Sunday 7 December 2014

የትምህርት ርዕስ እውነትን መናገር ወዳጅ ያሳጣል

የትምህርት ርዕስ

እውነትን መናገር ወዳጅ ያሳጣል



እንግዲህ ደስ ማሰኘታችሑ ወዴት አለ ? ቢቻልስ ዓይኖቻችሑን አውጥታችሑ
በሰጣችሑኝ ብዬ እመሰክርላችኋለሁ እንኪያስ እውነቱን ስለነገርኳችሑ
ጠላቶች ሆንኩባችሑን ?


ገላትያ 4 ፥ 15 እና 16 

እነዚህ የገላትያ ክርስቲያኖች የአይሁድ እምነት ተከታዮች ከሆኑት ክርስቲያኖች ተጽእኖ የተነሳ ለጳውሎስ የነበራቸው አመለካከት በመቀየሩ ምክንያት ለሰው ልጅ ውድ የሆነ ነገሩ ዓይኑ ነውና እንደ ዓይናቸው አድርገው የሚወዱትን ማንኛውንም ነገር ሳይቀር ለዚሁ ሐዋርያ ሊያካፍሉ ፈቃደኞች የነበሩ ሲሆኑ አሁን ግን ከአይሁድ ባገኙት የተዛባ አመለካከት ሃሳባቸው ተቀየረ ከዚህም የተነሳ የጳውሎስ የእውነት አነጋገር ለእነርሱ የጠላትነት አነጋገር ሆኖ ታያቸው ለተለያዩ አሉታዊ አስተሳሰቦች መዳረግና በእነርሱም ተጽእኖ ሥር መውደቅ የእውነትን ቃል እንዳንቀበል ፣ የእውነቱም ቃል ተቃራኒዎችና ጠላቶች ሆነን እንድንገለጥ ያደርጉናል ለዚህም ነው በዛሬዋ ቤተክርስቲያንም በብዙ ሰዎች ላይ ለውጥ የማይታየው ከዕድገት ይልቅ መቀጨጭና መጫጫት እንዲሁም መደንዘዝና መመንመን ጎልቶ ይስተዋላል ስለዚህም ሐዋርያው ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን ጆሮቻችሑም ስለፈዘዙ በቃል ልንተረጉመው ጭንቅ ነው አለን ዕብራውያን 5 ፥ 11 የጆሮ መፍዘዝ የሚመጣው ተራና መደዴ የሆኑ ነገሮችን ከመስማት ከመናገርና ከመጫወት የተነሳ ነው ይህ ዓይነት ልምምድ ያላቸው ሰዎች የእግዚአብሔር ቃል ለእነርሱ ቁምነገራቸው አይደለም ቢያስተምሩ ቢሰብኩ ቢዘምሩ እና ሌላም ሌላም ነገር ቢያደርጉ እንኳ እንዲያው ከልማድ በመነሳት እንጂ የእግዚአብሔር ቃል ምስጢሩ ገብቷቸው ተነክተውበትና ተለውጠው አይደለም ለዚህ ነው ጌታ ያዘዙአችሑን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ በማለት የተናገረው የማቴዎስ ወንጌል 23 ፥ 3 እንደገናም ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል አለ የማቴዎስ ወንጌል 15 ፥ 8 እንግዲህ ሰው በእውነት ቃል እስካልቆመና ለእውነት እስካልወገነ ድረስ ቢሰብክ ቢዘምር ቢያገለግል አገልግሎቱ ከከንፈር ያለፈ አገልግሎት አይሆንም ይህ ደግሞ ዋጋ ቢስና ከንቱ የሆነ አምልኮት ነው ዓመታትንና ወራትን እየጠበቁ እንዲሁ ጊዜ ከማጥፋት በስተቀር የሚፈይደው ነገር የለም የእግዚአብሔር ቃል የእውነት ቃልና የመዳን ቃል ነው በኤፌሶን መጽሐፍ ላይ እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል ይኸውም የመዳናችሑን ወንጌል ሰምታችሑ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሑ በተስፋው መንፈስ በመንፈስቅዱስ ታተማችሑ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል ይለናል ኤፌሶን 1 ፥ 13 እና 14 ታድያ ይሄ የእውነት ቃል ሰዎችን ያዳነ ቃልና ለተስፋውም መንፈስ መታተም ያበቃ ቃል በመሆኑ በቅነነት እንናገረዋለን እንጂ ፈጽሞ ልንለውጠው አንችልም የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገሩ አገልጋዮች የተፈተነ ማንነት ቢኖራቸውም እንኳ የማያሳፍሩ ሠራተኞች ናቸው 2ኛ ጢሞቴዎስ 2 ፥ 15 ዛሬ ግን በተቃራኒው የእውነት ቃል በቅንነት ሊነገር ሲገባው ሌላ ሌላ ነገር በመጅመሩ ምክንያት ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኞቻችን የምናሳፍር ሆነን ተገኝተናል ይህ ደግሞ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው ይህ ብቻ አይደለም የእውነት ቃል በግልጽነት በሚነገርበት ጊዜ ደግሞ ይህንኑ የእውነት ቃል የመቋቋም ኃይሉ ስለሌለን እንደገናም ቃሉን በመስማት ብቻ በቀላሉ ልናልፈው የማንችልና የሚለውጠን ስለሆነ ለውጥን ከመጥላት የተነሳ ይመስላል ምን ታይቶ ምን ተሰምቶ ተነገረ እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች እናነሳለን ለእነዚህ ጥያቄዎቻችን መልሱ አጭርና ግልጽ ነው በግዕዙ ቃል አማን አማን እብለከ ከመ ዘነአምር ንነግር ወበዘርኢነ ሰማእተ ንከውን ወስምዐነሰ ተአብዩነ ነሢአ ትርጉም እውነት እውነት እልሃለሁ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን ምስክርነታችንንም አትቀበሉትም ማለትን የሚያመለክት ነው የዮሐንስ ወንጌል 3 ፥ 11 _ 15 ይሁን እንጂ ምስክርነትን መቀበል ባይኖርም እኛ ግን አሁንም ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም የሐዋርያት ሥራ 4 ፥ 19 _ 21 ስለዚህም ነው ለዚህ የትምህርት ክፍል እውነትን መናገር ወዳጅ ያሳጣል የሚለውን አርእስት የመረጥኩት ሐዋርያውም እውነቱን ስለነገርኳችሑ ጠላት ሆንኩባችሑን ? ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ በቃ ይቅርብኝ በማለት እጁን አጣጥፎ ሲቀመጥ አናገኝውም እውነቱን በመናገሩ ምክንያት ሰዎች በጠላትነት የተመለከቱት እንኳ ቢሆንም እርሱ ግን በእግዚአብሔር ሃሳብ በመጨከንና ከሃሳቡም ወደ ኋላ ባለማለት ወደፊት ሲሄድ እንመለከታለን ለዚህ ሃሳቡም ያቀረባቸው ምክንያቶች ነበሩት የወንጌልም እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለእንድ ሰዓት እንኳ ለቀን አልተገዛንላቸውም አለ የጳውሎስ ሙግቱ የራስን ጥቅም የማስጠበቅ ጉዳይ አይደለም ወንጌል ነው የወንጌል እውነት ከራሱ አልፎ በሌሎች ሰዎች ሕይወት ውስጥ ጸንቶ እንዲኖር ዋጋ የከፈለ የጌታ ባርያ ነው ሥልጣንና የመሳሰሉት ነገሮች ቢሆኑ ክብሩን የጣለና ለዚህም ጉዳይ ግድ የማይለው በመሆኑ ለቆ ይገዛ ነበር ጉዳዩ ግን የወንጌል እውነት በመሆኑ አይደለም ለቆ መገዛት ለአንድ ሰዓት እንኩዋ ለቆ ያልተገዛ መሆኑን በግልጽ ይናገራል በዚህ ነገር አለቆች እንኳ ቢሆኑ የማይገደው መሆኑንም ይጠቁማል ይህ እንግዲህ የጳውሎስ ቀጥተኛ አቋሙ ነው ገላትያ 2 ፥ 5 _ 10 ወንጌል የእውነት ቃል በመሆኑ ሰዎችን የሚለውጥ ነው እንጂ በሰዎች የሚለወጥ አይደለም እኛም ከዘመኑና ከጊዜው ጋር በጣምራነት እናስኬደዋለን ብለን እንደፈለግን የምንለዋውጠው ነገር አይደለም መናገር ካለብን መናገር የሚገባን የተጻፈውን ቃልና እውነቱን ብቻ ነው ይህ የእግዚአብሔር ቃል እውነት ደግሞ ሳንበርዝ ሳንሸቅጥና ሳናስመስል ሳናለባብስ ከተናገርነው አርነት ያወጣል የዮሐንስ ወንጌል 8 ፥ 31 _ 33 ጌታችን ኢየሱስም በዮሐንስ ወንጌል 18 ፥ 37- 38 ላይ እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምጼን ይሰማል አለው ጲላጦስ እውነት ምንድነው ? አለው ይለናል እውነት ስንናገርና ለእውነት ስንመሰክር ሰዎች ሊተዉን እኛም ብቻችንን ልንቀር እንችላለን ለእውነት የመሰከረው እየሱስ ብቻውን ቀርቶአል ጳውሎስም ሁሉ ተዉኝ እስኪል ድረስ ብቻውን ቀርቶአል ጌታ ግን በአጠገቡ ቆሞ ያበረታው ነበር ስለዚህም ጌታም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነኛል ለሰማያዊውም መንግሥት ይጠብቀኛል በማለት ተናገረ ታድያ እውነትን ስንናገር ሰዎች ቢተዉንና እኛም ወዳጅ ብናጣ እውነተኛው ወዳጃችን የሆነው ኢየሱስ በአጠገባችን ቆሞ ያበረታናል 2ኛ ጢሞቴዎስ 4 ፥ 14 _ 18 በያዝነው እውነትም አጽንቶ በማቆም ለሰማያዊው መንግሥት ይጠብቀናል ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን አሜን

ይህንን መልእክት የምታነቡ ቅዱሳን ወገኖች ጌታ ይባርካችሑ ለማለት እወዳለሁ

በጌታ አገልጋያችሑና ወንድማችሑ የሆነው ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment