Wednesday 10 December 2014

የመናኙ ሰው ዕድል ፈንታው ክርስቶስ ሆነ Part one



የመናኙ ሰው ዕድል ፈንታው ክርስቶስ ሆነ


Part one










የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቅዱሳን ወገኖቼ ዛሬ ወደ እናንተ ይዤ የመጣሁት ሃሳብ ለየት ያለና ብዙዎቻችሁንም ለወንጌል ሥራ ይበልጥ እንድትነሳሱ እንድትጸልዩና የምሥራቹንም ቃል ወደ ሰዎች እንድታደርሱ እንድትሰብኩም የሚያደርግ መልዕክት ነው የዛሬው በጽሑፌ ላይ የማቀርብላችሁ እንግዳዬ አባ ዘውዱ ኪዳኑ ይባላል አባ ዘውዱን አንተ ብዬ መጥራቴና መጻፌ የቅርብ ጓደኛዬና የአገልግሎት ባልንጀራዬ ስለሆነ ከዚያም መልስ ደግሞ ጌታን ተቀብሎ አዲስ ፍጥረት በመሆኑ የሁላችንም ማለት የጌታ ልጆች ለሆነው ሁሉ ወንድም ስለሆነ ነው ከአባ ዘውዱ ኪዳኑ ጋር የብዙ ዓመታት ትውውቅ የነበረንና በወንጌል እውነት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛ የማዳን ሥራ በማመናችን ምክንያት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተባረርን የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ የክብሩ ወንጌል አገልጋዮች ነን  በሕይወታችን ብዙ ስደት ረሃብና መንገላታት እስራት ስድብና ዛቻ ድብደባ ሳይቀር አልፎአል በመጨረሻም የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ወደ ጥንተ መሠረቷ ወደ ወንጌል እውነት ለመመለስ የመነኮሳት ሕብረት በሚል ስያሜ ወደ ስድስት የምንደርስ መነኮሳት ተሰባስበን በ1996 ዓመተ ምሕረት በኤግዚቢሺን ማዕከል ባካሄድነው የቅዳሜና የእሁድ የሁለት ቀን ኮንፍረስ ብዙ ነፍሳት ድነዋል በሽተኞች ተፈውሰዋል ቅዱሳንም ተባርከውበታል ነገር ግን አገልግሎቱ የእግዚአብሔር የማዳኑ ጉልበት የተገለጠበት በመሆኑ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተነስታ እንዲሁ በስማ በለው የዘመኑ መናፍቃን ስትል አውግዛናለች እኛም ውግዘቱ ተገቢ አለመሆኑን ከእግዚአብሔር ቃል አስረጂ በማቅረብ ምላሽ ሰጥተንበታል ነገር ግን ይህ እንቅስቃሴ ከእኛም ሌላ ብዙዎችን ያፈራ በመሆኑ እስካሁን ድረስ ይበልጥ እየቀጠለና እየተፋፋመ ይገኛል Joshua Breakthrough Renewal Teaching and 
Preaching Ministry
ከዚያው የቀጠለና ያንኑ አገልግሎት ወደ ፍጻሜ ለማምጣት እየተንቀሳቀሰ ያለ አገልግሎት ነው  አባ ዘውዱ ኪዳኑ በአሁኑ ሰዓት የሚኖረው ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን እስካሁን ድረስ ጌታን በንጽሕናና በቅድስና በታማኝነት በእግዚአብሔር ጸጋ እየታገዘ የሚያገለግል የወንጌል አርበኛና የጸሎትም ሰው ነው አሁን በቅርቡ ደግሞ ከአንዲት የተባረከች እህት ጋራ በቤተክርስቲያን በቅዱሳንና በእግዚአብሔር ፊት የጋብቻ ስነ ሥርዓትን በመፈጸም  በቅዱስ ጋብቻ በትዳር ተጣምሮአል ጌታ ዘመኑን ሕይወቱን አገልግሎቱንና ቤቱንም ይባርክ ስል ልባርከው እወዳለሁ  ከዚህ በመቀጠል እንግዲህ የማካፍላችሁ ከሣቴ ብርሃን ከተባለ መንፈሳዊ መጽሔት ዝግጅት ክፍል ጋር ተገናኝቶ የሰጠውን የሕይወት ምስክርነት ጥቂቱን ወደ እናንተ በማቅረብ ይሆናል ምስክርነቱም ከዚህ እንደሚከተለው ነው

      ጋዜጠኛው አባ ዘውዱን ወደ ምስክርነቱ ጎራ ከመቀላቀሉ በፊት ስለ አባ ዘውዱ እንዲህ ሲል ያትታል ይህ ሰው የእድሜውን እኩሌታ ያሳለፈው ከገዳም ገዳም በመንከራተት ነው ለነፍሱ እረፍት አላገኘም እንጂ ጽድቅን ፍለጋ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም በዘመኑ ጽድቅን ፍለጋ ብዙ ተንከራትቻለሁ ከአገር አገር ዞሬያለሁ እግዚአብሔር ይገለጥልኝ ዘንድ በተራቆተ ሰውነቴ ላይ ሰንሰለት ታጥቄ ብዙ ጸልያለሁ ይሄ ሁሉ ደግሞ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ የመሻት በነፍሴም እረፍት ለማግኘት የነበረኝን ብርቱ ጉጉት የሚያሳይ ነው ሥራዬን ሁሉ ሠርቶ ያሣረፈኝ ጌታ በውስጤ ተገልጦ የማድንህ እኔ ነኝ የማጸድቅህ እኔ ነኝ የምቀድስሕ እኔ ነኝ የሚል ድምጹን በውስጤ እስከ ሰማሁባት አንዲት የተባረከች ሌሊት ድረስም ያለ ዕረፍት ተቅበዝባዥ ነበርኩ አንድያ ጽድቅን ፍለጋ እየተንከራተትኩም አዕምሮዬ በኃጢአተኝነት ይከሰስ ነበር በማለት ለመግቢያ ያህል ዘግቦ ጽፎልናል በመቀጠልም አባ ዘውዱ ወደ መድረኩ በመጋበዝ ጥሪያችንን አክብረው በመምጣትዎ በከሣቴ ብርሃን መጽሔት ዝግጅት ክፍል ስም ከልብ አመሰግናለሁ በማለት ወደ ጥያቄው ይገባል

   ከሣቴ ብርሃን አባ ዘውዱ በቅድሚያ የት እንደተወለዱና እንዳደጉ የመንፈሳዊ ሕይወትዎም መነሻ ምን ይመስል እንደነበር ቢያጫውቱን ?

አባ ዘውዱ ትውልዴ ሰሜን ሸዋ ተጉለት አውራጃ ውስጥ ነው ከደብረ ብርሃን የሦስት ሰዓት መንገድ ያስኬዳል አባቴና እናቴ ገበሬዎች ናቸው እስከ ሰባት ዓመቴ ድረስ እዚያ ቆይቼ ወደ ደብረ ብርሃን መጣሁ ከዚያ በፊት ግን ገጠር ሳለሁ እረኛ ነበርኩ ሆኖም ፊደልን እማር ነበር ቤተሰቦቼ ወደ ቄስ ትምህርት ቤት የሚልኩኝ ፊደል ቆጥሬ የቤተክርስቲያን አገልጋይ እንድሆንላቸው ነበር በአንድ ችግር ምክንያት ቀያችንን ለቀን ደብረ ብርሃን ስንገባም እኔ ያንኑ ትምህርት ቀጥዬ እስከ ዳዊት ደረስኩ አንድ ዕለት ግን መምሕራችን እኔንና አንድን ልጅ ጠርተው ወደፊት መሆን የምንፈልገውን ጠየቁን ሁለት ምርጫም አቀረቡልን ከድቁናና ከአስኳላ ( ዘመናዊ ትምህርት )የቱን ትመርጣላችሁ ? አሉን ልጁ ድቁና ሲመርጥ እኔ አስኳላ ይሻለኛል አልኩ እሳቸው ባመቻቹልኝ ዕድል ተጠቅሜም አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ትምህርት ቤት ገባሁ እዚያ ከአንድ እስከ ስምንት ተምሬ ሚኒስትሪ ስወድቅ ትምህርቴን አቋርጬ ወደ ቤተክህነት ተመለስኩ ሆኖም የቤተ ክህነቱን ትምህርት አጥብቄ እንዳልይዘው ዕለት ዕለት ውስጤን የሚፈታተነኝ ሃሳብ ውስጤ ይመላለስ ጀመር ይኸውም ጽድቅና ኩነኔ እንደሌለ የመቁጠር ሃሳብ ነው

 ከሣቴ ብርሃን ይህ ጽድቅና ኩነኔ እንደሌለ ማሰብ ከየት መጣ ዝም ብሎ በአዕምሮዎ የተፈጠረ ነው ወይስ ሃሳቡ የተቀዳበት ምንጭ አለው ?

አባ ዘውዱ ምንጭስ አለው እርሱም ከ1966 ዓመተ ምህረት አንስቶ የደርግ አብዮት ባቀጣጠለው የኮምኒዝም ርዕዮተ ዓለም አንዳንድ አስተሳሰቦች ከመማረኬ የመጣ ነው ታላላቆቹን መንፈሳዊ እሴቶች በማናናቅ እና በማዋደቅ የተገለጠው የዚያ ዘመኑ ርዕዮት ጠርጎ ሊወስደኝ ምንም አልቀረውም ነበር እግዚአብሔር ጣልቃ ገብቶ ባያስጥለኝ ኖሮ የዛሬውን ዘውዱ በዚህ ታሪክ አታገኘውም ነበር በድፍረት እግዚአብሔር የለም አላልኩም እንጂ ጽድቅና ኩነኔ የሚባል ነገር የለም ወደ ማለት ግን ደርሻለሁ

 ከሣቴ ብርሃን ጽድቅና ኩነኔ እንደሌሉ እርግጠኛ ከሆኑ ኮናኝና አጽዳቂውን የለም ለማለት ምነው ፈሩ ? ኮምኒስቶቹ እኮ ሁሉንም ነው የካዱት

አባ ዘውዱ አይ እኔ እግዚአብሔር የለም የሚል ሃሳብ አልነበረኝም ዝም ብሎ አዕምሮዬ ውስጥ የተቀመጠውና የገዛኝ ሃሳብ ጽድቅና ኩነኔ የሚባል ነገር እንደሌለ የመቁጠር ነገር ነው የእኔ ክህደት ከፊል ክህደት ነው ማለት ይቻላል ጌታ መልሱን የሰጠኝም በዚያው አቅጣጫ ነው አንድ እኩለ ቀን ላይ ቁጭ ባልኩበት ተመስጦ ውስጥ ገብቼና በነፍሴ ሽቅብ ተነጥቄ በገባሁበት መንፈሳዊ ዓለም ያየሁት ትዕይንት ነው ሲኦልና ገነት ጽድቅና ኩነኔ መኖራቸውን አምኜ እንድቀበል ግድ ያለኝ ትዕይንት እግዚአብሔር የክህደት ሃሳቤን የመታበት ስለነበር ከፍተኛ የጽድቅ ረሃብና የመዳን ጉጉት ውስጥ የገባሁትም ከዚያች ዕለት አንስቶ ነው ከዓለም ኃጢአት ሸሽቼ በእግዚአብሔር ጉያ ለመግባት መንከራተት የጀመርኩትም ከዚያች ቀን በኋላ ነው በማለት አባ ዘውዱ ኪዳኑ የገዳሙን ሕይወት በሰፊው ማውጋት ይጀምራሉ ይህንን በተመለከተ በቀጣዩ የክፍል ሁለት ዝግጅታችን እናቀርበዋለን እስከዚያው በጌታ ሰላም የምሰናበታችሁ


ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ







No comments:

Post a Comment