Sunday 16 February 2020

የሰው ልጅ በዚህች ምድር ላይ ሲኖር ለቅጽበትም ቢሆን አእምሮው ሊረሳውና ሊያቋርጠው የማይችለው ነገር ምን እንደሆነ አስባችሁት ታውቃላችሁ? ሰውነቱ በእንቅልፍ ተሸንፎ እንኳን ቢተኛም እያንቀላፋ አስታውሶ የሚያደርገው ክንውን የትኛው እንደሆነ አስተውላችኋል? እንደው አይሆንም እንጂ ሆኖለት ለደቂቃዎች ሰውነቱ ይህንን ተግባር በመርሳት ባያከናውነው ሕልውናው አጠያያቂ ሁኔታ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ይህ ሰውነታችን ልምድ ያደረገውና ለአፍታ እንኳን መቋረጥ የማይፈልገው ተግባር አየር ማስገባትና ማስወጣት ወይም መተንፈስ ነው፡፡

ለዚህ ጽሑፍ ይህን የተፈጥሮ እውነት እንደ መነሻ የተጠቀምነው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጸሎትን እንደ ነፍስ እስትንፋስ ይቆጥሯታል፡፡ አየር ያጠረው ወይም ወደ ሰውነቱ የማያስገባ ሰው በሕይወት የመቆየት ዕድሉ ጠባብ እንደሆነ ፤ እንዲሁ ከጸሎት የተለየች ነፍስም ወደ ሞት መንደር የመውረዷ ነገር የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ነፍሳችን ሕያዊት የምትሰኘው በአረጋዊ መንፈሳዊ መጽሐፍ ላይ ‹የነፍሴ ነፍሷ› ተብሎ ከተጠራው መንፈስ ቅዱስ ጋር በጸሎት ትስስርን ስትመሰርት ነው፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙም እንደሚያስተምረው ሰው ከእስትንፋሱ የበለጠ ዘወትር ፈጣሪውን በጸሎት ሊያስታውስ ይገባዋል፡፡

ጸሎት ማለት ምን ማለት ነው? ሃይማኖታቸው የቀና ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ ሊቃውንት በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 14 ላይ ‹ጸሎትስ ሰው ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የሚነጋገራት ነገር ናት› ሲሉ የጸሎትን ትርጉም ይነግሩናል፡፡ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን በልዩ ልዩ አይነት መንገድ ሊያናግራቸው ይችላል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በራእይ በመገለጥ ወይም ቅዱስ ዳዊት ‹እግዚአብሔር ለሕዝቡ በመጽሐፍ ይነግራቸዋል› ሲል እንደ ዘመረው በመጽሐፍ በኩል ማናገር ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ የሰው ልጆች ደግሞ ከፈጣሪያቸው ጋር የሚነጋገሩት ጸሎት በተባለ ድልድይ አማካኝነት ያነጋግሩታል፡፡

መተንፈስ ለሥጋዊው አካላችን የዕለት ተዕለት የማይቋረጥ ሥራው እንደሆነ ሁሉ የነፍስ እስትንፋስ የተባለች ጸሎትም ለክርስቲያን የየዕለት መንፈሳዊ ተግባር ናት፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹ሳታቋርጡ ጸልዩ› በማለት የሚመክረን (1ኛ ተሰ 5፡17)፡፡

በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ሶርያዊው አባ ይስሐቅ (ማር ይስሐቅ) ቅዱሳን ምንም ዓይናቸው በእንቅልፍ ሽፋሽፍት ቢያዝ እንኳን ነፍሳቸው ግን ከእግዚአብሔር ጋር በሚደረግ የማይቋረጥ ንግግር (ጸሎት) ውስጥ ስለምትገኝ ተኝተውም ቢሆን ጸሎትን እንደማያስታጉሉ ይናገራል፡፡ እኛ በዓለም የምንኖር ግን የሥጋ ድካም ስላለብን ቀኑንም ፣ማታውንም በጸሎት የማሳለፍ ብርታቱ የለንም፡፡ በመሆኑም ‹ሳታቋርጡ ጸልዩ› የሚለው የሐዋርያው ትዕዛዝ ይከብድብናል፡፡

በዚህም ምክንያት እንደ እኛ ሥጋ ለባሽ የሆኑ አባቶቻችን ይህን ድካማችንን አይተው ቀኑን ሁሉ በጸሎት ማሳለፍ ባትችሉ እንኳን ቢያንስ በቀን ሰባት ጊዜ እግዚአብሔርን ስለ እውነተኛ ፍርዱ አመስግኑት ሲሉ ሰባት የጸሎት ጊዜያቶች ወስነውልናል (መዝ 119፡164)፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አሁንም ከፈጣሪው ጋር ቀኑን ሙሉ በጸሎት የማሳለፍ ጽኑዕ ፍላጎት ላለው ክርስቲያን አባቶች የሚያስተምሩት ሌላ ‹ሳያቋርጡ የመጸለይ ጥበብ› አለ፡፡ ይህንን ጥበብ የምናገኘው ቅዱስ ጰላድዮስ (St. Palladius) የተባለው አባት ባሰባሰበውና የብዙ አባቶችን ዜና ሕይወት ይዞ በሚገኘው ‹መጽሐፈ ገነት› ላይ ነው፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው ፡-

በአንድ ወቅት አባ ሉቅዮስን (Abba Lucius) ለማየት የመጡ ጥቂት መነኮሳት እንዲህ አሉት ‹በእጃችን ምንም አይነት ሥራን አንሠራም፡፡ የቅዱስ ጳውሎስን ትዕዛዝ በማክበር ሳናቋርጥ እንጸልያለን እንጂ!›፡፡ አረጋዊው መነኩሴ አባ ሉቅዮስም ‹አትመገቡም? ወይም አትተኙምን?› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ‹አዎን! እንተኛለን ፤ እንመገባለን› ሲሉ መለሱ፡፡ አባ ሉቅዮስም ‹ወንድሞቼ ይቅርታ አድርጉልኝና የምትሉትን ነገር (ሳያቋርጡ መጸለይን) እየፈጸማችሁ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ በእጆቼ ሥራን እየሠራሁ እንዴት ሳላቋርጥ እንደምጸልይ አሳያችኋለሁ፡፡ ዘወትር ጠዋት በእግዚአብሔር እርዳታ የዘንባባ ዛፍ ቅሪቶችን እሰበስብና እነርሱን ሽጬ አሥራ ስድስት ሳንቲሞችን አገኛለሁ፡፡ ከዚያም ሁለቱን ሳንቲሞች ከቤቴ በር ደጃፍ ላይ አስቀምጥና በቀረው ምግብ እገዛበታለሁ፡፡ የገዛሁትንም ምግብ ተመግቤ ስተኛ ፤ ያ ከቤቴ ደጃፍ ላይ ሁለቱን ሳንቲሞች የወሰደው ነዳይ ደግሞ ስለ እኔ ይጸልያል፡፡ እንዲህ እያደረግሁ በእግዚአብሔር ረድዔት ሳላቋርጥ እጸልያለሁ› በማለት ልምዱን አካፈላቸው፡፡

ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ከጸሎት ጋር በቀን ማከናወን ያለበትን ሥራ ሥርቶ ከጨረሰ በኋላ አመሻሽ ላይ ከሚያገኘው ትርፍ ለነዳይ ቢመጸውት ብዙውን ሰዓት በእንቅልፍ የሚያሳልፍበትን ሌሊት በምጽዋት እያካካሰ ሳያቋርጥ ሊጸል ይችላል ማለት ነው፡፡
ሳናቋርጥ እንጸልይ!!!

No comments:

Post a Comment