Sunday 23 February 2020


የካቲት 2 -የመላእክት ወገን የሆኑ የገዳማውያን ሁሉ አለቃ የከበሩ አባ ጳውሊ ዕረፍታቸው ነው፡፡


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
የካቲት 2 -የመላእክት ወገን የሆኑ የገዳማውያን ሁሉ አለቃ የከበሩ አባ ጳውሊ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+ የቅዱሳን ዐፅም ቃል በቃል በማናገር የሃይማኖትን ነገር የተረዱት የደብረ ዝጋጉ አባ ለንጊኖስ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+ ዳግመኛም በዚህች ዕለት የከበረ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ አስገራሚ ተአምራት በማድረግ ብዙዎችን አስተምሮ አጥምቋል፡፡
አባ ለንጊኖስ ዘደብረ ዝጋግ፡- ትውልዳቸው ኪልቂያ ሲሆን በልጅነታቸው ገዳም ገብተው በመመንኮስ የአባ ሉክያኖስ ደቀ መዝሙር ሆነው በተጋድሎ ኖረዋል፡፡ መምህራቸው አባ ሉክያኖስን አበ ምኔትነት ሊሾሟቸው ሲሉ ውዳሴ ከንቱን በመጥላት አባ ለንጊኖስን ይዘው በድብቅ ወደ ሶርያ ሄዱ፡፡ በአንዲት ቤተ ክርስቲያንም ተቀምጠው ብዙ አስገራሚ ተአምራትን ያደርጉ ነበር፡፡ ዜናቸው በሁሉም ዘንድ ሲሰማ አሁንም ውዳሴ ከንቱን በመራቅ በአባታቸው ምክር አባ ለንጊኖስ ወደ ግብጽ ሄደው ደብረ ጽጋግ ገዳም ገቡ፡፡ በዚያም አበምኔቱ ሲያርፉ በእግዚአብሔር ትእዛዝ አባ ለንጊኖስን አበ ምኔት አድርገው ሾሟቸው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ መምህራቸው አባ ሉክያኖስ መጥተው የመርከብ ጣሪያ እየሠሩ አብረው በአንድ ልብ ሆነው በተጋድሎ ኖሩ፡፡ ድንቅ ድንቅ ተአምራት እያደረጉ ብዙ ከኖሩ በኋላ አባ ሉክያኖስ ሲያርፉ ‹‹የውሾች ጉባዔ›› እየተባለ የሚጠራውና ጌታችንን ‹ሁለት ባሕርይ› የሚለው የሮም የረከሰ እምነት በጉባዔ ተወሰነ፡፡ ከሃዲው ንጉሥ መርቅያኖስም በሀገሮች ሁሉ የጉባዔውን ደብዳቤ መላክ ጀመረ፡፡
የንጉሡንም ደብዳቤ መልአክተኞቹ ለአባ ለንጊኖስ አመጡላቸውና ‹‹በዚህ ጽሑፍ እንድታምኑና እንድትፈርሙበት ንጉሡ አዟል›› ብለው ሰጧቸው፡፡ አቡነ ለንጊኖስም ‹‹ከቅዱሳን አባቶቼ ጋር ልማከርበት እኔ ምንም ምን መሥራት አልችልም እንድንማከርበት እናንተም ከእኔ ጋር ኑ›› ብለው የቅዱሳን ዐፅም ወዳለበት ዋሻ ውስጥ ይዘዋቸው ሄዱ፡፡ አባታችንም ለአፅሞቹ እንዲህ ብለው ተናገሩ፡- ‹‹የከበራችሁ ቅዱሳን አባቶቼ ሆይ! እናንተ ዐርፈን ተኝተናል አትበሉ፣ እነሆ አንዱን ክርስቶስን ሁለት ባሕርይ የሚያደርግ በውስጡ የተጻፈበትን ይህን ደብዳቤ አምጥተዋልና በቃሉ አምን ዘንድ በውስጡም እፈርም ዘንድ ታዙኛላችሁን?›› እያሉ ዐፅሞቹን ጠየቋቸው፡፡ ያን ጊዜም የተላኩት ሰዎች ሁሉ እየሰሙ ከቅዱሳኑ አስክሬን ውስጥ እንዲህ የሚል ቃል ወጣ፡- ‹‹የአባቶቻችንን የሐዋርያትንና የ318ቱን የቀናች ሃይማኖትን አትተው፣ ይህንንም የረከሰ ደብዳቤ አትከተል፣ ከአስክሬናችን ቦታ አርቀው እንጂ›› የሚል ቃል ከቅዱሳኑ አስክሬን ወጣ፡፡ ይህንንም የሰሙት የንጉሡ መልእክተኞች እጅግ አድንቀው ወደ ንጉሡ አልተመለሱም፤ ይልቁንም ራሳቸውን ተላጭተው በዚያው መነኮሱ እንጂ፡፡ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸውም በታላቅ ተጋድሎ ኖሩ፡፡ የከበሩ አባ ለንጊኖስም ያማረ ተጋድሎአቸውን ጨርሰው በሰላም ዐርፈዋል፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!
+ + +
የከበረ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ ተአምራት በማድረግ ብዙዎችን እንዳጠመቀ፡- ይኸውም ጌታችን ወዳዘዘው ቦታ የከበረች ወንጌልን ሊያስተምር በወጣ ጊዜ ከመንገድም ፈቀቅ ብሎ ሳለ መልኩ በጣም የሚያምር ድንገት የሞተ አንድን ጎልማሳ አገኘ፡፡ ቅዱስ ቶማስም ‹‹አቤቱ ይህን ጥፋት አይ ዘንድ ወደዚህ አመጣኸኝን ነገር ግን ፈቃድህ ይሁን›› አለ፡፡ ከዚህም በኋላ ስለሞተው ሰው ጸለየ፣ ያንጊዜም ታላቅ ከይሲ ከድንጋዮች ውስጥ ወጥቶ በጅራቱ ምድርን እየደበደበ መጣና ‹‹የክርስቶስ ሐዋርያ ሆይ! እኔ ከአንተ ጋራ ምን አለኝ? ሥራዬን ልትዘልፍ ልታጋልጥ መጣህን!›› ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፡፡ ቅዱስ ቶማስም ‹‹ሥራህን ተናገር›› አለው፡፡ ከይሲውም ‹‹በዚህ ቦታ መልከ መልካም ሴት ነበረች፣ እኔ የምወዳት ናት፡፡ ይህም ጎልማሳ ሲስማት አየሁት፡፡ በሰንበት ቀንም ከእርሷ ጋር አደረ፡፡ ስለዚህም ነክሼ በመርዝ ገደልኩት›› አለው፡፡ ሐዋርያውም ‹‹በል አሁን መርዝህን ከእርሱ ትወስድ ዘንድ በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝዤሃለሁ›› አለው፡፡ ከይሲውም ሄዶ ከዚያ ከሞተው ሰው መርዙን መጠጠና ወሰደ፡፡ ወዲያውም ተነፍቶ አበጠና ተሰንጥቆ ሞተ፡፡ ሞቶ የነበረው ጎልማሳ ግን በሐዋርያው ጸሎት ከሞት ተነሣ፡፡ ስለዚህችም የሐዋርያው የቅዱስ ቶማስ ተአምር ብዙዎች በክብር ባለቤት በጌታችን አመኑ፡፡ ቅዱስ ቶማስም የቀናች ሃይማኖትን አስተምሮ አጠመቃቸው፡፡
የቅዱስ ቶማስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
ርዕሰ ገዳማውያን አቡነ ጳውሊ፡- አባታቸው የገንዘቡን መጠን እንኳን የማያውቁት እጅግ ባለጸጋ ነበሩ፡፡ አባታቸው ከሞቱ በኋላ ወንድማቸው ጴጥሮስ ንብረታቸውን በትክክል አላካፍላቸው ስላለ ተጣልተው ወደ ዳኛ ሄዱ፡፡ በመንገድ ላይ ሳሉ አንድ ሰው ሞቱ ሊቀብሩት ሲወስዱት አይተው አባ ጳውሊ አገኟቸው፡፡ የሞተው ማን እንደሆነም ሲጠይቁ የሞተው ሰው እጅግ ባለጸጋ እንደነበር በኃጢአት ውስጥም ሆኖ እንደሞተ ተነገራቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ጳውሊ ‹‹የዚህ የኃላፊ ዓለም ገንዘብ ለእኔ ምኔ ነው?›› ብለው ወደ ወንድማቸው ዞረው ወደ ዳኛ መሄዳቸውን ትተው ወደቤት እንዲመለሱ ለመኑት፡፡ የአባታቸውንም የተትረፈረፈ ሀብትና ንብረት ፈጽሞ እንደማይፈልጉት ነገሩት፡፡
ከወንድማቸውም ተደብቀውና ሸሽተው በመውጣት በአንዲት በመቃብር ቤት ገብተው መጸለይ ጀመሩ፡፡ በ4ኛ ቀናቸውም የታዘዘ መልአክ መጥቶ ነጥቆ ወስዶ ከአንድ በረሃ ውስጥ አደረሳቸው፡፡ አባ ጳውሊም ወደ አንዲት ኩርፍታ ገብተው ተጋድሎአቸውን ጀመሩ፡፡ በዚያች ዋሻ ውስጥም የሰውን ፊት ሳያዩ በጾም በጸሎት ብቻ ተወስነው 80 ዓመት ኖሩ፡፡
ልብሳቸውም ከሰሌን ቅጠል የተሠራ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደ ነቢዩ ኤልያስ ቁራን እየላከ ምግባቸውን ይሰጣቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን የጳውሊን ክብር ይገልጥ ዘንድ መልአኩን ወደ አባ እንጦንስ ዘንድ ላከው፡፡ አባ እንጦንስም በበረሃ ውስጥ በታላቅ ተጋድሎ ከኖሩ በኋላ በበረሃ መኖር የጀመሩት እሳቸው እንደሆኑ በልባቸው ማሰብ ጀምረው ነበር፡፡ መልአኩም ተገልጦላቸው ‹‹እንጦንስ ሆይ ከአንተ የሁለት ቀን ጎዳና ርቆ በበረሃ ውስጥ የሚኖር ሰው አለ፤ የዓለም ሰዎች ከሚረግጥባቸው የእግሩ ጫማዎች እንደ አንዲቱ ሊሆኑ የማይገባቸው ስለ እርሱም ጸሎት ዓለም ተጠብቆ የሚኖር ነው…›› እያለ የአባ ጳውሊ ክብር ነገራቸው፡፡
አባ እንጦንስም የአባ ጳውሊን በዓት ፈልገው አግኝተው ሄደው በብዙ ምልጃ በሩን ከፍተውላቸው ተገናኝተው ሁለቱም አብረው ከጸለዩ በኋላ ስለ ተጋድሎአቸውና ስለ አኗኗራቸው ተወያዩ፡፡ የታዘዘው ቁራ ሌላ ጊዜ የጳውሊን ምግብ የሚያመጣው ግማሽ እንጀራ ነበር ዛሬ ግን ሙሉ እንጀራ ስላመጣላቸው ሁሉቱም ቅዱሳን ደስ ተሰኝተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ አባ እንጦንስም ሥጋ ወደሙን ከወዴት እንደሚቀበሉ አባ ጳውሊን ሲጠይቋቸው በየሳምንቱ ቅዳሜና እሁድ መልአክ እያመጣ ሥጋ ወደሙን እንደሚያቀብላቸው ነገሯቸው፡፡
ከዚህም በኋላ አባ እንጦንስ ‹‹ይህ አስኬማ በምድር ላይ ይበዛ እንደሆነ ወይም አለመብዛቱን ትነግረኝ ዘንድ እሻለሁ›› አሏቸው፡፡ አባ ጳውሊም ወደፊት ስለሚመጡ መነኮሳት በመጸለይ ወደ ሰማይ ካዩ በኋላ በመጀመርያ ፈገግ አሉ፡፡ አባ እንጦንስም ‹‹ምን አየህ?›› ቢሏቸው አባ ጳውሊ ‹‹ነጫጭ ርግቦች በጠፈር መልተው አንተ እየመራሃቸው ተከትለውህ ሲሄዱ አየሁ›› አሏቸው፡፡ ‹‹ይህስ ምንድን ነው?›› ቢሏቸው ‹‹እሊህማ በዚህ በቆቡ የምትወልዳቸው ንጹሐን ጻድቃን ልጆችህ ናቸው›› አሏቸው፡፡ ‹‹ሁለተኛ አመልክትልኝ›› አሏቸው፡፡ ጳውሊም ካመለክቱ በኋላ አዝነውና ተከፍተው ተመለከቷቸው፡፡ ‹‹ምነው?›› ቢሏቸው ‹‹በክንፋቸው ጥቁር ተቀላቅሎባቸው አየሁ›› አሉ፡፡ ‹‹ምንድን ናቸው?›› ቢሏቸው ‹‹ጽድቅና ኀጢአት እየቀላቀሉ የሚሠሩ ልጆችህ ናቸው›› አሏቸው፡፡ እንጦንስም ካዘኑ በኋላ ‹‹ሦስተኛም አመልክትልኝ›› አሏቸው፡፡ አባ ጳውሊም ለሦስተኛ ጊዜ ካመለከቱ በኋላ በድንጋጤ ቃላቸውን ከፍ አድርገው ጮኹ፡፡ አባ እንጦንስም ‹‹ምነው?›› ቢሏቸው አባ ጳውሊ እንዲህ አሉ፡- ‹‹ነገር ግን በመጨረሻ ዘመን የሚነሡቱ እንደ ቁራ ጠቁረው አየሁዋቸው›› አሉ፡፡ ‹‹ምንድን ናቸው?›› ቢሏቸው ‹‹ሀሳሲያነ ሢመት (ሹመት ፈላጊዎች)፣ መፍቀሪያነ ንዋይ (ገንዘብ የሚወዱ) እና ከመኳንንትም ጋር በጥዋት ማዕድ የሚቀመጡ በፍጻሜ ዘመን የሚነሡ ኀጥአን ልጆችህ ናቸው›› አሏቸው፡፡ ይህን ጊዜ አባ እንጦንስ ‹‹ያለ ንስሓ ባይጠራቸው እስኪ አመልክትልኝ›› አሉ፡፡ አባ ጳውሊም አመለከቱ ነገር ግን የዚህ ምላሽ አልመጣላቸውም፡፡
ከዚህም በኋላ አባ ጳውሊ አባ እንጦንስን ወደ በዓታቸው ሄደው ቈስጠንጢኖስ ለሊቀ ጳጳሳት አትናቴዎስ የሰጣቸውንና አትናቴዎስ ደግሞ ለእሳቸው የሰጧቸውን የከበረች ልብስ አምጥተው በእርሷ ይገንዟቸው ዘንድ ጠየቋቸው፡፡ አባ እንጦንስም አባ ጳውሊ የተሰውረውን ሁሉ በማወቃቸው አደነቁ፡፡ ዳግመኛም አባ ጳውሊ ስለ ቆቡ አባ እንጦንስን ‹‹እንግዲህ ይህን ከራስህ ያደረግኸውን ለኔ ስጠኝ ላንተ ሌላ ሠርተህ አድርግ›› አሏቸው፡፡ አባ እንጦንስም ‹‹ይህንንስ እንዳልሰጥህ ከባለቤቱ ተቀብዬዋለሁ፡፡ ነገር ግን ሥራውን ለምጄዋለሁ ሌላ ሠርቼ ላምጣልህ›› አሏቸው፡፡ ጳውሊም ‹‹እንግዲያስ አትዘግይ ቶሎ ሠርተህ አምጣልኝ›› አሏቸው፡፡ እንጦንስም የ2 ሰዓት መንገድ ተጉዘው ወደ በዓታቸው ሄደው ቆቡን ሠርተው ይዘው ሲመጡ ጳውሊ ዐርፈው ነፍሳቸውን መላእክተ ብርሃን ይዘዋት ሲያርጉ ተመለከቱ፡፡ መላእክቱም ‹‹ጳውሊ ዐርፏልና ሄደህ ቅበረው›› አሏቸው፡፡ ‹‹ይህንሳ የያዝኩትን ቆብ ልተወውን?›› ቢሏቸው፡፡ ‹‹አትተው አድርግለት›› ብለው መለሱላቸው፡፡ ይህም በምንኩስና የሠሩት ሥራ ከንቱ እንዳይደለ ለማጠየቅ ነው፡፡ አባ እንጦንስም ቢሄዱ አባ ጳውሊ መጽሐፋቸውን ታቅፈው፣ አጽፋቸውን ተጎናጽፈው፣ ከበዓታቸው ዐርፈው አገኟቸው፡፡ እርሳቸውም የአባ ጳውሊን ሥጋ በልብሱ ሸፍነው በጸሎታቸው እንዲያስቧቸው እየተማጸኑ አለቀሱ፡፡ የሥጋቸውንም ጉዳይ ከእሳቸው ጋር እንዳልተማከሩ ሲያስቡ የታዘዙ አንበሶች መጥተው እጅ ከነሷቸውና እግራቸውን ከላሱ በኋላ የኣበ ጳውሊን ሥጋ የሚቀብሩበትን ቦታ አሳይተዋቸው ቆፈሩላቸው፡፡ አንበሶቹም ቆፍረው ሲጨርሱ ወጥተው ሰግደውላቸው እሳቸውም ባርከዋቸው ሄዱ፡፡ አባ ጳውሊንም በክብር ከቀበሯቸው በኋላ ወደ እስክንድርያ ሄደው ለአባ አትናቴዎስ የሆነውን ሁሉ ከነገሯቸው በኋላ የሰሌን አጽፋቸውን ሰጧቸው፡፡
የከበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ አትናቴዎስም ያችን የአባ ጳውሊን አጽፍ በክብር አስቀምጠው በዓመት ሦስት ጊዜ ብቻ ማለትም በልደት፣ በጥምቀትና በትንሣኤ በዓል ብቻ ይለብሷት ነበር፡፡ በሞተም ሰው ላይ ጥለዋት ሙት አስነሥተውባታል፡፡
የርዕሰ ገዳማውያን የአቡነ ጳውሊ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!

No comments:

Post a Comment