መጽሐፈ አርጋኖን
የአርጋኖን መጽሐፍ
Part one
ይህ አርጋኖን በመባል የሚታወቀው መጽሐፍ ከአባ ጊዮርጊስ ድርሰቶች አንዱ ነው ይባላል አባ ጊዮርጊስ የተባለው ሰው የመጽሐፈ ሰዓታ ደራሲ እንደሆነ ብዙ የኦርቶዶክስ መምህራን ይናገራሉ አርጋኖን የምሥጋና መሳርያ ሳይሆን አይቀርም በዚህ መጽሐፍ አባባል ግን ምሥጋና ማለት ነው ይህ መጽሐፍ በስተመጨረሻው የማቴዎስ ወንጌል ተጽፎበታል ይሉታል የተለያዩ የአስማት ጽሁፎች እንዳሉበትም ይነገራል ከዮሐንስ ወንጌል ከመጀመርያው ምዕራፍ ቁጥር አንድና ሁለት አለበት ይህ መጽሐፈ አርጋኖን በሰባቱ ዕለታት እንዲጸለይ ሆኖ የተከፋፈለ መሆኑም ይነገርለታል ዋናውና የምፈልገው ሃሳብ ግን
ከዚህ በመቀጠል ባለው ዓረፍተ ነገር ውስጥ ያለ ሃሳብ ነው እርሱም እንዲህ ይላል የማርያምን ስም እየጠራ ኤልያስን ከጌታ ጋር ያነጻጽራል አያይዞም ኤልያስ በእሳት ሠረገላ ወደ ብሔረ ሕያዋን ቢሻገርም ከራሱ አልፎ ማንንም ሊያሻግር አልቻለም ከአንቺ የተወለደው ክርስቶስ ግን መሐይምናንን ማለት በስሙ ያመኑትን አማኞችን ከሞት ወደ ሕይወት አሻገረ ካለማወቅ ወደ ማወቅ አመጣቸው ይለናል ይህ ብቻ አይደለም ኤልሳዕ ንዕማንን ከለምጹ እንዲድን ከማድረግ አንስቶ ብዙ ተአምራትን አሳየ መራራውንም ውሃ በጨው አጣፍጦ መካኖች ሴቶች እንዲወልዱ አደረገ አልጫ የሆኑትን ነፍሳት ግን ጣዕም እንዲኖራቸልው ለማድረግ አልተቻለውም ክርስቶስ ግን የሥጋንና የነፍስን ለምጻሞችን አነጻ ይለናል ምንጭ መጽሐፈ ጉባኤ ዘ፴ወ፬ መጻሕፍተ ልሳነ ግዕዝ እለ ኢተዐልዋ ኅበ ካልዕ
ልሣን ስንተረጉመው በአማርኛ ካልተተረጎሙና በሕትመት ላይ ካልዋሉ 34 የግዕዝ መጽሐፎች
ተጨምቆ የተዘጋጀና የመጻሕፍቱን ይዘትና ምንነት የሚያስረዳ መልካም ግንዛቤንም የሚያስጨብጥ መንፈሳዊ እና ሥጋዊ መጽሐፍ ሲሆን የሚገኘውም
www.ethiopianorthodox.org ላይ ነው
ወገኖች ሆይ ዛሬ እንግዲህ የምንመለከተው የአርጋኖን መጽሐፍ የዘገበልንን ከመጽሐፍቅዱሳችን ጋር በትክክል የሚዛማደውንና ሊጣላም የማይችለውን እውነት ነው ይኸው መጽሐፍ የማርያምን ስም እየጠራ ኤልያስን ከጌታ ጋር ማነጻጸሩ የሚደንቅ እውነት ነው ለምን ? ስንል አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ስለ በደላቸውና ስለ ኃጢአታቸው የሞተላቸውን ጌታ እንደገናም እነርሱን ስለማጽደቅ የተነሳውንና ያረገውን በአብ ቀኝ ተቀምጦም የሚማልድላቸውን በመጨረሻም ተመልሶ በክብር የሚመጣውን ጌታ ይህንን ሁሉ የሆነው ለእነርሱ እንደሆነ በውል ተረድተው ለደህንነታቸው ያልተቀበሉት በመሆናቸው ሮሜ 4 ፥ 23
_ 25 የአርጋኖን መጽሐፍ እንደተናገረው ከኤልያስ ጋር እና እርሱንም ከሚመስሉት ነቢያት ጋር ያወዳድሩታል አወዳድረውት ደግሞ የነቢያት ሁሉ ጌታ እና አዳኝ የሆነውን አዳኛችንን ኢየሱስን ቢመርጡትና እንደ ግል አዳኛቸው ጌታቸውም አድርገው ቢቀበሉት መልካም ነበር መጽሐፍ ሲናገር የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም ይለናልና ተቀብለውት የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ነበር የዮሐንስ ወንጌል 1 ፥ 11 _ 13 ነገር ግን ብዙዎች ይህን የሁሉ አዳኝ የሆነውን ኢየሱስን ከሚቀበሉ ይልቅ እርሱን ከሌሎች ነቢያት ጋር አወዳድረው አንዳንዶች ከእነዚሁ ነቢያት ጋር በተራ ነቢይነት መድበውት በእኩልነት ያስቀምጡታል ለዚህም ነው የሰማርያይቱ ሴት ጌታ ሆይ አንተ ነቢይ እንደሆንህ አያለሁ ያለችው የዮሐንስ ወንጌል 4 ፥ 19 ደቀመዛሙርቱም የእርሱን ትክክለኛ ማንነት እንዲያውቁ የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ? እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ ? ብሎ ለጠየቃቸው
መልስ ሲሰጡ ሰዎች የሚሉትን በትክክል ቢናገሩም ትክክለኛውን መልስ ግን እነርሱም አላወቁትም ነበርና ከእነርሱ በመልሱ ለየት ያለው ፣ ፈጠንም ብሎ የተናገረው ጴጥሮስ ትክክለኛውን መልስ ሰጠ የማቴዎስ ወንጌል 16 ፥ 13 _ 20 እንደገናም ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ዘጠኝ ሰዓትም በሆነ ጊዜ ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ በማለት በታላቅ ድምጽ ጮኸ ይህም አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውኸኝ ? ማለት ነው ነገር ግን በዚያ ከቆሙት ሰዎች ሰምተው ይህስ ኤልያስን ይጠራል አሉ ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠ፤ ሰፍነግም ይዞ ሆምጣጤ ሞላበት፥ በመቃም አድርጎ አጠጣው ሌሎቹ ግን ተው፥ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ አሉ ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ ይለናል ከዚህም የምንረዳው አንድ እውነት እነዚህ ሰዎች
ከሰማርያይቱ ሴት ፣ ደቀመዛሙርቱ ከጠቆሙአቸው ሰዎች ፣ከደቀመዛሙርቱም ሆነ ብቸኛና ትክክለኛም መልስ ከሰጠው ከጴጥሮስ ሳይቀር ፍጹም የተለዩ ነበሩ ኢየሱስን ከኤልያስ እንደሚያንስ አድርገው በመቁጠር ኤልያስን ይጠራል አሉ ይህም ብቻ አልበቃቸውም ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ አሉ ታድያ እነዚህ ሰዎች ወደመሲሁ እውቀት ያልተጠጉ መሲሁ ኢየሱስንም ያላወቁ ምናልባትም በኤልያስ ነገር ጀርባ ያሉና በኤልያስ ኋላ የቀሩ ናቸው ለማለት እንችላለን ከነዚህ የቃሉ እውነቶች የምናስተውለው ነገር ብዙ ሰዎች እንደ ሰማርያይቱ ሴት ኢየሱስን እንደ ነቢይ ቆጥረው ኢየሱስን ነቢይ ነህ ቢሉም አንዳንዶች ደግሞ
መጥምቁ ዮሐንስ ፣ ኤርምያስ ወይንም
ከነቢያት አንዱ ነህ ሲሉ ይስተዋላሉ ሌሎች ደግሞ ፍጹም ግንዛቤ በሌለበት ስሕተት ውስጥ ተዘፍቀው ኢየሱስን ከነቢያት ሳይቀር በማሳነስ የነቢያት እርዳታ እንደሚያሻው ያስባሉ ታድያ እነዚህ አባባሎች በሙሉ ለኢየሱስ የሚሰጡና እየሱስን የሚወክሉ አይደሉም ኢየሱስ በሰውነቱ ነቢይ ፣ ካህንና ንጉሥ ሆኖ የነቢይነትን የካህንነትንና የንጉሥነትን ሥራ ቢሠራም የአብ የባሕርይ ልጁ ሆኖ ለዘላለም የሚኖር እውነተኛ አምላክ ነው ይንንም አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱሳችን ተጨባጭ የሆነ ማስረጃ ይሰጠናል በዕብራውያን 1 ፥ 1 ላይ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል ስለዚህ ኢየሱስ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ የባሕርዩ ምሳሌና የክብሩም መንጸባረቅ ስለሆነ ከነቢያት ይበልጣል ከመላእክትም ይበልጣል ቃሉ መፍጠርና ማዳን የሚችል የሥልጣን ቃል ነው እንደገናም ኃጢአታችንን በራሱ አንጽቶ በሰማያት በግርማው ቀኝ የተቀመጠ ነው ስለ መላእክትና ስለ ልጁም ያለውን ልዩነት ሲናገር ከመላእክትስ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥ ደግሞም፦ እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማን ነው ? ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል ስለ መላእክትም መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ ይላል፤ ስለ ልጁ ግን አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትሕ በትር የቅንነት በትር ነው መላእክት ከእግዚአብሔር የተወለዱ የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም ለእግዚአብሔር የሚሰግዱ የእሳት ነበልባል የሆኑ የእግዚአብሔር አገልጋዮች መናፍስት ናቸው ኢየሱስ ግን አብ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው የአብ የባሕርይ ልጁ ነው እንደገናም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ ይላልና ቃሉ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው ከዚህ ሌላም ዙፋኑ እስከ ዘላለም ድረስ የሆነ የመንግሥቱም በትር የቅንነት በትር የሆነ ሕያውና ዘላለማዊ አምላክ ነው ታድያ እንዲህ ዓይነቱን አምላክ በነቢያት ተርታ መድቦ ነቢይ ብቻ ነው ፣ ከነቢያት አንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ኤርምያስና የመሳሰሉት ነው ወይንም ደግሞ ከነቢያት ሳይቀር በማሳነስ አምላኬ አምላኬ ብሎ አባቱን ጠርቶ ሳለ ኤልያስን ይጠራልና ኤልያስ መጥቶ ያድነው ማለት ፍጹም ስሕተትና መንፈሳዊ ዕውርነትም ነው እግዚአብሔር የልቡና ዓይኖቻችንን ያብራልን ብዙ ሰዎች መሲሁ ኢየሱስ መሥዋዕት የሆነበትን ሕይወት በትክክል ካለመረዳት የተነሳ ዛሬም ኢየሱስን ከኤርምያስ ከኤልያስና ከመሣሠሉት ነቢያት ጋር በማወዳደር ኤልያስን ይጠራል ኤልያስ መጥቶ ያድነው የሚሉ በኤልያስና በመሣሠሉት ነቢያት ጀርባ ያሉ ሰዎች አይጠፉም ታድያ እነዚህ ሰዎች ለመዳናቸው ሳይቀር ተስፋቸው ነቢያት ፣ መላእክት ጻድቃን ፣ ቅዱሳንና ድንግል ማርያም ጭምር ናቸው መላእክትን በተመለከተ በዕብራውያን 1 ፥ 14 ላይ
ከቶ ለማን ብሎአል ? ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን ? ስለሚለን መላእክት የሚያድኑ ሳይሆኑ ሰዎች ሁሉ ይድኑ ዘንድ ለማገዝ የሚላኩ ናቸው ጻድቃን ቅዱሳንን በተመለከተ በ2ኛ ቆሮንቶስ 5 ፥ 18 _ 20 መሠረት
ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን ሲሉ እንመለከታለንና እግዚአብሔር ከራሱ ጋር ያስታረቀን በክርስቶስ ነው እርሱ በታረቀን በክርስቶስ በኩል የክርስቶስ መልዕክተኞች ሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለው ይሰብኩናል ወይም ይነግሩናል እንጂ እነርሱ ራሳቸው ከእግዚአብሔር ጋር አያስታርቁንም ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቀን ኢየሱስ ብቻ ነው ከዚህም የተነሳ ነው ሐዋርያው በክርስቶስ በኩል ሙሉ የሆነ መታረቅን ከእግዚአብሔር ጋር ስላገኘ ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን ሲል የተናገረው ሮሜ 5 ፥ 10
እና 11 እናንብብ ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ለጳውሎስ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ለእኛ መታረቅን ያገኘንበት ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር እንድንመካ የሆንበት አስደናቂ ጌታችንና ባለውለታችንም ነው ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ጌታ እያለን ለደህንነታችን ለምናገኘውም የዘላለም ሕይወት በነቢያቱ በመላእክቱ በጻድቃን ቅዱሳን በድንግል ማርያም በምንላቸው ጀርባና ኋላ መሆናችን እጅግ የሚያሳዝን ነው ይህ አልበቃ ብሎን ደግሞ ከእነርሱ ጀርባ ሆነን በስማቸውም ተጓደን ዝክር እናዘክራለን አሻሮ እንቆላለን ጸበል ጻዲቅ እናዘጋጃለን የማናደርገው ምንም ነገር የለም መዳን ግን በዚህ አይገኝም ለዚህም ነው እንግዲህ የአርጋኖን መጽሐፍ ይህንን እውነት ተረድቶ ከኤልያስ ጋር በማነጻጸር ኤልያስ በእሳት ሠረገላ ወደ ብሔረ ሕያዋን ቢሻገርም ከራሱ አልፎ ማንንም ሊያሻግር አልቻለም ከአንቺ የተወለደው ክርስቶስ ግን መሐይምናንን ማለት በስሙ ያመኑትን አማኞችን ከሞት ወደ ሕይወት አሻገረ ካለማወቅ ወደ ማወቅ አመጣቸው በማለት የተናገረን ወገኖቼ ይህንን ትምህርት ገና የጀመርኩትና ሃሳቡንም ያልቋጨሁት ያልደመደምኩት ክፍል ሁለትና ሦስት እያለ የሚቀጥል በመሆኑ እዚህ ላይ ለጊዜው እቋጨዋለሁ ቀጣዩን የክፍል ሁለት ማብራርያ በሰፊው እንደሚገባ እስካቀርበው ድረስ ሰላም ሁኑልኝ እያልኩ የምሰናበታችሁ
ቀሲስ አባ ዮናስ ነኝ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
ወይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ
የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ
No comments:
Post a Comment