Friday, 5 December 2014

የቤተክርስቲያን ተልዕኮ ምዕራፍ ሁለት ክፍል አንድ



የቤተክርስቲያን ተልዕኮ


ምዕራፍ ሁለት



ክፍል አንድ




ከሐሰተኛ ነቢያት ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ራስንና መንጋውን መጠበቅ






የተወደዳችሁ ወገኖች በምዕራፍ አንድ ትምህርታችን ላይ ቤተክርስቲያን በሚል አርእስት ለተከታታይ እስከ ክፍል 26 ድረስ በመሄድ የቤተክርስቲያንን ማንነትና ምንነት ቤተክርስቲያንም እንደቃሉ ምን መሆንና ምን ማድረግ እንዳለባት በሰፊው በዝርዝር ተማምረናል ዛሬ ደግሞ በምዕራፍ ሁለት ትምህርታችን ላይ የቤተክርስቲያን ተልዕኮ በሚል ዋና አርዕስት ከሐሰተኛ ነቢያት ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ራስንና መንጋውን መጠበቅ  እንደሚኖርባት ለማስገንዘብ ከእግዚአብሔር ቃል ማስረጃ በመስጠት ተከታታይ የሆኑ ትምህርቶችን ጌታ ባበዛልን ጸጋ እንደሚከተለው እንማማራለን ጌታም በዚህ ትምህርት እንደሚባርከን አምናለሁ ጊዜያችሁን ሰጥታችሁ ይህንን ትምህርት የምትከታተሉ ሁሉ ጌታ ይባርካችሁ ለማለት እወዳለሁ  ወደ ትምህርታችን ስንመለስ ደግሞ መጽሐፍቅዱሳችን ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ ይለናል ፊልጵስዩስ 1 27 ለክርስቶስ ወንጌል የሚያኖር ደግሞ የክርስቶስን  ትምህርት የተማረ በመሆኑ ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና በማለት ሐዋርያው ይህንን ጽፎልናል 2 ዮሐንስ መልዕክት 1 9 _ 11 ታድያ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ የሚያኖር የክርስቶስ ትምህርት እንዳለ ሆኖ  ከመንግሥቱ ወንጌል የሚለይ የሐሰተኛ ነቢያትና የሐሰተኛ አስተማሪዎች ትምህርት ደግሞ አለ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለተለየበት ወንጌል ሲናገር እንዲህ አለ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ጳውሎስ በነቢያቱ አፍ በቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ለሰጠው ለእግዚአብሔር ወንጌል ተለየ በማለት ተናገረ ሮሜ 1 1  ስለዚህ ወንጌል የእግዚአብሔር ነው ሐሰተኛ አስተማሪዎችና ሐሰተኛ ነቢያት ጣልቃ ገብተው  ሲናገሩት ሲያስተምሩትና ሲሰብኩት ግን ወንጌል የሰው ይሆናል በመሆኑም ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየው ጳውሎስ ለእግዚአብሔር ወንጌል መለየት ብቻ አይደለም የእግዚአብሔርና የሰውን እንዲሁም የአጋንንትን ወንጌል ለይቶ ያወቀ በመሆኑ የገላትያ ክርስቲያኖችን ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም ካለ በኋላ የቀድሞ ሕይወቱን በማንሳት በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር በማለት በክርስቶስ ያገኘውን ሕይወት የአገልግሎት ጥሪና መረዳቱንም ጭምር ይናገራል ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥ ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥ ነገር ግን ወደ ዓረብ አገር ሄድሁ እንደ ገናም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ ከዚህ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቼ ከእርሱ ጋር አሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም ከዚያ ወዲያ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር መጣሁ በክርስቶስም ያሉት የይሁዳ ማኅበሮች ፊቴን አያውቁም ነበር ነገር ግን ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር አለን ገላትያ 1 11 _ 24 እንዲህ ለእግዚአብሔር ወንጌል የተለየውና በጸጋው ተጠርቶ ልጁ ኢየሱስ የተገለጠለት በዚህ ነገርም ከሥጋና ከደም ጋር ያልተማከረው ጳውሎስ ነው እንግዲህ እነዚህኑ የገላትያ ክርስቲያኖችን በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ ያላቸው ገላትያ 1 6 ይህን ለመግቢያ ያክል ካየን ይህ ሃሳብ ለትምህርታችን እንደ መንደርደርያ ሃሳብ ሆኖ ወደ ትምህርታችን መጀመርያ የሚወስደን ይሆናል ትምህርታችንን የምንጀምረው ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ ያለውን እውነታ እያየን የምንሄድ በመሆኑ  በዘዳግም 13 1 _ 5  የተጻፈውን ሃሳብ መነሻ በማድረግ ነው ቃሉ እንዲህ ይላል በመካከልህም ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቢነሣ፥ ምልክትም ተአምራትም ቢሰጥህ እንደ ነገረህም ምልክቱ ተአምራቱም ቢፈጸም፥ እርሱም፦ ሄደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ቢልህ አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ አምላካችሁ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ ነውና የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ያን ሕልም አላሚ አትስማ አምላካችሁን አግዚአብሔርን ተከተሉ፥ እርሱንም ፍሩ፥ ትእዛዙንም ጠብቁ፥ ቃሉንም ስሙ፥ እርሱንም አምልኩ፥ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ አምላክህ እግዚአብሔር ትሄድባት ዘንድ ካዘዘህ መንገድ ሊያወጣህ፥ ከግብፅ ምድር ካወጣችሁ ከባርነትም ቤት ካዳናችሁ ከአምላካችሁ ከእግዚአብሔር ሊያስታችሁ ተናግሮአልና ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ይገደል እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ አርቅ ይለናል የአንድ ትንቢት እውነተኛነት የሚረጋገጠው ትንቢቱ እንደተነገረው ሲፈጸም ነው ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል አጠንክሮ በዘዳግም 18 20 _ 23 ላይ ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝሁትን በስሜ በድፍረት የሚናገር ወይም በሌላ አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ፥ እርሱ ይገደል በልብህም እግዚአብሔር ያልተናገውን ቃል እናውቅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል ? ብትል ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም፥ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው ነቢዩ በድፍረቱ ተናግሮታል እርሱን አትፍራው የሚለን ትንቢትን በተመለከተ መጽሐፍቅዱሳችን እራሱ የትንቢት መጽሐፍ መሆኑን መጽሐፉ ራሱ  በተለያዩ ክፍሎች ላይ ይናገራል በራዕይ 22 18 እና 19 ላይ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል ለሚሰማ ሁሉ እኔ እመሰክራለሁ፤ ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ዕድሉን ያጎድልበታል ይለናል በራዕይ 22 7 10 ላይም እነሆም፥ በቶሎ እመጣለሁ የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው አለኝ ለእኔም ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው በማለት ይናገራል በ2ኛ ጴጥሮስ 1 19 _ 21 ላይ ደግሞ ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፥ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ በማለትም ይናገራል ይሁን እንጂ ታድያ በእኛና ከእኛም በኋላ ባሉት ዘመናት ሁሉ በሰው በኩል የሚነገረውን ትንቢት እንደ መጽሐፍቅዱስ ቃል ሥልጣን ሰጥተንና ከዚሁ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በእኩልነት አስተያይተን የምናየው የምንቀበለውም ትንቢት ለእኛ የለንም ሊኖረንም አይችልም መጽሐፍቅዱስ የትንቢት መጽሐፍ ቢሆንም የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ አንሽረውም ልንለውጠው ልናሻሽለውና ልናስተካክለው በፍጹም አንችልም ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍትም ሆነ ሰዎች በጸጋ ከሚያመጡት ትንቢታዊ ቃል ተለይቶና መለኮታዊ ሥልጣን አግኝቶ ብቸኛ የእግዚአብሔር ቅዱስ መጽሐፍና  ቅዱስ ቃል የተባለው ይህንንም እንድናውቅ እነዚህ ክፍሎች ለእኛ ተጻፉልን በዘዳግም 4 2 ላይ እኔ ያዘዝኋችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትጠብቃላችሁ እንጂ ባዘዝኋችሁ ቃል ላይ አትጨምሩም፥ ከእርሱም አታጎድሉም  አለን በራዕይ መጽሐፍ ምዕራፍ 22 18 ላይ ደግሞ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል ለሚሰማ ሁሉ እኔ እመሰክራለሁ፤ ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ዕድሉን ያጎድልበታል በማለት ተናገረ  ጌታ ደግሞ መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን ትሳደባለህ ትሉታላችሁን ? በማለት የመጽሐፉ ቃል ሊሻር እንደማይችል አስረዳን ዮሐንስ ወንጌል 10 35 አያይዞም ሐዋርያው ጳውሎስ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል የተሻረ አይደለም እነዚህ ከእስራኤል የሚወለዱ ሁሉ እስራኤል አይደሉምና፤ የአብርሃምም ዘር ስለሆኑ ሁላቸው ልጆች አይደሉም ነገር ግን በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል ተባለ በማለት ተናገረን ሮሜ 9 6 እና 7 በሉቃስ ወንጌል 16 17 ላይ ነገር ግን ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ሊያልፍ ይቀላል በማለት በወንጌሉ ቃል የተጻፈልን ሲሆን  በማቴዎስ ወንጌል 5 18 ላይም በተመሣሣይ ሃሳብ እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ በማለት ማቴዎስ በወንጌሉ  በድጋሜ ከሉቃስ  ወንጌል ጋር ተያያዥነት ያለው ሃሳብ መሆኑን አረጋገጠልን አጸናልን እንደገናም ይህ የመጽሐፍ ቃል የትንቢት መጽሐፍ ቢሆንም ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና  ለገዛ ራሳችን አንተረጉመውም በመሆኑም ቅዱሳን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ይህንን እውነታ አውቀው መጽሐፍቅዱስ ብቸኛ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ተገንዝበው ከሌሎች መጻሕፍት ጋር ሳይቀላቅሉና ሳይበርዙ በእኩልነትም ሳያስተያዩ እንደገናም በየዘመኑ የተነሱትንና የሚነሱትን እየተነሱም ያሉትን  የነቢያት ቃል እንደ መጽሐፍቅዱስ ቃል በመቁጠር እና በመቀበል እግዚአብሔር ወደማይፈልገው ጉዞና አካሄድ እንዳይሄዱ ለማስገንዘብ የተዘጋጀ ትምህርት ነው ከዚህም የተነሳ በ1ኛ ቆሮንቶስ 14 39 ላይ ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ትንቢት ለመናገር በብርቱ ፈልጉ፥ በልሳኖች ከመናገርም አትከልክሉ ያለን ቢሆንም ሁሉን ፈትኖ መያዝ እንደሚገባን ሊጠቁመን ወዶም ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ አለን 1 ተሰሎንቄ 5 20 እና 21 በመሆኑም ትንቢትን አትናቁ ስለተባለ የምንንቀው ትንቢት ባይኖርም መልካሙን ለመያዝ ግን በሰዎች የተነገረውን ትንቢት ሳይቀር በእግዚአብሔር ቃል እንፈትናለን እንመዝናለን በ1ኛ ቆሮንቶስ 14 29 ላይም ለዚህ ነው ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ይለዩአቸው በዚያ ለሚቀመጥ ለሌላ ግን አንድ ነገር ቢገለጥለት ፊተኛው ዝም ይበል የሚለን በዚህ ቃል መሠረት እንግዲህ የኔ ትንቢትም ሆነ የእኔ አገልግሎት የተዋጣለት ነውና በማንም አይመረመርም ማንም ደግሞ ሊለየው አይገባም የሚል ነቢይ እና አገልጋይ ካለ እርሱን ነቢይም ሆነ አገልጋይ ብለን ልንጠራው አንችልም እንደውም ከላይ ከመግቢያዬ ቀጥሎ በብሉይ ኪዳን ክፍል በጠቀስኩት ቃል መሠረት ነገር ግን ይናገር ዘንድ ያላዘዝሁትን በስሜ በድፍረት የሚናገር ወይም በሌላ አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ፥ እርሱ ይገደል በልብህም እግዚአብሔር ያልተናገረውን ቃል እናውቅ ዘንድ እንዴት ይቻለናል ? ብትል ነቢዩ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም፥ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው ነቢዩ በድፍረቱ ተናግሮታል እርሱን አትፍራው ነው የሚለን ስለዚህ ነቢዩ የተናገረው ቃል እንደ እግዚአብሔር ቃል ስንመረምረው ሐሰት መሆኑን በምናውቅበት ጊዜ እንደብሉይ ኪዳኑ ሕግ ፈጥነን እጆቻችንን በመጫን ልንገድለው ባንነሳም ነገር ግን ነቢይ ነው ብለን ሳንፈራው በእግዚአብሔር ቃል እንዲስተካከል እናርመዋለን እንመክረዋለን እናስተካክለዋለን እናቀናዋለን ሲያስፈልግም እንገስጸዋለን ከዛም ካልተመለሰ ከአገልግሎቱ ሳይቀር እንዲታገድና ቁጭ ብሎም እንዲማር ጥቆማ እናደርጋለን ይህ እንግዲህ ከእኛ ከአገልጋዮች የሚጠበቅ ነገር ነው ከዚያም ባሻገር  የቤተክርስቲያን ሥልጣንም ስለሆነ የቤተክርስቲያን መሪዎች ሃላፊነታቸውንና የተጣለባቸውንም አደራ ተመልክተው ዛሬም በዚህ ጉዳይ ላይ ጥብቅ ክትትል ሊያደርጉ እየሳቱ እያሳቱና እየተሳሳቱ ያሉትን ነቢያት እንደ እግዚአብሔር ቃል ሊመክሩ ሊያቀኑ እንደ አስፈላጊነቱም እርምጃ ሊወስዱ ይገባል በማለት ወንድማዊ አስተያየቴን በታላቅ ትሕትና ላበረክት እወዳለሁ ይህንን እንድል ያነሳሳኝም  ከአንድ (የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህር)ግንቦት 25 2006 ዓ/ም ከቀረበ ሪፖርት በመነሳት በቅርቡ በሀገራችን በኤግዚቢሽን ማዕከል ዜግነቱ ማላዊ በሆነ መጠሪያው ደግሞ ነቢይሼፐርድ ቡሽሪበተባለ ግለሰብ ‹‹ጸሎቱን የምትፈልጉ በስክሪኑ ላይ በምትመለከቱት አድራሻ ገንዘብ ላኩለብልጽግና የሚሆን ዘይት የምትፈልጉ ብልቃጦቹ በአድራሻዎቻችሁ እንዲደርሳችሁ በቅድሚያ ገንዘብ በመላክ መግዛት ትችላላችሁ›› ‹‹መሻታችሁ ትዳር ጤንነት የአሜሪካ ቪዛ  ወዘተ ከሆነም የተጸለየበት ውሃ አለ ከፍላችሁ በአድራሻችሁ ይደርሳችኋል ›› እያለ እና እያስባለ ሲያስተዋውቅ ፣  ሲቸበችብ እንደገናም  ነቢዩ በዚህ ሳያበቃ አጃቢዎቹ  በነብዩ ስም የተዘጋጁትንና የነቢዩ የፎቶ ምልክት ያሉበትን ውሃ ዘይት ሳሙና ስቲከር እራፊ ጨርቅ የእጅ ሪቫን ደርድረው መሸጥ መጀመራቸውን ውሃው (ነብዩ የጸለየበት የተባለ) 500 ብር የተጸለየበት ዘይት ብልቃጥ 200 ብር እራፊ ጨርቁን 200 ብር የእጅ ሪቫን 100 ብር ስቲከሩ 10 ብር ወዘተ ኪሳራ የሌለበት ታክስ የማይከፈልበት በዕዳ የማይጨነቁበት መንፈሳዊ መሳይ ንግድ ማካሄዱን ስንሰማ ለመሆኑ በሀገሩ ላይ ሃይ የሚሉ መንፈሳውያን ሰዎች ወይንም መሪዎች የሉም ወይ ? ስንል ልባችን በሃዘን በልቅሶና በቁጭት ሲቃ ውስጥ ገብቶ ሲማልል ሲዋትትም ከርሟል ነገር ግን ወዲያው ሳይቆይ የተባረከው ወንድማችንና አገልጋያችን ወንድም ማሙሻ ፋንታ ጌታ በሰጠው አስደናቂ መልዕክት በኢንተርኔት መስኮት ብቅ ብሎ ፎከሳችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ይሁን ፎከሳችን ሰዎች አይሁኑ እኛ የማንጠቅም ባርያዎች ነን የሚሉትንና ሌሎችንም የተቀላቀለ የአፍሪካ ክርስትና ወዴት እያመራ እንዳለ በመንፈስ ኃይል ተሞልቶ ከእግዚአብሔር ቃል እያጣቀሰ ያሻገረው መልዕክት ወደ ክርስትናው መሠረት የሚመልስ  ከልባችን የማይጠፋና ልብንም የሚነካ በመሆኑ ከወደቀብን ታላቅ ሃዘን በጥቂቱም ቢሆን ገርገብ እንድንል አድርጎናል ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ በዚሁ ሳያበቃ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ መሁኑን እየጠቆምኩ ወንድማችንንም ጌታ ይባርክህ ልለው እወዳለሁ ወገኖች እንግዲህ ትምህርቱ ከአሁን ጀምሮ በተከታታይ የሚቀጥልና የሚቀርብ በመሆኑ እንድትከታተሉት በአክብሮትና በፍቅር እየጠየኩ የክፍል አንድ ትምህርቴን በዚሁ አጠናቅቃለሁ

ጌታ እግዚአብሔር ሁላችሁንም ይባርክ

ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ

No comments:

Post a Comment