Friday, 5 December 2014

መጽሐፈ አርጋኖን ክፍል ሦስት



መጽሐፈ አርጋኖን


ክፍል ሦስት


በክፍል ሁለት ትምህርታችን ላይ ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር የተነጻጸረበትን ከእግዚአብሔር ቃል እውነት ጋር በማስተያየት የመጽሐፈ አርጋኖንን ጽሑፍ ተንተርሰን አይተናል በክፍል ሦስት ትምህርታችን ላይ ደግሞ ኤልሳዕ  ከኢየሱስ ጋር የተነጻጻረበትን ሃሳብ ከእግዚአብሔር ቃል እውነት ጋር በማስተያየትና ይህንኑ የእግዚአብሔር ቃል መረጃ በማቅረብ በዚሁ በመጽሐፈ አርጋኖን የተጻፈውን ክፍል መነሻ አድርገን እንነጋገራለን መጽሐፉ እንዲህ ይላል ኤልሳዕ ንዕማንን ከለምጹ እንዲድን ከማድረግ አንስቶ ብዙ ተአምራትን አሳየ መራራውንም ውሃ በጨው አጣፍጦ መካኖች ሴቶች እንዲወልዱ አደረገ አልጫ የሆኑትን ነፍሳት ግን ጣዕም እንዲኖራቸው ለማድረግ አልተቻለውም ክርስቶስ ግን የሥጋንና የነፍስን ለምጻሞችን አነጻ እያለ ይዘረዝራል መጽሐፉ እንዳለው ኤልሳዕ ንዕማንን ከለምጹ እንዲድን ከማድረግ አንስቶ 2 ነገሥት ምዕራፍ 5 በሙሉ መመልከት እንችላለን ብዙ ተአምራትን አድርጓል  ከተአምራቶቹም መካከል ጥቂቶቹን መጥቀስ ቢያስፈልግ ለነገሥታትና ለከብቶቻቸው የሚሆን ውሃ መጥቶ ሸለቆው በውሃ የሞላው በኤልሳዕ ትንቢታዊ ቃል ነው አሁንም 2 ነገሥት ምዕራፍ 3 በሙሉ እንመልከት የእስራኤል ጠላቶች የሆኑ ሶርያውያንን በጸሎቱ እንዲታወሩና በመጨረሻም ዓይናቸው እንዲገለጥ አድርጎአል 2 ነገሥት ምዕራፍ 6 ከቁጥር 8 እስከ መጨረሻው መመልከት ይቻላል የአህያ ራስና የርግብ ኩስ በሚሸጥበት በሰማርያ ኤልሳዕ ባመጣው የመገለጥ ቃል እህል ተሸምቶአል 2 ነገሥት 6 24 _ ፍጻሜ ምዕራፍ 7 1 _ 20 እነዚህና የመሣሠሉት ዋና ዋና ኤልሳዕ ያደረጋቸው ተአምራቶች ሲሆኑ ከዚህ በተጨማሪም የመጽሐፈ አርጋኖን ጸሐፊ እንደተናገረው በኢያሪኮ ያለውንም ምድሪቱ ፍሬዋን እንዳትሰጥ የሚያጨነግፈውንም ውሃ አዲስ ማሰሮ አምጡልኝ ጨው ጨምሩበት………….ይህን ውኃ ፈውሼዋለሁ ከዚህም በኋላ ሞትና ጭንገፋ አይሆንበትም በማለት ስለተናገረ ኤልሳዕ እንደተናገረው ነገር ውኃው እስከ ዛሬ ድረስ ተፈውሷል 2 ነገሥት 2 15 _ 22  በሚመጣው ዓመት በዚህ ወራት ወንድ ልጅ ትታቀፊያለሽ ባላት መሠረት ሱናማዊቷ ሴት ወንድ ልጅ ታቅፋለች 2 ነገሥት 4 8 _ 37  ነገር ግን አሁንም የአርጋኖን መጽሐፍ እንደነገረን ኤልሳዕ ይህንንና የመሣሠሉትን ተአምራቶች ያድርግ እንጂ የነፍሳት ሕይወትን ማለት አልጫ አልጫ የሚለውን የሰዎችን የውስጥ ሕይወት ጣዕም እንዲኖረው ለማድረግ አልተቻለውም በኤልሳዕ አገልግሎት የንዕማን የሥጋ ለምጽ ቢፈወስም በክርስቶስ አገልግሎት  ግን የሥጋም ሆነ የነፍስ ለምጽ ተፈውሷል የሚለው ሃሳብ ትክክለኛ እና የሚታመንም ሃሳብ ነው ወገኖቼ በብሉይ ኪዳን ዘመን በኤልሳዕ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ነቢያት የተለያዩ ተአምራቶች ቢደረጉም የሰው ልጅ ግን ውጪያዊው ደዌ ብቻ ሳይሆን ውስጣዊው ደዌ ጭምር ተፈውሶ አልጫ የሆነው ሕይወቱ ጣዕም አግኝቶ በዘላለም የእግዚአብሔር የኪዳን መንግሥት ውስጥ እንዲኖር የሚያስችለውን መሲህ አላገኘም ነበር  ስለዚህም መሲሁ ኢየሱስ ይህንን ለመስጠት ወደ ምድር ወደ እኛ መጣ መጽሐፍቅዱሳችን በግዕዙ ቃል እንዲህ ይላል ሠናይ ውእቱ ጼው ወእመሰ ጼው ለስሐ በምንት እንከ ይቄስምዎ አኮኑ ይገድፍዎ አፍአ ውስተ መሬት ዘቦ እዝን ሰሚአ ለይስማዕ ትርጉም ጨው መልካም ነው፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፈጣል ?  ለምድር ቢሆን ለፍግ መቈለያም ቢሆን አይረባም ፤ ወደ ውጭ ይጥሉታል የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ ይለናል የሉቃስ ወንጌል 14 33 እና 34 ይህ ቃል የራሱን የቃሉን ትርጉም ከመያዙም ባሻገር የሰዎችንም ሕይወት ያስታውሰናል የሰው ልጅም ሕይወት ጨው ሲኖረው መልካም ነው ለምን ? ስንል ጨው ያለው ሕይወት ሲኖረን ጣፋጭነታችንም በዚያው ልክ የበዛ ይሆናል አልጫ ሕይወት ሲኖረን ግን  የማንጣፍጥ ነንና ወደ ውጪ ከምንጣል በስተቀር ለምንም አንሆንም ሕይወታችን ኢየሱስን አግኝቶ ከመጣፈጡ በፊት እንዲህ ነበር አልጫነት ያለበትና የማይጠቅም በመሆኑ ወደ ውጪ የተጣለ ፤ ኢየሱስ ሲመጣ ግን የተጣለው ሕይወታችንና የማይጠቅመው እኛነታችን ተነሳ አልጫ የሆነው ውስጣዊ ሕይወታችንም ጣፈጠ ስለዚህ ዛሬ በዚህ ጌታ ሕይወታችን ለሰዎችም  ፣ ለእግዚአብሔርም ሳይቀር የጣፈጠ ስለሆነ ይኸው ከማጉረምረም ከምሬትና ከሐዘን ሕይወት ወጥተን በደስታ እንኖራለን ሁልጊዜም በጌታ ደስ ይለናል ፊልጵስዩስ 4 ፥ 4  ኢየሱስ ውስጣዊ ሕይወታችንን ብቻ ያጣፈጠ ሳይሆን በኃጢአት በሽታ የተመታውን  ሕመማችንን ፣ ደዌያችንንና ለምጻችንን ሳይቀር ፈወሰ ለዚህ ነው ኢሳይያስ በትንቢቱ የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን ያለን  ኢሳይያስ 53 3 _ 5 ከኢየሱስ ውጪ ይህንን ሊያደርግ የሚችል ማንም የለም ለዚህ ነው የመጽሐፈ አርጋኖን ጸሐፊ ግልጽ አድርጎ ኤልሳዕ ንዕማንን ከለምጹ እንዲድን ከማድረግ አንስቶ ብዙ ተአምራትን አሳየ መራራውንም ውሃ በጨው አጣፍጦ መካኖች ሴቶች እንዲወልዱ አደረገ አልጫ የሆኑትን ነፍሳት ግን ጣዕም እንዲኖራቸው ለማድረግ አልተቻለውም ክርስቶስ ግን የሥጋንና የነፍስን ለምጻሞችን አነጻ  በማለት የነገረን ስለዚህ በዚህ አሠራሩ ኢየሱስ ከማንም ጋር አይነጻጸርም ደግሞም አናወዳድረውም እርሱ አልጫ የሆነውን ለማንም ሊቀመስ የማይፈለገውን  ውስጣዊው ሕይወታችንን በማጣፈጥ ብቸኛ ነው ከእርሱ በቀር ደዌያችንን ሕመማችንንና ቁስላችንን የፈወሰ ማንም የለም ስለዚህ ጉዳይ እኛ ግን ሳይገባን ቀርቶ እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረ ብንቆጥረውም እርሱ ግን ስለመተላለፋችን የቆሰለ ስለ በደላችንም የደቀቀ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ የነበረ በእርሱም ቁስል እኛ የተፈወስን ስለሆንን በእርግጥም ደዌን የሚያውቅ ነው ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው ዛሬም ቢሆን ከእርሱ በቀር ደዌያችንን የሚያውቅልን የለም እነኤልሳዕ ፣ እነኤልያስ ፣ ኤርምያስ ከነቢያት አንዱን ብንጠራ ከሐዋርያትም መካከል ብንፈልግ  በዘመናችንም ጌታ ያስነሳቸውን ሰዎች ብንጠቀም ጌታ በሰጣቸው ጸጋ ስሙን ጠርተው በስሙ ውጪያዊውን ደዌያችንን ሊፈውሱ ይችላሉ በአባታችን በአዳም ኃጢአት ምክንያት የመጣውን  የውስጥ ደዌና ሞት አውቆ ሊፈውስ የሚችል ግን ኢየሱስ ብቻ ነው ለዚህም ነው በብዙዎች የሕግ መምሕራንና የመቅደስ አዛዦች ፊት ሳያንገራግር ፣ ሳያቅማማ ፣ ማንንም ሳይጠብቅና ምንም ሳይል በግዕዙ ቃል እንዲህ ይላል ወይቤላ ለይእቲ ብእሲት ተኀድገ ለኪ ኃጢአትኪ ትርጉም እርስዋንም ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል አላት የሚለን የሉቃስ ወንጌል 7 48 በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 9 6 ላይ ደግሞ በግዕዙ ቃል እንዲህ ይላል ከመ ታእምሩ ከመ ብዉሕ ሎቱ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይኅድግ ኃጢአተ በዲበ ምድር ወእምዝ ይቤሎ ለውእቱ መፃጒዕ ተንሥእ ወንሣእ ወፁር ዓራተከ ውእቱ ቤተከ ወተንሢኦ ነሥአ ዓራቶ ወሖረ ቤቶ ትርጉም ነገር ግን በምድር ላይ ኃጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፥ በዚያን ጊዜ ሽባውን ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትሕ ሂድ አለው ተነስቶም ወደ ቤቱ ሄደ ይለናልና ይህንን ያደረገው ከዚህ የተነሳ ነው ከዚህም  ሌላ ሸክማችንን አውቆ ሊያቀልልን እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና ሲል ጥሪ አስተላልፎልናል የማቴዎስ ወንጌል 11 28 _ 30 በመሆኑም ድካማችንን አውቀን ጌታችን ከማንም ይልቅ ደዌያችንንን የሚያውቅልን  መሆኑን ተረድተን በነቢያቱም ሆነ በጻድቃን ሰማእታት ምልጃ ሥርየት እናገኛለን ብለን ከምናስበውና ከምንደክምበት ይልቅ  እርሱ ሥርየትን ሊሰጠን ከነድካማችን የጠራን መሆኑን  በመረዳት ወደ እርሱ ብንመጣ አሁኑኑ ይህን የምንፈልገውን የኃጢአት ሥርየት በኢየሱስ እናገኛለን የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል 1 ዮሐንስ 1 7 ከዚህ የተነሣ ነው እንግዲህ እግዚአብሔር በዘመናችን ቀብቶ ያስነሳት የጉባኤ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ዘማሪ ዘማሪት አዜብ መለሰ በሚገርም ሁኔታ ዋስ ጠበቃዬ ካህኔ ኢየሱስ የነፍስ አባቴ ኢየሱስ የነፍስ አባቴ የሐዲስ ኪዳን ልጅ ነኝ ልጅ ነኝ ልጅ ነኝ የተሻለ ካህን አለኝ የተሻለ ኪዳን አለኝ ስትል የዘመረችልን ጌታ አብዝቶ ይባርካት ጸጋውንም ይጨምርላት እንላለን  በእርግጥም ኢየሱስ ዋስ ጠበቃ ነው የጊዜው ነፍስ አባቶች ቅር ቢላቸውም ሸክምን ሊያቀልል ለኃጢአትም ሥርየት ሃምሳና መቶ ፣ ሁለት መቶ ስገድ እያለ በወይራ ቸብችቦ በቀላሉ የማይለቅ እውነተኛው ነፍስ አባት ኢየሱስ ብቻ ነው የኦርቶዶክስ ምዕመናንና ካህናት በሚጠቀሙበት መልክአ ኢየሱስ በሚባለው  የጸሎት ድርሰት ውስጥም  ሰላም ለመላትሂከ በማለት ይጀምርና ኢየሱስ ክርስቶስ እስመ አበ ነፍስየ አንተ በሎሙ ለመላእክት ተፈስሑ ሊተ ረከብክዎ ለወልድየ በከንቱ ዘሞተ ይለናል ስንተረጉመው ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ አንተ የነፍስ አባቴ ነህ በከንቱ የሞተውን ልጄን አግኝቼዋለሁና መላዕክት  ደስ ይበላችሁ ማለትን የሚያመለክት ነው ጠፍቶ በተገኘው ንስሐም በሚገባው በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ታላቅ ደስታ አለና የሉቃስ ወንጌል 15 3 _ 7 መጽሐፈ አርጋኖንም ለዚህ ነው ብዙ ተአምራትንም ካደረገው ፣ መካንን ካስወለደው ፣ የጨነገፈውንም ውሃ ከፈወሰው ከኤልሳዕ ይልቅ የሚሻለውንና የተሻለንን ኢየሱስን ሊያሳየን የፈለገው እርሱ ስንመጣ ሁሉም ነገር በዚሁ ጌታ የተፈጸመልን በመሆኑ ከእኛ የሚፈለገው እውነተኛው  የኃጢአት ኑዛዜያችን  ነው ኃጢአታችንን በምንናዘዝበት ጊዜ ደግሞ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ስለሆነ ኃጢአታችንን ሁሉ ይቅር ይለናል እንግዲህ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን በእግዚአብሔርም ቤት ላይ የሆነ ታላቅ ካህን ስላለን መንገዱ ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ መቅረብ ነው ዕብራውያን 10 19 _ 22 ጌታ በዚህ ቃል ሁላችንንም ይባርከን


ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን


ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment