የመናኙ ሰው ዕድል ፈንታው ክርስቶስ ሆነ
|
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቅዱሳን ወገኖቼ ዛሬ ወደ እናንተ ይዤ የመጣሁት ሃሳብ ለየት ያለና ብዙዎቻችሁንም ለወንጌል ሥራ ይበልጥ እንድትነሳሱ እንድትጸልዩና የምሥራቹንም ቃል ወደ ሰዎች እንድታደርሱ እንድትሰብኩም የሚያደርግ መልዕክት ነው የዛሬው በጽሑፌ ላይ የማቀርብላችሁ እንግዳዬ አባ ዘውዱ ኪዳኑ ይባላል አባ ዘውዱን አንተ ብዬ መጥራቴና መጻፌ የቅርብ ጓደኛዬና የአገልግሎት ባልንጀራዬ ስለሆነ ከዚያም መልስ ደግሞ ጌታን ተቀብሎ አዲስ ፍጥረት በመሆኑ የሁላችንም ማለት የጌታ ልጆች ለሆነው ሁሉ ወንድም ስለሆነ ነው ከአባ ዘውዱ ኪዳኑ ጋር የብዙ ዓመታት ትውውቅ የነበረንና በወንጌል እውነት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛ የማዳን ሥራ በማመናችን ምክንያት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተባረርን የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ የክብሩ ወንጌል አገልጋዮች ነን
በሕይወታችን ብዙ ስደት ረሃብና መንገላታት እስራት ስድብና ዛቻ ድብደባ ሳይቀር አልፎአል በመጨረሻም የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ወደ ጥንተ መሠረቷ ወደ ወንጌል እውነት ለመመለስ የመነኮሳት ሕብረት በሚል ስያሜ ወደ ስድስት የምንደርስ መነኮሳት ተሰባስበን በ1996 ዓመተ ምሕረት በኤግዚቢሺን ማዕከል ባካሄድነው የቅዳሜና የእሁድ የሁለት ቀን ኮንፍረስ ብዙ ነፍሳት ድነዋል በሽተኞች ተፈውሰዋል ቅዱሳንም ተባርከውበታል ነገር ግን አገልግሎቱ የእግዚአብሔር የማዳኑ ጉልበት የተገለጠበት በመሆኑ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተነስታ እንዲሁ በስማ በለው የዘመኑ መናፍቃን ስትል አውግዛናለች እኛም ውግዘቱ ተገቢ አለመሆኑን ከእግዚአብሔር ቃል አስረጂ በማቅረብ ምላሽ ሰጥተንበታል ነገር ግን ይህ እንቅስቃሴ ከእኛም ሌላ ብዙዎችን ያፈራ በመሆኑ እስካሁን ድረስ ይበልጥ እየቀጠለና እየተፋፋመ ይገኛል የ Joshua
Breakthrough Renewal Teaching and
Preaching Ministry
ም ከዚያው የቀጠለና ያንኑ አገልግሎት ወደ ፍጻሜ ለማምጣት እየተንቀሳቀሰ ያለ አገልግሎት ነው
አባ ዘውዱ ኪዳኑ በአሁኑ ሰዓት የሚኖረው ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን እስካሁን ድረስ ጌታን በንጽሕናና በቅድስና በታማኝነት በእግዚአብሔር ጸጋ እየታገዘ የሚያገለግል የወንጌል አርበኛና የጸሎትም ሰው ነው አሁን በቅርቡ ደግሞ ከአንዲት የተባረከች እህት ጋራ በቤተክርስቲያን በቅዱሳንና በእግዚአብሔር ፊት የጋብቻ ስነ ሥርዓትን በመፈጸም
በቅዱስ ጋብቻ በትዳር ተጣምሮአል ጌታ ዘመኑን ሕይወቱን አገልግሎቱንና ቤቱንም ይባርክ ስል ልባርከው እወዳለሁ
ከዚህ በመቀጠል እንግዲህ የማካፍላችሁ ከሣቴ ብርሃን ከተባለ መንፈሳዊ መጽሔት ዝግጅት ክፍል ጋር ተገናኝቶ የሰጠውን የሕይወት ምስክርነት ጥቂቱን ወደ እናንተ በማቅረብ ይሆናል ምስክርነቱም ከዚህ እንደሚከተለው ነው
ጋዜጠኛው አባ ዘውዱን ወደ ምስክርነቱ ጎራ ከመቀላቀሉ በፊት ስለ አባ ዘውዱ እንዲህ ሲል ያትታል ይህ ሰው የእድሜውን እኩሌታ ያሳለፈው ከገዳም ገዳም በመንከራተት ነው ለነፍሱ እረፍት አላገኘም እንጂ ጽድቅን ፍለጋ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም በዘመኑ ጽድቅን ፍለጋ ብዙ ተንከራትቻለሁ ከአገር አገር ዞሬያለሁ እግዚአብሔር ይገለጥልኝ ዘንድ በተራቆተ ሰውነቴ ላይ ሰንሰለት ታጥቄ ብዙ ጸልያለሁ ይሄ ሁሉ ደግሞ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ የመሻት በነፍሴም እረፍት ለማግኘት የነበረኝን ብርቱ ጉጉት የሚያሳይ ነው ሥራዬን ሁሉ ሠርቶ ያሣረፈኝ ጌታ በውስጤ ተገልጦ የማድንህ እኔ ነኝ የማጸድቅህ እኔ ነኝ የምቀድስሕ እኔ ነኝ የሚል ድምጹን በውስጤ እስከ ሰማሁባት አንዲት የተባረከች ሌሊት ድረስም ያለ ዕረፍት ተቅበዝባዥ ነበርኩ አንድያ ጽድቅን ፍለጋ እየተንከራተትኩም አዕምሮዬ በኃጢአተኝነት ይከሰስ ነበር በማለት ለመግቢያ ያህል ዘግቦ ጽፎልናል በመቀጠልም አባ ዘውዱ ወደ መድረኩ በመጋበዝ ጥሪያችንን አክብረው በመምጣትዎ በከሣቴ ብርሃን መጽሔት ዝግጅት ክፍል ስም ከልብ አመሰግናለሁ በማለት ወደ ጥያቄው ይገባል
ከሣቴ ብርሃን ፦ አባ ዘውዱ በቅድሚያ የት እንደተወለዱና እንዳደጉ የመንፈሳዊ ሕይወትዎም መነሻ ምን ይመስል እንደነበር ቢያጫውቱን ?
አባ ዘውዱ ፦ ትውልዴ ሰሜን ሸዋ ተጉለት አውራጃ ውስጥ ነው ከደብረ ብርሃን የሦስት ሰዓት መንገድ ያስኬዳል አባቴና እናቴ ገበሬዎች ናቸው እስከ ሰባት ዓመቴ ድረስ እዚያ ቆይቼ ወደ ደብረ ብርሃን መጣሁ ከዚያ በፊት ግን ገጠር ሳለሁ እረኛ ነበርኩ ሆኖም ፊደልን እማር ነበር ቤተሰቦቼ ወደ ቄስ ትምህርት ቤት የሚልኩኝ ፊደል ቆጥሬ የቤተክርስቲያን አገልጋይ እንድሆንላቸው ነበር በአንድ ችግር ምክንያት ቀያችንን ለቀን ደብረ ብርሃን ስንገባም እኔ ያንኑ ትምህርት ቀጥዬ እስከ ዳዊት ደረስኩ አንድ ዕለት ግን መምሕራችን እኔንና አንድን ልጅ ጠርተው ወደፊት መሆን የምንፈልገውን ጠየቁን ሁለት ምርጫም አቀረቡልን ከድቁናና ከአስኳላ ( ዘመናዊ ትምህርት )የቱን ትመርጣላችሁ ? አሉን ልጁ ድቁና ሲመርጥ እኔ አስኳላ ይሻለኛል አልኩ እሳቸው ባመቻቹልኝ ዕድል ተጠቅሜም አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ትምህርት ቤት ገባሁ እዚያ ከአንድ እስከ ስምንት ተምሬ ሚኒስትሪ ስወድቅ ትምህርቴን አቋርጬ ወደ ቤተክህነት ተመለስኩ ሆኖም የቤተ ክህነቱን ትምህርት አጥብቄ እንዳልይዘው ዕለት ዕለት ውስጤን የሚፈታተነኝ ሃሳብ ውስጤ ይመላለስ ጀመር ይኸውም ጽድቅና ኩነኔ እንደሌለ የመቁጠር ሃሳብ ነው
ከሣቴ ብርሃን ፦ ይህ ጽድቅና ኩነኔ እንደሌለ ማሰብ ከየት መጣ ዝም ብሎ በአዕምሮዎ የተፈጠረ ነው ወይስ ሃሳቡ የተቀዳበት ምንጭ አለው ?
አባ ዘውዱ ፦ ምንጭስ አለው እርሱም ከ1966 ዓመተ ምህረት አንስቶ የደርግ አብዮት ባቀጣጠለው የኮምኒዝም ርዕዮተ ዓለም አንዳንድ አስተሳሰቦች ከመማረኬ የመጣ ነው ታላላቆቹን መንፈሳዊ እሴቶች በማናናቅ እና በማዋደቅ የተገለጠው የዚያ ዘመኑ ርዕዮት ጠርጎ ሊወስደኝ ምንም አልቀረውም ነበር እግዚአብሔር ጣልቃ ገብቶ ባያስጥለኝ ኖሮ የዛሬውን ዘውዱ በዚህ ታሪክ አታገኘውም ነበር በድፍረት እግዚአብሔር የለም አላልኩም እንጂ ጽድቅና ኩነኔ የሚባል ነገር የለም ወደ ማለት ግን ደርሻለሁ
ከሣቴ ብርሃን ፦ ጽድቅና ኩነኔ እንደሌሉ እርግጠኛ ከሆኑ ኮናኝና አጽዳቂውን የለም ለማለት ምነው ፈሩ ? ኮምኒስቶቹ እኮ ሁሉንም ነው የካዱት
አባ ዘውዱ ፦ አይ እኔ እግዚአብሔር የለም የሚል ሃሳብ አልነበረኝም ዝም ብሎ አዕምሮዬ ውስጥ የተቀመጠውና የገዛኝ ሃሳብ ጽድቅና ኩነኔ የሚባል ነገር እንደሌለ የመቁጠር ነገር ነው የእኔ ክህደት ከፊል ክህደት ነው ማለት ይቻላል ጌታ መልሱን የሰጠኝም በዚያው አቅጣጫ ነው አንድ እኩለ ቀን ላይ ቁጭ ባልኩበት ተመስጦ ውስጥ ገብቼና በነፍሴ ሽቅብ ተነጥቄ በገባሁበት መንፈሳዊ ዓለም ያየሁት ትዕይንት ነው ሲኦልና ገነት ጽድቅና ኩነኔ መኖራቸውን አምኜ እንድቀበል ግድ ያለኝ ያ ትዕይንት እግዚአብሔር የክህደት ሃሳቤን የመታበት ስለነበር ከፍተኛ የጽድቅ ረሃብና የመዳን ጉጉት ውስጥ የገባሁትም ከዚያች ዕለት አንስቶ ነው ከዓለም ኃጢአት ሸሽቼ በእግዚአብሔር ጉያ ለመግባት መንከራተት የጀመርኩትም ከዚያች ቀን በኋላ ነው በማለት አባ ዘውዱ ኪዳኑ የገዳሙን ሕይወት በሰፊው ማውጋት ይጀምራሉ ይህንን በተመለከተ በቀጣዩ የክፍል ሁለት ዝግጅታችን እናቀርበዋለን እስከዚያው በጌታ ሰላም የምሰናበታችሁ
ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ
No comments:
Post a Comment