Monday 17 February 2020

እመቤታችን ዐርጋለች? .. ጥንተ አብሶ የለባትም? መልሱ .. አዎን!

እመቤታችን በልዧ ሥልጣን ዐርጋለች ወይ፤ መልሱ አዎን ዐርጋለች!
        1.     የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የነበረ ትምህርቷ ነው፤
አንደኛው የምንረዳው የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ቋሚ ትምህርቷ ከምሥረታዋ ጀምሮ እንዲሁ በመኾኑ ነው፡፡ ይህ በራሱ የእመቤታችንን ሕይወት ለመረዳት በቂ ምንጭ ነው፡፡ እውነተኛው ወንጌልና እውነተኛው ትምህርት አንድ ጊዜ ብቻ ለቅዱሳን የተሰጠ በመኾኑ አይስተካከልም፡፡ “ለቅዱሳ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ኾነብኝ” እንዳለ ይሁ.1፣3፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የምትመሰክረውን ኹሉ ማመን ይኖርብናል፤ ርሷ የተመሠረተችውም ሲዠመር እውነትን እየመሰከረች ለመኖር ነው፡፡ ማቴ.16፣18 ሰዎች ማን ይሉኛል ብሎ ሐዋርያትን በፊልጵስዩስ ቂሳርያ ሲጠይቃቸው ብዙ የተሳሳተ ነገር እንደሚሉት ነገሩት፡፡ እናንተስ እውነቱን ማን ትሉኛላችሁ ሲላቸው የእግዚአብሔር ልዥ እንደሚሉት ነገሩት፡፡ ይህን እውነት ሲናዝዙ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን መሠረተ፡፡ “አንተ አለት ነህ በዚህ አለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እመሠርታለሁ የገሃነም ደጆች አይችሏትም” ብሎ
፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ስለክርስቶስ እውነት መጠየቅ ያለባት ቀዳሚ መምህር ነች ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ “የእውነት ዐምድና መሠረት የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን” ስለኾነች ነው፤ 1ጢሞ.3፣14
  
ጌታችን ወንጌልን በምድር ላይ ኾና አምና እንድታሳምን በአለት ላይ የመሠረታት ቤተ ክርስቲያን ስለክርስቶስም ኾነ ስለወንጌሉ መጠየቅ ያለባት አንደኛ ምስክር ነች ማቴ.18፣18፡፡ ስለወንጌልና ወንጌልን አገልግለው ስላለፉ ኹሉ ትክክለኛ መረጃ ያላት፣ መንፈስ ቅዱስ በእውነት አጽንቶ የሚጠብቃትና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም “አነ እሄሉ ምስሌክሙ ወትረ በኲሉ ጊዜ እስከ ሕልቀተ መዋዕል ፤ እነሆ እኔ እስከ ፍጻሜ ጊዜ ድረስ አብሬአችሁ እኾናለሁ” ብሎ ቃል የገባላት ማቴ.28፣20፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከምታስተምረው ውጭ በራስ በመነዳትም ኾነ በመመራመር፣ በመሰለኝና በደስ አለኝ የሚመጣ ትምህርት በተለይም ደግሞ በታሪክ መነሻው የሚታወቅ እንግዳና ሐዲስ ትምህርት እውነተኛ አይደለም፡፡
ከዚህ አንጻር እመቤታችን በልዧ ሥልጣን ዐርጋ በገነት ትኖራች የሚለው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሐዋርያዊና ለዘመናት የኖረ ትምህርት ሲኾን ከዚህ ተቃራኒ ትምህርት ማስተማር ግን ክርስቶስ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን መቃረንና ባለፉት ጥቂት ምዕት ዓመታት ብቻ የመጣ፣ የታሪክም ምስክርነት የሌለው እንግዳ ትምህርት ነው፡፡ ይህ ይኹን እንጂ በተሐድሶ ፕሮቴስታንቱ ዓለም ታላላቅ ተብለው ከሚወሰዱ ሰዎች መሐል ብዙዎች የእመቤታችንን በክርስቶስ ሥልጣን እንደልዧ ዐርጋ በገነት መኖሯን ያስተምሩ ነበር - ለዚህም ማርቲን ሉተርን እንደ አብነት መውሰድ ይቻላል፡፡ (The Works of Martin Luther Vol. X)
2.    ትንቢት ይህንኑ ያስረዳናል፤
በትንቢት በተለይም በዳዊት መዝሙር መዝ. 131፣8 ላይ “ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ - አቤቱ ወደዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” ይላል፡፡ ይህ ትንቢት በግልፅ ለክርስቶስ ትንሣኤ የተነገረ ሲኾን አያይዞም ግን በእርሱው ኃይልና ሥልጣን የምትነሣና የምታርገውን እመቤታችንን አብሮ ታቦት ብሎ ይጠራታል፡፡ እንደምናውቀው በብሉይ የታቦተ ሕጉ ዋና አገልግሎት በእግዚአብሔር ጣቶች እጅ የተጻፉ 10ቱ ቃላትን (ቃላተ እግዚአብሔርን) መያዝ ነው፡፡ እመቤታችንም የእግዚአብሔር አብን አካላዊ ቃል የባሕርይ ልዡን ኢየሱስ ክርስቶስን በማሕፀንም በጀርባ የተሸከመች ማኅደረ መለኮት ነች፡፡ እሷ እንዲያውም በጣት የተጻፈን ሳይኾን ሥጋን የተዋሐደውን የሕያው የእግዚአብሔር ቃል አካላዊ ወልድን የያዘች አማናዊት ታቦት ነች፡፡ 

በታቦተ ሕጉ ውስጥ እስራኤል 40 ዘመን በምድረ በዳ ይበሉት የነበረ ቂጣ (ኅብስት) ይቀመጥበት ነበር፤ ዘጸ.16፣33፡፡ እመቤታችንም ከሰማይ የወረደ ሕይወትን የሚሰጥ እውነተኛ መብል ክርስቶስን ይዛለችና ታቦተ ሕጉን ትመስላለች፤ ዮሐ.6፣55-58፡፡ በታቦተ ሕጉ ውስጥ የአሮን በትር ትቀመጥ ነበር፤ ዘኍ.17፥10፡፡ ይህችውም የእንጨት በትር ሳለች ሳይተክሏትና ውኃ ሳያጠጧት እንዲሁ አፍርታ ተገኝታለች፡፡ እመቤታችንም ያለወንድ ዘር በድንግልና ጸንሳ የሕይወትን ፍሬ አስገኝታለች፤ ሉቃ.1፥35::
በ2ሳሙ.6 እና በሉቃ.1 እንደምናየው የእመቤታችንና የታቦተ ሕጉ ንጽጽር እጅግ አስገራሚ በኾነ መልኩ ሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስ አስቀምጦታል፡፡ ታቦተ ሕጉ ከፍልስጥኤም ወደዳዊት ከተማ (በኤፍሬም አገር በሚገኝ ተራራማ ሥፍራ) ሲደርስ ንጉሥና ነቢይ ዳዊት ወጥቶ እየዘመረና እየዘለለ አመሰገነ፡፡ 2ሳሙ.6፣14 እመቤታችን ብሥራቱን ከሰማችበት ከገሊላ ወደይሁዳ አገር ተራራማ ሥፍራ ሄዳ ዘመዷን ኤልሳቤጥን በተሳለመቻት ጊዜ ነቢይና ካህን የሚኾን ቅዱስ ዮሐንስ በማኅፀን ኾኖ እየዘመረና እየዘለለ አመሰገነ፤ ሉቃ.1፣39-41፡፡
ታቦተ ሕጉ ወደዳዊት ከተማ ሲመጣ ሲገለጽ ከነበረው የእግዚአብሔር ኃይል የተነሣ ንጉሡ በአክብሮት በትሕትና “የእግዚአብሔር ታቦት ወደእኔ እንዴት ይመጣል” ብሎ አደነቀ፤ 2ሳሙ.6፣9፡፡ አማናዊት ታቦት እመቤታችን ኤልሳቤጥ በጸነሰች በ6ኛ ወር (ልትወልድ 3 ወር ሲቀራት) ወደተራራማው አገር ይሁዳ ስትመጣ የተደረገላትን ታላቅ የእግዚአብሔር ነገር በማወቅ ኤልሳቤጥ በአክብሮትና በትሕትና “የጌታዬ እናት ወደእኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይኾንልኛል” ብላ አደነቀች፤ ሉቃ.1፣43፡፡ ታቦተ ሕጉ በአቢዳራ ቤት ሦስት ወራት ቈይቶ ቤቱንና ርሱን ባረከ፤ 2ሳሙ.6፣11፡፡ እመቤታችንም ኤልሳቤጥ እስክትወልድ (ሦስት ወራት) ቈይታ ቤቱን የበረከት ቤት አደረገችው (ከሴቶች ተለይታ የተባረከች ናትና የማኅፀኗም ፍሬ ቡሩክ ነውና ቤቱን የበረከት ቤት አደረገችው)፤ ሉቃ.1፣42-45፡፡ ዖዛ በታቦተ ሕጉ ላይ በድፍረት እጁን ሲያነሣ ተቀሰፈ፡፡ ታውፋንያ በእመቤታችን ሥጋ ላይ በድፍረት በመነሣሣቱ እጆቹን ተቈረጠ፡፡ ታቦተ ሕጉ በሰማይ በእግዚአብሔር መቅደስ ኾኖ በራእየ ዮሐንስ ምዕ.11 ታየ፡፡ እመቤታችንም በሰማይ በእግዚአብሔር መንግሥት ኾና በራእየ ዮሐንስ ምዕ.12 ታየች፡፡ (ዮሐንስ ሐዋርያ ታቦተ ሕጉንም እመቤታችንንም በተከታታይ እንዳያቸው ጻፈ)
ከዚህ አንጻር “አቤቱ ወደዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” ሲል የተነበየው የቅዱስ ዳዊት ትንቢቱ እመቤታችን እንደ ጌታችን በእግዚአብሔር ሥልጣን እንደምትነሣ የሚተነብይ ነው፡፡ መዝ.131፣8
3.    የዮሐንስ ራእይ ምዕ.12 ላይ በክብር ተገልጣ ታይታለች፤
በራእየ ዮሐንስ ምዕ.11 ላይ “በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ የኪዳኑም ታቦት ታየ” ሲል እናገኘዋለን ራእ.11፣19 ከዚያ ይህኑ ምንባብ አስፍቶ ካስነበበን በኋላ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ አማናዊት ታቦት እመቤታችን ምዕ.12 ላይ ጨረቃን ተጫምታ፣ ፀሐይን ተጎናጽፋ በክብር እንደንግሥት ኾና የተገለጠች ሴት እንዳለች እናያለን፡፡ ይህች ሴት “አሕዛብንም ኹሉ በብረት በትር ይገዛቸውን ዘንድ ያለውን ልዥ ወንድ ልዥ” የወለደች እንደኾነች ሐዋርያው ይነግረናል፤ ራእ.12፣5፡፡ እንዲህ ያለ ልዥ በሰማይም በምድርም አንድ ብቻ እርሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ርሱን የወለደችው ደግሞ እናቱ ማን እንደኾነች ኹላችንም እናውቃለን፡፡
እዚህ ምእራፍ ላይ ሕፃኑና ሴቲቱ በዲያብሎስና በመንግሥቱ ላይ በጠላትነት የተነሡ መኾናቸውን እናያለን (ሙሉውን በጥንቃቄ ያነቧል)፡፡ በርግጥ ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ በቀዳማዊው አዳም ቦታ ተገብቶ በእርሱ ወደሰው ልዦች የመጣውን መርገምና እርኩሰት በጽድቅና በሕይወት ሊቀይር የመጣ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልዡ አካላዊ ቃል ነው፡፡ እዚህ ላይ የቀደመችቱ ሔዋን (ቀዳማዊት ሔዋን) ከቀዳማዊ አዳም ጋር በአንድነት ኾና ለሰው ልዥ ውድቀት ያበረከተችውን ያለማመንና ያለመታዘዝ አስተዋፅዖ ልብ ብሎ የሚያስተውል ሰው በሐዲሱ ኪዳን ይህን ታሪክ ሊለውጥና ባሕርያችንን ወደቀደመ ክብሩ ሊመልስ የመጣውን ዳግማዊ አዳም (ኢየሱስ ክርስቶስ) በዚህ አገልግሎት ላይ ዳግሚት ሔዋን እመቤታችን የሚኖራትን ሚና ማየት ይችላል፡፡ እመቤታችን ልዧን ከፊት አስቀድማ በዲያብሎስ ላይ በጠላትነት የዘመተች ተዋጊ መኾኗ ግልፅ ለክርስቲያኖች ነው፡፡ ለዚህም ነው በዘፍ.3፣15 “በአንተና በሴቲቱ በዘርህና በዘሯ ጠላትነትን አደርጋለሁ” ተብሎ ትንቢት የተነገረላት፡፡
ስለዚህ እመቤታችን (ሴቲቱ) ልክ እንደ ልዧ (ዘሯ) በአካለ ሥጋ በትፍስሕተ ገነት ትኖራለች፡፡
4.    የእርሷ ወደገነት በክብር መወሰድ አይገርምም፤
ሌሎች የእግዚአብሔር ባርያዎች ፈቃዱን ጠብቀው እስከኖሩ ድረስ ያልሞቱም ጭምር በክብር የተወሰዱ አሉ፤ እለ ሄኖክ (ዘፍ.5፣24)፣ እለኤልያስ ነቢይ (2ነገ.2፣11) እለዮሐንስ ሐዋርያ ወዘተ.
ነቢዩ ሄኖክ፡ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ፍጹም ትሑት ሰው እንደነበረ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ እናነባለን፡፡ ስለዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ሞትን ሳያይ በአካል ወደብሔረ ሕያዋን እንደወሰደው እናያለን፡፡ ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና፤” ዕብ.11፣5 በዚያም ቦታ በጸሎትና በአምልኮ እግዚአብሔርን እያገለገለ ዛሬም ይኖራል፡፡
ነቢዩ ኤልያስ፡ ኤልያስ ነቢይ በምድር ቈይታው በነቢየ እግዚአብሔርነት ካገለገለና የአምላኩን ስም ካስከበረ በኋላ በደመና ሰረገላ ተጭኖ ወደብሔረ ሕያዋን እንደሄደና ሞትን እንዳላየ ተገልጦልናል፡፡ ሲሄዱም። እያዘገሙም ሲጫወቱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ።” 2ነገ.2፣11፡፡
ዮሐንስ ወንጌላዊ፡ ዮሐንስ ወንጌላዊው እስካሁን ድረስ አልሞተም፤ በሕይወት ግን በብሔረ ሕያዋን ይኖራል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ለሐዋርያት በሚናገርበት ጊዜ ስለወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በአንድ ወቅት ለቅዱስ ጴጥሮስ እስከምፅዓት ድረስ እንደሚኖር ከዚያ እንደሚሞት ነግሮታል፡፡ “እስከዓለም ፍጻሜ ሞትን የማያዩ እንዳሉ ብልህ አንተ ምን ገድዶህ” ብሎታል፡፡ ጴጥሮስም ይህን አይቶ ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ ይህስ እንዴት ይሆናልአለው። 22 ኢየሱስም። እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ፥ ምን አግዶህአንተ ተከተለኝ አለው። 23 ስለዚህ።  ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚለው ይህ ነገር ወደ ወንድሞች ወጣ፤ ነገር ግን ኢየሱስ። እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህአለው እንጂ አይሞትም አላለውም።” ፤ ዮሐ.21፣22፡፡

እመቤታችን የውርስ ኃጢአት አለባት ወይ፤ መልሱ የለባትም ነው፡፡
1.     የውርስ ኃጢአት የሚባል ነገር ሲዠመርም የለም፤ ያለው የቀደመ ኃጢአት (ጥንተ አብሶ) ነው፤
የውርስ ኃጢአት ብሎ ነገር የለም፡፡ የአዳም ኃጢአት የሚወረስ ሳይኾን በባሕርየ ሰብእ በሙሉ የተሠራ ኃጢአት ነው፡፡ አንድ ጊዜ ተሠርቶ በዘር እየተላለፈ የሚመጣ ኃጢአት ነው ውርስ የሚባለው ይህ የቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በአዳም ምክንያት አንድ ጊዜ ኹሉም ሰው በድሏል ነው ብላ የምታስተምረው፡፡ አዳም የሠራው ያለማመንና ያለመታዘዝ በደል የኹላችንም ነው እንጂ በምንወለድበት ጊዜ ርሱው እየተወረሰ የሚመጣ ነው ብላ አታስተምርም፡፡
2.    እመቤታችን ለምን ንጽሕት መኾን እንዳለባት
እመቤታችን ፍጹም ከበደልና ርኲሰት ነጻ መኾን ያለባት ምክንያት ንጹሐ ባሕርይ የእግዚአብሔር ልዥ ከእርሷ ሥጋንና ነፍስን ነሥቶ ፍጹም ሰው ኾኖ በተዋሓደው ሥጋ ንጹሕ መሥዋዕት ኾኖ ዓለምን የሚያድን ስለኾነ ነው፡፡ ዓለም የሚድነው በፍጹም መሥዋዕትና በንጹሕ ቊርባን (በክርስቶስ ቤዛነት) እንደኾነ እየታወቀ (ኢዩ.1፣11) ክርስቶስ ከኃጢአትና ከርኵሰት ይወለድ ማለት ዘበት ነው፡፡ ጌታችን ከኃጢአት ሳይኾን ያለዘርዕ ከንጽሕት ድንግል ነው የተወለደው፡፡
የእመቤታችን ንጽሕና እኛ ለርሷ ስንል ያመጣነው ሳይኾን በቀጥታ ከድኅነተ ዓለም ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ከኹሉም በላይ ከላይ ታቦተ ሕጉ የእመቤታችን ምሳሌ ጥላ ነው ካልን በሰው እጅ እንኳ እስካይነካ ድረስ ንጹሕ ኾኖ እንዲጠበቅ ከተደረገ አማናዊት ታቦተ ኪዳን ዘሐዲስ እመቤታችንማ ምንኛ አብልጣ ንጹሕ ትኾን፤ ምክንያቱም ርሷ ንጹሑን መሥዋዕት ጌታችንን የምታስገኝ ናትና፡፡ የተዋሐደው ሥጋ ከሰማይ ይዞት የወረደ ሳይኾን ከርሷ ሥጋ የነሳው ነው፡፡ የኃጢአተኛ ሥጋ ደግሞ ንጹሐ ባሕርይ ኢየሱስ ክርስቶስ አይነሳም፡፡ ስለዚህ እመቤታችን ርኲሰት የሌለባት ክርስቶስን መውለድ የሚያስችል ንጽሕና ያላት ንጽሕት ናት፡፡
አለባት የሚል ሰው ካለ እንዴት ሊኖርባት እንደሚችል የማስረዳት ግዴታና ኃላፊነት አለበት፡፡
3.    ሉቃ.2 እና ዘሌ.12 ተናብበው እመቤታችን የቀደመ ኃጢአት አለባት ሊያስብሉ አይችሉም፤
ይህ ጌታችን ሕግን አክብሮ ሕግንና ነቢያትን ሳይሽር በአይሁድ ዘንድ ያለነቀፋ ኖሮ ወንጌልን የመሥራቱ ማሳያ እንጂ ሌላ ምንም የሚናገረው ነገር የለም፡፡
በብሉይ ኪዳን ሴት ልዥ በወለደች ጊዜ ርኵስ ስለምትኾን ከርኵሰቷ ትነጻ ዘንድ 7 ቀን ሲያልፋት መቅደስ ሄዳ የርግብና የዋኖስ ግልገሎች መብዓ እንድታገባ ሥርዓት ነበር፡፡ ብትችል ከጠቦቶች መርጣ ብታገባ፣ ብትደኸይና ምንም ባይኖራት ግን በዚህ መብዓ እንድትነጻ ሥርዓት ተሠርቷል፡፡
እመቤታችን ልዧን ኢየሱስ ክርስቶስን በወለደች ጊዜ 7 ቀን ሲያልፍ በ8ኛው እመቅደስ ተገኝታ እንደሥርዓቱ አድርጋለች፡፡ መርገምንና ርኵሰትን ሊሽር የመጣው ንጹሑ የእግዚአብሔር ልዥ አወላለዱ ላይ እንዲህ ያለ ጉድለት ነበረበት ማለት ፈጽሞ ያለማመን ትምህርት ነው፡፡ ርሱ ክብር ይግባውና ንጹሕ ነው፤ አወላለዱም ንጹሕ ከንጽሕት እናት ነበር፡፡
የርግብና ዋኖስ ግልገሎች ይዘው ቤተ መቅደስ የሄዱት ከርኲሰት ለመንጻት ሳይኾን የአይሁድን ትእዛዛቸውን ላለመሻርና ከዥምሩ ቊጣቸውን ላለማስነሣት ነው፡፡ ይህን ባያደርጉ ልዡም ወላዦቹም ከሥረ መሠረቱ የአይሁድንና የአባቶቻቸውን ልማድ የሚጥሱ አመጸኞች መስለው እንዳይታዩአቸው፡፡ ክርስቶስ ኋላ አድጎ ወንጌልን ለሕዝብና አሕዛብ የሚሰብክ ነውና እንዲህ ካለው አመፀኛና ሕግና ትእዛዝ የሚሽር ወንበዴ እውነት እንዴት ይገኛል ብለው ወንጌልን ለመቀበል እንዳይሰቀቁ ከሰው ሕግ አንዲትስንኳ ሳያስቀር ያለነቀፋ በመሄድ ኹሉንም ትእዛዛት ለማክበር ተጠንቅቆ ነው ጌታችን ያደገው፡፡
ለምሳሌ ያክል ጌታችን ተጸንሶ ከመወለዱ አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ ባወቀ ዮሴፍ ጠባቂዋ ይኾን ዘንድ ለርሱ ታጨች፤ ማቴ.1፣16፡፡ ኹላችንም ክርስቶስ የተወለደው በድንግልና (ያለአባት ዘር) እንደኾነ እናውቃለን፤ ሉቃ.1፣34-35፡፡ አይሁድ ግን አባቱ ዮሴፍ ነው ይሉ ነበር፤ ዮሐ.6፣42፡፡ እንዲህ እንዲሉ ያደረገው እግዚአብሔር ነበር፤ ምክንያቱም ወንድ በቤቱ ባይኖር ያለትዳር ማግጣ ልዥ ወለደች ብለው ይወነጅሏት ነበር፡፡ በአይሁድ ልማድ ከትዳር ውጭ ሴት ወደወንድ ብትሄድ በድንጋይ ትወገር ነበር፤ ዮሐ.8፣4-5፡፡ ይህን ለማለፍና ልማደ አይሁድን ላለመቃረን ለዮሴፍ ታጨች፡፡ የተወለደውም ልዥ በአይሁድ ልማድ የዮሴፍ ልዥ እየተባለ አደገ፡፡ ይህም በሕጋቸውና በትእዛዛቸው መሠረት የታጨላት ቢኾን ሚናው ግን ለክርስቲያኖች ግልጽ ነው፡፡ መጠበቅና ማገዝ ብቻ ነበር፡፡
ከዚህ አንጻር ሌላ ብዙ ትእዛዘ አይሁድን ላለመቃረን የተደረጉ ነገሮች አሉ፡፡ ጌታችን ያደረጋቸው እጅግ ብዙ የአይሁድ ሕግና ልማድ የኾኑ ነገሮች አሉ፡፡ ሉቃ.2፣41 ሕግንና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ ሲልም ጌታችን ይህንኑ እያጠየቀ ነው፡፡ ማቴ.5፣15-18 “ኹሉንም እንደጌታ ሕግ” እያደረጉ ይኖሩ እንደነበር ሐዋርያው ቊ.39 ላይ ይነግረናል፡፡
ምስጋና ለእግዚአብሔር!

No comments:

Post a Comment