Friday 5 December 2014

የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ምዕራፍ ሁለት ክፍል ሦስት



የቤተክርስቲያን ተልዕኮ


ምዕራፍ ሁለት



ክፍል ሦስት



ከሐሰተኛ ነቢያት ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ራስንና መንጋውን መጠበቅ



ስለዚህ ማንም በሰው አይመካ

1ኛ ቆሮንቶስ 3 21



የተወደዳችሁ ወገኖች በክፍል ሁለት ትምህርታችን ላይ የሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች መነሻ ሐሳብ በሚል ንዑስ አርዕስት ሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች ብዙ ጊዜ ከምንና ከየት መነሳት እንደሚወዱ የተመሠረቱበት ትክክለኛና እውነተኛ የእግዚአብሔር ሃሳብ የሌላቸው በመሆኑ ሁልጊዜ ለተሳሳተው አሠራራቸው እንደመነሻ አድርገው የሚጠቀሙት በአገልግሎታቸውም ሆነ በትንቢታቸው በአጋጣሚ የተፈጸሙትን ጥቂት እውነቶች ይዘው ራስ ወዳድ በመሆናቸው በሁሉም ነገር ከማንም ይልቅ ለራሳቸው ቅድሚያ የሚሰጡ ናቸውና እንደገናም በሁሉም ነገር ራሳቸውን ከሌሎች የተሻሉ አድርገው የሚቆጥሩ በመሆናቸው ራሳቸውን ቆልለው ጋራም አሳክለው በመቅረብ ከሌላው ይልቅ እነርሱ ጋር የተሻለ ነገር እንዳለ አድርገው የሚናገሩ በመሆናቸው አብዛኛውን ሕዝብ ወደ ስሕተት አሠራር የውሰዱ መሆናቸውን በክፍል ሁለት ማብራርያችን ላይ በሰፊው አይተናል የክፍል ሦስት ትምህርታችን ከዚሁ የቀጠለ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ ማንም በሰው አይመካ  ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና ጳውሎስ ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው ይለናል 1 ቆሮንቶስ 3 21 _ 23 እጅግ በጣም የሚደንቅ ቃል ነው በተለይ በሐዲስ ኪዳን ዘመን ያለን ክርስቲያኖች የክርስቶስ የሆንበትን ምስጢር በትክክል ከተረዳን ይኸው የራሱ ያደረገን ክርስቶስ ከሚያስመካን በስተቀር ሌላ የእኛ የምንለው ትምክህት የለንም እንደውም በዚህ ጉዳይ ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውን አንድ ሃሳብ እንይዛለን ሐዋርያው እንዲህ አለ ትምክህት የሚያስፈልግ ከሆነ፥ ከድካሜ በሚሆነው ነገር እመካለሁ ለዘላለም የተባረከ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት እንዳልዋሽ ያውቃል በደማስቆ አርስጦስዮስ ከተባለ ንጉሥ በታች የሆነ የሕዝብ ገዥ ሊይዘኝ እየወደደ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር በቅጥሩም ባለ መስኮት በቅርጫት አወረዱኝና ከእጁ አመለጥሁ አለ 2 ቆሮንቶስ 11 30 _ 33 የገባው ሰው ንግጝርም ሆነ ቋንቋ እንግዲህ ይሄ ነው የምህረቱንና የጸጋውን ብዛት እንዲሁም የየራሱን የድካሙን ልክ ያወቀ ሰው የሚለው ነገር ቢኖር ዛሬም ጳውሎስ ያለውን በመድገም ነው ለዘላለም የተባረከ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት እንዳልዋሽ ያውቃል ብሎ ይሄ ሐዋርያ የተናገረለት አምላክ በፊቱ የተገለጥን እንጂ ልንሠወር የማንችል ነንና በክርስቶስ የሆነውን እራስን ካለማወቅ ጠንቅ የተነሳ  እኛ እኮ እንዲህና እንዲያ ነን ብንልም እርሱ ግን ከነድካማችን ጠንቅቆ ያውቀናልና የሚደንቅ አይደለም አሁንም ጳውሎስ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው ከእኛ በተቃራኒው ነው እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ አለ 2 ቆሮንቶስ 12 9 ታድያ ዛሬ ክርስቲያኑ ሁሉ አገልጋዩና መሪው ሳይቀር ይሄን እውነት ቢያውቅና በሕይወቱም ቢተገብር የት በደረሰ ነበር ግን የተያዝንበት በሽታ ይሄ ስለሆነ  የእግዚአብሔር ፈውስ በሕይወታችን እስኪመጣ ድረስ ሁላችንም በዚህ ነገር ክፉኛ ታመናል እንዲያው ለነገሩ ሐሰተኛ ነቢያትና አስተማሪዎች አልን እንጂ እኛው  በቤቱ አለን ጤናማ ክርስቲያኖችና አገልጋዮች ነን እናገለግላለን እንመራለን እናስተዳድራለን እንመግባለን እንሰብካለን ወዘተ የምንል ሰዎች ሁሉ ሀገር ጉድ እስኪለን ድረስ መከባበርና መቀባበል መደጋገፍም አቅቶን እርስ በእርስ የሚያባላንና የሚያነካክሰን ነገር ይኸው በክርስቶስ የሆነውን ማንነት ካለመረዳትና  ራስንም ማወቅ  ከሌለበት የራስ ትምክህት የስም የአገልግሎትና የሥልጣን ትምክህት ተይዘን ነው እንደውም በእኛ ዘመን ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው አንድ የቤተክርስቲያን  አገልጋይ ነኝ ባይ ማንም ሰው ከእኔ ጋር ሳይስማማ ማገልገል አይችልም እያንዳንዱ ሰው Under me ( አንደር )ማለትም ከእኔ በታች ሆኖ ነው ማገልገል  ያለበት አለ እኔም ጥቂት አሰብኩና እርሱ እየተናገረበት ያለው ሃሳብና የተቀመጠበት ቦታ በፍጹም አብረው የማይሄዱ መሆናቸውን ካስተዋልኩ በኋላ ምንም ልለው ስላልፈለኩ በጊዜ ቢሮውን ለቅቄ ተሰናብቼው ወደ ቤቴ ሄድኩኝ በዚህ ጉዳይ በክርስቶስ በሆነው ማንነት ራሱን ከማንም በላይ ያወቀው ጳውሎስ ግን ስለ ጢሞቴዎስ ሲናገር ጢሞቴዎስም የመጣ እንደ ሆነ በእናንተ ዘንድ ያለ ፍርሃት እንዲኖር ተጠንቀቁ፤ እንደ እኔ ደግሞ የጌታን ሥራ ይሠራልና፤ እንግዲህ ማንም አይናቀው ነበር ያለን  ከእኔ በታች አንደር ሆኖ ነው የሚያገለግለው በማለት ሲንቀውና  ሲያናንቀው ሊቀበሉት በተዘጋጁ በሌሎችም ፊት  ሲያንኳስሰው  ግን አናየውም እንደ እርሱ የጌታን ሥራ የሚሠራ ነውና 1 ቆሮንቶስ 16 10 መጽሐፍቅዱሳችን አሁንም በ1ኛ ቆሮንቶስ 4 6 እና 7 ላይ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ ከተጻፈው አትለፍ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል ? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው ? ይለናል ነገር ግን አንዳንድ ሰነፍ ሰው እነዚህን የተጻፉትን የእግዚአብሔር ቃል እውነቶች ያውቃቸዋል እንኳ ቢባል እንዲያው በዘልማድ ከሚያውቅ በስተቀር ለሕይወቴ ጥቅም ብሎ በመውሰድ በውል ያልተረዳና ያላጣጣመም በመሆኑ አጠገቡ ያለውን ወንድሙን ንቆ ብቻ የሚተው አይደለም ተግባሩ ያማረበት ይመስል በሌሎች ሰዎች ፊት ሳይቀር ወንድሙንና የአገልግሎት አጋሩን ያናንቃል በዚህ ውስጥ ደግሞ እራሱ የተናቀ ሆኖ  ይገኛል ጎልያድ ዳዊትን ሲያናንቀው እስቲ ለነገ እንኳን  በማይባሉ ቃላቶች እጅግ በጣም አሳንሶ ነበር ነገር ግን በዚያው ቅጽበት የጎልያድ ውርደቱ ፈጠነ እንደገናም  ጎልያድ ብቻ ሳይሆን መርዶክዮስን ያናናቀውና ለሞቱም መስቀል ተክሎ ዘሮቹን ሳይቀር ሊያጠፋ አዋጅ ያስነገረለት ሐማም ውርደቱና ሞቱ በዚያው ልክ እጅግ የፈጠነ ነበር  ራሳቸውን ከፍ በማድረግ እኔ እበልጣለሁና ከእኔ ወዲያ ላሳር ሲሉ ሌላውን የሚያናንቁ ሰዎች በሕይወታቸው ፈጥነው ንስሐ ካልገቡ እንደ ጎልያድም ሆነ እንደ ሐማ ውርደታቸው የሚፈጥንና የሚቸኩል እነዚያው ሌላውን ሲያጥላሉና ሲያናንቁ የተገኙ ሰዎች ናቸው እስኪሆን ድረስ ግን ዛሬ ላይ ባለ ነገ ደግሞ ሊለወጥ በሚችል ምቾታቸውና ሹመታቸው ተመክተው ያቅራራሉ ይፎክራሉ ያናንቃሉ ስለዚህ ወገኖቼ ጌታ እግዚአብሔር ፍልስጥኤማዊ አስተሳሰብን ካዘለ ከከንቱ ማናናቅ የበዛበት ቀረርቶ እና ሽለላ ፈጽሞ  ይጠብቀን  ጳውሎስ በራሱ ጢሞቴዎስን እንደ እኔ የጌታን ሥራ የሚሠራ ነው ማለቱ እኔ ብቻ ከሚል ማንነትና እኔነት የወጣ መሆኑን በግልጽ ያሳያል ከዚህም ሌላ ጳውሎስ ብቻ ሳይሆን ጢሞቴዎስም እንደ ጳውሎስ የጌታን ሥራ የሚሠራ ነውና ጳውሎስ እንደ እኔ  የጌታን ሥራ የሚሠራ ነው በማለት መሠከረለት እንጂ ከራሱ አላሳነሰውም የጌታን ሥራ የሚሠራ ደግሞ ወረድ ጎንበስ ደፋ ቀና ቢልም የጌታን ሥራ ከመስራት የተነሳ እንጂ ከማንም የሚያንስ ስለሆነ አይደለም ይሄ ነው እንግዲህ በጳውሎስ ያለና በሌሎቻችንም ሊኖር የሚገባ የወንጌል የመረዳት ስፋት ነገር ግን ከዚህ ይልቅ በሌሎች ላይ ለመሠልጠን ብለን ወንጌልን ማለት ኢየሱስን በእኔነታችን እንዳንሸፍን መጠንቀቅ ይኖርብናል አለበለዚያ ልካችንን አውቀን እንደ ናቡከደነጾር ልዑሉን እስክንባርክ ድረስ እግዚአብሔር ልንማርበትና ልንሠራበት በወደደው መንገድ ፈቅዶ ይሠለጥንብናል ራስ ወዳድ የሆነውን የእኔነት ባሕርያችንንም በማይመቹ መንገዶች ውስጥ አሳልፎ በመግራት ያሰለጥነዋል  እርሱን ምን ታደርጋለህ ? ምንስ ትሠራለህ ? የሚለው ማንም የለም ትንቢተ ዳንኤል 4 35 ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 5 በሙሉ እንመልከት ጳውሎስ ስለዚህ ማንም በሰው አይመካ  ሲል እኛ የክርስቶስ ከመሆናችን የተነሳ ሁሉ የእኛ ሌላው ቀርቶ ያለውና የሚመጣው ሳይቀር የእኛ እኛም የክርስቶስ ክርስቶስም የእግዚአብሔር መሆኑን ተረድቶ ነው በዚህ በጳውሎስ የትምህርት አባባል ውስጥ የራሱ የሆነ ማንም የለም ይህ አስተምህሮ የገባው እያንዳንዱ ሰውም በትክክል ገብቶት  ከሆነ እኔ የራሴና ለራሴ ብቻ ነኝ እንጂ የሌላው አይደለሁም የሌላው ልሆንም አልችልም ወይም የእገሌና የነእገሌ ብቻ ነኝ  እንጂ የማንም አይደለሁም ማለት የሚችል አይሆንም ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ አሁንም በ1ኛ ቆሮንቶስ 3 1 _ 9 ላይ ይህንን የተናገረው እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም  ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን ?  እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን ? አንዱ እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ ሁለተኛውም እኔ የአጵሎስ ነኝ ቢል ሰዎች ብቻ መሆናችሁ አይደለምን ? አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው ? ጳውሎስስ ምንድር ነው ? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደ ሰጣቸው ያገለግላሉ እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፥ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል አለን ጌታ እግዚአብሔር ባለመረዳት ሕይወት ወተት ብቻ ከሚጋት የሕጻንነት ባሕርይ አውጥቶ እንደገናም ክርክርና ቅንዓት ከሞላበት ምድራዊ ሥጋዊም ሕይወት በማውጣት ለውጦ ለክርስቶስ ብቻ ልንሆን ጽኑ መብል ወደ ምንበላበት የሕይወት ከፍታ ይውሰደን እግዚአብሔር በምናነበው ቃል ተጠቃሚዎች ያድርገን አሜን


ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፥ ጆሮቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጕመው ጭንቅ ነው
ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ
ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም
ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና
 ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው

ዕብራውያን 5  11 _ 14

ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment