Sunday, 7 December 2014

የግጥሙ ርዕስ

ሆሳዕና ሆሳዕና ሆሳዕና ተብሎ 

 


ሆሳዕና ሆሳዕና ሆሳዕና ተብሎ 
ዝማሬው ውዳሴው ዕልልታው ቀጥሎ
ወዲያው በማግሥቱ ስቀሉት ተባለ 
ጌታችን ኢየሱስ ቀራንዮ ዋለ
ይገርማል ይደንቃል የሰዎች ነገር
በአንድነት ሆነው ፈጥረው ግርግር
በሃሳብ ሳይጸኑ ብለው ሆሳዕና
በርባንን መረጡ ጌታን ተዉትና
ይፈታልን ሲሉ በርባንን ወደውት
አሳልፈው ሰጡ ጌታችንን ለሞት
በርባን ወንበዴ ነው መልስ የማያመጣ
በክፉ ተግባሩ በመጣበት ጣጣ
ዓለም ግን መረጠ በርባንን ለክብር 
ሥራው ክፉ ሆኖ ፍጹም የሚያሳፍር
ኢየሱስ በበርባን ተተክቶ ቢሞት
ፍጹም ጻድቅ ሆኖ እንከን የሌለበት
ከኃጢአት እስራት ሊፈታን ወዶ ነው
በመስቀል ላይ ደሙን ለእኛ ያፈሰሰው
የዘመኑ ሰዎች ከጥቂቶች በቀር
በብዙ ሞቅታ በጊዜያዊ ፍቅር
በሆሳዕና ማግሥት ስቀለው ለማለት
ወዳጆች በመሆን ለታይታ ለወረት
ዛሬ እንነሳለን እንጀምራለን 
ላይፈጸም ላያልቅ ወዳጅነታችን
ሆይ ሆይ እንልና ወረቱ ሲያበቃ 
በጥል በክርክር በሽሙጡ ቋንቋ
ፈጥነን በመነሳት በወንድማችን ላይ
የወዳጅ ቅቤ አንጓች ሆነንበት ሸንጋይ
ጥላቻችን ወጣ ክፋታችን ገኖ
ኃጢአት አድብቶብን ነግሦና ሰልጥኖ
እንደ ክፉው ቃየል ጨካኝ ገዳይ ሆኖ
ሊመልሰን ብሎ ጌታ ቢያባብለን
አሻፈረኝ አልነው አመጸኞች ሆነን
የአመጽ ድንፋታው ቀረርቶው ዳንኪራው
ሐሜት አሉባልታው ቂምና ጥላቻው
ወዲያው ይለወጣል ላፍታም ሳይቆይ ቶሎ
የጌታን ውሳኔ ሰምቶ አስተውሎ
የቃየል ጩኸቱ ወዲያው ተቀየረ 
መቅበዝበዝ መጣበት ሕይወቱም መረረ
ፍጹም ተነሳበት ከርታታ ሊያደርገው 
እግዚአብሔር ራራለት ምልክትን ሰጠው
ወገኖች እንግዲህ እናስተውል በእውነት
ጌታ ያልሰጠንን ነፍሰ ገዳይነት
ይዘን ብንነሳ ወንድምን ለማጥፋት
ጌታ ይገለጣል በመንገዳችን ላይ
ሕይወትም ይሆናል የምድር ላይ ኮብላይ
ስለዚህ ይቅርብን ወንድምን ማጥፋቱ
ማሳደድ መጎንተል መበቀል በከንቱ
ጌታ መሐሪ ነው ፈጥኖ ይመልሰን
እኛም እንመለስ ቸርነቱን ቀምሰን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

አባ ዮናስ ጌታነህ



No comments:

Post a Comment