Sunday, 7 December 2014

የባልና የሚስት የግንኙነት ምስጢር ክፍል ሁለት



የባልና የሚስት የግንኙነት ምስጢር

ክፍል ሁለት

በክፍል አንድ ትምህርታችን ላይ ሰዎች ወደዚህ የጋብቻ ሕይወት በብዙ መንገድ እንደሚመጡ ከሚመጡበትም አንዱ መንገድ በሥጋ ፈቃድ ውስጥ እየተገለጠ ባለ የዓይን አምሮት ውስጥ እንደሆነ ይህ ሁኔታ ደግሞ ወደከፋ ነገር ውስጥ እንደሚወስድና ሌሎች ሌሎችንም ሃሳቦች በማከል ጨምረን በሰፊው ማብራራታችን ይታወሳል ዛሬ ደግሞ ከዚሁ የቀጠለውን ሃሳብ እናያለን ከሁኔታዎች የተነሳም ይሁን ከዓይን አምሮት የሚመጣ ፍቅር ያልቃል ትላንት በነገሮች ተነስተን ወይም በዓይን አምሮት ተይዘን ባገባነው ሰው ወይም ባገባናት ሴት ምክንያት ወደድናችሁ ሞትን ተቀበርን እንዳንቺ እንዳንተ ያለ አላየንም በማለት ጨርቃችንን እስክንጥል ድረስ ክንፍ እንድንል ያደረጉን ነገራቸው በነገው ሕይወታቸው ተቀይሮ ስናይ የምንለው ነገር ለሁላችንም ግልጽ ነው አንዳንዶቻችን የጌታ ነገር ስለገባን አይደለም የመልክ የውበት የኃብትና የመሳሰሉት ነገሮች መቀየር በሰው ሕይወት ላይ የሚደርስ አስከፊ ነገር እንኳ ቢመጣ በትላንቱ የፍቅርና አብሮ የመኖር አቋማችን ሳይለውጥ በዚያው እንደሚቀጥል የታመነና የታወቀም ነገር ነው ይሁን እንጂ ታድያ ለአብዛኞቻችን ይህ የትላንቱ ያማረውና ልባችንንም የረታው ነገር በዛሬው የሕይወት ውጣ ውረድ በመለወጡ ምክንያት እኛም ነገሩ ሳይዋጥልን ቀርቶ አቋማችንን የምንለውጥ ደግሞ ብዙዎች ነን የኢዮብ ሚስት ኢዮብ በነበረው በትላንት መልካም ኃብቱና ባለጸግነቱ ተደስታ የተከበርከው ባሌ ስትል ሁሉ ከሞላለትና ካማረበት ከባለጸጋው ኢዮብ ጋራ ተስማምታና አብራ በደስታ ትኖር ነበር ነገር ግን የኢዮብ ነገር እንደነበረ አልቀጠለምና ኢዮብ በፈተና ኃብቱና ንብረቱ በወደመ ጊዜ ልጆቹንም በሞት ምክንያት ባጣቸው ሰዓት ይህም ብቻ አይደለም ኢዮብ ራሱ ገላው ሳይቀር በቁስል በተመታ ጊዜ እግዚአብሔርን ከመባረክ በስተቀር በዚህ ሁሉ ኢዮብ አልበደለም ለእግዚአብሔርም ስንፍናን አልሰጠም ይለናል ቃሉ የኢዮብ ሚስት ግን ከኢዮብ በተቃራኒው ነበረች የኢዮብ ቁስል እርሷም ላይ ደርሶ እንዲህ ያለችና የተናገረች ቢሆን ኖሮ እንደ ቃሉ የሆነ ሚዛን የደፋ አስተያየት በኖረን ነበር ነገር ግን የኢዮብ ሚስት በኢዮብ ከደረሰው መከራ ቅንጣቱም እንኳ በእርሷ ላይ አልሆነም በእርግጥም እንደማንኛውም ሰው ልጆችዋ ሞተውባታል ያም ቢሆን ልጆቹ የእርሷ ብቻ ሳይሆኑ የኢዮብም ናቸው ንብረቱም ቢሆን ከኢዮብ ጋር በጋራ ያፈሩት ንብረት ነው እንጂ ለብቻዋ የሆነ ንብረት አይደለም በተረፈ ግን በኢዮብ ላይ እንደሆነው በኢዮብ ሚስት ላይ የመጣ የጤና መታወክና በቁስለትም የመመታት ነገር የለም ታድያ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የኢዮብ ሚስት ከኢዮብ ተለይታ ኢዮብን እስካሁን ፍጹምነትህን ይዘሃልን ? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት ስትል የስንፍና ምክር መከረችው ወገኖች ይህንን በተመለከተ አያይዛችሁ ከግሪኩ የተጨመረውን ቀጣይ ሃሳብ ብታነቡት ደግሞ በጣም ትገረማላችሁ ኢዮብ ግን የሃሳቧ ተባባሪ ሳይሆን በእግዚአብሔርም ላይ በቁጣ ሳይነሳ የገዛ ሚስቱን እንዲህ ሲል ገሰጸ አንቺ ከሰነፎቹ ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን ? አላት በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም ይለናል በመልካም ዘመንማ አይደለም የኢዮብ ሚስት የኢዮብ ባልንጀሮችም እንኳ ሳይቀሩ መልካም ነበሩ ችግሩ ግን ምንድነው በመከራው ቀን ከኢዮብ አጠገብ የቆመ አንድም ሰው አልነበረም ቢያንስ ቢያንስ ግን የኢዮብ ሚስት እንኳ ሙሉ የሆነ የመከራው ተካፋይ ባትሆንም በጥቂቱም ቢሆን ጌታ ባስቻላት ጸጋና የሚስትነትም ፍቅር ካጠገቡ ልትሆን ይገባ ነበር ነገር ግን ያም ሳይሆን ቀርቶ በምትኩ ለባልዋ እግዚአብሔርን ስደብና ሙት የሚል የዓመጽ መልዕክት አስተላለፈች በዚህም እራሷን በኢዮብ ፊት አስገመተች የሚስትነቱንም ክብር አጣች ይህንን ክፍል ይበልጥ ለማጥናት መጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ 1 እና ምዕራፍ 2 መመልከቱ እጅግ ጠቃሚ ነገር ነውና ክፍሉን ሄደን እንድናነበው እጋብዛለሁ ታድያ ዛሬም ብዙ የኢዮብን ሚስት የሚመስሉ ሚስቶችም ሆኑ ባሎች ብዙዎች ናቸው ነገር እስከ ተቃናና እስከ ሰመረ ሁሉም ነገር እስከ ሞላና እስከ ተትረፈረፈ ድረስ እነርሱም ባሉበት ሁኔታ በኑሮአቸው ሰላም ናቸው ደህና ናቸው መልካም ባል ወይም መልካም ሚስት ሆነው አፋቸውን አጣፍጠው የፍቅር ሰዎች መስለው ይኖራሉ አንድ ቀን ግን የፈተና ጊዜ ይመጣና ነገር ዘንበል ሲል ኑሮ ሲጎድል ቤት ሲራቆት ጤና ሲቃወስ እነርሱም የችግሩ ተካፋይ መሆን ሲገባቸው እንደ ኢዮብ ሚስት ችግሩ እነርሱን እንደማይመለከት አድርገው በመቁጠር የስንፍናን ቃል ይናገራሉ ከዚህ ሌላም የራሳቸውን የማምለጫ መንገድ ሲያበጁ መሰላላቸውንም ሲዘረጉ ይታያሉ ይህም አልበቃ ብሎአቸው የትላንቱን ባለውለታቸውን እግዚአብሔርን ሳይቀር ተራግመው የትዳር ባልንጀራቸውንም ለክህደት የሚያነሳሳ ተግባር እንዲያካሂድ ወይም እንድታካሂድ ይነዘንዛሉ በብርቱም ያነሳሳሉ በቤት ውስጥም ያለውን ሰላም ያደፈርሳሉ ለዚህ ነው ትላንት ያማረ የሚመስለውና አቤት ፍቅራቸው ሲያስቀና የሚያስብለው ትዳር ዛሬ ላይ መልኩን ለውጦ እንደባቢሎን ግንብ ተንዶ የምናየው የትዳር መሰረቱ ገንዘብ የፈራ ኃብትና ንብረት ሳይሆን በእውነተኛው በክርስቶስ ፍቅር ላይ የተመሠረተ የጋብቻ ሕይወት ነው ስለዚህ ታድያ ሰዎች አሁንም ያገቡት የትዳር ጓደኛቸውን ሳይሆን ከትዳር ጓደኛቸው ጀርባ ያለውን ኃብት ንብረት ዝና እውቀት ክብርና የመሳሰሉትን ነገሮች ነው በመሆኑም ነገር እንደነበረ መቀጠል በማይችልበት ጊዜ እነርሱም ቶሎ ብለው የራሳቸውን መንገድ አዘጋጅተው ይለያሉ በዚህ ሁኔታቸውም አብራ የምትኖረውን ወይም የሚኖረውን የትዳር ጓደኛን ልብ ክፉኛ በሆነ መንገድ ይሰብራሉ ከዚህም የተነሳ ይህ ሁኔታ ስለደረሰባቸው ይህንኑ ነገር መቋቋም አቅቷቸው በጤናቸው ሳይቀር የተጎዱትንና ከጥቅምም ውጪ የሆኑትን ሰዎች ቤት ይቁጠረው እላለሁ ከዚህም ሌላ እነዚህ ሰዎች ለወዳጅ ለዘመድ ለጓደኛና ይህንን ሁኔታ ለሚያውቅ ሰው ሁሉ ጸጸትና ሰቀቀን ይሆናሉ ለቤተክርስቲያንና ለእግዚአብሔር መንግሥት ሥራም እንቅፋት እየሆኑ ይስተዋላሉ ወገኖቼ እግዚአብሔር ከዚህ ዓይነቱ አሰቃቂ ድርጊት ይጠብቀን መጽሐፍቅዱሳችንን ስናጠና ቤትና ባለጸግነት ከአባቶች ይወረሳሉ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት ይለናል ምሳሌ 19 14 አብዛኛው ሰው ግን መጽሐፉን ገልብጦ ስለሚያነበው አስተዋይ ሚስት አስተዋይ ባል አገባሁ ይላል ታድያ በአብዛኛው አስተዋይ ሚስት ወይም ባል ከእግዚአብሔር ተቀብዬ አገባሁ ሚስትን ያገኘ በረከትን አገኘ ሲል በአፉ ይናገር እንጂ ልብ ብለን ስንመለከተው ያገባው ቤትና ባለጸግነትን ነው ሚስቲቱ ወይም ባልየው የተፈለጉትም ለዚሁ ለቤቱና ለባለጸግነቱ ሲባል ነው ይህ ባለጸግነቱም ሆነ ቤቱ ባይኖር ግን ሚስቲቱም ሆነ ባልየው ፈላጊ የላቸውም ነበር እንዲህ ስል ግን ሚስትን ያገኘ በረከትን አገኘ ከእግዚአብሔር ሞገስን ይቀበላል ስለሚል ቃሉ ምሳሌ 18: 22 በረከት የለም አይገኝም እያልኩ እንዳልሆነ ለሁላችሁም ግልጽ ሊሆን ይገባል በረከት ደግሞ ማቴርያልና ቁሳቁስ ብቻ እንዳልሆነ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው ታድያ የበረከት መንገዱ ሚስት ወይም ባል እንጂ ከእነርሱ ጀርባ እኛ እነርሱን ለማግኘት ስንል ተደብቀን ያየነው ኃብትና ቤት ሀገርንም በተመለከተ አሜሪካና ካናዳ አውስትራልያና የመሳሰሉት አይደሉም አንዳንዱ አሜሪካ ካናዳ እግሩ እስኪገባ ድረስ ሚስት ወይም ባል ያገባል እዚያ ከደረሰ በኋላ ግን እርሷን ወይም እርሱን የት አውቀዋለሁ ? የት አውቃታለሁ ? በማለት ሽምጥጥ አድርጎ ይክዳል ትክዳለች ጉዳዩ ሁሉንም የሚመለከት ነውና የራሱንም ኑሮ ይጀምራል ወይም ትጀምራለች ማለት እንችላለን ስለዚህ በፊቱንም ያገባው ወይም ያገባችው የአሜሪካንን ግሪን ካርድ ወይም የካናዳ ፓስፖርትን ነው እንጂ ባልን ወይም ሚስትን አይደለም ይህ እንግዲህ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነውና እግዚአብሔር ከዚህ ክፋታችን ፈጥኖ ይፈውሰን ከማለት በስተቀር የምለው የለኝም አንዳንዱ ደግሞ ኃብትን ገንዘብን መኪናን ተደብቆ በማየት ባል ወይም ሚስት አገባሁ ይላል ታድያ በመጨረሻም ይሄን የሚፈልገውን ኃብትና መኪና በእጁ ካደረገ በኋላ ቀስ ብሎ ይሸበለላል እርሷም እንዲሁ ትሸበለላለች ይህ እንግዲህ ወገኖቼ በዘመናችን በትዳር ውስጥ የሚታይ መርገም ነው ይህ ሁሉ እንዲህ እየሆነ እግዚአብሔር እንዴት በመካከላችን ይስራ ? እንዴትስ ይታረቀን ? ኃብትና ባለጸግነት ቃሉ እንደሚለው ከአባቶች የምንወርሰው ወይም ሰርተን የምናገኘው እንጂ ባል ወይም ሚስት አድርገን በመውሰድ የምናገባው አይደለም እግዚአብሔር አስተሳሰባችንን በቃሉ ይለውጥልን እግዚአብሔር በሃብት በመኪና ሊባርከን ከፈለገ የሚሰጠን ሃብትና መኪና ነው እንጂ ሚስት ወይም ባል አይደለም በሚስት ወይም በባል ሊባርከን ከፈለገ ደግሞ የሚሰጠን ያንኑ ሚስት ወይም ባልን ነው ዛሬ ግን ከሚስትም ሆነ ከባል ቁሳቁስ ስለበለጠብን ለዚሁ ለቁሳቁሱ ስንል የማናወርደው የጥቅስ መዓት የማንፈነቅለውም ድንጋይ የለም አሁንም እርሱን ሰጥቶሻል እርሱዋን ሰጥቶሃል እየተባለ ትንቢቱ ሳይቀር የሚዥጎደጎደው ለዚሁ ለቁሳቁሱና ለዕላቂው ነገር ሲባል ነው እንጂ ለእውነተኛውና ቅድስና ለሞላበት የእግዚአብሔርም ፈቃድ ላለበት ትዳር ታስቦ አይደለም ስለዚህ ለዚሁ የስንፍና ስራችን እግዚአብሔር ይቅር ይበለን እግዚአብሔር ግን ይሄንን ሁሉ ስለሚያውቅ የሥራችንን ይከፍለናል የዘራነውንም ያሳጭደናል እንደገናም የዓይን አምሮታችን ወሰን ስለሌለው ባልን ወይም ሚስትን ሳይሆን ዝናን መልክን ቁመናን እውቀትንና የመሳሰሉትን እናገባለን አንድ መልክን ያገባ ሰው ምሳሌ በጥቂቱ ላጫውታችሁ እጮኛው በጣም ቆንጆ የነበረች ወጣት ነበረችና ገና ከመጋባታቸው በፊት እንቅፋት ሲመታት ሲያይ እኔን ይምታኝ እንደዚህና እንደዚያ ልሁንልሽ ይል ነበር ጃኬት ሳልደርብ ወጣሁ በረደኝ ስትል ደግሞ ጃኬቱን አውልቆ እኔን ብርድ ያድርገኝ እንቺ አንቺው ልበሽልኝ ይል ነበር ጊዜው ደረሰና ተጋብተው ዓመታት ካስቆጠሩ በኋላ ባለቤቱና የትላንት ተወዳጇ እጮኛው ከዚህ በፊት እንደሆነው እንቅፋቱ ሲመታት ይኸው ያገባት ሰው እኔን ይምታኝ የሚለው የፍቅርና የማሽሞንሞን ቃሉ ሁሉ በቅጽበት ተለወጠና እያየሽ አትሄጂም እንዴ ? ዓይን የለሽም ? ማለት ጀመረ ብርድ በረደኝ ስትል ደግሞ ጃኬቱን ደርበሽ አትወጪም ? ምን ዓይነትዋ ናት ? እያለ ያሳጣት ጀመረ በዓይን አምሮት የተጀመረ ፍቅር እንግዲህ ውጤቱ ይሄ ነው በትላንት ነገሩ ሞትኩ አበድኩ ከነፍኩና ሌላም ሌላም ነገር እንዳላለ ሁሉ አሁን ደግሞ ይህን የሚመስል መራር ነገር መናገር ጀመረ ታድያ እንዲህ ዓይነቱ ጊዜያዊ የሆነ የዓይን አምሮት ፍቅር ዘለቄታነት የለውምና በትንሽ ነገር ይቀየራል ያልቃል ይቀዘቅዛል በምሬትም ይለውጣል የዚህ ሰው ፍቅር ለሚስቱ ጊዜያዊ የሆነ የዓይን አምሮት ፍቅር ስለነበረ ወዲያው ተለወጠ ለዚህ ነው እንግዲህ በዘመናችንም አንዳንድ ጐረምሶችና ኮረዶች ትላንት የጀመሩትን ፍቅር በእግዚአብሔር ጸጋና በኪዳኑም ኃይል ታምነው እስከመጨረሻው መፈጸም ሲገባቸው ሜዳ ላይ ከጣሉት በኋላ ከወገኖች መሐል ምነው እህቴ ? ምነው ወንድሜ ? ምን ነካችሁ ? ተብለው ለእነርሱ ሲባል መፍትሔ ለማምጣት ለተጠየቁት ጥያቄ የሚሰጡት መልስ እጅጉን አሳዛኝ ነው መልሱም እንዲህ የሚል ነው ትላንት የሆነ ነገሯን የሆነ ነገሩን አይቼ ወደድኩት ወደድኳት ዛሬ ግን አስጠላችኝ አስጠላኝ በቃ ምን ላድርግ ? አቦ ተዉና ? ሙዳችንን አትሥረቁብን ? የሚል የቀበጦችና የአላዋቂዎች መልስ ነው በመሆኑም ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሰው እንዲህ ዓይነት መልስ አይሰጥም እነዚህ ወጣቶች ታድያ በፊቱኑም ሊቀብጡ ሊዘሉ ፈልገው እንጂ አልተዋደዱም ወይም በእውነተኛው የክርስቶስ ፍቅር ተዋደው የጀመሩት ነገር አይደለም በጣም የሚገርመውና ድንቅም የሚለው ግን ይህ ሁኔታ በወጣቶቹ ሳያበቃ ሁለት መልክና ሁለት ጸጉር ወዳወጣው ሽማግሌውና አሮጊቱ መድረሱ ነው እንደገናም ከመግረምም በላይ እጅግ የሚደንቀው ይሄ ጉዳይ አገልጋዩንና አስተማሪ ነኝ ባዩን ሳይቀር መነካካቱ ነው እግዚአብሔር ከዚህ ማስተዋል ከሌለበት አስደንጋጭ የወረርሺኝ በሽታ ይታደገን ይሰውረን ያድነን ጌታ በተጋቢዎች መሃል በትክክል ያፈሰሰው ፍቅር ሲሆን ግን መልክ ውበት ደምግባት መኪና ቤት ገንዘብ ዝና ክብር መክሳት መጥቆርን ማማር አለማማርን የማይመለከት ስለሆነ ተለዋዋጭ አይደለም ለዘላለምም አይለወጥም ለዚህ ነው ሐዋርያው ሲናገር ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም ያለን ስለዚህ ጌታ ያፈሰሰው በትዳር ውስጥ ያለፍቅር ለዘወትር አይወድቅም 1 ቆሮንቶስ 13 8 እንደውም በመኃልይ መጽሐፍ ላይ እንደሚነግረን ፍቅር እንደሞት የበረታ ነውና መኃልይ 8 6 እስከሞት ድረስ ይሄዳል እስከሞት ድረስም ይታመናል የክርስቲያን ጋብቻም በሞት ካልሆነ አይፈታም ሮሜ 7 2 1 ቆሮንቶስ 7 39 ወገኖቼ በትዳር አለመጣጣም ምክንያት በየጓዳው የወደቀውን ፍቅር ጌታ እግዚአብሔር እንደገና መልሶ ያድስልን የፈረሱ ቤቶችን የተበተኑ ትዳሮችንም ይስራልን ይመልስልን ተባረኩልኝ

ከዱሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎች ይሠራሉ የብዙ ትውልድም መሠረት ይታነጻል አንተም ሰባራውን ጠጋኝ የመኖሪያ መንገድን አዳሽ ትባላለህ

ትንቢተ ኢሳይያስ 58 12

ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ

No comments:

Post a Comment