Friday, 5 December 2014

በመጽሐፈ አርጋኖን ዙርያ የተዘጋጀ የግጥም መነባንብ መጽሐፈ አርጋኖን



በመጽሐፈ አርጋኖን ዙርያ የተዘጋጀ የግጥም መነባንብ



             መጽሐፈ አርጋኖን



የጸሎት መጽሐፍ ነው ብለው ሰይመውህ
ሊያነቡህ ሊደግሙህ ደግሞም ሊጸልዩህ
የተቀመጥክ ሆነህ ተርታ ተመድበህ
እንዲህ ተደብቀህ ምነው መሰንበትህ
በውስጥህ የተጻፈ የሚደንቅ ቃል አለ
የእግዚአብሔር ቃል ሆኖ ሊሰወር ያልቻለ
አንባብያን መጡ ፈልፍለው ሊያወጡህ
ቃሉን የተረዱ ለትውልድ ሊያሳዩህ
ከእግዚአብሔር ቃል ጋራ ፍጹም የማይጋጭ
በአንተ ውስጥ ተገኘ ተጽፎ በግላጭ
አሁን በአስረጂነት ለእግዚአብሔር ቃል እውነት
ልንጠቅስህ ተነሳን እኛም ካለንበት
አንተን መጥቀሳችን አስረጂ ለቃሉ
በውስጥህ ተቀምጠው ተረት ተረት ሚሉ
ስላሉ ነው እንጂ አይደለም ለሌላ
የእግዚአብሔር ቃልማ ለሁሉም ነው ጥላ
አንተም ስትናገር እንዲህ ብለህ አልከን
ኤልያስን ከኤልሳዕ ጠቅሰህ ልታሳየን
ኤልያስ ቢያርግና ወደ ሰማይ ቢወጣም
ለራሱ ነው እንጂ ለሌሎች አይደለም
ከፍ ብሎ ወጥቶ በላይ ባረገልን
ከሞት ወደ ሕይወት ይኸው ተሻገርን
ብለህ ስትናገር ስለዚሁ ጌታ
ልባችን በቃሉ ፈጽሞ ተረታ
እኛም ምንፈልገው ይህንን ነበረ
የልብ ወለድ ድርሰት ተረት ሆኖ ያልቀረ
ተጽፎ ሊነበብ በቃሉ የሰፈረ
ይህንኑ እውነት አጽንቶ ሊያሳየን
መጽሐፈ አርጋኖን ይኸው ብቅ አለልን
መጽሐፈ አርጋኖን ጉደኛ መጽሐፍ ነው
በዚህ አላበቃም ኤልሳዕን ተረከው
ኤልሳዕ ተአምር ቢያደርግ ለምጽን ቢፈውስም
የነፍስን ለምጽ ግን  መታደግ አልቻለም
ከኃጢአት በሽታ እኛን ሊታደገን
የነፍሳችን ቤዛ ኢየሱስ መጣልን
ኃጢአት ባመጣበት የደዌ መጋኛ
ተኝቶ የቀረ የአልጋ ቁራኛ
ተነሣ ተባለ አልጋህን ተሸከም
የኃጢአትን ሥርየት ሰጠው መድኃኔዓለም
በአዲስ ማሰሮ ጨውን የጨመረ
የኢያሪኮን ውሃ ፈውሶ ያሳመረ
ነገር ግን አልቻለም የሰዎችን ሕይወት
ፍጹም ሊያጣፍጠው ጨውን ጨምሮበት
በድንገት በመሐል ሕይወት የሚያጣፍጥ
መድኃኒት ተገኘ ለሰዎች የሚሰጥ
ብሎ ተናገረ የአርጋኖን መጽሐፍ
ሳይደብቅ ሳይሰውር ለሰው ሊያትረፈርፍ
የጌታን ትንሣኤ የገድሉን ምዕራፍ
እንግዲህ ወዳጆች እንንቃ በቶሎ
ዘመን ሳይቆጠር አንድ ሁለት ብሎ
ጌታን መቀበሉ ለእኛ ይበጀናል
አዳኝ ነው ኢየሱስ ፍጹም ያዋጣናል
ጌታን መቀበሉ ለእኛ ይበጀናል
አዳኙ ኢየሱስ ፍጹም ያዋጣናል




ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment