Sunday 23 February 2020

ልመናዋ ክብሯ በእኛ ለዘላለም ይደርብንና አምላክን የወለደች ክብርት እመቤታችን ያደረገችው ተአምር ይህ ነው

ልመናዋ ክብሯ በእኛ ለዘላለም በእውነት ይደርብንና አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን ያደረገችው ተአምር ይህ ነው፡- ለነቢያት ለሐዋርያት ለጻድቃንና ለሰማዕታት ሁሉ እመቤታቸው ድንግል ማርያም ናት፡፡ ምንም እንኳን ከአምላካቸው ዘንድ ለእነዚህ ሁሉ የድኅነት ቃልኪዳን ቢሰጣቸውም የቃልኪዳኑ መመኪያ አክሊል እናታችን ድንግል ማርያም ናት፡፡ ይህን የእርሷ ቃልኪዳን በመስማት አምነው አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ስም በመጥራት የዳኑትን ምን ያህል እንነግራችኋለን! በላዔ ሰብእ ትክክለኛውና የቀድሞ ስሙ ስምዖን ይባላል፡፡ አስቀድሞ ቅምር በሚባል አገር የሚኖር እጅግ ባለጸጋ ሰው ነበር፡፡ እንደ አብርሃም እንግዶችን እየተቀበለ ድኆችን እየመገበ የሚኖር ጻድቅ ነበር፡፡ የበጎ ነገር ሁሉ ጠላት ሰይጣን በዚህ ሥራው ቀናበትና ሊፈትነው በሦስት አረጋዊ ሽማግሌዎች ተመስሎ ‹‹ሥላሴ ነን›› ብሎ እንደ አብርሃም እንደተገለጠለት ሆኖ ተገለጠለት፡፡ ‹‹ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣል›› እንዳለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ 2ኛ ቆሮ 11፡14፡፡
ስምዖንም የዕውነት ሥላሴ መስለውት ተቀበላቸውና ተንከባከባቸው፡፡ የሚበሉት ምግብ ሲያቀርብላቸው እነርሱ ግን ‹‹ምግብ አንበላም፤ የምንጠይቅህን ግን ትፈጽምልን ዘንድ ቃል ግባልን›› አሉት፡፡ ስምዖንም የሚጠይቁትን ለመፈጸም ቃል ገባላቸው፡፡ እነርሱም ቃል ካስገቡት በኋላ ‹‹እንግዲያውስ የምትወደን ከሆነ አንድያ ልጅህን ሰዋልን›› አሉት፡፡ ስምዖን መጀመሪያ ላይ ቢደነግጥም በኋላ ግን ‹‹አብርሃም ልጁን ሊሠዋ አልነበረምን፣ እኔንም ሊፈትኑኝ ይሆናል›› ብሎ ለማረድ ወሰነ፡፡ አንድያ ልጁንም ሊሠዋው በተዘጋጀ ጊዜ ‹‹ተው›› የሚል ድምጽ የሚሰማ መስሎት ቢጠብቅ የሚሰማው ድምጽ ስላጣ አንድያ ልጁን አረደው፡፡ እንዲመገቡም ይዞላቸው ቀረበ፡፡ እነርሱም ‹‹መጀመሪያ አንተ ቅመስልን›› ሲሉት ቀመሰው ነገር ግን ወዲያው እነዚያ ሰዎች ከእርሱ ተሰወሩበት፡፡ ስምዖንም ሰይጣን በፈተና እንደጣለውና እንደተጫወተበትም ሲያውቅ አእምሮውን ሳተ፡፡ ከዚያ በኋላ ምግብ የሚባል ነገር አላሰኘውም፡፡ ይልቁንም የሰው ሥጋ የሚበላ ሆነ እንጂ፡፡ በመጀመሪያ የራሱን ቤተሰቦች አንድ በአንድ በላ፡፡ ቀጥሎም ጎረቤቶቹን፣ ጓደኞቹን ሁሉ በላ፡፡ አንት የውኃ መንቀልና ጦር ብቻ ይዞ ከቤቱ ወጥቶ በመሄድ በመንገድ ላይ ያገኘውን ሰው ሁሉ እየገደለ ይበላ ጀር፡፡ የበላቸውም ሰዎች ቁጥር በአጠቃላይ 78 ሆነ፡፡
ከዚህም በኋላ በመንገድ ሲጓዝ ተቀምጦ የሚለምን በደዌ የታመመ አንድ ደኀ አገኘና ሊበላው ፈለገ፡፡ ነገር ግን ወደ እርሱ በተጠጋ ጊዜ ቁስሉን አይቶ ተጸየፈው፡፡ ደኀውም ሰው ‹‹ስለ እግዚአብሔር ብለህ ከያዝከው ውኃ አጠጣኝ›› አለው፡፡ ስምዖንም ዝም ብሎት ሄደ፡፡ አሁንም ድኀው ‹‹በውኃ ጥም ልሞት ነውና ስለ ጻድቃን ብለህ ከያዝከው ውኃ አጠጣኝ›› አለው፡፡ ስምዖንም ዝም ብሎት ሄደ፡፡ ዳግመኛም ለ3ኛ ጊዜ ድኀው ‹‹ስለ አዛኝቷ አምላክን ስለወለደች ስለ ድንግል ማርያም›› አለው፡፡ በዚህም ጊዜ ስምዖን የእመቤታችንን ስም ሲጠራ ሲሰማ ሰውነቱን አንዳች ነገር ወረረው፡፡ ወደ ድኀውም ተመልሶ ‹‹አሁን የጠራከውን ስም እስኪ ድገመው? ስለ ማን አልከኝ?›› አለው፡፡ ድኀውም ‹‹ስለ አዛኝቷ አምላክን ስለወለደች ስለ ድንግል ማርያም›› አለው፡፡
ስምዖንም ‹‹ይኽቺስ ደግ እንደሆነች፣ በምልጃዋም ከሲኦል ነፍሳትን እንደምታወጣ ከህፃንነቴ ጀምሬ ሰምቼው ነበር እናትና አባቴ ይነግሩኝ ነበርና›› አለው፡፡ ድኀውም ‹‹አሁንም በእርሷ ተማጽኜብሃለሁ›› አለው፡፡ በዚህም ጊዜ ስምዖን ‹‹በል ንሣ አምላክን ስለወለደች ስለ ክብርት ድንግል ማርያም እንካ ጠጣ›› ሰጠው፡፡ ከማነሷም የተነሣ ከጥሪኝ ውኃ በቀር ወደ ጉሮሮው አልወረደም፡፡ በለዔ ሰብእም ከዚያች ጊዜ በኋላ አእምሮው ተመለሰለት፡፡ እንዲህም አለ፡- ‹‹በአንድ ዋሻ ውስጥ ገብቼ ስለ ኃጢያቴ አለቅሳለሁ፣ ሥጋዬ ከአጥንቴ እስኪጣበቅ እጾማለሁ፣ ወዮሊኝ ወዮታ አለብኝ›› አለ፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ዋሻ ገብቶ ምግብ ሳይበላ ውኃም ሳይጠጣ 21 ቀን ኖረና በረኀብ ሞተ፡፡ የጨለማ አበጋዞች ሰይጣናትም እያስፈራሩ እጅግ እያስደነገጡ ነፍሱን ወደ ሲኦል ሊወስዷት መጡ፡፡ ክብርት እመቤታችንም ፈጥና በመካከላቸው ተገኘችና አንዳች የሠራት በጎ ነገር እንዳለች መረመረች፡፡ እነርሱም እመቤታችንን ‹‹ከሰማይ በታች ከዚህ ኃጢአት የበለጠ አለን?›› አሏት፡፡ ክብርት እመቤታችንም ስለስሟ ብሎ ለድኀው ምጽዋት አድርጎ የሰጣትን ያችን ጥርኝ ውኃ በጎኑ አይታ ደስ አላት፡፡ ያችንም ነፍስ በመፍራትና በመንቀጥቀጥ ከእግዚአብሔር ፊት አደረሷት፡፡ ‹‹ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት የሥቃይ ቦታ ውሰዷት›› የሚል ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ፡፡ ክብርት እመቤታችንም ‹‹ልጄ ወዳጄ ይህችን ነፍስ ማርልኝ›› እያለች ሰገደች፡፡ ጌታችንም ‹‹እናቴ ሆይ! ሰባ ስምንት ነፍሳትን የበላ እንዴት ይማራል?›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹ልጄ ሆይ! የካቲት 16 ቀን በጎለጎታ የገባህልኝ ቃልኪዳንህን አስብ እንጂ፤ ‹ስምሽን የጠራውን፣ መታሰቢያሽን ያደረገውን፣ በስምሽም ቀዝቃ ውኃ ያጠጣውን፣ የተራበ ያለበላውን እምርልሻለው› ብለኸኝ የለምን?›› አለችው፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችንም ‹‹እውነት ነው መሐላዬን አላፈርስም›› አላት፡፡ ወዲያውም መላእክቱን ‹‹እስኪ ሚዛን አምጥታችሁ ያችን ጥርኝ ውኃ በአንድ ሚዛን፣ እነዚህንም 78 ነፍሳት በአንድ ሚዛን አድርጋችሁ በሚዛን አስቀምጡ›› ብሎ አዘዛቸው፡፡ መላእክትም በሚዛን ቢያስቀምጧት ጥርኝ ውኃዋ ከሰባ ስምንቱ ነፍሳት ይበልጥ መዝና ተገኘች፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ‹‹ስለ አንቺ ስል ምሬያታለው›› አለ፡፡ ያችም ነፍስ አምላክን በወለደች በክብርት እመቤታችን አማላጅነት ድና ወደ መንግሥተ ሰማያት ገባች፡፡
የበላኤ ሰብእ እመቤት የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክ ከቃልኪዳኗ ረድኤት በረከት ትክፈለን! (ገብረሥላሴ)

No comments:

Post a Comment