ቤተክርስቲያን
ክፍል ሃያ አራት
በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል
እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና
ገላትያ 6 ፥ 15
ባለፈው በክፍል ሃያ ሦስት ትምህርታችን ላይ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው አሮጌው ነገር አልፎአል እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል በሚል ሃሳብ ዙርያ አዲስ ፍጥረት የሆንበት ምስጢር ምን እንደሆነ ፣ ሰው በክርስቶስ የመሆኑ ምስጢር ምን
እንደሆነ ሊረዳ የሚችለው አዲስ ፍጥረት መሆን ሲችል ብቻ እንደሆነ ፣ አዲስ ፍጥረት የሆነ ሰው ደግሞ በጌታ የሆነና ጌታንም እንደ ግል አዳኙ አድርጎ የተቀበለ መሆኑን ፣ ጌታን ያልተቀበለ ሰው አዲስ ፍጥረት መሆን እንደማይችልና ከዚህም የተነሳ ጌታን እንደ ግል አዳኙ አድርጎ መቀበል
ለእርሱ ቀላል ነገር እንዳልሆነ የሚሉትንና ሌሎችንም ጉዳዮች አንስተን በሰፊው መማማራችን ይታወሳል ዛሬ ደግሞ ከዚሁ የቀጠለውንና የምናጠቃልለውን በገላትያ 6 ፥ 15 ላይ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና የሚለውን የማጠቃለያ ሃሳብ በሰፊው እንማማራለን ሐዋርያው እንዳለው በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት የመሆን ምስጢር የገባው ሰው አሁንም
በገላትያ 6 ፥ 15 ላይ በተጻፈልን ቃል መሠረት በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል በማለት በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት የመሆንን ዕድል ምርጫው ያደርጋል እንጂ እንደገና ወደ ኋላ ወደ ኦሪት ሥርዓት ተመልሶ መገረዝን አይከተልም መገረዝ የሚጠቅመን ቢሆን ኖሮ ሐዋርያው ጳውሎስ በግልጽ መገረዝ ይጠቅማልና ተገረዙ ይለን ነበር እንጂ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል አይለንም ነበር መገረዝም ሆነ አለመገረዝ የማይጠቅምና በሕይወታችንም ላይ ለውጥ የማያመጣ የኦሪት ሥርዓት በመሆኑ አይጠቅመንም አለን ስለዚህ የማይጠቅመን ነገር አሁንም አይጠቅመንም የሚጠቅመን በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ስለሆነ የሚጠቅመንን በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት የመሆን ሕይወትን ልንይዝ ይገባል ሰዎች በዚህ አዲስ የሕይወት ሥርዓት ውስጥ ገብተው እንዲመላለሱና በክርስቶስ ኢየሱስ
አዲስ ፍጥረት የመሆን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሐዋርያው አጠንክሮ በሕይወት አቋም ውሳኔ በማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና ሲል ተናገረ አስተማረ ይህንን መናገር ለሐዋርያው ዋጋ የሚያስከፍለው ሆኗል ስለዚህም በገላትያ 5 ፥ 11 ላይ ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል ? እንኪያስ የመስቀል ዕንቅፋት ተወግዶአል አለ በመሆኑም ሐዋርያው መገረዝን ባለመስበኩ ምክንያት ስደት እንዳጋጠመው በግልጽ ቢነግረንም ባጋጠመው ስደት ሳይፈራና ወደኋላም ሳይል አልፎ በመሄድ እንኪያስ የመስቀል ዕንቅፋት ተወግዶአል አለን እንግዲህ መገረዝን ሐዋርያው እንደነገረን በመስቀሉ በኩል አምጥተን ስናሳልፈው ከጠቃሚነቱ ይልቅ ጎጂነቱ የከፋ በመሆኑ ዕንቅፋት ነው በመስቀሉ በኩል የተገለጠው የደህንነት ሥራ ያላስወገደው ምንም ነገር የለምና ግዝረትም የመስቀል እንቅፋት በመሆኑ ተወግዷል ለመዳናችን የመስቀሉ ቃል በቂ ነው ስለዚህም ሐዋርያው የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና አለን 1ኛ ቆሮንቶስ 1 ፥ 18
የመስቀሉ ቃል የሆነው ኢየሱስ ስለበደላችን ዋጋ ሊከፍል በመስቀል ላይ ራቁቱን የሞተልን ሆኖ ለብዙዎች ሞኝነት ቢመስልም ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይሉ ፣ ማሸነፉ ፣ የማዳኑ ሥልጣንና ክብሩን የገለጠበት በመሆኑ ከሰይጣን ባርነትና ከኃጢአት ሰንሰለት ተፈተናል ከሲኦል ድነናል
ከዘላለም ሞት አምልጠናል በመሆኑም ሐዋርያው አሁንም የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና ጥበበኛ የት አለ ? ጻፊስ የት አለ ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን ? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና በማለት ግልጽ አድርጎና አብራርቶ ጻፈልን 1ኛ ቆሮንቶስ 1 ፥ 19 _ 25 ስለዚህ የሚያድነን በስብከት ሞኝነት እንድናምን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ የተገለጠበት የተሰቀለልን ኢየሱስ እንጂ ግዝረት አይደለም ተሰቅሎም ያልቀረና እኛንም ስለማጽደቅ ሕያው ሆኖ ከሙታን ተለይቶ የተነሳልን ኢየሱስ እያለልን የሥጋን ቊልፈት በሚያስወገደው ግዝረት እንጸድቃለን ብለን አንደክምም ይልቁንም በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና ስንል በግልጽ በመስበክ ቅልቅልና ድብልቅ የሌለበትን የአዲስ ፍጥረት ማንነታችንን እናጠናክራለን ግዝረት የሥጋን ሸለፈት መቊረጥ ሲሆን ለአብርሃም የተሰጠ የቃልኪዳን ምልክት ነው ይህም ለወንድ ልጅ ብቻ ነበር ዘፍጥረት 17 ፥ 7 _ 14 በሙሴም ዘመን ለእስራኤል ሕዝብ ምልክትና መለያ ሆነ ዘጸአት 12 ፥ 43 _ 45 ፣ 1ኛ ሳሙኤል 17 ፥ 36 ይህንን ሃሳብ በሐዲስኪዳን አምጥተን ስንመለከተው በሐዲስ ኪዳን የቃልኪዳን ምልክታችንና መለያችን ግዝረት ሳይሆን የክርስቶስ ደም ነው ራዕይ 19 ፥ 13 ፣ ራዕይ 12 ፥ 11 ፣ ራዕይ 7 ፥ 14 ፣ ራዕይ 5 ፥ 9 _ 10 ፣ ዕብራውያን 9 ፥ 12 ፣ ዕብራውያን 10 ፥ 19 እና 20 ፣ ዕብራውያን 12 ፥ 24 ፣ ዕብራውያን 13 ፥ 20 ፣ 1ኛ ጴጥሮስ 1 ፥ 1 እና 2 ፣ 18 እና 19 ፣ ቆላስያስ 1
፥ 19 _ 20 ሌሎችንም ብዙ ተመሳሳይ ጥቅሶች መስጠት እንችላለን ለጊዜው ግን እነዚህ ይበቃሉ እነዚህን ጥቅሶች በማስተዋል ሆናችሁ አንብቧቸው ፈሪሳውያንና የሕግ አስተማሪዎች ይህንን ግዝረት በሙሴ ዘመን ለእስራኤል ሕዝብ ምልክትና መለያ ሆኖ እንደተሰጠ ስለሚያውቁ ሕዝባዊና ሕጋዊ ምልክት አድርገው ቆጥረውት ነበርና በሐዋርያት ሥራ 15 ፥ 1 _ 11 ላይ በተጻፈው ቃል መሠረት አንዳንዶችም ከይሁዳ ወረዱና እንደ ሙሴ ሥርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ብዙ ጥልና ክርክር በሆነ ጊዜ፥ ስለዚህ ክርክር ጳውሎና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት ወደ ሽማግሌዎችም ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ዘንድ ተቈረጠ ቤተ ክርስቲያኑም በመንገድ እየረዳቸው እነርሱ የአሕዛብን መመለስ እየተረኩ በፊንቄና በሰማርያ አለፉ፥ ወንድሞችንም ሁሉ እጅግ ደስ አሰኙአቸው ወደ ኢየሩሳሌምም በደረሱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት ሽማግሌዎችም ተቀበሉአቸው፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ አወሩ ከፈሪሳውያን ወገን ግን ያመኑት አንዳንዶቹ ተነሥተው ትገርዙአቸው ዘንድና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ታዙአቸው ዘንድ ይገባል አሉ ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ስለዚህ ነገር ለመማከር ተሰበሰቡ ከብዙ ክርክርም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው ወንድሞች ሆይ፥ አሕዛብ ከአፌ የወንጌልን ቃል ሰምተው ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በመጀመሪያው ዘመን ከእናንተ እኔን እንደ መረጠኝ እናንተ ታውቃላችሁ ልብንም የሚያውቅ አምላክ ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው ልባቸውንም በእምነት ሲያነጻ በእኛና በእነርሱ መካከል አንዳች አልለየም እንግዲህ አባቶቻችንና እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን እግዚአብሔርን አሁን ስለ ምን ትፈታተናላችሁ ? ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንደ እነርሱ ደግሞ እንድን ዘንድ እናምናለን በማለት ሲወስን ያዕቆብም በበኩሉ የኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን መሪ ነበርና ስለዚህ ከአሕዛብ ወደ እግዚአብሔር የዞሩትን እንዳናስቸግራቸው ነገር ግን ከጣዖት ርኵሰትና ከዝሙት ከታነቀም ከደምም ይርቁ ዘንድ እንድንጽፍላቸው እቈርጣለሁ በማለት የበኩሉን ውሳኔ አስተላለፈ የሐዋርያት ሥራ 15 ፥ 13 _ 20 በገላትያ መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ፥ 2 _ 6 መሠረት ሐዋርያው ጳውሎስ እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም ሕግንም ሁሉ እንዲፈጽም ግድ አለበት ብዬ ለሚገረዙት ሁሉ ለእያንዳንዶች ደግሜ እመሰክራለሁ በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና በማለት የመስቀል እንቅፋት ተወግዶ ሳለ ይህንን እውነት ባለመቀበላቸው ምክንያት በጊዜው በመገረዝ እንድናለን ብለው ለሚያምኑ የገላትያ ሰዎች ለጊዜው ቢያሳድዱትም
የቃሉን እውነት ይነግራቸዋል አሁንም በእኛ ዘመን የሚጠላም ይሁን የሚያሳድዽ ቢነሳም አንድ እውነት ግን እንናገራለን በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምም እንላለን ሌላው በብሉይ ኪዳን ያሉት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ክፋትን ከሕይወታቸው የሚያስወግዱት በመገረዝ ነው በዘዳግም 10 ፥ 16 ላይ እንግዲህ አምላካችሁ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፥ ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም፥ በፍርድ የማያደላ፥ መማለጃም የማይቀበል ነውና እናንተ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ፥ ክእንግዲህ ወዲህም አንገተ ደንዳና አትሁኑ አላቸው በኤርምያስ 4 ፥ 4 ላይ ደግሞ እናንተም የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሆይ፥ ስለ ሥራችሁ ክፋት ቍጣዬ እንደ እሳት እንዳይወጣ የሚያጠፋውም ሳይኖር እንዳያቃጥል፥ ለእግዚአብሔር ተገረዙ፥ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ ይላቸዋል ይህንን ሃሳብ አሁንም ወደ ሐዲስ ኪዳን ስናመጣው መገረዝ ዋናው ነገር የልብ መለወጥ ነውና በፊልጵስዩስ 3 ፥ 3 ላይ እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና ስለሚለን ቃሉ የቃሉ አማኞች የሆኑ ቅዱሳን በመንፈስቅዱስ የተገረዙ እና የሚገረዙም ናቸው እንደገናም በሐዲስ ኪዳን ዘመን ጥምቀት በግዝረት ፈንታ ገብቷል በቆላስያስ 2 ፥ 11 እና 12 ላይ የሥጋንም ሰውነት በመገፈፍ፥ በክርስቶስ መገረዝ፥ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ፥ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ፥ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ ይለናል በመሆኑም ከእነዚህ ሁሉ እውነቶች አንጻር የሚጠቅመው በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ነው እንጂ ግዝረት አሁን አይጠቅምም ጌታ እግዚአብሔር የምናነበውን ቃል ይባርክልን
ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ
No comments:
Post a Comment