Friday, 5 December 2014

ሃይማኖተ አበው



ሃይማኖተ አበው

እኛስ ጋብቻ ንጹሕ እንደሆነ መዋለድም ርኲሰት እንደሌለበት እንናገራለን እግዚአብሔር ሕዝቡ ይበዙ ዘንድ አዳምንና ሔዋንን ፈጥሮአቸዋልና

የተወደዳችሁ ወገኖቼ ዛሬ ደግሞ የምንማማርበት ሃሳብ Joshua Breakthrough Renewal Teaching and
Preaching Ministry
በሚለው አገልግሎት ዙርያ ለአማኞችና ለአገልጋዮች የሚሆን ትምህርት ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ኦርቶዶክስን ወደ ጥንተ መሠረቷ ወደ እግዚአብሔር ቃል እውነትና ወደ ወንጌል ሃሳብ እንድትመለስ የሚያስችሉ መሠረታዊ የእግዚአብሔር ቃል እውነቶች በተለያዩ መጻሕፍቶችዋ ላይ ሠፍረው ስላሉ እነዛን እውነቶች ከእግዚአብሔር ቃል ጋራ በማገናኘትና በማመሳከር የተለያዩ ትምህርቶችን ማቅረባችን ይታወሳል አሁንም እንደሚከተለው እናቀርባለን ይህንን ትምህርት መከታተል ለምትፈልጉ ሁሉ ይህ አገልግሎት የኔ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ሁላችሁንም የሚመለከት አገልግሎት ስለሆነ የዚህ አገልግሎት ተባባሪና ደጋፊ በመሆን አገልግሎቱ ለብዙዎች እንዲደርስ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ማድረግ የምትችሉ መሆናችሁን ከወዲሁ ላሳስብ እወዳለሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ
ዛሬ የምንመለከተው አሁንም በቀጣይነት ሃይማኖተ አበው በተባለው አንጋፋ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ላይ የሠፈሩ አስደናቂ የሆኑ የእግዚአብሔር ቃል ሃሳቦች ሲሆኑ ከእነርሱም መካከል በቀጣይነት ልንማማርበት ያዘጋጀነውን ሃሳብ በስፋት ልንማማርበት እንመለከተዋለን ሃሳቡ እንዲህ የሚል ነው
የሐዋርያት አመክንዮ በአማርኛ
ምዕራፍ 7 ቁጥር 17
ወንሕነሰ ንብል ከመ ሰብሳብ ንጹሕ ወልደት ዘአልቦ ርኩስ እስመ ፈጠሮሙ
እግዚአብሔር ለአዳም ወለሔዋን ከመ ይብዝኊ ሕዝብ
ትርጉም እኛስ ጋብቻ ንጹሕ እንደሆነ መዋለድም ርኲሰት እንደሌለበት
እንናገራለን እግዚአብሔር ሕዝቡ ይበዙ ዘንድ አዳምንና ሔዋንን
ፈጥሮአቸዋልና
የተወደዳችሁ ወገኖች የዚህ ትምህርት ተካፋዮች የሆናችሁ በሙሉ ይሄ የሐዋርያት አመክንዮ የቤተክርስቲያኒቱን መሠረተ እምነት የሚገልጽ ቤተክርስቲያኒቱ የእምነቴ መግለጫ ነው ብላ አንቀጽ በአንቀጽ ካሰፈረችው ክፍል የተወሰደ ነው ቤተክርስቲያኒቱም ለሰዎች የምታሳየው የምታስተምርበት አንዱና ዋናው ክፍል ይሄ ነው የቤተክርስቲያኒቱ ዶግማ ወይም ዶክትሪን ነው ተብሎም ይነገርለታል እንግዲህ የቤተክርስቲያኒቱ የእምነት መግለጫና ዶክትሪኑም ይሄ ከሆነ በዚሁ በሐዋርያት አመክንዮ በተጻፈው ቃል ምክንያት ቤተክርስቲያኒቱም እኛስ ጋብቻ ንጹሕ እንደሆነ መዋለድም ርኲሰት እንደሌለበት እንናገራለን እግዚአብሔር ሕዝቡ ይበዙ ዘንድ አዳምንና ሔዋንን ፈጥሮአቸዋልና በማለት በእምነት መግለጫዋ ላይ ባሠፈረችው ቃል መሠረት እንናገራለን ብላለችና የጋብቻንና የመዋለድን ንጽሕና የምትናገር ከሆነ በቤትዋ ውስጥ የነበሩ ባሕታውያንና መነኮሳት የጋብቻን ቅዱስነትና ክቡርነት እንደ መጽሐፍቅዱሱ ቃል አውቀው ሲያገቡና የአንዲት ሚስት ባል ሲሆኑ ለሴቶችም ደግሞ የአንድ ባል ሚስት ሲሆኑ መቃወሟ ለምን ይሆን ? እንደገናም ይህንን ቅዱስ ጋብቻ መቃወሟ እራሷ የእምነቴ መግለጫ ነው ሰዎችን አስተምርበታለሁ ብላ የነደፈችውን የእምነት መግለጫ በሌላ መንገድ እየተቃወመች መሆኗን ሳትገነዘብ ቀርታ ይሆንን ? መጽሐፉም እኮ የሚለው እንዲህ ነው በግዕዙ ቃል እንዲህ ይላል ወአእሚሮ እግዚእ ኢየሱስ ሕሊናሆሙ ይቤሎሙ ኲላ መንግሥት እንተ ትትናፈቅ በበይናቲሃ ትማስን ወኢትቀውም ወኲላ ሀገር ወእመሂ ቤት እንተ ትትናፈቅ በበይናቲሃ ኢትቀውም ትርጉም ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው፦ እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፥ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም የማቴዎስ ወንጌል 12 25 ስለዚህ ሰው ራሱን ከራሱ ጋር በተቃውሞ ካቆመ መጨረሻው መጥፋት ነው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናችንም በተለይ የጥንቷ ሐዋርያዊትዋና ኦርቶዶክሳዊትዋ ሳትሆን የአሁንዋ እየተቃወመች ያለችው እናገረዋለሁ ብላ በእምነት መግለጫዋ ላይ ያሰፈረችውን የጋብቻንና የመዋለድን ቅዱስነት የሚያበስረውን ዶክትሪንዋን ነው እንጂ በቅድስና በመጽሐፍቅዱሱ ቃል መሠረት እያገቡ ያሉትን ባሕታውያንና መነኮሳትን ብቻ አይደለም ከራስ ጋር መጣላት ራስን መቃወም ደግሞ በራስ ላይ ጥፋትን ያመጣልና በጣም ከባድ ነገር ነው እንደገናም ሌሎችን ለመርታት ስንል ለምንሰጠው መልስ እራሳችን በገዛ መጽሐፋችን ከምንረታ በስተቀር መልስ የለንም ሌላው ደግሞ ጋብቻ ቅዱስ ሆኖ ሳለ መዋለድም ርኲሰት እንዳልሆነ ተነግሮና በጽሑፍም ሠፍሮ ሳለ ሰዎች ከጋብቻ ተከልክለው እስከመጨረሻው ላይዳሩ ላይኳሉ ላያገቡ ላይጋቡ ላይዋለዱ ቃል ኪዳን ገብተው ባሕታዊ እንዲሆኑ እንዲመነኩሱም ማድረግ እንደ ቤተክርስቲያኒቱ የእምነት መግለጫ ማለት እንደ ሐዋርያት አመክንዮ እንደ እግዚአብሔር ቃልም ስንመለከተው ፍጹም ስሕተት ነው ሰዎች በዚህ በብሕትውናና በምንኩስና ሥርዓት ሄደው እንዲመነኩሱ የሚያነሳሱ መጻሕፍት ተጽፈዋል እነዚህም መጻሕፍት 1 ፊልክስዩስ 2 አረጋዊ መንፈሳዊ 3 ማር ይስሐቅ የሚባሉ መጻሕፍት ናቸው ለብሕትውናና ለምንኲስና ሥርዓት ለመዘጋጀት እነዚህን መጻሕፍት እያጠና ላለ ሰው መጽሐፍቅዱስ እንዲያነብ አይመከርም ይህ የሚደረገው ይህ ሰው መጽሐፍቅዱስን ካነበበ የሚሆነው ነገር ስለሚታወቅ ነው እነዚህ ሦስቱ በሦስት ክፍል መጻፋቸው ለጀማሪ ለወጣኒና ለፍጹማን እንዲሆኑ ተደርገው የተጻፉ በመሆናቸው ነው በነዚህ መጻሕፍት ውስጥ በጥቂቱ ከሠፈሩ ሃሳቦች መካከል ኢትርአይ ገጻ ወኢትስማዕ ድምፃ ለአንስት የሚሉ ቃሎች ተጽፈዋል ስንተረጉመው የሴትን ፊትዋን አትይ ድምጿንም አትስማ የሚል ትርጉምን የያዘ ነው ይህ ብቻ አይደለም የሰራችውንም አትብላ የሚል ቃልም አለበት ከዚህም ሌላ የጣፈጠ ምግብ አትብላ ለቁመተ ሥጋ ብቻ አንድ ጊዜ ብላ የሚል ቃልም ተጽፎበታል በመጨረሻም መኝታም እንኳ እንዳይኖረውና ሰንሰለት ታጥቆ ጤዛ ልሶ ድንጋይ ተንተርሶ በመኖር አሥሩ ማዕረግ ላይ እንዲደርስ ሥላሴንም በልዕልና አይቶ እንዲነጠቅ ለማድረግ እነዚህ ሦስቱ መጻሕፍት የተቻላቸውን ያክል በብዙ ይመክራሉ በነዚህ መጻሕፍት ተመክረው ገዳምም ገብተው ከመነኮሱት መካከል አንዱ እኔ ነኝ ጌታ ኢየሱስ ሕይወቴን አግኝቶ እስከ ለወጠውና የራሱም እስካደረገኝ ድረስ ሕይወቴ በነዚህ ነገሮች ውስጥ በብዙ አልፎአል ከአባነቴና ከባሕታዊነቴም ባሻገር ለመጽደቅ ብዬ ያልሆንኩት ነገር የለም ሰንሰለት በሰውነቴ በውስጠኛው ክፍል ላይ ታጥቄያለሁ ሰሌን ላይ ተኝቻለሁ የጣፈጠ የጣመ ምግብ አልበላም ነበር ማለት ምግቤ ብዙውን ጊዜ ጥራጥሬ ነበር ከጋብቻ ተከልክዬ ከሴት ርቄ ለዓመታት ኖሬያለሁ ማለትም ሴቶች እህቶችን ሳይ የሚያረክሱኝ እየመሰለኝ በብዙ ማይልስ እርቃቸውና እሸሻቸውም ነበር በአጠቃላይ ፊታቸውን አላይም የሠሩትንም አልበላም ነበር ሥላሴንም በልዕልና አይቶ ለመነጠቅም በየገዳማቱ እየዞርኩ ለረጅም ወራት ሱባዔ እገባ ነበር ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ግን ስለወደደኝ በነዚህ ነገሮች እና በሕይወቴ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ነጥቆ ያራሱ አደረገኝ እኔን ያየ አብን አይቷል በማለት አብን ብቻ ሳይሆን መንፈስቅዱስንም ለዘለዓለም አጽናኝ ሆኖ ከእኔ ጋር እንዲኖር ስለሰጠኝ ከራሴ ጽድቅ ሳይሆን ከዚህ ጌታ የተነሳ እርሱ ስላዳነኛና ስላጸደቀኝ ጥንት ልጸድቅ ብዬ በተንከራተትኩበት ወራት ሳይሆን ዛሬ ብቻውን አዳኝ ሆኖ ባጸደቀኝ በዚህ ጌታ ምክንያት ሥላሴን በልዕልና አይቻለሁ ዮሐንስ ወንጌል 14 9 ዮሐንስ ወንጌል 15 26 እና 27 ዛሬ ታድያ በዚህ ጌታ የዳንኩና የጸደቅሁ በመሆኔ ለመጽደቅ ብዬ ከዚህ በፊት በገዳም ውስጥ እንደማደርገው ዛሬ አላደርግም ይህን ስል ስለጸደቅሁኝ ለመጽደቅ ስል ዛሬ ሰንሰለት አልታጠቅም የጣፈጠ ምግብ አልበላም አልልም ባማረ ፍራሽና አልጋ ላይ በማዕረግ ተነጥፈውም ባሉ የተዋቡ አንሶላዎችና ብርድልብሶች እንዲሁም አልጋ ልብሶች ውስጥ ገብቶ መተኛት ኃጢአት አይደለምና አልጋ ላይ አልተኛም ብዬና ከአልጋ ወርጄ እንደቀድሞው ሰሌን አንጥፉልኝ ብዬ ሰሌን ላይ አልተኛም መኖርያዬም የዘላለም አምላክ ሆኖልኛልና ድንጋይ ተንተርሼ ጤዛ ልሼም አልኖርም ሌላ ሌላም ከዚህ በፊት እጸድቅ ብዬ የሆንኳቸውን ዛሬ ላይ እንዳልሆን ኢየሱስ በመስቀል ላይ የኃጢአት ዕዳዬን ከፍሎ በሞቱና በትንሣኤው ስላጸደቀኝ ለመጽደቅ ብዬ የማደርጋቸው ከዚህ በፊት የነበሩ እነዚያ ሁሉ የሥጋ መከራዎችና ድካሞች ዛሬ ላይ የማይታሰቡ ሆነው ለአንዴና ለዘላለም ከእኔ ተወግደዋል ስለዚህ አሁን መጽሐፍቅዱሳችንም ሆነ የሐዋርያት አመክንዮ መጽሐፍ እንዳስተማረን እኔ ዛሬ የዛሬ 9 እና 10 ዓመት ጌታ በክብር ድሮኝ የተከበረችና የተዋበች የአንዲት ሚስት ባል ሆኛለሁ እንደገናም የወንጌል ሰባኪና አስተማሪ ነኝ ቀድሞ ወደነበርኩበት ገዳም ብሄድም እንኳ በዛ ያሉ ሰዎች ለኃጢአታቸው የሞተላቸውን ጌታ አምነው እንዲጸድቁ ይህን የምሥራቹን ቃል ለመስበክ ከምሄድ ውጪ ያጸደቀኝን ጌታ አግኝቼዋለሁና እንደ ድሮው እንደጥንቱ ሰንሰለት ታጥቄና ቢጫ ወይባ ለብሼ ለእግሬም በረባሶ አድርጌ ለመጽደቅ ስል ወደ ገዳም የምሄድ አይደለሁም ክብሩ ለእግዚአብሔር ይሁን ይሄ እንግዲህ ጥቂቱ የሕይወት ምስክርነቴ ነው ወደፊት እንደ አስፈላጊነቱ በሰፊው የምመሰክርበትን ጊዜና ሁኔታ ጌታ ያመቻችልኛል ያኔ በሰፊው እመሰክራለሁ ከዚህም ሌላ እንዲሁ እንደ እኔ ክርስቶስ በሰጣቸው የዘላለም ሕይወት እኔን የሚመስሉ አስደናቂ በሆነ የሕይወት ከፍታም የሚመላለሱ የጋብቻን ቅዱስነት አምነው በሕይወታቸው የፈጸሙ የተገበሩ ብዙ መነኮሳትና ባሕታውያን አሉ ወደፊትም ጋብቻ ቅዱስ ነውና እያገቡ በዚሁ ሰማያዊ ሥርዓት የሚመላለሱ በቁጥር ይህን ያህል ናቸው የማይባሉ መነኮሳትና ባሕታውያን እንደሚኖሩ አልጠራጠርም ትልቁ የማግባታችን ቁም ነገር ሚስት ወይም ባል ስላስፈለገን ወይም ስላማረን ሳይሆን ጌታ ኢየሱስ የሕይወታችን ጌታና አዳኝ ስለሆነ ነው የዳነ ሰው ደግሞ ያዳነውን ጌታ ያውቃልና በጌታ የተፈቀደለትን ነገር ሁሉ ያደርጋል ጌታ ሲያድነንና የዘለዓለም ሕይወት ሲሰጠን ሚስት አታግቡ ወይም ባል አታግቡ ሚስት ወይም ባል ማግባት ኃጢአት ነው አላለንም ከዚህ የተነሳ ነው ሐዋርያው ጳውሎስም ስለ ደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም፥ ነገር ግን የታመንሁ እሆን ዘንድ ከጌታ ምሕረትን የተቀበልሁ እንደ መሆኔ ምክር እመክራለሁ ሲል የጻፈልን 1 ቆሮንቶስ 7 25 _ 28 በሌላኛው ክፍሉ ላይ ደግሞ እንደ የሐዋርያት አመክንዮ አነጋገር የጋብቻን ንጽሕና በመመስከር ክቡር አውስቦ በኲለሄ ወለምስካቦሙኒ አልቦቱ ስእበት ለዘማውያንሰ ወለእለ ያረኲሱ ሥጋሆሙ ይኴንኖሙ እግዚአብሔር አለን ትርጉም መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል ዕብራውያን 13 4 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስኪዳን የሚቃወመው ጋብቻን ሳይሆን አመንዝራነትን ነው እግዚአብሔር የደገፈውን መደገፍ የተቃወመውን ደግሞ መቃወም ትልቁ የክርስቲያኑ ኃላፊነትም ሆነ ግዴታው ሊሆን ይገባል ጋብቻን መከልከል ግን የውሸተኞች ተግባር ስለሆነ ከዚህ አሠራር ፍጹም ልንርቅና እንደ እግዚአብሔርም ቃል ፈጽመን ልንቃወመው የሚገባ መሆኑን ከውዲሁ ላበስር እወዳለሁ በዚህ የውሸት አሠራር ደግሞ ተጠልፈው በሜዳ የቀሩ በጣም ብዙ ሰዎች እንዳሉ ለሁላችንም ግልጽ ነው 1 ጢሞቴዎስ 4 3 ታድያ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎችን እኛ የበራልን ሰዎች አግኝተን በጌታ ቃል ልናክማቸውና አስተሳሰባቸውን ልንፈውስ ይገባል ወገኖቼ ጌታ ዘመናችሁን ይባርክ እነዚህን ቃሎች እንግዲህ በማስተዋልና በቅን ልብ ሆናችሁ ለመጠቀምና በቃሉም ፍሬ ለማፍራት በሚሆን ክብር አንብቧቸው ደግማችሁ እና ደጋግማችሁም አጥኗቸው ያን ጊዜ ጌታ እግዚአብሔር በቃሉ እውነትና መረዳት ይባርካችኋል የምናነበውን ቃል እንድናስበው እንድናሰላስለውና እንድንጠቀምበት ጌታ ይርዳን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment