Sunday, 7 December 2014

የጫጫታው ብዛት

የጫጫታው ብዛት

 
 
 
የሰዎች መንጫጫት አረ ምን ይጠቅማል
አዬ ጉድ አዬ ጉድ እንዲያው ጉድ ይባላል 
ኑኃሚን ስትመጣ በሐዘን በምሬት 
የከተማው ሰዎች ተንጫጭተው ጮሁላት
አሉ ተናገሩ ይህቺ ኑኃሚን ናት
ለውስጥ ሐዘንዋ ግን ምላሽን የሚሰጥ
ትካዜ ልቅሶዋን ሮሮዋን ሊለውጥ
ለባዶ ነገሯም ሙላትን ለማምጣት
አንድም አልተገኘ ከምድር ፍጥረታት
እርስዋም ተናገረች በሙላት ወጣሁኝ
ጌታ እግዚአብሔር ባዶዬን መለሰኝ
ሁሉን የሚችል አምላክ በጣም አስጨነቀኝ
አዋረደኝ እንጂ መቼ አከበረኝ
ማራ በሉኝ ብቻ ኑኃሚን አትበሉኝ
ይኸው ነው ታሪኬ ሁላችሁ እወቁኝ
እንዲህ ብላ ስትል እንዲያ ስትናገር 
ሳይገለጥላት የአምላኳ ምስጢር
እግዚአብሔር ተገኘ በነገሯ መሐል
ምንም ሳይታሰብ ማንም ምንም ሳይል
በትንሽ ጀምሮ በትልቅ ጨረሰ
በሩት በምራትዋ እግዚአብሔር ደረሰ
ከቃርምያ አንስቶ በመከሩ መሐል
ማስገኘት የሚችል እግዚአብሔር ኃያል
መመስገን ጀመረ ዋርሳ ያላሳጣሽ
ሆኖ ለኑኃሚን እግዚአብሔር ደራሽ
የሕይወት ተሃድሶ ደግሞም ምግብና
ለኑኃሚን ሊሰጥ ላለች በእርጅና
ልጅን አስገኘላት ከሩት ከምራትዋ
ኑኃሚን ደስ አላት ከነጎረቤትዋ
ወገኖች በሙሉ እናስተውል በእውነት 
በሥፍራችን ሆነን የእግዚአብሔርን ሰዓት
ታማኝ ሆነን ቆመን ብንጠባበቀው
ከጫጫታው ወጥተን ደግሞም ከሁካታው
እግዚአብሔር ይመጣል ከመልሳችን ጋራ
በመማጸኛችን ባለንበት ሥፍራ 
መልስ የሚሰጥ ሆኖ በተራ በተራ
መልስ የሚሰጥ ሆኖ ሁሉንም በተራ

ወይትባረክ እግዚአብሔር አሜን

ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment