው የእግዚአብሔር ቃል የሚገለጥበት አይደለም ስለዚህ ቅዱሳን ለምንጀምረው ለማንኛውም ራዕይና የራዕይ አገልግሎት  እግዚአብሔር በቃሉ ሊናገረን እኛም የእግዚአብሔርን ቃል ልንሰማ የእግዚአብሔርም ቃል ማረጋገጫ ሊኖረን ይገባል በእግዚአብሔር ቃል የጀመርነው ራዕይ በእሳት ውስጥ ቢገባ በልዩ ልዩ ፈተናዎች ውስጥ ቢያልፍ ውጤቱ ያማረና አስደሳችም ነው የዮሴፍ ራዕይ በእስር ቤት የተፈተነ ነበረ ነገር ግን ራዕዩ የእግዚአብሔር ቃል የተገለጠበት ስለነበር ተፈትኖ በእስር ቤት ሳይፈጸም እንዲያው የቀረ አልነበረም ወደ ንጉሥ ቤት መጥቶ ዮሴፍን የንጉሥ ቤት አለቃና ገዢ አደረገው ለዚህም ነው በእግዚአብሔር ቃል ላይ በፊታቸው ሰውን ላከ ዮሴፍ ለባርነት ተሸጠ እግሮቹም በእግር ብረት ደከሙ፥ እርሱም በብረት ውስጥ ገባ ቃሉ እስኪመጣለት ድረስ፥ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው ንጉሥ ላከ ፈታውም፥ የአሕዛብም አለቃ አስፈታው የቤቱ ጌታ፥ የጥሪቱ ሁሉ ገዢ አደረገው፥ ተብሎ የተጻፈልን መዝሙር 104 ( 105 ) 17 _ 21 ሌሎችንም ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸውን ራዕያቸው ተጀምሮና በብዙ ፈተና ውስጥ አልፎ የተፈጸመላቸውን ሰዎች ማየት እንችላለን ላሁን ግን ዮሴፍን ለምሳሌነት ካየን ይበቃናል ለዚህ ነው እንግዲህ ወደ ዳዊት ታሪክ ስንመጣ  በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ እንዲህም አለው ካለን በኋላ እንደዚህ ቃል ሁሉ እንደዚህም ራእይ ሁሉ ናታን ለዳዊት ነገረው ያለን ራዕያችን ሊጠናቀቅ የእኛም ዕጣ ፈንታ ይሄ ይሁንልን ለራዕያችንም ፍጻሜ እና አደራረግ ዕለት ዕለት የእግዚአብሔር ቃል ይምጣልን ከዚህ ጋራ በተጓዳኝነት በሐዲስኪዳን አሁንም ራዕይ የእግዚአብሔር ቃል የሚገለጥበት መሆኑን እንመለከታለን በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 1 22 ላይ በወጣም ጊዜ ሊነግራቸው አልቻለም፥ በቤተ መቅደስም ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፤ እርሱም ይጠቅሳቸው ነበር፤ ድዳም ሆኖ ኖረ ይለናል ታድያ ዘካርያስ በቤተመቅደስ ራዕይ እንዳየ በዚያን ዘመን የነበሩ ሰዎች አስተውለዋል በመሆኑም ለምን ድዳ ሆኖ ኖረ ? ብለን ስንጠይቅ መልሱን ከዚሁ ከእግዚአብሔር ቃል እናገኛለን መልአኩም መልሶ፦ እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፥ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፤ እነሆም፥ በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም አለው ይለናል የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 1 20 የዘካርያስ ራዕይ በመልአኩ አማካኝነት የተገለጠው በቃል ነው የተፈጸመውም በዚሁ በእግዚአብሔር ቃል ነው በመሆኑም ዘካርያስ ራዕዩ የተገለጠበትን የእግዚአብሔር ቃልና የሚፈጸምበትን ቃል ባለማመኑ ነው ድዳ የሆነው ቢያምን ኖሮ ይሄ ሁሉ ድዳነት በሕይወቱ አይመጣበትም ነበር ቃሉን የተናገረ ራዕዩንም የሰጠ እግዚአብሔር ይፈጽማልና በመጨረሻው ሰዓት የዘካርያስ አንደበት ተከፈተ እዚህ ላይ ለእኔ በጣም የሚገርመኝ የዘካርያስ አንደበት መዘጋት መከፈቱ ሳይሆን ካህኑ ዘካርያስ ምንም እንኳ የእግዚአብሔርን ቃል በመጠራጠሩ ምክንያት ይሄ ቢደርስበትም የእግዚአብሔር ቃል በተገለጠበትና በተፈጸመበት  ራዕይ ማገልገሉ ግን እጅግ ደስ  የሚያሰኝ ነገር ነው  ስለዚህ ዘካርያስ በጊዜው የነበረ ባለራዕይና ካህን ነው ብንል ማጋነን አይሆንብንም በሐዋርያት ሥራ 18 9 እና 10 ላይ ደግሞ ጌታም ሌሊት በራእይ ጳውሎስን እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ ማንም ክፉ ሊያደርግብህ የሚነሣብህ የለምና አትፍራ፥ ነገር ግን ተናገር ዝምም አትበል፤ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና አለው በመካከላቸውም የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማረ ዓመት ከስድስት ወር ተቀመጠ ይለናል ስለዚህ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማረ ዓመት ከስድስት ወር መቀመጡና የእግዚአብሔርንም ተልዕኮ መፈጸሙ ካየው ራዕይ የተነሳ ነው  በዚህም ምክንያትና ጳውሎስ ባያቸው የእግዚአብሔርም ቃል በተገለጠባቸው ራዕዮች ነው ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ስለዚህ ከሰማይ የታየኝን ራእይ እምቢ አላልሁም ያለው  የሐዋርያት ሥራ 26 19 ታድያ እኛም እንደ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ቃል የሚገለጥበት ይሁን እንጂ ከሰማይ የታየንን ራዕይ ከዚህ በፊት እንቢ አላልንም አሁንም እንቢ አንልም ሐዋርያው ከሰማይ የታየኝን ራዕይ እንቢ አላልሁም በማለት አላበቃም ነገር ግን አስቀድሜ በደማስቆ ላሉት በኢየሩሳሌምም በይሁዳም አገር ሁሉ ለአሕዛብም ንስሐ ይገቡ ዘንድና ለንስሐ የሚገባ ነገር እያደረጉ ወደ እግዚአብሔር ዘወር ይሉ ዘንድ ተናገርሁ ስለዚህ አይሁድ በመቅደስ ያዙኝ ሊገድሉኝም ሞከሩ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ረድኤት ተቀብዬ ለታናሹም ለታላቁም ስመሰክር እስከዚች ቀን ድረስ ቆሜአለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን፥ ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በሙታንም ትንሣኤ ለሕዝብና ለአሕዛብ ብርሃንን በመጀመሪያ ሊሰብክ እንዳለው፥ ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም እንዲህም ብሎ ስለ ራሱ ሲመልስ ፊስጦስ በታላቅ ድምፅ ጳውሎስ ሆይ፥ አብድሃል እኮ፤ ብዙ ትምህርት ወደ እብደት ያዞርሃል አለው ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ፦ ክቡር ፊስጦስ ሆይ፥ የእውነትንና የአእምሮን ነገር እናገራለሁ እንጂ እብደትስ የለብኝም በእርሱ ፊት ደግሞ በግልጥ የምናገረው ንጉሥ ይህን ነገር ያውቃል፤ ከዚህ ነገር አንዳች እንዳይሰወርበት ተረድቼአለሁና፤ ይህ በስውር የተደረገ አይደለምና አለ ዛሬም የእግዚአብሔር ቃል የሚገለጥበት ሆኖ ከሰማይ የታየንን ራዕይ እንቢ ባለማለታችን ምክንያት ከብዙዎች አለመረዳት የተነሳ እብድና አዙሪት ይዞሃል የሚያሰኝ ስያሜ ቢያሰጠንም እኛም እንደ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ሥራ በመመስከርና በመስራት እስከዚች ቀን ድረስ ቆመናልና የእውነትንና የአእምሮን ነገር እንናገራለን እንጂ እብደት የሚባል ታሪክ እኛም ጋር ይሁን ጳውሎስ ጋር በፍጹም የለም ይልቁንም ራዕይና ሕልም አስተዋይ ያደርጋልና እኛም እንደ ዳንኤል በራእይና በሕልም ሁሉ አስተዋይ ሆንን ዳንኤል 1 17 እንደገናም የእግዚአብሔር ቃል በሚገለጥበት ራዕይ ውስጥ ያልተካተተ አምልኮ የከንፈር አምልኮ ነው በኢሳይያስ 29 13 _ 15 ላይ ጌታም፦ ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና፥ በከንፈርቹም ያከብረኛልና፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና፥ በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ ድንቅ ነገርን በዚህ ሕዝብ መካከል፥ ድንቅ ነገርን ተአምራትንም፥ እንደ ገና አደርጋለሁ የጥበበኞችም ጥበብ ትጠፋለች፥ የአስተዋዮችም ማስተዋል ትሰወራለች ምክራቸውን ጥልቅ አድርገው ከእግዚአብሔር ለሚሰውሩ፥ ሥራቸውንም በጨለማ ውስጥ አድርገው ማን ያየናል ?  ወይስ ማን ያውቀናል ? ለሚሉ ወዮላቸው ይለናል ይህ አምልኮና አገልግሎት በሰዎች ጥበብ ላይ የተመሠረተ የከንፈር አምልኮና አገልግሎት በመሆኑ ከእግዚአብሔር የተሰወሩ የሚመስሉና ማንስ ያውቀናል ? በሚል ጨለማን ለብሰው የሚካሄዱ ምክሮች ያሉበት  ፍጻሜውም ጥፋት የሆነ ነው እንግዲ ዛሬም በዘመናችን እየሆነ ያለው ታሪክ ይሄ ነው በዘመናችን  አንዳንዶቹ  ሲታዩ እናመልካለን እንዘምራለን እንሰብካለን እንመግባለን ባዮች ናቸው ይህንንም አስመልክቶ የሰው ድምጽ እና እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን ድምጽ ማጉያዎችና የሙዚቃ መሳርያዎች ሳይቀር በብዙ የከፍታ ድምጽ የሚያስተጋቡ እና የሚጮኹ ናቸው ነገር ግን ከበስተጀርባው ዞር ብለን ስንመለከት ማንስ ያውቀናል ? ሲሉ  ምክራቸውን ጥልቅ ያደረጉ ጨለማን ለብሰው በክፋትና በተንኮል የጽድቅ አገልጋዮችን  ቅዱሳንንም ጭምር  የሚተናኮሉና የሚናደፉ የእግዚአብሔርም ሥራ በትክክል እንዳይሄድ የሚከለክሉ ብዙ የሆኑ መጥፎ ድርጊቶችንም የሚፈጽሙ ሆነው አግኝተናቸዋል  ይሁን እንጂ ለእነዚህ ክፉ ለሆኑ ጉዳዮቻቸው አሁንም እግዚአብሔር ወዮላቸው እያለ ይገኛል የእግዚአብሔር ቃል በሚገለጥበት ራዕይ ውስጥ ግን እነዚህ ነገሮች የሥጋ ሥራዎች ናቸውና በፍጹም አይገኙም ሊኖሩም አይችሉም የእግዚአብሔር ቃል በሚገለጥበት ራዕይ ውስጥ  በዘኊልቊ 23 20 እና 21 ላይ እርሱ ያለውን አያደርገውምን ? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን ? እነሆ፥ ለመባረክ ትእዛዝን ተቀብያለሁ እርሱ ባርኮአል፥ እመልሰውም ዘንድ አልችልም በያዕቆብ ላይ ክፋትን አልተመለከተም፥ በእስራኤልም ጠማምነትን አላየም፤ አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነው፥ የንጉሥም እልልታ በመካከላቸው አለ በሚል በእግዚአብሔር ቃል የተጻፈልን በመሆኑ ያለው ነገር  የማይመለስ የእግዚአብሔር ባርኮትና የንጉሥ ዕልልታ ነው ከዚህም ሌላ  በሐዲስ ኪዳን እውነት ውስጥ የገባን በመሆኑ የበጉ ሠርግ ስለደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን ሐሤትም እናድርግ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ ይባላል እንደገናም መንፈሱና ሙሽራይቱም   ይላሉ የሚሰማም ይበል የተጠማም ይምጣ፥ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ በሚል የተባረከ ቃል በዘላለም የሕይወት ውሃ ከጥሟ የረካችውንና በፍጻሜው ዘመን በሚል ጥሪ ብቻ ሳይሆን ተሞሽራ ሙሽራውን ለምትጠብቀው ሙሽሪት ቤተክርስቲያን ሙሽራው ኢየሱስ ሊወስዳት ይመጣል ራዕይ 19 6 _ 8 ራዕይ 22 17 እኛም  ሊወስደን በሚመጣው ጌታ  በመስማማት አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ እንላለን አሜን ማራናታ ጌታ ኢየሱስ ሆይ ትምህርቱ ይቀጥላል


ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ





ጌታ ይባርካችሁ

No comments:

Post a Comment