ቤተክርስቲያን
ክፍል አስራ ሦስት
እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን
በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው ? የተቀመጠው አይደለምን ? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ
የሉቃስ ወንጌል 22 ፥ 26 _ 27
በኢየሱስ ክርስቶስ ያለ መንፈሳዊ ሥልጣንና አገልግሎት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ጥቅም የሆነ መንፈሳዊ ሥልጣንና አገልግሎት ስለሆነ ይህንን እውነት በጽኑ ይለማመዳል ያደርገዋልም ስለዚህ ከላይ እንደ መግቢያ ጥቅስ አድርጌ በተጠቀምኩት ቃል ላይ እንዲህ የሚል መመርያ ለደቀመዛሙርቱ ሲሰጣቸው እንመለከታለን እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው ? የተቀመጠው አይደለምን ? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ ይላቸዋል በእንግሊዘኛው እንዲህ ብሎ ያስቀምጠዋል Christ
said to let << he who governs [ be] as he who serves >> _____
following His own example of selflessly serving and giving በመሆኑም እነዚህ ደቀመዛሙርት ከጌታችን ሕይወት የማገልገልና የመሰጠትን ምሳሌነት በጽኑ ተመልክተው እንዲከተሉ ያበረታታቸዋል ነገር ግን እናንተ ግን እንደዚህ አትሁኑ ሲል ምን ለማለት የፈለገ ይመስላለ ? ደቀመዛሙርቱስ ምን ሆነው ነበር ? ጌታስ ምን አይቶባቸው ይህንን ሊላቸው ቻለ ? ይህንን ጉዳይ ዛሬ ላይ ወዳለነው ወደ እኛም ሕይወት አምጥተን እኛንስ ዛሬ ምን ይለናል ? እና የመሣሠሉትን ጥያቄዎች ሁሉ ልናነሳበት እንችላለን ጌታ ኢየሱስ ከደቀመዛሙርቱ ሕይወት የተመለከተው እርሱ የሚጠብቀውን ሕይወት አልነበረም እርሱ የሚጠብቀው
ሕይወት ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ የሚገዛም እንደሚያገለግል የሆነ የአገልግሎት ሕይወት ነው ይህ ደግሞ ማገልገልን ብቻ ሳይሆን መሰጠትንም የሚጠይቅ
የሕይወት ውሳኔ ነው ታድያ ያልተሰጡ ሰዎች መድረኩን ስላገኙ ብቻ አጋጣሚው በፈጠረላቸው ዕድል ተጠቅመው ሊያገለግሉ ሌላም ብዙ ብዙ የሆኑ የእግዚአብሔርን መመርያዎች ሊናገሩ ይችላሉ ነገር ግን አገለገሉ የእግዚአብሔርንም የሕይወት መመርያዎች ተናገሩ ማለት ግን የተናገሩትን ለመተግበር ታናሽ ሊሆኑ የሚገዙ ሆነው ሳሉም ለማገልገል ተሰጡ ወይም ዝቅ አሉ ማለት ግን
አይደለም ንግጝርና ተግባር የተለያዩ ነገሮች ናቸው ይሁን እንጂ ታድያ ሰው ተናገረ ማለት ተገበረ ማለት
ስላልሆነ መጽሐፍቅዱሳችን እንድንናገር ብቻ ሳይሆን የተናገርነውን እንድንተገብር በብዙ ቦታዎች ላይ ይናገራል ኢየሱስ እራሱ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ፊት በሥራና
በቃል ብርቱ ነቢይ የነበረ መሆኑን መጽሐፍ ይናገራል የሉቃስ ወንጌል 24 ፥ 19 _ 21 እንደገናም በ1ኛ ጢሞቴዎስ 4 ፥ 11 ጀምሮ ይህን እዘዝና አስተምር በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ፥ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ ይለዋል ስለዚህ አገልግሎታችን በመስበክ በማስተማር በመምከርና በመሣሠሉት የሚጠቃለል ወይንም የሚያበቃ ሳይሆን በኑሮም ጭምር የሚገለጥ ነው በመሆኑም አገልጋይ የሰበከውን ለመኖር አለበለዚያም ደግሞ የሚኖረውን ለመስበክ መነሳት አለበት እዚህ ላይ አንድ ሰባኪ ያደረገውን በምሳሌነት የቀረበ አባባል እንደሚከተለው ላቀርበው እወዳለሁና ተከታተሉ ሰባኪው ነጭ ነው የስብከቱ ተራ ደርሶ ሲሰብክም የግሪክ ሰው የለ ጨዋ የለ ወንድ የለ ሴት የለ ሁላችን በክርስቶስ አንድ ነን ወንድማማቾች ነን እያለ ይሰብካል ስብከቱንም በጨረሰ ጊዜ መኪናውን አስነስቶ በቀጥታ ወደ ቤቱ ይሄዳል በዚህን ጊዜ ስብከቱን በማስተዋል ሆኖ የተከታተለ አንድ ጥቁር ክርስቲያን በጣም ችግረኛ ነበርና
ይሄ ሰባኪማ ወንድሜ ነው ለምን ቤቱ ድረስ ሄጄ ችግሬን አላዋየውም ? እንዲረዳኝስ ለምን አላደርገውም ? ይልና በቀጥታ ወደ ሰባኪው ቤት ይሄዳል እዚያም በደረሰ ጊዜ ሰባኪው የግቢ ዘበኛ ነበረውና የግቢውን በር አንኳኩቶ ዘበኛው ሲመጣለት ሰባኪውን ፈልጌ ነው ይለዋል ለምን ጉዳይ ፈለግኸው ? ቢለው ወንድሜ ስለሆነ ይላል ዘበኛውም በመደነቅ እርሱ ነጭ አንተ ጥቁር በዚህ ላይ በምንም ሁኔታ የማትገናኙ ናችሁ እንዴት ሰባኪውን ወንድሜ ነው ትላለህ ? ይሄ ነገር ሊሆን አይችልም ቢለው እባክህ ፍቀድልኝ ? ወንድሜ ነው ሲል ይዘበዝበዋል ዘበኛውም እንግዲያስ ሄጄ ልጠይቀው እዚሁ ቆየኝ ይለውና ሰባኪው ወዳለበት ሳሎን ገባ በማለት ሰባኪ ሆይ አንድ ጥቁር ሰው የሰባኪው ወንድም ነኝ ይላል ላስገባው ወይ ? ሲል ሰባኪውም መልሶ እንዲህ ዓይነት ጥቁር ሰው ወንድም አለኝ እንዴ እኔ ? በማለት ለማንኛውም እስቲ አስገባው የሚሆነውን እናያለን ሲል ይፈቅዳል በመቀጠልም ያ ጥቁር ክርስቲያን ይህንኑ የመግባት ፈቃድ አግኝቶ ወደ ሰባኪው ቤት ይገባል ጥቂት ሰላምታ ከተለዋወጡም በኋላ ጥቁሩ ክርስቲያን የመጣበትን ጉዳይ በማስረዳት እንድትረዳኝ ተቸግሬ ነው የመጣሁት ደግሞም በዚህ ላይ ደግሞ አንተ እኮ ወንድሜ ነህ
? ቢለው ሰባኪውም መለስ አድርጎ በመገረም ደግሞ እንዳንተ ዓይነት ወንድም
አለኝ እንዴ ? ቢለው ጥቁሩም ክርስቲያን ሲመልስ ቅድም በቤተክርስቲያን የግሪክ ሰው የለ ወንድ የለ ሴት የለ ጨዋ የለ ባርያ የለ ሁላችን በክርስቶስ አንድ ነን ወንድማማቾች ነን ብለህ ሰብከኸን አልነበረም እንዴ ? ለዚህ ነዋ ወንድሜ ስለሆንክ እንድትረዳኝ የመጣሁት ቢለው ሰባኪውም ሲመልስ እርሱንማ እዚያው ቤተክርስቲያን አልኩህ እንጂ መች እዚህ አልኩህ አለው ይባላል ወገኖቼ የእግዚአብሔርን ቃል ለማለት ብቻ የምንል የማንኖርበትም ከሆነ ማለታችን ወይንም መናገር መስበካችን ብቻ ዋጋ የሌለው ይሆናል የእግዚአብሔር ቃል እኛ ባንናገረውም የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ተጽፎልናል ዋናው ቁም ነገሩ ግን እኛ ተናግረነው ብቻ እንድናልፈው የተጻፈ መጽሐፍ ሳይሆን እንድንኖረውም የተጻፈ መጽሐፍ ነው ስለዚህ በቤተክርስቲያንም ይሁን በማንኛውም ቦታ የተናገርነውን ቃል ልንኖረው የግድ ይለናል አለበለዚያ ግን ልንናገረው አይገባም ታድያ ብዙዎች አገልጋዮች እኔንም ጨምሮ የመድረክ ላይ ተናጋሪዎች ነን የቤት ሕይወታችንና የጓዳው እኛነታችን ሲፈተሽ ግን ሌሎች ሰዎች ነን ሌላው ቀርቶ ለሰዎች የምንሰጠው መልሳችን እንኳ መድረክ ላይ ካለው አገልግሎታችን ጋር ፍጹም የሚቃረንና አብሮም የማይሄድ ስለሆነ ሰዎች በብዙ ታዝበውናል ለአንዳንዶችማ እንኳን ጊዜ ሰጥተው ሊሰሙን በእኛም ሊገለገሉ ቀርቶ ለዓይኖቻቸው ሳይቀር አስጠልተናቸው የሚሸሹን በቁጥር ብዙ ናቸው ይህንን የምለው የአገልጋዮችን ሕይወት ለማንኳሰስ ለመውቀስና
ለመክሰስ ሳይይሆን ካለፈው ስሕተታችን ተምረን ሕይወታችንን በማስተካከል
ለተሻለና ለበለጠ ክብር እንድንነሳ ነው ያኔ ብዙዎች በእኛ መሰናከላቸውን አቁመው መዳን መትረፍ ማምለጥንም ገንዘብ ያደርጋሉ ወደ ተነሳሁበት መጠይቅ ስመጣ ደግሞ ጌታ ኢየሱስ እናንተስ እንዲህ አትሁኑ ሲል እርሱ ከሚጠብቀው ሕይወት ውጪ የሆነ ሕይወት በመሆኑ ይህንኑ አይቶ እናንተስ እንዲህ አትሁኑ ማለትን ፈልጎ የተናገራቸው ነው
መጽሐፉን ስንመለከት ደግሞም ማናቸውም ታላቅ ሆኖ እንዲቈጠር በመካከላቸው ክርክር ሆነ እንዲህም አላቸው፦ የአሕዛብ ነገሥታት ይገዙአቸዋል፥ በላያቸውም የሚሠለጥኑት ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው ? የተቀመጠው አይደለምን ? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ ነገር ግን እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በአሥራ ሁለቱ በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ አላቸው ይለናል የሉቃስ ወንጌል
22 ፥ 24 _ 30 ደቀመዛሙርቱ የማያምርባቸውን እጅግም የሚያስጠላባቸውን እንደገናም ግምገማ ውስጥ ሳይቀር ገብተው እንዲቀሉ ያደረጋቸውን ነገር ሊነሳ በማይገባው ሥፍራና ተገቢም ባልሆነ ቦታ ሊያውም የመታሰቢያ ጽዋ በሚነሳበት ኅብስቱም በሚቆረስበት ሥፍራ ታላቅ ሆኖ የመቆጠር ክርክራቸውን ሲያጦፉና ሲያቀልጡት እንመለከታለን ይህ ታላቅ ሆኖ የመቆጠር ሃሳብ በዚያን ወቅት ባሉበት ሁኔታ እንኳን ሊነሳ ሊታሰብ እንኳ የማይገባው ጉዳይ ነበር ነገር ግን ይሄ ጉዳይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳይና ዋና አጀንዳም ሆኖባቸው ክርክር ውስጥ የከተታቸው በመሆኑ ኢየሱስ መሃላቸው ገብቶ የዳኘው ባይሆን ኖሮ እጅግ የከፋ ነገር ውስጥ ይገቡ ነበር ለዚህ ነው ጌታ ነገሩን በትሕዝብት መልክ አይቶ እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ ያለው ወገኖቼ እዚህ ላይ ደቀመዛሙርቱ ብቻ አይደሉም አንዳንዴ እኛም የምንሆነው ነገርና እያደረግነውም ያለ ነገር አይደለም ጌታ እና የጌታ ሰዎች በዓለም ያሉ ሰዎች ሳይቀር የሚጠብቁብት ነገር ባለመሆኑ እጅግ አስከፊ ነው ስለዚህ ነገሩን የሰሙ አንዳንድ ሰዎች እናንተም ጋ ይሄ ተፈጠረ እንዴ ? እናንተም እንዲህ ሆናችሁ ? በማለት አያበቁም ጌታችንና ትክክለኛ የጌታ ሰዎች የኛው የራሳችን ናቸውና ሊመክሩን ፈልገው እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ ቢሉንም ሌሎች በደጅ ያሉ ሰዎች ግን
ነገራችንን የታዘቡ በመሆናቸው በምጸትና በትሕዝብት ቃል በእናንተስ እንዲህ አይሁን ይሉናል
ወገኖቼ እንግዲህ አንዳንዱ ነገራችን ከእኛ አልፎ ሌሎች ጋር የደረሰ በመሆኑ እጅግ እጅግ አስጠልቶብናልና ይህ ቅጥ ያጣው ነገራችን ደግሞ ወደ ከፋ
ሁኔታ ውስጥ እንዳይከተን እንደገናም ከእኛ ጋር ይዘናል ብለንም ከምንናገረው እውነተኛው ነገራችን ጋር የማይሄድ ግንጥል ጌጥና የማያምርብንም በመሆኑ በእኛ ሊሆን የማይገባው አሁንም አይሁን አሜን የተስማማ ከእኔ ጋር አሁንም አሜን ይበል ወገኖቼ ሆይ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ አጀንዳ ግን ታላቅ የመሆን አጀንዳ ወንበርና ዙፋንንም የመስጠትና የማደላደል አጀንዳ ሳይሆን ሰዎችን የማገልገል አጀንዳ ነው ያለው ለዚህም ነው በማርቆስ ወንጌል 10 ፥ 43 _ 45 ላይ በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም ያለው እንግዲህ አገልግሎት ማለት ታላቅ እና ፊተኛ የመሆን ፣ ዙፋንንም የማግኘት ፣ ራስንም የመጥቀምና የማገልገል ሕይወት ሳይሆን የሌሎች አገልጋይና ባርያ መሆን ፣ አልፎም ሄዶ ነፍስን እስከ መስጠት ድረስ የሚያደርስ የመሥዋዕትነት ሕይወት ነው በዚህ ጉዳይ ላይ ሐዋርያው ሲናገር እንዲህ አለ እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፥ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና 1ኛ ተሰሎንቄ 2 ፥ 8 እውነተኛ አገልግሎት ውስጥ የገባ በእውነትና በጽድቅም ጌታን ሊያገለግል የጨቀነ ሰው መንፈስ እንዲህ ነው ከራስ ወዳድነት ወጥቶ እንደ ጳውሎስ የሚያገለግለውን ሕዝብ በእውነት የሚወድ ነውና የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሱን ጭምር ሊያካፍል በጎ ፈቃዱ ይሆናል ታድያ ዛሬ ማነው ጀግና ? እንዲህ ዓይነት መንፈስ ያለው የወንጌል አርበኛ ? መልሱን ትምሕርቱን ለምትከታተሉ ወገኖች ለእናንተው እተወዋለሁ ቁጣችን ቅንዓታችንና የውስጥ ትኩሳታችን ይሄ ሊሆን ይገባል የእግዚአብሔርን ወንጌል ማካፈልና አልፎም ለሌሎች ነፍስን ሳይቀር መስጠት ነገር ግን ከዚህ ይልቅ እንደ ዘብዴዎስ ልጆች ሥጋዊ ፍላጎታችን ንሮና ከፍ ብሎ ወጥቶ እያንገበገበን እያክለፈለፈንም ዙፋንን በፊተኝነት ምክንያትም እናገኛለን ብለን የምናስበውን አንቱታንና ከበሬታን ለማግኘት ከወዲያ ወዲህ ብንል ፣ እንደገናም ይህንኑ ለማግኘት ውሃ ቀጠነ ብለን በትንሽ በትልቁ ከሰዎች ጋር ስንነታረክ ፣ ስንጣላና ስንገነፍል ብንውል ከዚህም ሌላ ጾምና ጸሎት እንኳ ሳይቀር ይዘን ብንጠይቅ የምትምትለምኑትን አታውቁም ተብለን መልስን ከሚሰጠን በቀር ምንም ዓይነት ለውጥ የማናገኝ ሰዎች ነን እግዚአብሔር ወደ ማስተዋላችን ይመልሰን ዕድሉን አግኝተን መድረኩም የእኛ ሆነ ዙፋኑም ተሰጠን የምንል ሰዎች ብንኖር ደግሞ ጌታ የሚጠብቅብን በዙፋን መቀመጥንና በክሩሴዶች በኮንፍረንሶችና በእሁድ ለእሁድ አገልግሎቶች በተዋቡ መድረኮቻችን ላይ ሱታችንን ደርበን ከረባታችንን አስረንና ሽቶአችንንም ተርከፍክፈን ሃሌሉያ እግዚአብሔር ይመስገን ቅዱሳን እያልን ስብከታችንን ብቻ እንድናቀልጠው ሳይሆን ዝቅ ብለን ፣ በቢሮአችን ከተቀመጡ ዙፋኖቻችንና ከተዋቡ መድረኮቻችንም ላይ ወርደን ለሌሎች ባርያ በመሆን ጊዜያቸውን ወስደን አንድ ጊዜ ስሙኝ ያልናቸውንና የሰበክናቸውንም ሰዎች የራሳቸው ጉዳይ ከማለት ይልቅ በተግባር ቤቶቻቸው ድረስ በመሄድ በመጎብኘትና ችግሮቻቸውንም ጭምር አብሮ በመካፈልና በመፍታት ልናገለግል ሲያስፈልግም ነፍሳችንን ሳይቀር ልናካፍላቸው በጎ ፈቃዳችን ሊሆን እንደሚገባ ነው ለዚህ ደግሞ አሁንም ጌታ እግዚአብሔር በዚህ እውነት እንዲያስበን የሁላችንም ጸሎት ሊሆን ይገባል ወገኖች ይህ መልዕክት የሚጠቅማችሁና ለአገልግሎታችሁም ፈር ቃዳጅ የሆነ መልዕክት ስለሆነ በማስተዋል ሆናችሁ አንብቡት አጥኑት ሊደርሳቸው ለተገቡ ለሌሎችም አስተላልፉት እላለሁ በሚቀጥለው የትምህርት ክፍለ ጊዜ እስከምንገናኝ ጌታ
ዘመናችሁን ይባርክ እያልኩ የምሰናበታችሁ
በጌታ አገልጋያችሁ የሆንሁ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ
ተባረኩልኝ ለዘላለም
No comments:
Post a Comment