“ሐዋርያነት”፡ “ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ” ሮሜ.10፥14-15።


ብርሃናተ ዓለም ሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስ ወማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ጳውሎስ
ሐዋርያነት፡
“ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ” ሮሜ.10፥14-15።

የቃሉ ፍቺ

“ሐዋርያ” -- የሚለው ቃል መነሻ መሠረቱ ጽርዕ (የግሪክ ቋንቋ) ሲኾን በዚያም “አፖስቶሎስ” ብሎት ይገኛል። “አፖስቶሎስ” የሚለው ግሪክ በቀጥታ “የተላከ” ለሚል አማርኛ ይቆማል፤ እንዲያ ይተረጐማል። ከዚሁ ውስጥ “ኤፒስቶሊስ” የሚለው ደግሞ “መልእክት” የሚለውን አማርኛ (ግእዝ) (በተለይም የቅዱሳን ሐዋርያትን መልእክታት) የሚገልጥ ቃል ነው።

በእኛው ግእዝ “ሖረ” ካለው ቀዳማይ ግስ የሚረባ፥ ትርጕሙም ሄደ፥ ተራመደ ካለው መንገደኛ፥ መላከተኛ፥ የተላከ ማለት ነው። በዘይቤ ለአንዳች ዓላማ ግብ አንግቦ የሚዞር፣ ሕይወቱን ለዚሁ የሰጠ ሐዋርያ ይባላል፡፡ የመንገድ ዙረት (ጉዞ) እና አንዳች ዓላማን ማስረጽ፣ ዘብ መቆም አላባውያኑ ናቸው፡፡

በቁሙ ሹም (መንፈሳዊ)፥ መምህር፥ ዙሮ የሚሰብክ፥ የሚያስተምር፥ ባለምሥራች፥ ዐዋጅ ነጋሪ መኾኑ በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ሰፍሯል፤ አ.ኪ.ወ.ክ. (ሰ.ግ.ግ.መ.ቃ ገጽ 437)።

ማነው ሐዋርያ …


ታዲያ በክርስትና ውስጥ የተገኘው ሰው ኹሉ እንዲያው “አፖስቶሎስ” - “ሐዋርያ” አይባልም። በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ለምንኖር ሰዎች ከጅማሬውም ቢኾን ተሹሞ፥ ተልኮ መባረክ፥ ተሹሞ፥ ተልኮ ማስተማር፥ መጠበቅ ማለት ፍጹም መለኮታዊ ተግባር እና በእግዚአብሔር ሥልጣን ተመክተው ብቻ ሊደረግ የሚችል ልዕልና ያለው ተግባር ነው። ከዚህ ውጪ ቢደረግ ትልቁ አደጋ ምንድን ነው ቢባል በፈጣሪ ዘንድ ብዙ ነውርና ነቀፋ ማትረፍ፥ በተለይም ደግሞ “ሐሰትን” መስበክ፥ ሕዝብን ከእግዚአብሔር መስረቅ ይኾናል።

የሰው ልጆች ከእስራታቸው የሚፈቱትና አርነት የሚያገኙት “በእውነት” አማካኝነት ሲኾን ሳይላኩ የሚሰብኩት ስብከት፥ ሳይሾሙ የሚያስተምሩት ትምህርት አደጋው፣ የሚባርኩት መባረክ እና የሚጠብቁት መጠበቅ ሳይላኩ ያደረጉት በመኾኑ የባርነታችንን ማሠሪያ ማጥበቅ፥ መጠፍነግ ይኾናል። ለዚህም ነው በትምህርተ ሐዋርያት ውስጥ “ተዐቀቡኬ እምሐሳውያን ከሐሰተኞች ተጠበቁ” የሚል ማሳሰቢያ ደጋግመን የምናገኘው።

በሐዋርያነት ተግባር ውስጥ መስበክ፥ ማስተማር ማለት እውነትን መግለጥ ነው። እውነት ደግሞ ትክክለኛ መገኛ ምንጯ እግዚአብሔር ብቻ ስለኾነ ከእግዚአብሔር ካላገኙት በቀር ለማካፈል አይቻልም። ከእግዚአብሔር ደግሞ እውነትን ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው ሲባል ያን ጊዜ የሐዋርያነት ወይም “የመላክ” ጽንሰ አሳቡ ይመጣል፤ ሐዋርያነት የሚገኘው ከእግዚአብሔር ነው። የምናስተምረው ትምህርት እውነት እንዲኾን (ወይም ደግሞ የምናስተምረውን ትምህርት በሥልጣን ማስተማር ለመቻል) ከእግዚአብሔር የተላክን፥ እግዚአብሔር ራሱ ለማስተማር የሾመን መኾን ይገባናል። ይህ ሹመት በተለያየ መንገድ ይፈጸማል፤ ኋላ እናየዋለን።

ጠቅለል ስናደርገው “ሐዋርያ” የሚለው ቃል የተጣራ ትርጕሙ “ከእግዚአብሔር የተላከ” “እግዚአብሔር የሾመው” የሚል ኾኖ ሦስት ድርጊቶችን ለማድረግ የሚያበቃ ተልእኮት ነው። መባረክ (የምሥጢር ካህን)፥ ማስተማር (መምህረ ወንጌል) እና መጠበቅ (ቸር እረኛ)። ቃሉ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአምስት መንገድ ጥቅም ላይ ውሏል።

1. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሐዋርያ” ተብሏል


ከሦስቱ አካል አንዱ አካላዊ ቃል የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ የኾነው ወልድ “ሐዋርያ” ተብሏል። ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን አማኞች በጻፈው መልእክቱ ላይ “ርእይዎ ለሐዋርያክሙ ሊቀ ካህናት የሃይማኖታችን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ” ይላል፤ ዕብ.3፥1። “ሐዋርያ” የሚለው ቃል እዚህ ጋር የተጠቀሰው “የተላከ” በሚል አገባብ ሲኾን ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ተልኮ ወደ ምድር የመጣ መኾኑን ያጠይቃል፤ ዮሐ.8፥16 ፤ ዮሐ.8፥18 ፤ ዮሐ.8፥26 ወዘተ.።

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ነው ስንል ከእግዚአብሔር ተልኮ የመጣ ነው ለማለት ነው። አብ ላኪ ወልድ ተላኪ መኾናቸው የባሕርይ ተወራጅነት እንዳለ ያሳያል ወይስ አያሳይም ለሚል ሰው መልሱን እናቆይ። ጌታችን የተላከ መባሉ የሚከተሉትን ሦስት ነገሮችን እንድናውቅ፥ እንድናምን እና ከእቅዱ ጋር እንድንተባበር ያስገድደናል።

አንደኛ፡ የሰውን ባሕርይ ሊቀድስና ሊያከብር የመጣ ክርስቶስ መኾኑን፤ (የመባረክ ባሕርያዊ ሥልጣኑ)

ሁለተኛ፡ የእግዚአብሔርን አኗኗርና የአብን እውነት ሊገልጥልን የመጣ ክርስቶስ መኾኑን፤ (የማስተማር ባሕርያዊ ሥልጣኑ)

ሦስተኛ፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ ድኅነት የሚመራበት አንድያ ልጁ ክርስቶስ መኾኑን፤ (የመጠበቅ ባሕርያዊ ሥልጣኑ)

እነዚህ ሦስቱ ተግባራት ማለትም መባረክ፥ ማስተማርና መጠበቅ የክርስቶስ የሐዋርያነቱ (የተላከ መኾኑ) ተግባራቱ ናቸው። የናዝሬቱ ኢየሱስ እንዲህ መኾኑን እንዴት እናውቃለን፤ በሌላ አጠያየቅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲጠበቅ የነበረው ከእግዚአብሔር ተልኮ የሚመጣ መሲሕ፥ የተላከው መኾኑን እንዴት እናውቃለን የሚለው ጥያቄ ሌላ ነው።

በዘመኑ ለነበሩት አይሁድ የናዝሬቱ ኢየሱስን የአብ አካላዊ ቃሉ፥ የባሕርይ ልጅ፥ “እግዚአብሔር ወልድ” ነው ብሎ ለመቀበል ሦስት ነገሮችን ማጥራት ያስፈልጋቸው ነበር። አንደኛ የሚያደርጋቸውን አይቶ ሥርየት የሚገኝበት ይህ ነውን ብሎ መመርመር (እንደ ዕውሩ ዘተወልደ አይነቶቹ፤ ዮሐ.9፥31-33)። ሁለተኛ የሚያስተምረውን ሰምቶ የእግዚአብሔር እውነት እንዲህ ይኾንን ብሎ መመርመር (እንደ ሰብአ ማዕዶተ ዮርዳኖስ፤ ማቴ.7፥29 ፤ ዮሐ.10፥41)። ሦስተኛ እረኝነቱን ተመልክቶ እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚጠብቀው እንዲህ ነውን ብሎ መመርመር ነው (እንደ ሰብአ ኢየሩሳሌም፤ ዮሐ.10፥21)። ለሦስቱም በቂ ምላሽ የሚሰጥ ሕይወትን ጌታችን ኖሮ አልፏል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት ርሱ ከእግዚአብሔር የተላከ፥ መሲሑ እንደኾነ እና ሌሎች ግን እንዳይደሉ በሚያረጋግጥ ቃል “የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው፤ አላወቃችሁትምም፥ እኔ ግን አውቀዋለሁ። አላውቀውም ብል እንደ እናንተ ሐሰተኛ በኾንሁ፤ ዳሩ ግን አውቀዋለሁ፤” ይላል፤ ዮሐ.8፥54-55። አጽንቶ የሚናገር የነበረው “የላከኝ እውነተኛ ነው እኔም ከርሱ የሰማሁትን ይህን ለዓለም እናገራለሁ፤” “ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁ፤” “የሰጠኝ አባቴ ከኹሉም ይበልጣል፤” “እኔም በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ስለ እኔ ይመሰክራል፤” “የላከኝ አብ ስለ እኔ ይመሰክራል፤” “እኔ ከላይ ነኝ፤” “እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም፤” “እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤” “ርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁም፤” የመሳሰሉትን ሲናገር ክርስቶስ ነኝ ማለቱ እንደኾነ እንረዳለን፤ ዮሐ.8 ፤ ዮሐ. 10። በዚህም ባሕርያችንን ይቀድስልን ዘንድ የምንጠብቀው (የሚባርከን ካህናችን)፥ ወንጌልን ከርሱ ልንሰማ የምንፈቅደው (የሚያስተምረን መምህራችን)፥ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይመራናል ብለንም የምንጠብቀውም (የሚጠብቀን እረኛችን) እግዚአብሔር ወልድ በእውነት የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ ሌሎች ክርስቶሶች ሐሰተኞች እንደኾኑ እናውቃለን።

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ የተላከ መኾን (ሐዋርያ መባል) ሦስት ነገሮች እንዲፈጸም አድርጓል።

ሕይወቱ ልጅነትን የምናገኝበት ኾኗል፤


ይህ የመባረክ፥ የመለየት፥ የማክበር፥ የመቀደስ የባሕርይ ሥልጣኑ ነው። ያጣነውን ቅድስና የሚሰጠን፥ ከመርገምና ርኲሰት የሚያነጻን እንደኾነ ያሳያል። ማንም ሰው ጸልዮ ሊያጸድቀን፥ ባርኮ ሊፈውሰን፥ ተሠውቶ ሊያድነን በማይችልበት ዐውድ ውስጥ ይህን ማከናወን የሚችል ኾኖ በመካከላችን የተገለጠ ርሱ ነው። ርሱ ሲጸልይ ተፈወስን፥ ሲሞትልን ሕያዋን ኾንን፥ እጆቹን ሲጭንብን ቅዱስ መንፈስን ነሳን፥ እፍፍ ሲልብን ክህነትን ተሾምን። ርሱ የገዛ ኃይሉን ጠቅሶ ማናቸውንም ነገር በእጁ ማከናወን ይቻለዋል። ርኲስ የነበረውን ታሪኩን ለውጦ ቅዱስ ማድረግ ይችላል፤ ለምን ቢሉ ከአብ ወጥቶ ወደ ምድር የመጣ እንጂ ከምድር የመጣ ስላልኾነ ነው።

በልደቱ አንጻር ከተመለከትነው ሕዝቡን ኹሉ ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል የሚል የምሥራች በመላእክት ተነግሯል። መወለድ በርሱ አልተጀመረም፤ ብዙዎች ተወልደዋል። ነገር ግን ርሱ ሲወለድ ሰውና መላእክት፥ ሰውና እግዚአብሔር፥ ሰማይና ምድር፥ ሕዝብ እና አሕዛብ ታርቀውበታል። ጌታችን ሲወለድ ሰውና መላእክት ለመጀመሪያ ጊዜ አብረው መዘመራቸው ስለ ጌታችን የሚናገረው ነገር የሰውን ልጅ ወደ እግዚአብሔር አንድነት ሊመልስ መምጣቱንና ተግባሩንም በይፋ መጀመሩን ነው። ኪደተ እግሩ የግብፅን፣ የኖብንና የኢትዮጵያን ምድሮች ቀድሷል፡፡ የእግሩ መሄድ ቅድስናን ለሣር ቅጠሉ የሚያድል የተቀደሰ አመጣጥ መጣ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ ስም አጠራሩ የተመሰገነ ይኹን፡፡

ዳግመኛም በጥምቀቱ አንጻር ከተመለከትነው ባሮች ተብለን በተዋረደ ስብእና የምንኖረውን ዘግናኝ ፍጥረታት የልጅነትን ብርሃን አጎናጽፎን በሞገስ ወደ መንግሥቱ የሚያመጣን መኾኑን ሲያሳይ ዮርዳኖስ ወርዶ ልጅነት የምናገኝባትን ጥምቀታችንን ሲባርከልን አብ በሰማይ ኾኖ የምወደው ልጄ ርሱ ነው፤ ርሱን ስሙት ሲል ምስክርነት ሰጥቷል። ልጄ ርሱ ነው ሲል እግዚአብሔር አብ የነገረን ነገር ልጅነታችሁ የሚመለሰው በርሱ ነው ማለቱ ነው። ስለዚህ ባሕርያችን የሚከብርበት ሐዋርያ ርሱ ነው ማለት ነው።

በሞቱና ትንሣኤው አንጻር ከተመለከትነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም መሥዋዕት እና ንጹሕ ቊርባን ኾኖ ራሱን ለሰው ልጆች ቤዛ አድርጎ መስጠት የሚችል ኹነኛ መሥዋዕት ነው። ደሙ ሥርየተ ኃጢአትን መስጠት የሚችል፤ ሥጋው እስከ ዘላለም ድረስ የሚቀድሰን መሥዋዕት ነው። ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ ሲል መምጫው እግዚአብሔር አብ መኾኑ ላይ አጽንዖት ሰጥቶ ሕይወትን እንደሚያድለን ደግሞ ይናገራል። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ነው፤ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነው ደግሞ አለ። ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤ ሥጋዬን የማይበላ ደሜን የማይጠጣ የዘላለም ሕይወት የለውም አለ። ስለዚህ ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ወደ አባቱ ማሳረግ የሚችል መሥዋዕት ጌታችን ነው፤ ዮሐ.6፣29-63።

የሚያደርጋቸው ማናቸውም የክህነት ተግባራት ግዳጃቸውን ይፈጽማሉ፤ ለምን ሲባል ከአብ ወጥቶ ወደ ምድር የመጣ በመኾኑ፤ በሥልጣን ከአባቱ ጋር አንድ በመኾኑ፤ የክህነት ሥልጣኑ ከማንም ያልተቀበለው የባሕርይ ገንዘቡ በመኾኑ ነው። ክብር ምስጋና ለስም አጠራሩ ይሁንልን፤ አሜን።

ስብከቱ ነጻነትን የሚያድል እውነተኛ ኾኗል፤


ክርስቶስ በምድር በነበረበት ዘመን የሰዎች ኹሉ ትልቅ ጥያቄ እውነት ርሱ እንደሚለው ክርስቶስ ይኾንን የሚለው ነበር። ክርስቶስ ማለት እግዚአብሔር የላከው፥ እግዚአብሔር የሾመው ማለት ሲኾን ርሱ ወደ ምድር ቢመጣ ትክክለኛው እግዚአብሔርን መስሎ የመኖር ትምህርት የሚያስተምረንና ያላየነውን እግዚአብሔርን የሚተርክልን መኾኑ በትንቢትና በሱባኤ ቀድሞም የታወቀ ነበር። ታዲያ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመጣና በአይሁድ ዘንድ ትምህርቱ ሲደመጥ እንደ ባለሥልጣን (አንዳች የመናገር፥ የመዝለፍ ሥልጣን እንዳለው፥ ከራሱ አፍልቆ እንደሚያስተምር እንደ መንፈሳዊ ሹም) እንጂ እንደጻፎቻቸውና እንደ ፈሪሳውያን እንዳላስተማረ በተመለከቱ ጊዜ ደጋግመው ይጠይቁት የነበረው “እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሬ ታቈየናለህ፤ አንተ ክርስቶስ እንደ ኾንህ ገልጠህ ንገረን፤” የሚል ጥያቄ ነበር፤ ማቴ.7፥ፍ.ምዕ. ፤ ዮሐ.10፥24።

ጌታችን ሲያስተምር ሥርዓትን መሥራት እንደሚቻለው፥ ሕግን ማገግ እንደሚቻለው እያሳየ “እብለክሙ እላችኋለሁ” እያለ እንጂ እንደጻፎቻቸውና ፈሪሳውያን አላስተማረም። በዚህ ምክንያት በጠየቁት ጊዜ ጌታችንም ደጋግሞ አብ የቀደሰው፤ ወደ ዓለምም የላከው መኾኑን ገልጦ ይነግራቸው ነበር።

ስለዚህም የእግዚአብሔርን እውነት፥ ሰዎች እንዲያውቁትና ነጻ እንዲወጡበት የተዘጋጀውን እውነት ከርሱ ሌላ ከማንም ልንሰማው ዝግጁ አልነበርንም ማለት ነው፤ ይህን ማድረግ የሚችል በእቅፉ ያለ አንድያ ልጁ ርሱ ስለኾነ።

ሥልጣኑ ኹሉንም የሚያስማማ ሕጋዊ ኾኗል።


ይህች ደግሞ የመጠበቅ፥ የእረኝነት፥ የኖላዊነት ሥልጣኑ ነች። በበጎቹ ላይ ትክክለኛ ሥልጣን ያለው፥ እውነተኛ የበጎች ጠባቂ፥ መልካም እረኛ ጌታችን ርሱ እንደኾነ ብዙ ጊዜ ተምረናል። ሌሎች እረኞች አብ ያልሾማቸው፥ ያልተላኩ ጠባቂዎች በትክክል እረኞች ሳይኾኑ ዘራፊዎች ናቸው። ድኅነታችንን የሚፈልግ፥ እንደሚጠብቀንና በለመለመ መስክ እንደሚያሳድረን፥ በዕረፍት ውኃ ዘንድ እንደሚመራን፥ ለአባቱ ርስት አድርጎ እንደሚያስገባን የምንተማመንበት እውነተኛ ቸር እረኛ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። “አባግዕየሰ እሊአየ ይሰምዓኒ ቃልየ፤ አነ አአምሮን ወእማንቱ ይተልዋኒ በጎቼ ድምጾቼን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ … ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም፤ የሰጠኝ አባቴ ከኹሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም፤ እኔና አብ አንድ ነን፤” ይላል፤ ዮሐ.10፥27-30።

ሌሎቹ ጠባቂዎች የእውነት ጠባቂዎች ያይደሉ፥ አብ የማያውቃቸው፥ አርደው ሊበሉን ቢፈልጉ እንጂ በጓችንን አይመኙልንም።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ወቅት ሲያስተምር እውነተኛ የበጎች ጠባቂ ወደ በጎች በረት በበሩ በኩል ይገባል አለ። በረኛውም ይከፍትለታል፤ ርሱ ፊት ፊት ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። እረኛቸው ካልኾነው ሰው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፤ ድምፁን አያውቁምና ይላል። ከዚያም አጽንቶ “አማን አማን እብለክሙ” አነ ውእቱ አንቀጸ አባግዕ፤ ወኵሎሙ እለ መጽኡ እምቅድሜየ ሰረቅት ወጕሕልያ እሙንቱ እውነት እውነት እላችኋለሁ እኔ የበጎች በር ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡት ኹሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሟቸውም፤” አለ፤ ዮሐ.10፥7-8። “አነ ውእቱ ኖላዊ ኄር ወአአምር ዘዚአየ መርዔትየ ወያአምራኒ እሊአየ መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ አብም እንደሚያውቀኝ፥ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለበጎች አኖራለሁ፤” አለ፤ ዮሐ.10፥14-15።

እውነተኛው ጠባቂ ከአብ የተላከ እና እውነተኛ መኾኑ የሚታወቅበት አንዱ መንገድ ነፍሱን ለበጎቹ አሳልፎ የሚሰጥ በመኾኑ ነው። ጌታ ሲናገር “መልካም እረኛ ነፍሱን ስለበጎቹ ያኖራል፤ እረኛ ያልኾነው በጎቹም የርሱ ያልኾኑት ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል፤” ይላል፤ ዮሐ.10፥11-12።

ከላይ ባልናቸው ሦስት ነጥቦች ትልቁ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው እውነተኛውን አብ የላከውን (ሐዋርያ) ከሐሰተኛው መለየት ነው። ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። በአጠቃላይ አነጋገር የክርስቶስን “የተላከ” መባል፥ ወይም “ሐዋርያነት” ጠቅለል ስናደርገው የሚከተሉትን እጅግ በማስተዋል መገንዘብ ይገባናል፡

·         እግዚአብሔር እውነተኛ እንደኾነ፤
·         ለሰው ልጆች እውነትን ሊያቀብል የሚችል እግዚአብሔር ብቻ እንደኾነ (ከርሱ ውጪ የመነጨ እውነት ቢኖር ሐሰት እንደኾነ)፤
·         ለሰው ልጆች እውነትን ለማቀበል እግዚአብሔር ቢፈልግ ራሱ መውረድ ቢያሻውም መላክተኛ ሹሞ ለመላክ ባለ ሥልጣን እንደ ኾነ (የመሾም ሥልጣን እንዳለው)፤
·         እግዚአብሔር አንድ የባሕርይ ልጅ ብቻ እንዳለውና ልጁም (ወልድ) ተቀዳሚም ተከታይ የሌለው አንድያ መኾኑን፤
·         እግዚአብሔር ለሰው ልጆች እውነትን ይገልጥላቸው ዘንድ ወደ ዓለም የላከው አንድያ ልጅ ወልድ ብቻ እንደኾነ፤

ይህን ከላይ የሠፈረውን ባለ ነቁጦች አሳብ ከተረዳነውና ልብ ካደረግነው በኋላ ከዚያ በተለይ በተለይ ደግሞ የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 8 እና 10 እናንብብ።

አብ ወልድን ከላከ፥ … ወልድ ለአብ ከተላከ … ታዲያ …


እንግዲያውስ ወልድ ታናሽ ነው ማለት ይኾንን፤ … እዚህ ላይ የእግዚአብሔር አብ ላኪ መኾንና የእግዚአብሔር ወልድ ደግሞ ተላኪ መኾን በወልድ ላይ (በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ) የደኃራዊነት፥ የተወራጅነት ትምህርት ማስተማር አይኾንም ወይ የሚል ጥያቄ የሚነሣባቸው ይኖራሉ። መላክ እና መላክ (አቤት “ላ” ጠብቃ ብትነበብልኝ ደስታዬ) በሥላሴ ዘንድ የባሕርይ ተወራጅነትን አያስከትልም።

ቃል በልባችን ኖሮ ኖሮ ስንፈቅድ ጊዜ በአንደበታችን እንደሚነገር እንደሚባል ኹሉ የሥላሴ ልብ የተባለ አብ፥ የሥላሴ ቃል የተባለ ወልድ እናም የሥላሴ እስትንፋስ የተባለ መንፈስ ቅዱስ ናቸው። በእነዚህ መሐል የባሕርይ ተወራጅነት የለም። ሦስቱም ቀዳማውያን ናቸው፥ ሦስቱም ባለ ሥልጣን ናቸው፤ ሦስቱም አካል አንድ መለኮት (አንድ እግዚአብሔር) ነው።

አብ ወልድን ላከው ስንል ራሱ ጌታችን ኢየሱስ “እምኀበ አብ ወጻእኩ ወመፃእኩ ከአብ ዘንድ ወጥቼ መጥቻለሁ” እንዳለው ነው። ቃል በልብ ቆይቶ በአንደበት እንደመነገሩ ያለ ባሕርይ ዘእምባሕርይ አካል ዘእምአካል ከአብ ተወልዶ በአብ ዘንድ የሚኖር ወልድ ወደ ዓለም መጣ። መሾም፥ መቀባትም ኹሉ እንዲያው ነው፤ የባሕርይ ተወራጅነትን አያሳዩም፤ ይህን የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ይህንን ጽሑፍ እና ይህንን የእንግሊዝኛ ጽሑፍ በማንበብ ከተረዱ በኋላ መምህራንንም ቀርቦ ማዋየቱ አስፈላጊ ነው።

2. ዐሥራ ሁለ ደቀ መዛሙርት “ሐዋርያት” ተብለዋል፤


ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት የተለየ ሞገስ ያላቸው፥ ንዑዳን ክቡራን ናቸው። እነዚህ የተለዩ የሚያደርጓቸው፡

አንደኛ፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዐይነ ሥጋ ያዩ፥ የተመለከቱ፥ ድምፁን በእዝነ ሥጋ የሰሙ፥ ያዳመጡ፥ በዋለበት ቦታ የዋሉ፥ ባደረበት ቦታ ያደሩ፥ የአንደበቱን ትምህርት፥ የእጁን ተኣምራት የተመለከቱ ናቸው፤

ሁለተኛ፡ ከኹሉም በላይ በንፍሐት ንስኡ መንፈሰ ቅዱሰ ብሎ የሾማቸው፤ ዮሐ.20፥21፥ “ሑሩ ወመሐሩ” የሚል አምላካዊ የመምህረ ወንጌልነት ተልእኮት የተሰጣቸው፥ በቀጥታ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምሩ ዘንድ የሾማቸው፥ የቀባቸው ናቸው።

ይህም ማለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ከአብ ዘንድ ይዟቸው የመጣቸውን ሀብታት በጸጋ የተቀበሉ፥ በስጦታ ያገኙ፥ በምድር ላይ የጌታቸን የኢየሱስ ክርስቶስ እንደራሴዎች፥ በቤተ ክርስቲያን ተደማጮች፥ አዛዦች፥ ባለ ሥልጣኖች ናቸው ማለት ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት በዋነኛነት ሦስት ሀብታት አሏቸው።

የመባረክ ጸጋ፡


“ባረከ” የሚለው ቃል የግእዝ ቀዳማይ ግስ ሲኾን ለየ፥ አከበረ ማለት ነው። ሐዋርያት ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በስጦታ ባገኟቸው ሀብታት ተጠቅመው መባረክ ይችላሉ ስንል በጸሎታቸው በመንፈስ ቅዱስ የሚያከብሯቸውንና የሚቀድሷቸውን ነገሮች ማመልከታችን ነው።

ይህ ጠቅለል ባለ መልኩ ምሥጢራትን የመፈጸም ጸጋ ነው።

በዮሐንስ ወንጌል ላይ ጌታችን “አብ እንደላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ” ብሎ ቀድሞ ያወራነውን ለርሱ ብቻ ያለውን ክብር ጸጋ አድርጎ ለመረጣቸውና እስከ መጨረሻው ላፈቀራቸው ንዑዳን ክቡራን አበው ሐዋርያት ተልእኮት ሰጠ (ላካቸው - ሐዋርያ ኾኑ ማለት ነው)፤ ዮሐ.20፥21። ይህን ግን ዝም ብሎ አላደረገውም፤ ይህ “የመላክ” ጸጋና ሥልጣን የሚጸናበትን ምሥጢር ፈጸመላቸው ምሥጢሩም በመንፈስ ቅዱስ ታተመ። “ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ” ይላል፤ ዮሐ.20፥22። ይህ ማለት ፈጽሞ የመባረክ ሥልጣንን በጸጋ ገንዘብ ማድረግ እንደኾነ ሲያሳይ የክህነታቸውን አመክንዮአዊ ውጤቱን “ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችሁላቸው ኹሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል” በማለት ገለጠው፤ ዮሐ.20፥23። ይህም ፍጹም የካህንነት ተግባር መኾኑን ያስተውሏል። በባሕርዩ ኃጢአትን ይቅር የሚልና ይህንም ሊያደርግ ወደ ምድር የመጣው የአብ አንድያ ልጅ ርሱ ሲኾን ከዚህ ገንዘቡ ሐዋርያትን በጸጋ ተሳታፊዎች አደረጋቸው።

ለምሳሌ ያክል በውኃ ስመ ሥላሴን ጠርተው እየጸለዩ የሚያጠምቋቸው ሰዎች በነፍሳቸው ሥርየተ ኃጢአትን፥ ድኅነተ ነፍስን ያገኛሉ፤ ማለት ሐዋርያት በጸሎታቸው ሰዎችን የእግዚአብሔር ልጆች ማሰኘት የሚያክል ሰማያዊ ሥራ ይሠራሉ። ሌላም ምሳሌ ኅብስት አምጥተው ቢጸልዩበት ሥጋ መለኮት፥ ወይን አምጥተው ቢጸልዩበት ደመ መለኮት ወደ መኾን ይለወጥላቸዋል። በዚህም ምግበ ሥጋ የነበረውን ኅብስትና ወይን ነፍስን የሚያጸድቅ ሥጋን የሚቀድስ ሰማያዊ ምግብ (ቊርባን - የጌታችን ሥጋና ደም) ያደርጉታል። ኃጢአቱን ለሚናዘዝ ሰው እግዚአብሔር ይፍታ ብለው ቢጸልዩለት በኃጢአት የታሠረችን ነፍስ በመንፈስ ቅዱስ አሠራር፥ በክርስቶስ ሥልጣን መፍታት፥ ማሠር ይችላሉ። ንሳእ መንፈሰ ቅዱሰ መንፈስ ቅዱስን ንሳ ብለው በአንብሮተ ዕድ (እጅን በመጫን) እና በንፍሐት (በአፋቸው እፍፍፍ በማለት) መንፈስ ቅዱስን ማሰጠት ይችላሉ፤ ማለት ሌሎችንም ሐዋርያት ይኾኑ ዘንድ ሐዋርያነትን ለመሾም ይችላሉ።

በተለይም ደግሞ መጨረሻ ላይ ያነሣነው መንፈስ ቅዱስን በማሰጠት መሾም የሚለው ተግባራቸው ቅዱሳን ሐዋርያ እነርሱ በሐዋርያነታቸው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በስጦታ ያገኟቸውን ሀብታት በሙሉ ቤተ ክርስቲያንን ሊጠቅሙበትና ምእመናንን ሊጠብቁበት ለሚችሉ ለሌሎች ደግሞ መስጠት (መሾም መቀባት) ያስችላቸዋል። በዚህም ከአብ ዘንድ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለሐዋርያት የተሰጠችው ሰማያዊት “የመላክ” “የሐዋርያነት” የክህነት ሀብት በቤተ ክርስቲያን እንዳይቋረጥና እንዲቀጥል ለማድረግ ይቻላቸዋል፤ ይህም “ሐዋርያዊ ውርስ” የምንለውን ጽንሰ አሳብ ያመለክታል።

የማስተማር ጸጋ፡


ማስተማር የምንለው እዚህ ጋር ትምህርት ሰጥቶ የመጨረስ ወይም አንድን ስብከት ጀምሮ ለማጠናቀቅ የሚያስፈልግን ችሮታ ማለት አይደለም። የማስተማር ጸጋ ከላይ አስቀድመን እንዳልነው የእግዚአብሔርን “እውነት” ለሰው ልጆች የመተረክ የመግለጥ ሥልጣንን ነው። ይህ “ጸጋ” ከጸጋ ይልቅ ሥልጣን ተብሎ መጠራቱ ይገልጠዋል። ምክንያቱም “እውነት” ምንድን ነው ብለን በምናጠያይቅበት ጊዜ (ክርክርም ከተፈጠረ) እውነትን አረጋግጦ የመንገር፥ እልባት የመስጠት ሥልጣን ሐዋርያት ተሰጥቷቸዋል ማለት ነው።

ከላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ የተላከ ብቸኛው በመኾኑ እውነትን ልንሰማ እና እግዚአብሔርን መምሰልን ልንማር የምንፈቅደው ከርሱ ብቻ ነው ብለን ነበርን። ጌታችን ለሐዋርያት ሥልጣንን በንፍሐት ሰጥቶ ሾማቸው ማለት ርሱ ወደላከው ወደ አብ በሚሄድበት ጊዜ በምድር ላይ የእርሱን እውነት ለመጠበቅ፥ ለማስጠበቅ ዘብ አድርጎ ሐዋርያትን አቁሟቸዋል ማለት ነው። በዚህም በምድር ላይ ለሚሰበከው የክርስቶስ ወንጌል ኹሉ ቀዳሚ ተጠቃሾች፥ ተመሳካሪዎች፥ ተጣቃሾች እነርሱ ናቸው፤ እነርሱን መቀበል የእግዚአብሔርን እውነት ለመረዳት ቊልፍ ነው ማለት ነው።

በማቴዎስ ወንጌል ላይ ጌታችን ነገርን ኹሉ ፈጽሞ ወደ ሰማይ ሊያርግ ባለበት አጋጣሚ ቅዱሳን ሐዋርያትን ሰብስቦ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ኹሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያስተማርኳችሁንም ኹሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤” ብሏቸዋል፤ ማቴ.28፥20። እዚህ ጋር አጥምቋቸው ሲል ከላይ ያልነውን ልጅነትን በማስሰጠት የሚደረግ የመባረክ ጸጋን፥ አስተምሯቸው ሲል ደግሞ እንደ ርሱ እንደ ጌታችን ኾነው የአብን እውነት ለሰዎች እንዲገልጡ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል ማለት ነው።

ልብ ብለን ይህን በዮሐንስ ወንጌል የሰፈረ ቃል እንይ፡ “ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲኾኑ በስምህ ጠብቃቸው። ከእነርሱ ጋር በዓለም ሳለሁ የሰጠኸኝን በስምህ እኔ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም መጽሐፉም እንዲፈጸም ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም። አሁንም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በእነርሱም ዘንድ ደስታዬ የተፈጸመ እንዲሆንላቸው ይህን በዓለም እናገራለሁ። እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው። ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም። በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው። ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እንዲሁ እኔ ወደ ዓለም ላክኋቸው፤ እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ።”፤ ዮሐ.17፥11-19።

የማስተማር ጸጋ የምንለው የማስተማር ክህሎትን አይደለም። ሥልጣንን እያመለከትን ነው፤ ማለት ጌታችን ከላይ “ቃልህ እውነት ነው” እንዳለ የሐዋርያትን ትምህርት አንቀበልም ብንል ክርስቶስን አንቀበልም እንዳልን ይቈጠራል፤ ክርስቶስን ባንቀበል ደግሞ አብን አልተቀበልንም ማለት ነው፤ እግዚአብሔር አብን የማይቀበል ደግሞ እውነትን በአመፃ የሚከለክል፥ በኃጢአት ማሰሪያ ታስሮ የሚኖር ስለኾነ ለድኅነት ሊበቃ አይችልም። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ይህን ተልእኮ ሲሰጣቸው የሰው ልጆችን ነፍስ የሚገዙበት ሥልጣን እየሰጣቸው መኾኑን ሲያጠይቅ አስቀድሞ “ሥልጣን ኹሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” ብሎ ነው። የሰማይና የምድር ሥልጣኑን ጠቅሶ ጀምሮ ከዚያ እነርሱን ሂዱ እንዲህ አድርጉ ሲል ሥልጣኑን ጭምር እየሰጣቸው መኾኑን ልብ ይሏል፤ ማቴ.28፥18። በዚህም ሐዋርያት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር አብ ጋር የተሳመረ የተልእኮት መስመር ላይ ገብተዋል።

የመጠበቅ ጸጋ፡


የመጠበቅ ሥልጣን ሐዋርያት ተሰጥቷቸዋል ስንል በአጭሩ በምእመናን ላይ እረኞች መኾንን ሰጥቷቸዋል ነው። ቤተ ክርስቲያን የበጎች መንጋ ናት። የክርስቶስ በጎች መንጋ። እነዚህ በጎች እግዚአብሔር ያሰባሰባቸው በጎች ናቸው። እነዚህን በጎች የሚጠብቃቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሐዋርያትን ግን እረኞች አድርጎ ሾማቸው፤ ዮሐ.21፥15-17።

ጠቅለል ስናደርገው የሐዋርያትን “የመላክ” ወይም “የሐዋርያነት” ሥልጣን ስናስብ እነዚህን በአጽንዖት እንመረምራለን።

·         ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ የተላከ የአብ አንድያ ልጁ እንደኾነ፤
·         ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተልእኮትን እስከ መጨረሻ ለተከተሉት ለ12ቱ ደቀ መዛሙርቱ እንደሰጠ፤
·         12ቱ ደቀ መዛሙርቱ ይህን “የሐዋርያነት” ተልእኮት ርሱ በባሕርዩ የሚያደርገውን በጸጋ እንዲያደርጉ እንዳስቻላቸው
·         12ቱ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሀብት የያዙ በምድር ላይ ብቸኞቹ መኾናቸውን፤ ሌሎች ይህ እንደሌላቸው ነው፤

ይህን ከላይ በነቁጥ የተገለጠውን አሳብ በደምብ ከተረዳነው ከዚያ በኋላ የሐዋርያት ሥራንና ጌታችን ሐዋርያቱን ለመጨረሻ ጊዜ ያነጋገረባቸውን አብነቶች በአጽንዖት መመርመርና የሐዋርያት እንቅስቃሴ እንዴት ሰማያዊ ሀብታቱን ጥቅም ላይ እንዳዋሏቸው መከታተል ነው።

3. የሐዋርያት ተከታዮች “ሐዋርያት” ተብለዋል፤


ጌታችን እና በሐዋርያት ዘመን የኖሩ የሐዋርያትን የሚመስል ለቤተ ክርስቲያን የማነጽ፥ የመጠበቅ፥ የእረኝነት ሥራ የሠሩ ኹሉ እንዲያ ይባላሉ። በተለይ መጽሐፈ ስንክሳር እሊህን የመሰሉ አበው “ሐዋርያው” “ሐዋርያ” ሲላቸው ይገኛል። ሐዋርያው ሉቃስ፥ ሐዋርያው ማርቆስ፥ ሐዋርያው ክርስቶፎሮስ፥ ሐዋርያው አግናጤዎስ (ምጥው ለአንበሳ) ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህን ሐዋርያት ያስባላቸው ሦስት ዐበይት ምክንያቶች፡

ሀ) በሐዋርያት ዘመን የኖሩ

ለ) ሐዋርያትን ያዩ፥ ከእነርሱው የተማሩ፥ እነርሱን የተከተሉ (አንዳንዶች እንዲያውም ጌታችንን ጭምር ያዩ፥ የተከተሉ)

ሐ) እንደ ሐዋርያት ኾነው ጳጳሳትን እረኞችን እየሾሙ ቤተ ክርስቲያንን ያደረጁ፥ የጠበቁ፥ ያስተማሩ፥ የባረኩ ናቸው።

እነዚህ ኹሉ ታዲያ ሐዋርያት ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ። የስም አጠራሩ ግን ከላይ ለ12ቱ ባስቀመጥነው መልኩ ሳይኾን በቅርበታቸው ምክንያት ነው። ከፈረንሳይ ውጪ ያለውን አውሮጳዊውን ኹሉ “ፈረንጅ” (ፍሬንች) እንደማለት ያለ ነው።

እነዚህ ቀደምት የሐዋርያት ተከታዮች ታዲያ አብዛኞቹ ከሐዋርያት በአንብሮተ ዕድ (እጅን በመጫን) እና በንፍሐት መንፈስ ቅዱስን እየነሱ በጵጵስና የተሾሙ በመኾናቸው እነዚያ ሐዋርያት ከጌታችን የተቀበሉት ሥልጣን ኹሉ የመባረክ፥ የማስተማርና የመጠበቅ ሥልጣን ለእነርሱም አላቸው። የመባረክ ሥልጣን (የሐዋ.8፥38-39)፥ የማስተማር ሥልጣን (ቲቶ.2፥15) እና የመጠበቅ ሥልጣን (የሐዋ.20፥28)። እዚህ ጋር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ዘንድ ይዞት የመጣውን ሥልጣን ለሐዋርያት፥ ሐዋርያትም ለተከታዮቻቸው ሰጧቸውን እንማራለን። ምክንያቱም እነዚህ ሀብታት በዘመናት ሂደት ውስጥ ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊዋ ስለኾኑ ነው።

በአጠቃላይ ስለ ሐዋርያት ተከታዮች “የተላኩ መኾን” ወይም “ሐዋርያነት” ስናወራ በአጽንዖት ልንመረምር የሚገባን ነገር፤

·         ሐዋርያት የተላኩ እንደኾኑ፤
·         ሐዋርያት የእግዚአብሔርን በረከት፥ እውነትና ጥበቃውን ለሰዎች መስጠት እንዲችሉ በጌታችን መሾማቸውን፤
·         ሐዋርያት ይህን የክህነት ሥልጣን ለተከተሏቸው ጳጳሳት መስጠታቸውን፤
·         ሐዋርያትን የተከተሉና ይህን የክህነት ሥልጣን በጵጵስና የተቀበሉም ለሌሎች ይህን መስጠታቸውን ነው።

ለዚህም የሐዋርያት ወራሾች የኾኑ እነዚህ አባቶች ኹሉ ይህን ሀብተ ክህነት፥ ሰማያዊውን የመባረክ፥ የማስተማር እና የመጠበቅ ሥልጣን ለሌሎች ይህን መረከብ ለሚችሉ አደራ ሰጥተዋል። ለዚህም በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በተላከች ዳግሚት መልእክት ላይ ምዕራፍ 3 ላይ ከቊጥር 1 ጀምሮ እስከ 10 ድረስ እንዴት አድርጎ ሊሾም እንደሚገባው መመሪያ ሰጥቷል። ተመሳሳይ መመሪያም ለቲቶ ተሰጥቶታል።

የሐዋርያነትን የተልእኮት ሥልጣን ከእነዚህ የተቀበሉም እንዲሁ ለሌሎችም እየሰጡ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ሥልጣነ ክህነት (ጵጵስና) ለዘላለም እንደሚኖርም ከትምህርተ ሐዋርት መረዳት እንችላለን። በጢሞቴዎስ ሁለተኛ መልእክት ላይ “ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ አደራ ስጥ” ሲል ይህን እናውቃለን፤ 2ኛ ጢሞ.2፥2። እዚህ ጋር ልብ ካልን ሐዋርያው ከጌታ ተልእኮቱን የተቀበለው አለ፤ ከርሱ የተቀበለ ጢሞቴዎስ አለ፤ ርሱ አደራ የሚሰጣቸው (የሚሾማቸው) አሉ፤ እነርሱ ሊያስተምሯቸው የሚችሉ (የሚሾሟቸው) አሉ። እንግዲህ የሐዋርያነት ተልእኮት በሐዋርያት ዘመን እንኳ እንዲህ ዐራት አምስት ደረጃ ሲሄድ እናያለን።

ጳውሎስ ሐዋርያስ …


እዚህ ጋር የጳውሎስ ሐዋርያ “ሐዋርያነት” እንዴት ያለ ነው የሚል ጥያቄም ሊነሣ ይችላል። ምክንያቱም ርሱ ከ12ቱ ወገን አልነበረምና፤ ዳግመኛም “ሐዋርያነቱ” የእነርሱን ያክል የሚበረታ እንጂ የተከታዮቹን ያክል ዝቅ ያለ አይደለምና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከ12ቱ ወገን አይደለም። ነገር ግን የሐዋርያነት ክብሩ ከእነርሱ በማናቸውም ኹኔታ የሚያንስ አይደለም።

ምክንያቱም የእነርሱን ሐዋርያነት ከፍ የሚያደርጉ ነጥቦች ያልናቸው ጌታን ማየታቸው፥ ድምፁን መስማታቸውና ይልቁንም የማስተማሩን በአጠቃላይ የሐዋርያነት ተልእኮቱን በቀጥታ ከባለቤቱ ከጌታችን መቀበላቸው ነው። እነዚህ ደግሞ ኹሉም ለቅዱስ ጳውሎስም መቀጸል ይችላሉ። እንደነርሱ ዞሮ ከርሱ አይማር እንጂ ዐይኑን አይቷል፥ ድምፁን ሰምቷል፥ ይልቁኑም የማስተማር ተልእኮቱን የተቀበለ ከርሱው በቀጥታ ነው።

በደማስቆ ጌታን ተገናኝቶ መመሪያውን ከተቀበለ ኋላ ከተማ ገብቶ ሐናንያን ተገናኝቶታል። ጌታም ራሱ “በአሕዛብም፥ በነገሥታትም፥ በእስራኤልም ልጆች ዘንድ ስሜን ይሸከም ዘንድ የተመረጠ ዕቃ” ብሎታል። ዳግመኛ ራሱ ሐዋርያው በቆሮንጦስ ቀዳማዊ መልእክቱ “እኔ ነጻ አይደለሁምን፤ ሐዋርያስ አይደለሁምን፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስንስ አላየሁትምን፤ … የሐዋርያነቴ ማኅተም በጌታ እናንተ ናችሁና፤” ሲል ይገልጣል፤ 1ኛ ቆሮ.9፥1-2።

4. በተለያየ ዘመን የተነሡ ሐዋርያውያን


በማናቸውም ዘመን የተነሡ ነገር ግን በሕይወታቸው፥ በተጋድሏቸው፥ በእምነት ትሩፋታቸው ኹሉ ፍጹም ሐዋርያትን የሚመስሉ፤ እነርሱን አኽለው፥ እነርሱን መስለው የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ያገለገሉትን ቅዱሳን አበው “ሐዋርያውያን” እንላቸዋለን። ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ፥ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ ከሐዋርያት የጎደለባቸው ጌታን በዐይነ ሥጋ አላዩም፥ ድምፁን አልሰሙም፥ አስተምሩ የሚለውን መለኮታዊ ተልእኮት “ሐዋርያነትን” ከጌታችን በቀጥታ የተቀበሉ ያይደሉ ነገር ግን በሐዋርያዊ ውርስ ውስጥ ይኸው ሥልጣን የተሰጣቸው ናቸው።

5. የክርስቶስ ተከታይ፥ ማናቸውም የተጠመቀ ክርስቲያን


የክርስቶስ ተከታይ የኾነ ኹሉ እንዲያ ይባላል። የተጠመቁትን ኹሉ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ መባል አግባብ ነው። ራሱ በምድር ዙራችሁ አሕዛብን ኹሉ ያስተማርኋችሁን ትእዛዝ እንዲጠብቁ እየነገራችኋቸው በሥላሴ ስም እያጠመቃችሁ ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው ብሎ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ አላፊነት ሰጥቷል። ስለዚህ እነርሱ የሚያጠምቋቸው ኹሉ ደቀ መዛሙርት፥ ሐዋርያት መባል ይችላሉ። እንዲያውም በአንጾኪያ ከተማ “ክርስቲያኖች” የሚለው ስም ሳይሰጣቸው በፊት በክርስቶስ ትምህርትና በሐዋርያት ስብከት አምነው የተጠመቁ በሙሉ “ደቀ መዛሙርት” ይባሉ እንደነበር ትምህርተ ቤተ ክርስቲያን ያስረዳል።

ነገር ግን ይህ ስም አጠራር ለግለ ሰብእ በነፍሰ ወከፍ አይወርድም፤ ማለት “ሐዋርያው ጨቡዴ፥ ሐዋርያው ተኮላ፥ ሐዋርያው ከበደ” አያስብልም። ይህ ግብርን ለመግለጽ ብቻ የሚያገለግል፤ ማለት አንድ ሰው የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመኾን መነሣቱንና መጀመሩን ብቻ የሚያመለክት ነው። ይህን ውሳኔ እና ይህን ግብር ለመግለጥ “ተከታይ” “ደቀ መዝሙር” ለማለት “ሐዋርያ” ሊባል ይቻላል። “ተለውኒ” “ተለዉኒ” እያለ 12ቱን እንደጠራቸው “ወዘኢነሥአ መስቀለ ሞቱ ወኢተለወ ድኅሬየ” ያላቸው አለያም “አነ አአምሮንን ወእማንቱ ይተለዋኒ” ያላቸው የመንጋው በጎች ኹሉ ሐዋርያ ናቸው።

ሦስቱ ሀብታት በእነዚህ እንዴት ይገለጣል ቢሉ እነዚህ ያላቸው የመባረክ ሥልጣን ውሱን ነው። ማዕዳችንን ስንባርክ ሌላው ሌላውም ኹሉ፥ ምኞታችንን፥ ፍትወታችንን መሥዋዕት ስናደርግ፥ ሰውነታችንን የተቀደሰ መሥዋዕት አድርገን ለእግዚአብሔር ስናቀርብ የመባረክ፥ የመቀደስ የመለየት ሥልጣን ይባላል። በማስተማር ረገድ ኹላችንም ከጥምቀታችን የተነሣ ወንጌልን ላልሰሙት የመንገር፥ የመመስከር ጸጋ ሲኖረን ይህ ማለት ግን እንደ ሐዋርያት ወይም ደግሞ እንደ ቅዱስ ሲኖዶስ ለእውነቱ ተጠቃሽ፥ ተመሳካሪ እንኾናለን ማለት ግን አይደለም።

ማጠቃለያ

እንግዲህ ከእነዚህ ከአምስቱ ውጪ ሐዋርያ የለም። በዘመናችን የምናያቸው ሐዋርያ ነን ባዮች ኹሉ ያልተላኩ መምህራን፤ ሐሰተኞች ደቀ መዛሙርት ናቸው። የቤተ ክርስቲያን ተልእኮት ከእግዚአብሔር አብ ጀምሮ ማን ማንን እንደላከ በግልጽ የሚታወቅ የተልእኮት ሰንሰለት (በቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊ ውርስ (Apostolic Succession) የምንለው) አለ። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ክርስቶስን ወክሎ፥ ሐዋርያትን አኽሎ ለመባረክ፥ ለመቀደስ፥ ወንጌልን በሥልጣን ለማስተማርና መንጋውን ለመጠበቅ የሚያስችለው ሥልጣን ከክርስቶስ በሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በኩል በሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ መጥቶ በነዲዮናስዮስ፥ በነጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት፥ በእነ እስክንድሮስ፥ በእነ አትናቴዎስ በኩል ፍሬምናጦስ እያለ መጥቶ ዛሬ የምናውቃቸው ጳጳሳተ እግዚአብሔር ጋር ደርሷል።

ከእግዚአብሔር አብ መንጭቶ በጌታችን በሐዋርያት በጳጳሳት እያለ ከሚሄደው ሐዋርያዊ ውርስ ውጪ ዘመን የፈለፈላቸው ኹሉ ያልተላኩ ሰባኪዎች ናቸው። ካልተላኩ ቢቀድሱ አያከብሩም፥ በፈትቱ አይለውጡም፥ ቢያጠምቁ ልጅነትን አያሰጡም። ሐዋርያ ካልኾኑና ካልተላኩ ማስተማር አይችሉም፤ ለእውነቱ ምስካሪ ማጣቀሻ መኾን አይችሉም። የራስን ፍልስፍና ካልኾነ በቀር ትክክለኛ የእግዚአብሔርን መገለጥ ለሰው ዘር ማድረስ አይቻልም። ሐዋርያው ራሱ እንዳለው ነው፡፡ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና። እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል፤ ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ፤ ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ፤” ካለ በኋላ ዋናውንና ወሳኙን ሰባኪ ለመኾን የሚያስፈልገውን መለኪያ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤ “መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸውተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ” ሮሜ.10፥14-15።

ዘመኑ ክፉ ነው፡፡ አጋንንት ራሳቸውን ቅዱሳን መናፍስትን እስኪያስመስሉ ድረስ መለወጥ መቻላቸውን ብዙ ሰዎች ያስተዋሉም አይመስልም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ከለላ ሥር ያሉ የሚመስላቸው ሰዎች ነገር ግን በመናፍስት አሠራር የተያዙ፤ ቅዱስ መንፈስን ጠርተው በርሱ ሥልጣን የሚያደርጉት የሚመስላቸውን፣ ነገር ግን ልብ ብለው በእምነት መንገድ ቢመረምሩት ዋጋቸው ከቻይና ዕቃ ይልቅ በወረደ አጋንንትና ኑ ሲሏቸው በሚመጡ ርካሽ መንፈሶች የሚሠሩትን ኹሉ እንደ ግብረ መንፈስ ቅዱስ የሚቈጥሩ፣ ሰይጣን ራሱን ፍጹም እስኪለውጥ ድረስ ብርሃናዊ መልአክን የሚያስመስል መኾኑንና ምንጩ ያልታወቀ ውስጣዊ ደስታ፣ መፍነክነክና ትፍስሕት እየሰጠ እያታለለ መውሰድ፣ በጀ ካሉትም ዕድሜ ሙሉ እንዲሁ ማኖር እንደሚችል፣ ይህንንም ደግሞ ሲፈልግ የተመረጡትንና ልባሞች ነን የሚሉትን እንኳ እያሳተ ሊያደርግ እንደሚችል፣ የሰውም ልጅ ይህንን ክፋቱን ሊያውቅበት ከፈለገ እንዲያው እንደ ዋዛ በቆሌና በዐይን በማየት ብቻ የማይታወቅ መኾኑን፣ ይልቁኑም በወንጌል እንደታዘዘ ልብ ብሎ በትሑት ልቡና በአማኝ ሕሊና መንፈስን ኹሉ ከየት እንደኾነ የመመርመር ግዴታ የተነገረለት መኾኑን ይዘነጋሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሚታወቀው በአማኝ ልቡናና የዚህን ዓለም ጣዕም ንቆ፣ ፍቅረ እግዚአብሔርን ናፍቆ፣ ሥጋን በመጎሰምና ምኞትን በማረም ሕይወት ውስጥ እንጂ በዓለም ሽብርቅርቅ ውስጥ እየፏለሉ ከኮራ እንቅልፍ ላይ ባንነው እንዲሁ ጠራኝ! አስነሣኝ! ገለጠልኝ! እያሉ እነ ነቢዩ ጨቡዴ እና ሐዋርያው ጓንጉል እንደሚፎግሩት አይደለም፡፡ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራና እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል፤ የሐዋ.14፣22፡፡ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ነው እንደ  መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና፤ 1ኛ ዮሐ.4፣1።


ስብሐት ለእግዚአብሔር ልዑል

አስተያየቶች