Sunday 23 February 2020

በሰሙነ ሕማማት የሚፈጸሙ እና የማይፈጸሙ ሥርዓቶች

1.ስግደት:-በሰሙነ ሕማማት 41 ጊዜ ኪርያላይሶን 12 ጊዜ አቡነ ዘበሰማያት
እየተዜመ እጅግ አብዝቶ ይሰገዳል::
2. ጸሎት:- በሰሙነ ሕማማት ከ24 ሰዓት ውስጥ 10 የጸሎትና የንባብ ሰዓታት
ይገኛሉ እነዚህም ከጠዋቱ 1 ሰዓት; 3ሰዓት; 6ሰዓት; 9ሰዓት; 11ሰዓት
እንዲሁም ከምሽቱ 1 ሰዓት; 3ሰዓት; 6ሰዓት; 9ሰዓት; 11ሰዓት ናቸው::
በነዚህም ሰዓታት የጌታን ስቃይ ለማዘከር መዝሙረ ዳዊትና ግብረ ሕማማት
ድርሳነ ማኅያዊ አብዝተው ይጸለያሉ::
3.ጾም:-በሰሙነ ሕማማት ብዙ አዝማደ መባልዕት /አዘውትረን የምንመገባቸው
ምግቦች/ አይበሉም:: በዚህም ሳምንት እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት እንድንጾም;
ይኸውም ቆሎ;ዳቦ;ወኃና ጨው ብቻ እንደታዘዙ በግብረ ሕማማት ላይ ተጽፎ
ይገኛል::
4.አለመሳሳም:-አይሁድ ጌታችንን ለመስቀል እየተንሾካሾኩ ስለተመካከሩና
ይሁዳ ጌታችንን በመሳም አሳልፎ ስለሰጠው መሳሳም አይፈቀድም:: መስቀልም
በዘመነ ኦሪት የወንጀለኛ መቅጫ የእርግማን ምልክት ስለ ነበር ጌታችን በክቡር
ደሙ ቀድሶ የድል አርማ እስኪያደርግልን ድረስ አንሳለመውም ገላ. 3:13
ማቴ.10:38 ማቴ. 26:29
5.አክፍሎት:-እመቤታችን; ያዕቆብና ዮሐንስ የጌታችን ትንሳኤ ሳናይ እህልና ውኃ
አንቀምስም ብለው እስከ ትንሳኤው መቆየታቸውን በማሰብ የሚጾም ነው::
6.ጉልባን:-ከባቄላ ከስንዴ ከገብስ የሚዘጋጅ በጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ
ንፍሮ ሲሆን ትውፊቱም የስቅለቱ ሐዘን መግለጫ ነው::
7.ጥብጠባ:-ይህ ምዕመናን በሰሙነ ሕማማት የፈጸሟቸውን ኃጢአቶች ለካህን
እየተናዘዙ በወይራ ቅጠል ቸብቸብ እየተደረጉ ስግደት የሚቀበሉበት ነው::
ይህም የጌታ ምሳሌ ነው::
8.ቄጠማ:-ጌታችን ብርሃነ ትንሳኤዉን እንደገለጠልን የምናስብበት ሲሆን የእሾህ
አክሊል በመድፋቱ ምሳሌም በራሳችን ላይ እናስረዋለን::
===//============
በስሙነ ሕማማት በሚገኙ ዕለታት ስያሜ እና የተፈፀመባቸው ድርጊት:-
1ኛ ዕለት እሁድ ዕለተ ሆሳዕና
ሆሳዕና፡- የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን መድኃኒት፣ ‹‹አቤቱ እባክህን አሁን አድን›› የሚል ትርጉም አለው፡፡ (መዝ. 117፥25) ይህ በዓል በኦሪት (በብሉይ) የመጸለት 7ኛ ዕለት ሲሆን ለሐዲሱ ኪዳን ግን ከትንሣኤ በፊት ያለ እሑድ የሚከበር ነው፡፡ (ዘሌ.23፥39-44/ማር.11፥10/ዮሐ.12፥13)
በዚህ ዕለት ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ጌታችን በአህያዋና በውርንጭላዋ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በሚገባበት ጊዜ ሕዝቡም የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት በማለት ማመስገናቸው ይታስብበታል (ዘፍ.49፥11/ሕዝ.9፥9-10/ኢሳ.40፥10/ዮሐ.12፥13)
ከላይ እንደተመለከትነው የዘንባባ ዝንጣፊ ይዞ ማመስገን በሕግ ከመነገሩ በፊት (ዘሌ.23፥39-44) አባታችን አብርሃም ይስሐቅን የመውለዱ ተስፋ በተፈጸመለት ጊዜ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዞ አመስግኗል፡፡ (መ.ኩፋ.13፥21) በመቀጠልም ሕዝብ እስራኤል በሕግ ታዘው ይፈጽሙት ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- ባሕረ ኤርትራ በተሸገሩ ጊዜ፣ ዮዲት ጠላትዋን ድል ባደረገች ጊዜ ይህንን ሥርዓት ፈጽመዋል፡፡ በዘመነ ሐዲስም ጌታችንን የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው አመስግነውታል፡፡ (ማቴ.21፥1-11/ማር.11፥1-11/ ዮሐ.12፥12-16) ፡፡ ዛሬም ምዕመናን ከምሥጋናውም በረከትን ለማግኘት ተሳታፊዎች ለመሆን በካህናት የተባረከውን የዘንባባ ዝንጣፊ ወደ ቤታቸው ይወስዳሉ፡፡ በዚህ ዕለት ከሌሎች ጊዜ በተለየ ከበሮ ጸናጽል የሚያጅበው የምሥጋና መዝሙር የሌሊት ማኅሌት ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም ለስሙነ ሕማማት ሁሉ የሚሆን ጸሎተ ፍትሐት የሚደረግበት ዕለት ነው፡፡
2ኛ ዕለት ሰኞ
ይህ ዕለት አንጽሖተ ቤተ መቅደስ እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለተ ነው፡፡ በቅዱስ ማርቆስ ወንጌል እንደተገለጠልን ጌታችን ከቢታንያ ወጥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ተራበ፡፡ በለስም ከሩቅ አየ፣ በለስዋ ግን ከቅጠል ብቻ በቀር ፍሬ ምንም አላገኘባትም ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ፍሬ አይገኝብሽ ከአንቺ ፍሬ የሚበላ አይኑር አላት ያን ጊዜውንም በለሲቱ ደርቃለች (ማር.11፥12-19/ማቴ.21፥19/ሉቃ.1945-46)
በለስ የተባለች ኦሪት ናት፡- በለስ አገኘ ማለቱ ኦሪት በዚህ ዓለም ሰፍና አገኛት ሲል ነው፡፡ ወደ እርስዋም ሄደ ማለት ፈጻሜ ሕግ ተባለ (ሥርዓተ ኦሪትን ማለት በ8 ቀን መገዘር በ40 ቀን መሥዋዕት ማቅረብን… እየፈጸመ አደገ) ማለት ነው፣ ፍሬ አላገኘባትም፡. ሕግ ከመባል …..ድኅነትን አላደረገባትም ፍሬ አይገኝብሽ አላት ሲል፡- ባንቺ ድኅንነት አይደረግ አላት፡፡ ይህም ቅዱስ ዳዊት ‹‹መሥዋዕትን ቁርባንን አልወደድሁም ሥጋህን አንጻልኝ፣ የሚቃጠለውንና ስለኃጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልወደድሁም ሲል የኦሪትን ሕግ (አሠርቱ ትዕዛዛትን) አሳለፋቸው ማለት አይደለም፡፡ ቅዱስ ዳዊት እንደነገረን በመሥዋዕተ ኦሪት ፍፁም ድኅንነት አለመገኘቱን አውቆ ማሳለፉን እና ፍፁም ድኅንነት የምናገኝበትን ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡን ያሳያል፡፡›› አንድም በለስ ያለው ኃጢአትን ነው፡፡ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነ ኃጢአትን በዚህ ዓለም ሰፍና አገኛት፡፡ ወደ እርሷ ሄደ ፍሬም አላገኘባትም ማለት በአይሁድ አንደበት በሐሰት ኃጢአተኛ ተባለ እንጂ (ስለ እኛ መተላለፍ እንደበደለኛ ተቆጠረ እንጂ) ኃጢአትን አልሠራም ሲል ነው፡፡ ፍሬ አይገኝብሽ ሲል፡- ባንቺ በመጣ ፍዳ የሚያዝ አይኑር አላት ማለት ነው፡፡
ከዚህ በመቀጠል ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፡፡ ቤተ መቅደሱም ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምስያጥ (የንግድ ቤት) ሆኖ ቢያገኘው ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ በዚያ ያሉትን ሁሉ አስወጣቸው፡፡ ይኸም በጠቅላላው ማደሪያው ቤቱ የነበርን የአዳም ለጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኙን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡ (ማቴ.21፥12-17/ማር.11፥15-24/ሉቃ.19፥4)
ይቀጥላል …..
እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ጻማ ወድካም
ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ ለብርሃነ ትንሳኤሁ እግዚአብሔር በፍስሐ ወበሰላም::

No comments:

Post a Comment