Sunday 7 December 2014

የመልዕክት ርዕስ

እስመ ውእቱ ክርስቶስ ዘየኃድር ላዕሌክሙ ተስፋ ስብሐቲነ

የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው

ቆላስያስ 1 ፥ 27


አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት


ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው 

አንቺ ነሽ 



ምንጭ ፦ ቅዳሴ ማርያም ዘአባ ሕርያቆስ


ይህንን መልዕክት የምታነቡ ወገኖቻችን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እናቶችና አባቶች በሥምረተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፣ በፈቃደ እግዚአብሔር ይህንን ቃለ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ይዘን መጥተናል ዛሬ ከላይ በጠቀስኳቸው በመጽሕፍቅዱሱ ቃልና በቅዳሴ ማርያሙ ቃል ላይ ያለውን ዝርዝር ሃሳብ በንፅፅር እንመለከተዋለንና ተከታተሉ 
ከዚያ በፊት ግን በቆላስያስ መጽሐፍ ላይ የተጻፈውን የዚህን ምዕራፍ ክፍል ሙሉ ቃሉን እንመለከታለን ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለጠግነት ምን እንደሆነ ሊያስታውቅ ወደደ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው በማለት የሚናገር ነው ቆላስያስ 1 ፥ 26 - 28 ሐዋርያው ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር በማለት ሊገልጸው የወደደው የእግዚአብሔርን መሠረታዊ ዓላማ የያዘ በመሆኑ ነው በኤፌሶን 1 ፥ 9 እና 10 ላይ እንዲህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ተጽፎ እናገኛለን በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው በማለት ይናገራል እንደገናም በአሕዛብ ዘንድ የዚህ ክብር ምሥጢር ምን እንደሆነ ሊያስታውቅ ወደደ ማለቱ ምሥጢሩ ክርስቶስ በአሕዛብም ውስጥ የማደሩ ጉዳይ ነው ቀደም ሲል አሕዛብ እንደ አይሁድ የክርስቶስ አካል በሆነችው ቤተክርስቲያን ውስጥ የተስፋውን ቃል እንደሚካፈሉና አብረው እንደሚወርሱ አልተገለጸም ነበር ኤፌሶን 3 ፥ 6 አሁን ግን ይሄ እድል ደርሷቸው በውስጣቸው ከማደሩ የተነሳ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና የአይሁድ ጌታ የሆነው ኢየሱስ የአሕዛብም ጌታ ሆነ ሮሜ 10 ፥ 12 እና 13 ይህ ተስፋ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ምክንያት የማያልፈውንና እድፈት የሌለበትን ርስት ለመቀበል እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የተወለድንበት ስለሆነ ሕያው የሆነ ተስፋ ነው 1ኛ ጴጥሮስ 1 ፥ 3 - 5 ለዚህም ነው የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው የተባልነው ተስፋችን ሕያውና የክብር ተስፋ ነው ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን አሜን ታድያ መጽሐፍቅዱሳችን ይህንን የመሰለ ተስፋ በእናንተ ውስጥ ነው እያለን ሰዎች ግን ተስፋ ሊሆናቸው የማይችለውን ነገር ይዘው ተስፋ ያደርጋሉ አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው አንቺ ነሽ ምንጭ ቅዳሴ ማርያም ዘአባ ሕርያቆስ ከዚህ ሃሳብ የተነሳ አዳም ብቻ ሳይሆን በአሁን ዘመን ያሉ በዚህ መረዳት ውስጥ የሚገኙ በስደት ውስጥ እንዳሉ አድርገው እራሳቸውን ይቆጥራሉ ከዚህ ስደታቸው ሊወጡ የሚችሉትም በማርያም ተስፋ እንደሆነ በማመን ይኖራሉ ይናገራሉ ያስተምራሉ መጽሐፍቅዱሳችን ግን አሁንም ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረው ምስጢር ተገልጦአል ይህም የክብር ተስፋ የሆነው ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ መሆኑ ነው ይለናል በመሆኑም እነዚህ ሰዎች በተሳሳተ ተስፋ ውስጥ ገብተው የሚዳክሩት ይህ ተሰውሮ የነበረው ምሥጢር እና በኋላም ለቅዱሳኑ የተገለጠው የክብር ተስፋ የሆነው ክርስቶስ ምሥጢር ስለሆነባቸው ነው ይህ የክብር ተስፋ የሆነውን ክርስቶስን ግን ወደ ውስጣቸው ቢያስገቡ ሁሉ ነገር ግልጽ ይሆንላቸዋል የተሸሸገ ወይም የተሰወረ ነገር አይኖርም እነርሱም እስካሁን ድረስ በስደት እንዳሉ አድርገው እራሳቸውን አይቆጥሩም ስለ እኛ የተሰደደ ጌታ አለ መዝሙረኛው ዳዊት ናሁ ሰማእናሁ በኤፍራታ ወረከብናሁ ውስተ ኦመ ገዳም ንበውእ እንከሰ ውስተ አብያቲሁ ለእግዚአብሔር ወንሰግድ ውስተ መካን ኀበ ቆመ እግረ እግዚእነ ትርጉም እነሆ በኤፍራታ ሰማነው በዱር ውስጥም አገኘነው ወደ ማደርያዎቹ እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን መዝሙር 131 (132)፥ 6 እና 7 ኢየሱስ በኤፍራታ ዱር ውስጥ የተገኘው እኛን ከስደት አውጥቶ ወደ ማደርያዎቹ ሊያስገባን ነው ለዚህ ነው ዳዊት እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን ያለው በትንቢተ ሆሴዕ መጽሐፍ ላይም እምግብጽ ጸዋእክዎ ለወልድየ በማለት ይናገራል ትርጉሙም ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት ማለት ነው ትንቢተ ሆሴዕ ምዕራፍ 11 ፥ 1 እና 2 ፣ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ፥ 16 - 22 የኢየሱስ ወደ ግብጽ መሰደዱ እኛን ከግብጽ ለማውጣት ነው የግብጽ ኑሮ ስቃይና መንገላታት የበዛበት የስደትና የባርነት ቤት ኑሮ ነው ዘጸአት 20 ፥ 2 ፣ ዘዳግም 4 ፥ 20 ፣ 1ኛ ነገሥት 8 ፥ 51 ኢየሱስ ወደ ግብጽ ተሰዶ የቀረ አይደለም ከግብጽ ተመልሶአል የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ፥ 19 - 23 እንደገናም እኛም ከግብጽ የወጣን ብቻ አይደለንም በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ሆነናል ስለዚህ መጽሐፍቅዱሳችን እምይእዜሰ ኢኮንክሙ ነግደ ወፈላሴ አላ አንትሙ ሰብአ ሀገሪቶሙ ለቅዱሳን ወሰብአ ቤቱ ለእግዚአብሔር ትርጉም እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም ኤፌሶን 2 ፥ 19 አለን በክርስቶስ ምክንያት ይሄ ሁሉ ሆኖለት የእግዚአብሔር ቤተሰብ የሆነ ሰው ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት የተወለደ ስለሆነ በውስጡ ባለው በዚህ የክብር ተስፋ ይጽናናል እንጂ ተስፋ እንደሌለው ሰው ማርያም ሆይ ከገነት በተሰደድኩ ጊዜ ለእኔም ተስፋዬ አንቺ ነሽ አይልም እንደገናም ይህ አስተሳሰብ የብዙዎች ነውና ብዙዎች በዚህ አሳዛኝ እና ፍጻሜ በሌለው ተስፋ ውስጥ አሉ አዳም ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው ክርስቶስ እንጂ ማርያም አልነበረችም የቅዳሴ ማርያም ባለቤት የሆነው ሕርያቆስ ከወዴት አግኝቶ ይህንን እንደተናገረው ባላውቅም እኛ ግን የታዘዝነው ጌታን በልባችን እንድንቀድስ እንጂ ወዳሴ ማርያም ቅዳሴ ማርያም እያልን ማርያምንና ሌሎችንም ፍጡራን እንድንቀድስ እና እንድንወድስ አይደለም መዝሙር 41 ፥ 13 ፣ መዝሙር 72 ፥ 18 - 20 በተለይ መዝሙር 72 ፥ 18 ን ስንመለከት ብቻውን ተአምራትን የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ የምስጋናው ስም ለዓለምና ለዘላለም ይባረክ ምስጋናውም ምድርን ሁሉ ይሙላ ይሁን ይሁን ይለናል በትንቢተ ኢሳይያስ 6 ፥ 3 ላይም አንዱም ላንዱ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያሉ አምላካቸውን አመሰገኑ እንጂ ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም ሠርተው ማርያምን ሲያመሰግኑ አላገኘንም ምስጋና የሚገባው እግዚአብሔር ብቻ ነውና 2ኛ ሳሙኤል 22 ፥ 4 ፣ የዮሐንስ ወንጌል 1 ፥ 3 ፣ ሮሜ 11 ፥ 36 መጽሐፍቅዱሳችን ላይ አዳም በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው ማርያም ናት የሚል አልተጻፈም ማርያም በፍጥረት መጀመርያ አልነበረችም የስብሐተ ፍቁር ደራሲ ግን አሁንም ከየት እንዳመጣው በማይታወቅ ሃሳቡ የእግዚአብሔርን ሕላዌ ለማርያም በመስጠት እምቅድመ ሰማያት ወምድር ሐልወትኪ ፀሐይ ወወርኅ ኢቀደሙኪ መላዕክተ ሰማይ ይትለአኩኪ አለ ትርጉም ከሰማይና ከምድር መፈጠር አስቀድሞ ነበርሽ ፀሐይና ጨረቃም አልቀደሙሽም የሰማይ መላእክትም ያገለግሉሽ ነበር ምንጭ ስብሐተ ፍቁር ዘማርያም ገጽ 162 ከሰማይና ከምድር መፈጠር አስቀድሞ የነበረ መጀመርያና መጨረሻ የሌለው አልፋና ኦሜጋ እግዚአብሔር ብቻ ነው ዘጸአት 3 ፥ 14 ፣ ራዕይ 1 ፥ 18 እርሱን እንኳን ጸሐይና ጨረቃ ማንም አይቀድመውም እርሱ በኪሩቤል ሠረገላ ላይ ያለና በቅድምና የሚኖር ጌታ ነው ማርያም ግን እንዲህ አይደለችም እርሷ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው የታጨች ድንግል ናት ኢየሱስን ከወለደች በኋላም በዚህ ምድር ላይ የነበራትን ዘመን ጨርሳ ወደ አምላኳ ሄዳለች የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 1 ፥ 26 - 56 ከዚህ ባለፈ ሁኔታ የእግዚአብሔር ቃል ስለ እርሷ የሚነግረን ነገር የለም ነገር ግን እንዲሁ ከሰው የመጣውን ልብ ወለድ ድርሰት ይዘን ከሰማይና ከምድር መፈጠር አስቀድሞ ነበርሽ ጸሐይና ጨረቃ አይቀድሙሽም መላዕክት ይላኩሻል ብንል አይሆንም እንዲሁ ለሕዋው መናገር ጉም መዝገን ይሆንብናል እንግዲህ ብዙዎች ይህንን ካለመረዳት የተነሳ ነው ከሰማይና ከምድር መፈጠር አስቀድሞ ነበረች ጸሐይና ጨረቃ አይቀድሟትም የሚለውን ልብ ወለድ ሃሳብ ይዘው አዳም ከገነት በተሰደደ ጊዜ ለአዳም ተስፋው አንቺ ነሽ ብለው የተነሱት የሰው ልጆች ተስፋ ግን ለማርያምም ሳይቀር ኢየሱስ ነው እርሱ በውስጣችን ያለ የክብር ተስፋ ነው ስለዚህም በቃሉ ውስጥ ያለ እውነት ደግሞ የሚናገረው ይህንኑ ነውና ከዚህ ጌታ ውጪ ሌላ ነገር ተስፋ አናደርግም እነዚህ ሰዎች ታድያ ማርያምን ተስፋ በማድረግ የተቀመጡ ብቻ ሳይሆኑ ኪዳን ወይም ውል አላት ብለውም በኪዳኗ የሚታመኑ ስለሆኑ ዝክር ዘክረው ማኅበር ጠጥተው በስሟ የሚማጠኑ ናቸው ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ተስፋውን ፈጽሞ ሊዋሽ በማይችልና በማይፈርስ ኪዳን ለአንዴና ለዘላለም የእግዚአብሔር አድርጎናል ዕብራውያን 9 ፥ 11 - 28 ፤ ዕብራውያን 10 ፥ 1 - 31 በዘላለም ኪዳን ደም ከኃጢአቱ ነጽቶ ለእግዚአብሔር የሆነ ሰው እግዚአብሔር ኪዳን ወዳልገባበት ውል ወዳልፈጸመበት ነገር ውስጥ ገብቶ አይቸገርም ይህ በማርያም በኩል ተገባ የተባለው ውል በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተጻፈ አይደለም እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ በኩል የፈጸመው ኪዳን ስላለ ሌላ ኪዳን ለሰው ልጆች አይገባም ታድያ መምጣት ያለብን ወደዚህ ኪዳን ነው ከዚህ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው ይላል ጌታ በልባቸው ሕጌን አኖራለሁ በልቦናቸውም እጽፈዋለሁ ብሎ ከተናገረ በኋላ ኃጢአታቸውንና ዓመፃቸውን ደግሜ አላስብም ይላል የእነዚህም ሥርየት ባለበት ዘንድ ከዚህ ወዲህ ስለ ኃጢአት ማቅረብ የለም ይለናል ዕብራውያን 10 ፥ 15 - 18 ይህ ኪዳን ልጅነትን ያስገኘ የኃጢአትን ሥርየት ያመጣ ስለሆነ የሚተካከለው የለም ለዚህ ነው በውዳሴ ማርያም ዘእሁድ ላይ ወኮነ አራቄ ለሐዲስ ኪዳን በውሂዘ ደሙ ቅዱስ አንጽሆሙ ለመኃይምናን ወለሕዝብ ንጹሐን ያለን ትርጉም ቅዱስ ደሙን በማፍሰስ አማኞቹንና ሕዝቡን በማንጻት የሐዲስ ኪዳን አስታራቂያችን ሆነ ይለናል በመሆኑም መታረቅን ያገኘና አስታራቂ ያገኘ ሰው ሌላ መታረቅያ መንገድ አይፈልግም ለመታረቅም ብሎ ዝክር አይዘክርም ሰንበቴ አይጠጣም እንዲህ ማድረግ ደግሞ የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር መቁጠር የጸጋውንም መንፈስ ማክፋፋት ነውና ፍርድን ያመጣል ዕብራውያን 10 ፥ 29 - 31 እንደገናም በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና አካሉ ግን የክርስቶስ ነው እያለ ይናገራል ቆላስያስ 2 ፥ 16 - መጨረሻው የተጻፈውን እናንብብ ወደ ክርስቶስ የመጣና ራስ በሆነው በክርስቶስ በኩል የአካሉ ብልት ሆኖ የተገጠመ ሰው ለደህንነትሕ በዓላትን እያከበርክ ዝክር እየዘከርክና ጸበል ጸዲቅ እየቀመስክ ኑር አይባልም ከዚህ ተርታ ወጥቶአልና ከዚህ ተርታ የሚያወጣን ደግሞ የሞተልን ኢየሱስ ነው ወደ ኢየሱስ ስንመጣ ይሄ ሁሉ እንደማያስፈርድብን ገብቶን ዝክሩንም ሆነ በዓል እያከበሩ መማጸኑን ማንም ተዉ ሳይለን እንተዋለን እግዚአብሔር ወደዚህ ወደ ዘላለሙ ተስፋና ኪዳን በምሕረቱ ይጥራን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰው አሜን

ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment