Sunday, 7 December 2014

የባልና የሚስት የግንኙነት ምስጢር ክፍል አንድ


የባልና የሚስት የግንኙነት ምስጢር

ክፍል አንድ


ብዙ ሰዎች ከትውውቅና ከእጮኝነት ባለፈ ሁኔታ ባልና ሚስት ሊሆኑ ወደ ውሳኔ የመጡበት የግንኙነት ምስጢር ልዩ ልዩ ዓይነት ነው በመክብብ መጽሐፍ ላይ ከንቱ በሆነ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ከምትወዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ ይላልና መክብብ 9 9 ለመጋባት መዋደድ ዋናውና ዓይነተኛው ጉዳይ ቢሆንም ሰው ስለተዋደደ ብቻ ግን የሚጋባ አይደለም ለምን ? ስንል ሰዎች የተዋደዱት ውጫዊውን ውበትና ደም ግባት አይተው ወደ ውስጥ ሳይገቡ በውጪ ባለው የሚታይ ነገር ብቻ ተስበው ሊሆን ይችላልና ነው ለዚህ ጉዳይ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ሶምሶን ነው በመጽሐፈ መሣፍንት 14 ቁጥር 1 ጀምሮ የተጻፈውን ክፍል ስንመለከት ሶምሶንም ወደ ተምና ወረደ በተምናም ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አየ ወጥቶም ለአባቱና ለእናቱ በተምና ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አይቻለሁ አሁንም እርስዋን አጋቡኝ አላቸው አባትና እናቱም ላቀረቡለት ጥያቄ ሲመልስም ለዓይኔ እጅግ ደስ አሰኝታኛለችና እርሱዋን አጋባኝ የሚል መልስ ነበር ለአባቱ የሰጠው ታድያ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ላይ ምክንያት ፈልጎ ነገሩ ከእርሱ ሆነ ቢለንም አባቱና እናቱ ግን አላወቁም ይለናል ሁለተኛውና ዋናው ነገር ደግሞ ነገሩ ከእግዚአብሔር ሆነ ቢለንም ሶምሶን ከተምና ሴት ጋር የተጋባበት መንገድ በዓይን አምሮት ላይ የተመሠረተ መንገድ ነው ለዚህ ጉዳይ አሁንም መጽሐፍ ቅዱሳችን የሚሰጠን መልስ አለ ውበት ሐሰት ነው ደም ግባትም ከንቱ ነው እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች ይለናል ምሳሌ 31 30 ስለዚህ የሶምሶን ምርጫ እግዚአብሔርን ከምትፈራ ሴት ጋር በተገናኘ መልኩ የሆነ ምርጫ ሳይሆን ውበትና ደም ግባት ላይ ያተኮረ በማየት ብቻ የሆነ ምርጫ በመሆኑ እየዋለና እያደረ ዋጋ ሲያስከፍለው እንመለከታለን ወገኖች በጋብቻችን ላይ ምንም ይሁን ምን በቅድሚያ ያሳደጉን ቤተሰቦቻችን ሊያውቁ በጉዳዩ ሊስማሙበትና ሊመክሩም ይገባል ወላጆቻችን ናቸውና እነርሱ የሌሉበትን ያልፈቀዱትንና ያልተስማሙበትንም ጋብቻ ማድረግ አንችልም ለዚህም ነው መጽሐፍቅዱሳችን ሰው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለን የማቴዎስ ወንጌል 19 5 _ 12 ተባብረን አንድ ሥጋ ወደምንሆንበት ቅዱስ ጋብቻ ሳንመጣ አባትና እናቶቻችንን በመጫን ያቀርቡትን ሃሳባቸውንም በመቃወምና እነርሱንም አላግባብ በመተው የምናመጣው ጋብቻ የምንወልዳቸው ፍሬዎች የቤተሰቦቻችንን ልብ ሳይቀር የሚያሳዝኑ ይሆናሉ እና ልንጠነቀቅ ይገባል በእግዚአብሔር ቃል ላይ ሰፍሮ እንደምናገኘው ዔሳውም አርባ ዓመት ሲሆነው የኬጢያዊ የብኤሪን ልጅ ዮዲትን የኬጢያዊ የኤሎንን ልጅ ቤሴሞትንም ሚስቶች አድርጎ አገባ እነርሱም የይስሐቅንና የርብቃን ልብ ያሳዝኑ ነበር ይለናል ዘፍጥረት 26 35 እና 36 ርብቃ ለይስሐቅ ሚስት ሆና በምትሰጥበት ጊዜ በጋብቻው የርብቃ ወላጆች ሳይቀሩ የተጠየቁና በመጨረሻም እነዚህ ወላጆች ፈቅደው ርብቃንም መርቀው ያሰናበቷት መሆኑን መጽሐፍቅዱሳችን በሚገባ ያስተምረናል ከዚህም ሌላ ርብቃ ወላጆችዋ ያልተስማሙበትንና ያልፈቀዱትን ጋብቻ አላደረገችም ዘፍጥረት ምዕራፍ 24 በሙሉ የተጻፈውን እንመልከት ስለዚህ አባትና እናታችንን የምንተወው ለተቀደሰ ጋብቻ በመመረጥ እንደ ርብቃ እልፍ አዕላፋት ሁኚ ዘርሽም የጠላቶችን ደጅ ይውረስ ተብለን በመመረቅ ነው እንጂ እነርሱን አለአግባብ በመተው ምክራቸውንም በመናቅና እንቢ በማለት ምርጫን ካለማስተካከል የተነሣ ባመጣነው የተሳሳተ የጋብቻ መዘዝ በሕይወታቸው ላይ የልብ ሐዘን ለማምጣት አይደለም ይህ ብቻ አይደለም ጋብቻችን ምስክርነት ያለበት እና ሊኖረውም የሚገባ በመሆኑ ጋብቻችንን ቤተክርስቲያን ሳይቀር ልትስማማበትና ቅዱስ መሆኑንም ልታረጋግጥ በመድረኮችዋም ላይ ጋብቻን በመባረክ ልታጸድቅ እኛም ነቀፋ በሌለበት ቅዱስ ጋብቻ የተጣመርን መሆናችንን ልታውጅልን የጋብቻ ሠርተፊኬትም ልትሰጠን ይገባል ይህ እንዲሆንልን ታድያ እኛ ተጋቢዎችም እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የሰጠውን መንፈሳዊ ሥልጣንና አደራም ጭምር በመረዳት ከማግባታችን በፊት የምናገባውን ሰው አምጥተን እግዚአብሔር ላስቀመጣቸው መንፈሳዊ መሪዎች ልናሳውቅ በሥርአት በእግዚአብሔርና በእግዚአብሔር ሕዝብ ፊት አጋቡኝ ልንል ይገባል ለምን ስንል ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን የወደደው በአደባባይ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት ነው እንጂ በድብቅ ጓዳ ለጓዳ አይደለም የጋብቻ ምስጢር ደግሞ ታላቅ የሆነ የክርስቶስና የቤተክርስቲያን ምስጢር ነው እንጂ በጓዳ ታፍኖ በድብቅ የቀረ ምስጢር አይደለም ኤፌሶን 5 32 ከዚህም ባሻገር ቤተክርስቲያን ያጸደቀችው ቅዱስ ጋብቻ ከምንዝርና በጸዳ መልኩ ለሀገር ለወገን ለእግዚአብሔርም ሥራ ሳይቀር የሚጠቅም በመሆኑ የተባረከ ዜጋን ለማፍራት የሆነ ነው መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል ስለሚለን ቃሉ ዕብራውያን 13 4 ቤተክርስቲያን ልታጋባ ይሄንን ሃላፊነት በምትወስድበት ጊዜ ተጋቢዎቹ በዝሙት ኃጢአት ተላልፈው ያልወደቁ ንጹሕ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ካሉበት አጥቢያ ቤተክርስቲያን እንዲያመጡ ታደርጋለች ካላመጡ አታጋባም በዚያው አጥቢያ ቤተክርስቲያን ሥር ካሉ ደግሞ ተከታትላ ንጽሕናቸውን ታረጋግጣለች ይህ ይሆን ዘንድም ጠንቃቃ በሆኑ በአንዳንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያኖች 3 ወር ወይም 6 ወር ጊዜ እንደሚሰጥ አውቃለሁ ይህ ደግሞ ለጥንቃቄና የጌታ ቤትም እንዳይሰደብ በመሆኑ መልካምና የተቀደሰ ሃሳብ ነው በተጨማሪም በቅዱስ ጋብቻ ተጣምረው አንድነታቸውን እስኪያረጋግጡ ድረስ ቅድመ ጋብቻ የጋብቻ ትምህርት ታስተምራለች ከጋብቻ በኋላም የቤተሰብ አያያዝና አስተዳደግ ትምህርት ለምዕመኖችዋ ትሠጣለች ተጋቢዎቹም ከመጋባታቸው በፊት ከኤችአይቪ ኤድስ ነጻ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ከሆስፒታል እንዲያመጡ ታደርጋለች ይህም ደግሞ ለጥንቃቄና መልካም ዜጋን ለማፍራት የተደረገ በመሆኑ ቤተክርስቲያን አሁንም በዚህ ነገሯ እንድትቀጥልና እንድትበረታበት የሚያደርጋትና የሚያነሳሳት በመሆኑ መልካም ነው እንላለን ይህንን ትምህርት በተከታታይ በቀጣይነት የማስተላልፈው ስለሆነ ቅዱሳን ወገኖች እንዲሁም ይህንን መልዕክት የምታነቡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሁሉ የሚለቀቀው ትምህርት ሳያመልጣችሁ ሁሉንም ትምህርት በየተራ በአግባቡ እንድትከታተሉ በጌታ ፍቅር አሳስባለሁ

የጌታ ሰላም ይብዛላችሁ ተባረኩልኝ የምላችሁ

ወንድማችሁ እና አገልጋያችሁ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ



No comments:

Post a Comment