ቤተክርስቲያን
ክፍል አምስት
ቤተክርስቲያን ቅርጽና መልክ ያላት ሕያው ድንጋይ ናት በመሆኑም በ1ኛ ጴጥሮስ 2 ፥ 4 _ 6 ላይ በሰውም ወደ ተጣለ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠና ክቡር ወደ ሆነው ወደ ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ እየቀረባችሁ እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ በመጽሐፍ። እነሆ፥ የተመረጠና የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም ተብሎ ተጽፎአልና ይለናል ታድያ ሕያዋን ድንጋዮች ሆነን ለመገጣጠምና ቅርጽና መልክ ያለን ሆነን ለመታየት መሠራት የሚለው ሃሳብ በሕይወታችን ሊፈጸም የግድ ነው ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች በእግዚአብሔር ቤት ተወልደው ከተጠመቁ በኋላ የደቀመዝሙርነትን ሕይወት ናፍቀው የእርሱ ተከታይ ሊሆኑና ትክክለኛ የደቀመዝሙርነት ሕይወት ሊያሳዩ ለመሠራት ወደ ሕያው ድንጋይ ከሚቀርቡ ይልቅ ቶሎ ብለው ባገኙት ጸጋ በመገለጥ ጌታን ለማገልገል ሽተው ሐዋርያ መጋቢ ሽማግሌ ነቢይ ወንጌላዊ እና የመሳሰሉትን ስሞች ተቀብለው ሲያገለግሉና ከላይ ታች ሲሉ ይስተዋላሉ ነገር ግን የተሠራ ሕይወት ይዘውና ጊዜያቸውን ጠብቀው ያልወጡ በመሆናቸው የእግዚአብሔርን መንጋ ሲያመሠቃቅሉ አዳዲስ የሚድኑ ነፍሳትን ሳይቀር ሲያሰነካክሉ ይታያሉ እግዚአብሔር ግን በተለያዩ የአገልግሎት ጸጋዎችና ስያሜዎች ተገልጠን ቤቱን ከመሥራታችን በፊት በቅድሚያ እኛ መሥራት እንዳለብን ይጠቁመናል ባልተሠራ ማንነት የሚሰጥ አገልግሎት ከግንባታው ይልቅ አፍራሽነቱ የበዛ ነው በመሆኑም ያልተሠሩ ሰዎች ቦታውን ስለያዙ እንሠራለን ይላሉ ግን ሲያፈርሱ ይገኛሉ ለዚህ ነው የዛሬዋ ቤተክርስቲያን በአብዛኛው ቅርጿና መልኳ ፍጹም ተበላሽቶና ጠፍቶ የምናየው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ፥ 3 ላይ ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ያፈርስ ነበር፤ ወደ ሁሉም ቤት እየገባ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጐተተ ወደ ወኅኒ አሳልፎ ይሰጥ ነበር ይለናል ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ሕይወቱ ፍጹም ተለውጦ መንፈስቅዱስ በሚሠራበት አገልግሎት ውስጥ ከገባ በኋላ ግን የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፥ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል አለን 1ኛ ቆሮንቶስ 3
፥ 10 _ 15 ወገኖቼ ጸጋ ተሰጥቶን የምናገለግለው አገልግሎትና የምንሠራው ሥራ እንኳ ቢኖር የምንሠራው ጳውሎስ እንዳለው እንደተሰጠን ጸጋ መጠን ነው እንደገናም እንደ ብልሃተኛ አናጺ በመሆን ሰዎች መሠረት ይዘው እንዲያድጉ በማድረግና በማነጽ ነው መጽሐፉ የሚነግረን ይህንን ነው በጉልበት በጩኸትና በማስፈራራት የሚሠራ ምንም ዓይነት አገልግሎት የለም አለ የምንል ከሆነ ደግሞ ይኽ አገልግሎት ሳውል ባልተለወጠ ዘመኑ ባልተቃና ማንነቱ ይሰጥ የነበረው የማነጽ ሳይሆን የማፍረስ አገልግሎት ነው መጽሐፍ ደግሞ አሁንም ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ ይለናልና የምናገለግል ሰዎች በብርቱ ልንጠነቀቅ ይገባል 1ኛ ቆሮንቶስ 3 ፥ 17 ጳውሎስ ሳውል ከሚለው ሕይወቱ ወጥቶ በጌታ በሆነው እውነት በመዋጀት ጳውሎስ የሚለውን ስያሜ ይዞ ከተገለጠ በኋላ በተሠራ ሕይወት መምጣቱ በብዙ ጠቅሞታል ይኸውም አገልግሎት በጉልበት በጉብዝናና በኃይል ሳይሆን በጸጋ መሆኑን ተረድቶ እንደተሰጠኝ ጸጋ መጠን አለ እንደገናም የሐዲስ ኪዳን አገልግሎት
ጥንቃቄ የሚያሻው አገልግሎት በመሆኑ የስማ በለው የውዽድርና የፉክክር አገልግሎት ስላይደለ እንደ ብልሃተኛ አናጺ አለ ከዚህ ሌላም የተሰጠው አገልግሎት በፍጻሜው በእሳት የሚፈተን ነውና ከጉዳት ለመዳንና በጌታ በሆነው ሙሉ ደሞዝ ውስጥ ለመግባት ቤቱን በምን መሥራት እንዳለብን ጠቆመን ታድያ ጳውሎስ ወደዚህ የመረዳት አገልግሎት ውስጥ የገባው ጌታ አግኝቶት ሕይወቱ ከሠራውና ስሙን ከለወጠለት በኋላ ነው ይህንን እውነት ወደ እኛ ስናመጣው ዛሬ የተሠራ ሕይወት ስለሌለን ሁሉንም ነገር እኛ መሆን እንፈልጋለን ቤተክርስቲያን የእኛ አገልግሎት ሁሉ የእኛ ይመስለናል እኛ ያልነው ካልሆነ ሁሉም ነገር ሥህተት ይመስለንና በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ ቆንጨራ እናነሳለን እናሳድዻለን ሲያስፈልግም እንገላለን እግዚአብሔር ይቅር ይበለን መሠራት ከመሥራት የሚቀድም ነገር ነው የተሰጠንን ለማወቅ እንደብልሃተኛ አናጺ ለመሆን ቤቱንም በሰንፔር በወርቅ በብርና በከበረ ድንጋይ ለመገንባት መሠራት የግድ የሚለን ነገር ነው መሠራት ከሐዋርያነት ከነቢይነት ከመጋቢነት እና ከመሳሰሉት የአገልግሎት ኦፊሶችና ስያሜዎች የሚቀድም ነገር ነው ስንሠራ በስማችን በተሰጠን ቦታና አገልግሎት አንመካም ስንሠራ ሌሎች እንዲሰሩ ሌሎችን ማስቀደም ለሌሎች ቦታ መስጠት እንጀምራለን ሐዋርያው አሁንም የተሠራ ሕይወት ስለነበረው ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም እንግዲህስ እኔ ብሆን እነርሱም ቢሆኑ እንዲሁ እንሰብካለን እንዲሁም አመናችሁ አለን 1ኛ ቆሮንቶስ 15 ፥ 8 _ 11 ዛሬ ግን በተቃራኒው ሰዎችን ከእግዚአብሔር ቤት የሚያባርረው ስማችን ሆኗል እርስ በእርሳችሁ ተከባበሩ የተባልን ሆነን መከበር ቢያስፈልገንም ሰዎች ስማችንን አክብረው አቆላምጠው ፈርተውና ተንቀጥቅጠው የማይጠሩን ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ቤተክርስቲያን ውስጥ ልናያቸው አንፈልግም ይህ እንግዲህ ትልቅ በሽታ ያልተሠራ ማንነትና እኔነት ነው እግዚአብሔር ይፈውሰን ሐዋርያው ግን ከሁሉ የማንስ ጭንጋፍ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንኩኝ ነኝ አለ የተሰጠውንም ጸጋ በማክበር ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም አለ በስማችን ከበሬታን ፈልገን የምናስፈራራ ሳንሆን ልጠራ የማይገባኝ በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንኩ ነኝ ስንል በእውነተኛው ልባችን እንደ ሐዋርያው እግዚአብሔርን ለማክበር እርሱ ይርዳን ይህ መልዕክት ሃሳቡ ሰፊ የሆነ በመሆኑ በዚሁ ልቋጨው የማልችለው ነገር ነውና በቀጣዩ የክፍል ስድስት ትምህርት ላይ በስፋት እመጣበታለሁ እስከዚያው በጌታ የተወደዳችሁ ቅዱሳን ወገኖች ይህንኑ ክፍል እያነበባችሁ ለሌሎችም እያስተላለፋችሁ ቆዩኝ ተባረኩልኝ
ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ
No comments:
Post a Comment