Thursday, 4 December 2014

ቤተክርስቲያን ክፍል አስራ አምስት



ቤተክርስቲያን


ክፍል አስራ አምስት


ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና ከዝሙት እንድትርቁ፥
እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፥
ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ፤
አስቀድመን ደግሞ እንዳልናችሁና እንደ መሰከርንላችሁ፥ ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ
የሚበቀል ነውና ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ ወንድሙንም አያታልል ለርኵሰት
ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና

1ኛ ተሰሎንቄ 4 3 _ 7


ባለፈው በክፍል አስራ አራት ትምህርታችን ላይ ብኩርናን በተመለከተ ክርስቶስን ራስ ያደረገች ቤተክርስቲያን የበኩራት ማኅበር መባሏ እኛም ኢየሱስን እንደ አዳኛችንና ጌታችን አድርገን በመቀበላችን ወደ በኩራት ማኅበር ደርሳችኋል መባላችን ወደ በኩራት ማኅበር የደረሰ ሰው ክርስቶስን ወደ መምሰል ማደግ እንደሚጠበቅበት የሐዲስ ኪዳን የበኩራት ማኅበርን ለእግዚአብሔር በኩር ተብለው ከተጠሩ ከእስራኤል ጋር አገናዝበን በኩሬ ያላቸው እስራኤል  ሕይወት ያላቸውን ቃላት ሙሴ ከእግዚአብሔር ተቀብሎ ነበርና ለዚህ ቃል ባለመታዘዛቸው ምክንያት የሆኑትን ማለት ለነውር እንደተለዩ እንደረከሱ በልባቸው ወደ ግብጽ እንደተመለሱ ሙሴንም ይህ ሙሴ ምን እንደሆነ አናውቅም ብለው አገልጋያቸውን እንደገፉ ጥጃ እንዳደረጉ እግዚአብሔርም ዘወር እንዳለና አሳልፎ እንደሰጣቸው በዚህ ውስጥ ለእኛ የሚቀርልን ዛሬም ለእግዚአብሔር ቃል ባልታዘዝን ቁጥር ለነውር እንደምንለይና እንደምንረክስ በዚህም ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ከእስራኤል ዘወር እንዳለ ዛሬም ከእኛ ዘወር እንደሚል ከገፋንበትና ካልተመለስን ደግሞ አሳልፎ ሳይቀር እንደሚሰጠን ቤተክርስቲያንም የተጠራችው ለርኩሰት እና ለነውር ሳይሆን በውሃ መታጠብ ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ስለሰጠ እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነች ቤተክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ ብለን በሰፊው ተማምረናል 

         ዛሬ በክፍል አስራ አምስት ትምህርታችን ላይ የምንማማረው ሃሳብ ደግሞ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና …………………. ስለዚህ ለርኩሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናል ስለሚለን ቃሉ የእግዚአብሔር ሕዝብ የእግዚአብሔር ፈቃድ ወዳለበት የቅድስና ሕይወት ውስጥ ገብቶ በተጠራበት የእግዚአብሔር ቅድስና ልክ መመላለስ እንዳለበት ቃሉ ይጠቁመናልና ስለዚህ በዚህ የቅድስና ልክ ልንመላለስ ራሳችንን ለዚህ ጌታ መስጠት ይጠበቅብናል ቅድስና እኛ የምናመጣው ሕይወት ሳይሆን እግዚአብሔር የሰጠን ነው በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 1 2 ላይ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎልናል በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን ይለናል ስለሆነም ይህ የእኛ አምላክ እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናል የጠራን ደግሞ ቅዱሳን ለመሆን ነው ቅድስና የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ እንደመሆኑ መጠን የእኛም ሊሆን ይገባል መጽሐፍቅዱሳችን አሁንም በ1ኛ ጴጥሮስ 1 15 እና 16 ላይ ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ ይለናልና ቅዱሳን ለመሆን በኑሮአችንም ተቀድሰን ለመገኘት ሁልጊዜ መቀደስን መፈለግ አለብን ስለዚህም ነው የዕብራውያን ጸሐፊ ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና የሚለን ዕብራውያን 12 14 በመሆኑም የመቀደስ ፍለጋችንና መሻታችን የአንድ ጊዜ የአንድ ሰሞን የአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜና የዘላለም ነው ሕይወታችን በምድር እስካለ ድረስ ማለት እኛ ወደ ጌታ እስክንሄድ ወይንም ጌታ ወደ እኛ እስኪመጣ ድረስ ቅድስናን መናፈቅ ደግሞም መፈለግ አለብን በሕይወታችንም ያለው ቅድስና የአንድ ጊዜ ቅድስና ብቻ ሳይሆን አዳጊ ቅድስና ነው በእርግጥ ለደህንነታችን አንድ ጊዜ ተቀድሰናል ታጥበናል ጸድቀናል ዕብራውያን 10 10 14 1 ቆሮንቶስ 6 9 _ 11 ይህ ማለት ግን ከዚያ በኋላ ቅድስና አያስፈልገንም ማለት አይደለም የማያስፈልገን ቢሆን ኖሮ ትቀደሱ ዘንድ ፈልጉ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና ተብሎ አይጻፍልንም ነበር እንደውም የተባልነው በ1ኛ ተሰሎንቄ 5 23 እና 24 ላይ የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል የሚል ነው  መቀደሳችን የሁለንተና ወይንም ሁለንተናዊ ነው መንፈስ ተቀድሶ ነፍስ አይቀርም ነፍስ ተቀድሶ ሥጋ አይቀርም አንዱ ከሌላው ሳይነጠል ሳይለይ ሁሉም ጌታችን እስኪመጣ ድረስ ያለነቀፋ ይሆን ዘንድ ሊቀደስ ያስፈልገዋል ስለዚህ ቅድስናን የዕለት ተዕለት ተግባራችን ልናደርግና ልናዳብር ያስፈልጋል በዚህም ምክንያት ነው እንግዲህ በ2ኛ ቆሮንቶስ 7 1 ላይ እንግዲህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ የዚህ ተስፋ ቃል ካለን፥ በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ ተብሎ የተጻፈልን ቅድስና የሚለውን አርዕስት ይዘን በሰፊው ወደ ውስጥ ከገባን ራሱን የቻለ ስፊ ሃሳብ ያለው ትምህርት ስለሆነ ሁሉንም ልናቀርብ አንችልምና ጊዜያቶች ይወስዱብናል አሁን ግን ለተነሳንበት ትምህርት እንደ መግቢያና መንደርደርያ ስለሆነ ትክክለኛ መልክና ግልጽ የሆነን የትምህርት ይዘት ይሰጠዋል ብዬ አምናለሁ ወገኖቼ የቅድስናን ምንነትና ማንነት በጥቂቱ ካየን ለቅድስና ቅዱስ ለመሆንም የተጠራና ቅዱስ የሆነ ሕዝብ ለነውር ሲለይ ተራ በሆነም አልባሌ የራስ ፍላጎት ሲነወር ማየት እጅግ ያበሳጫል ደግሞም ያሳዝናል ከቅዱስ ሕዝብ የሚጠበቀው የእግዚአብሔር ምስጋናና ዕልልታ እንጂ መዝፈንና ማመንዘር መስከር ከእግዚአብሔር ሕዝብ የሚጠበቅ ነገር አይደለም እንኳን ልንጠብቀው ለአንዲት ሴኮንድ እንኳ ቢሆን በቅዱስ ሕዝብ መካከል ሊታይ አያስፈልግም አይገባምም  በዘኁልቁ 23 21 _ 24 ድረስ ባላቅ ግራ እስኪጋባ የሚይዘውን የሚጨብጠውን እስኪያጣ ድረስ ረጋሚው በለዓም አንደበቱ በእግዚአብሔር ተለውጦ እንዲህ ሲል ባርኮአል በያዕቆብ ላይ ክፋትን አልተመለከተም በእስራኤልም ጠማምነትን አላየም፤ አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነው የንጉሥም እልልታ በመካከላቸው አለ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶአቸዋል ጕልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ነው በያዕቆብ ላይ አስማት የለም፥ በእስራኤልም ላይ ምዋርት የለም፤ በጊዜው ስለ ያዕቆብና ስለ እስራኤል እግዚአብሔር ምን አደረገ፦ ይባላል እነሆ፥ ሕዝቡ እንደ እንስት አንበሳ ይቆማል፥ እንደ አንበሳም ይነሣል፤ ያደነውን እስኪበላ፥ የገደለውንም ደሙን እስኪጠጣ አይተኛም……………………………………….. ይለናል እስራኤል በተቀደሰበትና ለእግዚአብሔርም በተለየበት ጊዜ እንዲህ ነበር የንጉሥ ዕልልታ በመካከሉ ነው እግዚአብሔር ከግብጽ ስላወጣው ጉልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው  ነው እና የመሳሰሉት ነገሮች አሉበት  በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ስለተፈጠርን ዘወትር ለእግዚአብሔር የምሥጋና መሥዋዕት ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በእርሱ እናቀርብለታለን ዕብራውያን 13 15 ምስጋና የቅድስናችን ምልክት ነው ምስጋና ጉልበታችን ነው ኃይላችን እና ብርታታችን ነው መስከር መዝፈንና ማመንዘር ግን የሥጋ ሥራ ስለሆነ በቀን ሳይሆን በሌሊት የሚደረግ ነው በ1ኛ ተሰሎንቄ 5 4 _ 11 ላይ እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም፤ እንግዲያስ እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉና፥ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉና፤ እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን፥ የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እየለበስን በመጠን እንኑር እግዚአብሔር ለቍጣ አልመረጠንምና፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ ይለናል ስለዚህ ክርስቲያን ከሌሊት ስላልሆነ የሌሊት ሥራ አይሰራም እነዚህ የሌሊት ሥራዎች የሥጋ ሥራዎች ስለሆኑ ገላትያ 5 19 _  22 ክርስቶስን ራስ አድርጋ የበኩራት ማኅበር የሆነችዋን ቤተክርስቲያን ራሷን ካልጠበቀችና የመንፈስን ፍሬ አፍርታ  በመንፈስም ካልተመላለሰች ገላትያ 5 22 _ 26 ገላትያ 5 16 እንደገናም ከቀን ስለሆነች የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እየለበሰች በመጠን ካልኖረች ያነውሩአታል አልፈውም የፊት መጨማደድን ያስከትሉባታል ለክርስቶስ ያላትን ፍጻሜም ያበላሹባታል

     ለነውር በተለየው የእግዚአብሔር በኩር በሆነው ቅዱስ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሙሴ ተበሳጨ ቁጣው ተቃጠለበት ጽላቶቹንም ከእጁ ጥሎ ከተራራው በታች ሰባበራቸው እያለ ይነግረናል ይህ ብቻ አይደለም በሰፈሩ ደጅ ቆሞ የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ወደ እኔ ይምጣ፦ አለ የሌዊም ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ እግዚአብሔር ሊያደርግ የወደደውንም ለሌዊ ልጆች በመንገር የሌዊን ልጆች ለእግዚአብሔር ሥራ ሲያዘጋጃቸው እንመለከታለን ዘጸአት 32 በሙሉ እናንብብ ለነውር በተለየ ሕዝብ የሚበሳጩ ተበሳጭተውም ሳይቀሩ አቋም የሚይዙ ማለት እንደ ሙሴ ብቻ ሳይሆን እንደ ጳውሎስም ምን ትወዳላችሁ ? በበትር ወይስ በፍቅርና በየውሃት መንፈስ ልምጣባችሁን ?  የሚሉ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥነት የሚናገሩ እንደገናም የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን የሚሉ አሉ  1 ቆሮንቶስ 4 21 የሐዋርያት ሥራ 13 46 በዚያው ልክ ደግሞ ሊነወር ለተዘጋጀ ሕዝብ ግድ የማይሰጣቸው የሚያነውሩ ብቻ ሳይሆኑ አብረው ከሕዝቡ ጋር ሊነወሩ ጥጃ የሚሠሩ በሐዲሱ ኪዳን ደግሞ ከአሕዛብ ጋር ሲበሉ ከርመው አይሁዳዊ ነን ለማለት አይሁድን አይተው የሚያፈገፍጉ ሌሎችንም በግብዝነታቸው ሳይቀር እንዲሳቡ በማድረግ ምክንያት የሚሆኑ
አሉ ዘጸአት 32 1 _ 6 21 _ 25 ገላትያ 2 11 _ 21 ይህ ሁሉ እንግዲህ በትክክለኛው በእግዚአብሔር ቃል ካልተፈተሸና ካልተመረመረ ማነወርም መነወርም ነው ለእርኩሰት ሳይሆን እግዚአብሔር  በቅድስና ጠርቶናል ቅድስና የሕይወት መጀመርያችን ሳይሆን የሕይወት መጨረሻችን ነው የምናነበውን ቃል እግዚአብሔር ይባርክልን


ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment