ቤተክርስቲያን
ክፍል ሰባት
የሐዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን በመሆንዋ ለእግዚአብሔር የተለየ መታወቅያውና ማዕረጉ ልትሆን የተጠራች ለዚያም የደረሰች ናት በመሆኑም በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 20 ፥ 28 ላይ
በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ አለን ለምን ስንል አሁንም ሐዋርያው ገና ብዙዎች የዳኑ የሚድኑና ሊድኑም የተዘጋጁ ቅዱሳን በመኖራቸው ለእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ማሰናከያ አትሁኑ አለ ለዚህም ነው በ1ኛ ቆሮንቶስ 10 ፥ 32 እና 33 ላይ እኔ ደግሞ ብዙዎቹ ይድኑ ዘንድ ለጥቅማቸው እንጂ የራሴን ጥቅም ሳልፈልግ በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ እንደማሰኝ፥ ለአይሁድም ለግሪክም ሰዎች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም ማሰናከያ አትሁኑ በማለት የተናገረው የሐዋርያው ፍለጋና ናፍቆት በቤቱ ብዙዎች ይድኑ ዘንድ ነው ከዚህም የተነሳ ለብዙዎች ጥቅም የሚሰራና የራሱንም ጥቅም ሳይፈልግ በሁሉ ነገር ሰውን ሁሉ ደስ የሚያሰኝ በመሆኑ በጊዜው ለነበሩ ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች ለእግዚአብሔር ቤተክርስቲያንም ማሰናከያ አትሁኑ አለ ለእግዚአብሔር የተለየ መታወቅያውና ማዕረጉ ልትሆን በተጠራች
ቤተክርስቲያን ሰው የራሱን ጥቅም ሲፈልግ ለብዙዎች ደስታ ሳይሆን ለራሱ መሥራት ሲጀምር በእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ውስጥ መሰናክል ይሆናል የነፍሳት መዳን ይጠፋል ማለት ነፍሳት አይድኑም በዚያው በደጅ ሳሉ ተሰናክለው ይቀራሉ ለዚህ ነው ሐዋርያው አሁንም በራሱ ሕይወት ውስጥ የነበረውን አደራረግና አሠራር የመንፈስ ልጁ በሆነው በጢሞቴዎስ ሕይወት ውስጥ ስላየው ነገር ግን ኑሮአችሁን ሳውቅ እኔ ደግሞ ደስ እንዲለኝ ፈጥኜ ጢሞቴዎስን ልልክላችሁ በጌታ በኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ
እንደ እርሱ ያለ፥ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፥ ማንም የለኝምና ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም ነገር ግን ልጅ ለአባቱ እንደ ሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል እንደ አገለገለ መፈተኑን ታውቃላችሁ እንግዲህ እንዴት እንደምሆን ባየሁ ጊዜ፥ እርሱን ቶሎ እንድልክ ተስፋ አደርጋለሁ ራሴ ደግሞ ግን ፈጥኜ እንድመጣ በጌታ ታምኜአለሁ ያለው ፊልጵስዩስ 2 ፥ 19 _ 24 ጢሞቴዎስ የጳውሎስ ዓይነት ሕይወት የነበረው ከራሱ ይልቅ የብዙዎች ሕይወት ግድ የሚለው የራሱንም ጥቅም ሳይፈልግ ለብዙዎች ጥቅም የሚሠራ ነው ሊያውም በቅንነትና በመልካምነት ታድያ ዛሬ የሚያስፈልጉን እንዲህ ዓይነት ሰዎች ናቸው በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ተገኝተው የእግዚአብሔር ሥራ በሚሠራበት ጊዜ በእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ማሰናከያ ከሚሆን ይልቅ የነፍሳት መዳን በብዙ ይሆናል እግዚአብሔር በቤቱ ሕዝብን ያበዛል ኢየሱስም ለዚህ ነበር ደቀመዛሙርቱ ብላ ብለው በለመኑት ጊዜ እርሱ ግን፦ እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ አላቸው ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ የሚበላው አንዳች ሰው አምጥቶለት ይሆንን ? ተባባሉ
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው እናንተ ገና አራት ወር ቀርቶአል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን ? እነሆ እላችኋለሁ፥ ዓይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል፥ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘላለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኖአልና ሲል የተናገረው ዮሐንስ ወንጌል 4 ፥ 31 _ 36 ኢየሱስ በዚያ በጠራራ ጸሐይ ወደ ሰማርያ ሊመጣና በዚያም ሊያልፍ ግድ የተሰኘበት ጉዳይ በጥቅሉ ከአገልግሎቱ የድካም መልስ የነጣ አዝመራን ለማግኘት ነው እንጂ የምሳ እና የመብል ጉዳይ አልነበረም አንባብያን ወገኖች የእኛም ጉዳይ ይሄ ሊሆን ይገባል ለአንድም ሰው ቢሆን ደክመን ከዚያ ከደከምንበት ሰው ጀርባ የወንጌል አዝመራን ማግኘት ማጨድና ወደ ጎተራ ማስገባት ፤ በመሆኑም ኢየሱስ ከሴት ጋር በመነጋገሩ ለደቀመዛሙርቱ ለአይሁዳውያንም ሆነ ለሳምራውያን የወንጌልን የሥራ ፍሬ ከማስገኘቱ ውጪ ያመጣው ኪሳራ ወይንም ለውጥ የለም ስለዚህ የእግዚአብሔር ቅዱሳን ወገኖች እኛም የእግዚአብሔር ሕዝቦች በየትኛውም አቅጣጫ ተልእኮአችን ወንጌልና የእግዚአብሔር ሥራ በሚሆንበት ጊዜ ወደ ጎተራ የሚገባ የበሰለ ፍሬና የነጣ አዝመራ ይገኛል ያን ጊዜ ለእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ማሰናከያ አንሆንም ሌላውና ሁለተኛው ሃሳብ ደግሞ ቤተክርስቲያን ለእግዚአብሔር የተለየ መታወቅያውና ማዕረጉ ልትሆን የተጠራች ለዚያም የደረሰች እንደ መሆንዋ መጠን የእግዚአብሔር ማኅበር ናትና በየትኛውም ሁኔታ የተናቀች አይደለችም ሐዋርያው ይህን ጉዳይ በተመለከተ በቆሮንቶስ ላለች ቤተክርስቲያን የጌታን እራት በማንሳት እንግዲህ አብራችሁ ስትሰበሰቡ የምትበሉት የጌታ እራት አይደለም በመብላት ጊዜ እያንዳንዱ የራሱን እራት ይበላልና፥ አንዱም ይራባል አንዱ ግን ይሰክራል የምትበሉባቸውና የምትጠጡባቸው ቤቶች የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ማኅበር ትንቃላችሁን ? አንዳችም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን? ምን ልበላችሁ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን ? አላመሰግናችሁም በማለት ይናገራል 1ኛ ቆሮንቶስ 11 ፥ 20 _ 22 በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን መካከል ትልቅ የሆነ መለያየት ስለነበረ የጌታን እራት የሚወስዱት በልዩነት ውስጥ ሆነው ነውና በጥንቃቄና በማስተዋል አልነበረም ስለዚህ በመብላት ጊዜ እያንዳንዱ የራሱን እራት ይበላልና፥ አንዱም ይራባል አንዱ ግን ይሰክራል የምትበሉባቸውና የምትጠጡባቸው ቤቶች የላችሁምን ? ወይስ የእግዚአብሔርን ማኅበር ትንቃላችሁን ? አንዳችም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን ? ምን ልበላችሁ ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን ? አላመሰግናችሁም አላቸው ከልዩነት የተነሳ እንግዲህ እያንዳንዱ አንዱን እንጀራ የሆነውን የጌታን እራት ሳይሆን የራሱን እራት ነበረ የሚበላው ስለዚህም አንዱ ይራባል ሌላው ደግሞ ይሰክራል እንድንበላ የታዘዝነው ግን ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያለን ስለሆንን አንድ ሥጋ ነንና ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለን 1ኛ ቆሮንቶስ 10 ፥ 16 _ 18 በዚህም ድርጊታቸው ታድያ የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን አንዱን እንጀራ ሊካፈሉ ሲገባቸው የየራሳቸውን እራት የሚበሉ ናቸውና የእግዚአብሔርን ማኅበር የናቁ በመሆናቸው የምትበሉባቸውና የምትጠጡባቸው ቤቶች የላችሁምን ? ወይስ የእግዚአብሔርን ማኅበር ትንቃላችሁን ? በማለት ሲናገራቸው እናያለን ዛሬም በእኛ ዘመን በቅዱሳን መካከል የእግዚአብሔር ማኅበር የሚናቅበት ብዙ አካሄድና ብዙ አሠራር አለ እግዚአብሔር እንደ ቃሉ ያልሆነውን ይህን አካሄድና አሠራራችንን ይለውጥልን እንደገናም ይቅር ይበለን በእኛ ስሕተትና እንደሚገባ አለመሆን ምክንያት በውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጪ ባሉት ሰዎች ዘንድ ሳይቀር የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ፣ የእግዚአብሔር ማኅበር ተንቃለች እየተናቀችም ትገኛለች እኛ ግን የተጠራነው የእግዚአብሔር ቤት የእውነት ዓምድና መሠረት የሕያው የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ስለሆነ የቤቱ ነገር ግድ ብሎን ስሙን ለማስከበር ነው እንጂ የእግዚአብሔርን ቤት ለማስናቅና መዘበቻም ለማድረግ አይደለም 1ኛ ጢሞቴዎስ 3 ፥ 14 _ 16 ፣ 2ኛ ቆሮንቶስ 11 ፥ 28 ፣ ዮሐንስ ወንጌል 2 ፥ 13 _ 18 ለዚህም ነው ከላይ በመግቢያዬ ላይ በጠቀስኩት ቃል መሠረት በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ ያለን የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 20 ፥ 28 ለመንጋው ብቻ ሳይሆን ለራስም ጭምር መጠንቀቅ አስፈላጊነቱን ጌታ ተናግሮአል አንዳንዴ ለመንጋው የተጠነቀቅን እየመሰለን እራሳችን እናጠፋለን ሰበባችን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብና መንጋው ነው 1ኛ ሳሙኤል 15 ፥ 24 _ 35 የእግዚአብሔርን ቤት መጠበቅን በተመለከተ ሌላው እጅግ ደስ የሚለውና የሚያረካው ጌታ የተናገረውና የጸለየው ነገር ነው ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፥ እነርሱም በዓለም ናቸው፥ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው አለ የዮሐንስ ወንጌል 17 ፥ 11 ክርስቶስ ለሞተላት ቤተ ክርስቲያን በመራራት ታማኝ እረኛ ሆኖ መንጋውን በአግባብ የሚጠብቅ ቢጠፋም ኢየሱስ ለአባቱ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው በሚል ጸሎት ቤተክርስቲያንን ያስረከባት በመሆኑ አንዳች የምትሆነው ነገር የለም
አብርሃም ባያውቀን እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ አቤቱ፥ አንተ አባታችን ነህ፥ ስምህም ከዘላለም ታዳጊያችን ነው
ትንቢተ ኢሳይያስ 63 ፥ 16
የምናነበውን ቃል እንድናስተውለውና እንድንጠቀምበት እግዚአብሔር ይርዳን ጸጋውንም ያብዛልን
ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ
No comments:
Post a Comment