Sunday 23 February 2020

2. የመላእክት በሩካቤ መታማት! Part Two (በአማን ነጸረ)

2. የመላእክት በሩካቤ መታማት!
መላእክት እንደማያገቡና እንደማይጋቡ ጌታ በማቴ.22 ቁ 30 ነግሮናል፡፡በሌላ በኩል በዘፍጥረት 6 ቁ.2 ‹‹የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደሆኑ አዩ፤ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ›› ተብሎ ተጽፏል፡፡ለመሆኑ እነዚህ በዘፍጥረት ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች››፣ወይም በግእዙ ‹‹ደቂቀ እግዚአብሔር››፣በእንግሊዝኛው <<Sons of God>> የተባሉ ፍጥረታት እነማን ይሆኑ? በሚል ጥያቄ ሲቀርብ ከሚሰጡት 3 መልሶች አንዱ መላእክት ሳይሆኑ አይቀርም የሚል ነው፡፡3ቱን ብሂሎች በጥቂቱ እንይ፡፡ብሂሎቹ ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች›› የተባሉት፡- (1)አላውያን ነገሥታት ናቸው፣(2) መላእክት ናቸው፣(3) ደቂቀ ሴት ናቸው በሚሉ መላ ምቶች ዙሪያ ይሽከረከራሉ፡፡
2.1 አላውያን ነገሥታት (Despot) ናቸው የሚሉ የሚያቀርቧቸው ጥቅሶች አሉ፡፡(1) ‹‹አንሰ እቤ ‹አማልክት› አንትሙ ‹ወደቂቀ ልዑል› ኵልክሙ–እኔ ግን አማልክት ናችሁ ሁላችሁም ‹የልዑል ልጆች ናችሁ› እላለሁ›› የሚለው መዝ 81 ቁ. 6፣(2) በትንቢተ ዳንኤል 3 ቁ. 26 ‹‹የአራተኛውም መልአክ ‹የአማልክትን ልጅ› ይመስላል›› የሚሉት እና (3) በዘፍጥ 4 ቁ. 17 የቃየል ልጆች ከተማ መመስረታቸው መጻፉ እንዲሁም በዘፍጥ 6 ቁ.4 ጀምሮ የተጠቀሱት ኔፊሊም (Nephilim) ኃያልነት ድምር ነው ለኣላዊው ብሂል መነሻ፡፡ሆኖም ይሕ አመለካከት በፈንጆቹ ነው የሚንጸባረቀው፡፡የኛን ሊቃውንት አቋም በዚህ ቃል ዙሪያ እንይ ብንል ‹‹መለከ›› የሚለውን ቃል ‹‹ገዛ››፣‹‹ተመልአከ›› የሚለውንም ‹‹አለቃ ሆነ›› ብለው ይፈቱታል፡፡‹‹ኒቆዲሞስ…መልአኮሙ ለአይሑድ›› የሚል ቃል በቅ/ያሬድ ጾመ ድጓ ይደጋገማል፤ትርጉሙ ‹‹የአይሑድ አለቃ›› ማለት ነው፤መልአክ ማለት አይደለም፡፡ይሕን ግምት ውስጥ አስገብተን ሊቃውንቶቻችን ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች›› የተባለውን ትርጉም እንደ ፈረንጆቹ ለአላውያን ነገሥታት(የሕዝብ አለቆች) ሰጥተው ይተረጉሙታል ልንል እንችል ይሆናል፡፡ሆኖም እንሳሳተለን!ምክንያቱም አክሲማሮስ እንደሚተርከው ከዳዊት ጀምሮ ነው የነገሥታት ዘመን መቆጠር የሚጀምረው፡፡ አባቶቻችን የነቃየልን ዘመን ‹‹ዘመነ አበው›› እንጂ ‹‹ዘመነ-ነገሥት››(የአምባገነን አለቆች ዘመን) አይሉትም፡፡የዳንኤል ንባብም ቢሆን የተጻፈው ቅዱስ ገብርኤልን ለማመላከት ነው ተብሎ ታሪኩ ለታሕሳስ ገብርኤል ይተረካል፡፡ቅዱስ ያሬድ ‹‹ገብርኤል ብሂል ወልደ እግዚአብሔር›› ይላል ምዕራፍ በተሰኘ ድርሰቱ፡፡Gabriel የሚለውን ቃል ለጎግል ብናጎርሰው የሚሰጠን ትርጓሜ Son of God የሚል ነው፡፡በአጠቃላይ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይሕ ለዘፍጥረት 6 ቁ.1-4 ላለው ቃል የተቀመጠ ‹‹የአላዊነት›› ትርጉም ተቀባይነት የለውም ብንል የምንሸነፍ አይመስለኝም፡፡
2.2 ነገሥታት ካልሆኑ ‹‹መላእክት›› ናቸዋ!በሚል የሚቀርበው መከራከሪያ ሌላኛው ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች›› ትርጓሜ ነው፡፡የመከራከሪያውን መሪ ጥቅሶች እናመላክት፡፡
(1) ኢዮብ 2 ቁ.1 ‹‹ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤‹የአምላክ ልጆች› በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ››፣
(2) ኢዮብ 38 ቁ.7 ‹‹አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ ‹የእግዚአብሔር ልጆች› ሁሉ እልል ሲሉ መሰረቶቿ በምን ተተክለው ነበር››፡፡
(3) 2ኛ ጴጥ 2 ቁ.4 ‹‹እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጭለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠብቁ አሳልፎ ሰጣቸው››፡፡
(4) ይሑዳ ቁ.6-7 ‹‹መኖሪያቸውንም እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን ‹መላእክት› በዘለዓለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል፡፡እንዲሁም ‹እንደ እነርሱ› ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘለዓለም እሳት እየተቃጠሉ ምሳሌ ሆነዋል፡፡ዘፍጥ 19 ቁ 24፡፡››፡፡
(5) ኩፋሌ 6 ቁ.9 ‹‹የአዳም ልጆች በዓለሙ ሁሉ ይበዙ ዘንድ በጀመሩ ጊዜ እንዲህ ሆነ፤ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው፡፡‹የእግዚአብሔር መላእክትም› በዚሁ ኢዮቤልዩ በአንዲቱ ዓመት እነዚህን አዩአቸው…ሚስት ሊሆኑአቸው አገቡአቸው፤ወንዶች ልጆችንም ወለዱላቸው እነዚህም ረዓይት ናቸው››፡፡
(6) ከላይ ያሉት ጥቅሶችና መጽሐፈ ሄኖክ ምዕራፍ 2 ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች›› የተባሉ መላእክት ከሴቶች ጋር ልቅ ሩካቤ ፈጽመው ረዓይትን ወልደዋል ለሚለው አመለካከት ዋና መነሻ ሆነዋል፡፡የኢዮብ ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች›› የሚሉ ቃላት ቀጥታ መላእክትን ስለሚያመላክቱ ከዘፍጥር 6ቱ ቃል ጋር ተናበው ‹‹የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደሆኑ አዩ›› የተባለው ለመላእክት ነው የሚለውን አመለካከት ለመደገፍ ውለዋል፡፡የጴጥሮስና የይሑዳ መልእክታት በመላእክት የዝሙታዊ ድርጊትና ቅጣት መገለጫነት እንዲሁም ኩፋሌና ሄኖክ የመላእክትና የሰው ሩካቤ-ሥጋ ስለመኖሩ ቃል በቃል ጽፈዋል ተብለው በፈረንጅ ደባትር በተደጋጋሚ ተጠቅሰዋል፡፡ደባትሩ እንዳሻቸው!እነሱ እህ!ካሏቸው የማይሉት የለም፡፡እኔ ሀገራዊ የደብተራ ካባዬን ደርቤ ቀጥታ ወደ 3ኛው ኦርቶዶክሳዊ ብሂል እሻገራለሁ፡፡
2.3 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አቋም ‹‹የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደሆኑ አዩ›› በሚለው የዘፍጥረት ጥቅስ ውስጥ ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች›› ተብለው የተጠቀሱት ‹ሰማያውያን መላእክት አይደሉም፤ደቂቀ ሴት እንጂ› የሚል ነው፡፡የፊደል ተራ እየሰጠን የቻልነውን ያህል ከቤተክርስቲያናችን ያገኘናቸውን ማስረጃዎች እንጠቃቅስ!ከዚያ በፊት ግን ሴት ማለት አቤል በቃየል እጅ ከተገደለ በኋላ በአቤል ምትክ ለአዳምና ሔዋን የተወለደላቸው ወንድ ልጅ እንጂ እንደ አማርኛችን አነጋገር አንስታይ ጾታ ለመግለጽ የዋለ ቃል አለመሆኑ ይሰመርበት፡፡የስሙ ትርጓሜ ‹‹ምትክ›› ማለት መሆኑ በዘፍጥረት 4 ተጽፏል፡፡የሴት ዘሮች (ደቂቀ ሴት) ከቃየል ልጆች የተለዩ ቅዱሳን/ቅዱሳት፣ጸሎተኞች፣ምድር በጥፋት ውሃ ስትጠፋ በኖኅ በኩል ዘራቸው ተርፎ ከልጅ ልጃቸው ጌታ የተወለደ፣ለእግዚአብሔር ራሳቸውን የለዩ፣የመጀመሪያው ነቢይ፣ፀሐፊ፣መናኝና ወደ ብሔረ ሕያዋን የተነጠቀው ሄኖክ የወጣባቸው ቀደምት ቅዱሳን/ቅዱሳት ናቸው፡፡በቅድስናቸውና በንጽሕ አጠባበቃቸው የተነሳ መላእክት ተብለዋል፡፡ለዝርዝሩ ኦርቶዶክሳውያን መጻሕፍት ይጠሩ፡-
ሀ. መ/ር ተክለ ሚካኤል በተባሉ መተርጉም በኩል ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በማኅበረ ቅዱሳን አሳታሚነት እጃችን የገባው ገድለ አዳም ደቂቀ ሴትን መላእክት ያሰኛቸውን አኗኗር እንዲህ ይተርከዋል፤ ‹‹አዳም ከሞተ በኋላም ሴት ከቃኤል ልጆች የእርሱን ልጅ፣የልጅ ልጆቹን ለየ፡፡ቃየልና ዘሩም አቤልን በገደለበት በስተምዕራብ ጫፍ(እንደ ዘፍ.4 ቁ 16 ከዔደን በስተምራቅ) ወረዱ፡፡ሴትና ልጆቹ ግን በቤተ መዛግብት በሚገኘው ተራራ ደቡባዊ ክፍል ተቀመጡ፡፡…ከእነርሱ(ከሴት ልጆች) አንዱ ስንኳን ወደ ቃኤል ልጆች ይወርድ ዘንድ አልፈቀደም፡፡ስለ ንጽሕናቸውና ‹ስለወደቁት ሠራዊተ-መላእክት› ፈንታ የእግዚአብሔር ልጆች ተባሉ›› ሲል መላእክት የተባሉበትን ምስጢር ይገልጽልናል(ገድለ አዳም፡ገ.122)፡፡አዳም ከገነት ከወጣ በኋላ በሩ ላይ ሱራፊ ቢቆምም በቀቢጸ-ተስፋ ርቆ አልሄደም፡፡በእግረ-ገነት ሆኖ መላእክት በአፀደ-ገነት ሲያመሰግኑ ይሰማ ነበር፤ልጆቹም ርቆ ከሄደው ቃየልና ቤተሰቡ ውጭ የመላእክትን ምስጋና እየሰሙ ‹‹…እነርሱም በገነት መንገድ ያመሰግኑ፣ያከብሩም ነበር፡፡…ዳግመኛ ገነት ከእነርሱ ሩቅ አልነበረችም፡፡በመንፈሳዊ/በመልአክ/ ክንድ 15 ክንድ ነው፤ይህም በሰው 45 ክንድ (ወይም 22.5ሜትር) ይሆናል፡፡ሴትና ልጆቹም በተራራው ላይና በተራራው ታች ይኖሩ ነበር፡፡አይዘሩም፤አይለቅሙም፡፡ሥጋዊ ምግብም ስንዴም አያዘጋጁም፡፡ቁርባን ብቻ ነው እንጂ፡፡ከማደርያቸው ተራራም ከሚጣፍጡ ዕፀዋት ፍሬ ይመገቡ ነበር›› ይላቸዋል(ዝኒ ከማሁ፡ገ.124)፡፡ደቂ ሴት በዚህ የምስጋና ሕይወታቸው የተነሳ ‹‹እግዚአብሔርም መላእክት/ልጆቼ/አላቸው፤ታላቅ ደስታንም ተደሰተባቸው›› ተብሎላቸዋል(ዝኒ ከማሁ፡ገ.139)፡፡እንዲህ የተባለላቸው ደቂቀ-ሴት ቃየል አቤልን ገድሎ ደርቦ ካገባት ውቢቷ መንትያ እህቱ ሉድ በተወለዱ ቆነጃጅት ተማርከው ከደብር ቅዱስ ቁልቁል ተመዝገዘጉ፡፡መላእክት የሰው ልጆችን አገቡ የተባለ በዚህ ምክንያት ነው፡፡አወዳደቃቸውን እንይ!
ለ. የኦሪት ዘፍጥረት 6 ቁ.2 ትርጓሜ ፡- ‹‹ወሶበ ርእዩ ደቂቀ እግዚአብሔር ከመ ሠናያት እማንቱ አዋልደ ደቂቀ እጓለ እመሕያው ነሥኡ ሎሙ አንስትያ እምእለ ኃረዩ፡፡…የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑት ደቂቀ ሴት ደቂቀ ቃየልን መልከ መልካሞች እንደሆኑ ባዩ ጊዜ አንዱም አንዱ የወደዱዋትን የመረጡዋትን አንድ-አንድ አገቡ፤በአንዲት ሚስት ፀኑ ማለት አይደለም የጊዜውን መናገር ነው›› ይላል(መጻሕፍተ ብሉያት ክልኤቱ፡ገ.54)፡፡ በምን አይነት እይታ እንደወቀዱ ሲተርክ፤‹‹ከዕለታትም አንድ ቀን ደቂቀ ቃየል ሐፍረታቸውን አውጥተው እንደባዝራ እንደ አለሌ ሲንጠላጠሉ አይተው በሐፀ ዝሙት ተነደፉ፤ንዑ ንረድ ወንንሣዕ አሐተ አሐተ እምአዋልደ ደቂቀ እጓለ እመሕያው(ኑ!እንውረድ!ከሰው ልጆች ቆነጃጅት አንድ-አንድ እንውሰድ) ብለው ወርደው ቀርተዋል›› በማለት ነው(ዝኒ ከማሁ)፡፡‹‹ሰው›› የተባለ ቃኤል ነው፤‹‹መልአክ›› የተባለ ሴት!
ሐ. ቀሌምንጦስ ደቂቀ ሴት እንዴት ከንጽሕና ወደ ርኵሰት እንደወረዱ የሚተርክበት ቋንቋ እጅጉን ገላጭ ነውና እንሂድበት፤‹‹…የሴት ልጆች በሰይጣን ተታልለው የቃየል ልጆችን መከተል ጀመሩ፡፡በዚሁ በጣፈጠውም ዘፈን ዜማ ተመሰጡ፡፡ይህንንም መነሻ አርድገው ከደብር ቅዱስ እንደወረዱ ከክፉዎች የቃየል ልጆች ጋር ተጨመሩ፡፡የሴት ልጆች በዘፈን ተጠምደው ወደቁ፡፡በመብል፣በመጠጥና በዝሙት ተያዙ፡፡ሴቶች ጎልማሳዎችን በመከተል ተሯሯጡ፡፡ወንዶች እንደ ዱር አውሬ ዕራቁታቸውን እየሆኑ በገበያው ይዞሩ ጀመር፡፡…እጅግ ተሳሳቱ ሥጋቸውንም አረከሱ፡፡በቃየል ልጆች አመነዘሩ፤ብዙ የረከሰ አድራጎትን ፈጸሙ፤…ሰውነታቸውን አሳደፉ፡፡ነፍሳቸውን ረስተው በኃጢኣት ተጠመዱ፡፡…እንደ እንስሳት ሆነው ተገናኙ፡፡ግልጽ የአመንዝራነት ተግባር ፈጸሙ፡፡ሁለት ሦስት ሆነው ባንዲት ሴት ላይ ተገናኙ፤ምድርንም በመላዋ አረከሷት፡፡…በወደቀና በረከሰው ውድቀታቸው የሚያሰሙት ጩኸትና ዋይታቸው እንደ ባዝራ ፈረስ እስከ ደብር ቅዱስ ተሰማ›› ብሏል(መጽሐፈ ቀሌምንጦስ፣ምዕ.3 ቁ 40-44፡ገ.33-34)፡፡እነዚያ ከገነት በ22.5ሜትር ርቀት ላይ የነበሩ ንጹሐንና ንጹሐት ደቂቀ ሴት ባንድ ጊዜ እንዲህ ረከሱ፡፡ያገራችን ሰው ‹‹ጨረቃ ጥሶ የመጣ ዝናብ፣ቆብ ቀዶ የመጣ ሰይጣን መመለሻ የለውም›› ያለው የደቂቀ ሴትን ታሪክ ሰምቶ መሆን አለበት!
መ. በቀደመ ግብራቸው መላእክት የተባሉትን የደቂቀ ሴት በዝሙት የመውደቅ ታሪክ በመጽሐፈ ሄኖክና በመጽሐፈ ኩፋሌ እንዝጋው፡፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እነዚህን ቀደምት መጻሕፍት በብራና ጽፋ፣ደጉሳ፣ኋላ ኅትመት ሲመጣም ነጠላና አንድምታ ትርጓሜያቸውን አዘጋጅታ ቁጥራቸውን ከቅዱሳት መጻሕፍት በማካተቷ ያልተወራባት ነውር፣ያልተነገረባት ሐሜት የለም፡፡የሐሜቱ ትልቁ መነሻ 2ቱ መጻሕፍት ‹‹መላእክት ሩካቤ-ሥጋ ያደርጋሉ›› የሚል ምንባብ አለባቸው የሚል ነው፡፡ርእሱ በአጋጣሚ ሲነሳ ከዚህ በፊትም ነካክተነዋል፤ቢሆንም ሩካቤውን የተመለከተውን አመለካከት ነጥሎ ዳግም ማየቱ አይከፋም፡፡ዘርዘር አድርገን ሐሜቱን በኦርቶዶክሳዊ መንሽ እናበጥረው–እንዳቅማችን፡-
(1) በኦሪት ዘፍጥረት ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች›› ወይም በግእዙ ‹‹ደቂቀ-እግዚአብሔር›› የሚለው ምንባብ በኢኦተቤክ ‹‹የኦሪት ዘፍጥረትና ዘፀዐት ክፋይ (ኩፋሌ)›› በምንለው መጽሐፈ ኩፋሌ 6 ቁ.9 ‹‹የእግዚአብሔር መላእክት›› ወይም በግእዙ ‹‹መላእክተ-እግዚአብሔር›› ተብሎ ነው ደረቁ ንባብ የቀረበው፡፡መጋቤ ብሉይ ሠይፈሥላሴ ዮሐንስ ኩፋሌ 6.ቁ 9ን፤‹‹ደቂቀ ሴት…በደብር ቅዱስ እንደ መላእክት ቅዱስ!ቅዱስ!ቅዱስ! እያልን እንኖራለን፣ከደቂቀ ቃየል አንጋባም ብለው ነበርና ስለዚህ ‹መላእክት› አላቸው›› ሲሉ ትርጓሜውን አሰምተውናል፡፡መላእክት=ደቂቀ ሴት!
(2) ለቁጥር የሚያታክቱ ፈረንጅ የሥነ መለኰት ‹‹ተማራማሪዎች›› መጽሐፈ ሄኖክን ስለመላእክትና ስለሰው ሩካቤ ጽፏል እያሉ ያሳስታሉ፡፡እሱ ግን በግልጽ በምዕራፍ 4 ቁ.82-83፡- ‹‹አባቶቻቸው ከደብር ቅዱስ ከወረዱ ከደቂቀ ሴት ተወልደው ነበርና ወገኖቻቸው ከሚሆኑ ከሴት ክፉ ልጆች ተወለዱ፡፡ቀድሞ የንጽሕና መሰረት የነበሩ እነዚህም በዚህ ዓለም ክፉ ልጆች ይሆናሉ፤ክፉ ልጆችም ይባላሉ›› ሲል መላእክት የተባሉት ደቂቀ ሴት እንደነበሩ ይጠቁመናል፡፡
(3) በደቂቀ ሴትና በደቂቀ ቃየል ተራክቦ የተወለዱት ልጆች በግእዙ ‹‹ያርብሕ››፣በአንድምታው አማርኛ ‹‹ረዓይት››፣በመደበኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ‹‹ኃያላን››፣በእንግሊዝኛ‹‹Giants›› ይባላሉ፡፡ግእዛችን ‹‹ኔፊሊም›› የሚለውን ቃል አይጠቀምም፤‹‹ያርብሕ›› ነው የሚላቸው–አርበኛ ማለት ነው፡፡
(4) እርግጥ ነው፤የመጽሐፈ ሄኖክ ምዕራፍ 2 ትርጓሜ ረዓይት 2ትና 3ሺሕ ክንድ የሚረዝሙ ግዙፍ ፍጥረታት መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ሆኖም ግዝፈታቸው ከመላእክት ስለተወለዱ እንዳልሆነ እዚያው ዝቅ ብሎ በምዕራፍ 5 ቁ.1 ‹‹ወገኖቻቸው ከሚሆኑ ከደቂቀ ሴት የተወለዱ የረዓይት ሞታቸው በወጡበት ቦታ ነው›› ይላል፡፡ከሥጋ ለባሽ የተገኙ ሥጋ ለባሾች መሆናቸውን አልካደም፡፡ግዝፈታቸውም በዘፍጥረት 6 ቁ. 4 በግልጽ የተመለከተ ነው፤ልዩነቱ ሄኖክ ቁመታቸውን በክንድ አስቀመጠው፡፡
(5) የሄኖክ 2 አንድምታ ‹‹…የሰማያት ልጆች እነርሱን አይተው ወደዱአቸው፤መላእክት የተባሉ ደቂቀ ሴት ናቸው፤‹ወሰምዮ መልአከ በእንተ ንጽሑ› እንዲል ›› ይላል (መጽሐፈ ሄኖክ፣አንድምታ ትርጓሜ፡ገ.10)፡፡ሴትን ‹‹ስለ ንጽሕናው መልአክ ብሎ ጠራው›› እያለን ነው!
(6) እንደ መጽሐፈ ሄኖክ ምዕራፍ 2 አንድምታ ‹‹የእግዚአብሄር መላእክት›› የሚለው ቃል ባለክንፍ ረቂቃን መላእክትን ሳይሆን ደቂቀ ሴትን የሚገልጽ አነጋገር ነው፡፡መላእክት የተባሉትም፡- በንጽሕናቸው፣ከፍ ካለው ደብር ከደብር ቅዱስ የመላእክትን ምስጋና እየሰሙና እያመሰገኑ በመኖራቸው፣መዓርጋቸው ከፍ ካለው መዓርግ ስለደረሰ ነው፡፡እንጂ ሥጋ ለባሽነታቸው አልተዘነጋም፤ቃሉም ለመላእክት ሳይሆን ለነሱ የተነገረ ዘይቤአዊ አነጋገር ነው!ምነው እኛስ ‹‹እከሌ እኮ መልአክ ነው›› እንል የለ፤ሄኖክና ኩፋሌም እንዲያ ማለታቸው ነው፡፡
(7) የኦሪት ዘፍጥረት ከምዕራፍ 6 እስከ ምዕራ 11 የሚዘልቁ የፈጣሪ ቁጣ፣እግዚአብሔር ሰውን በመፍጠሩ መፀፀቱ፣ኖኅን ለይቶ አስቀርቶ ሌላውን ትውልድ መደምሰሱ፣…የሚያሳዩት ከላይ በቀሌምንጦስና በዘፍጥረት አንድምታ የተገለጹ ነገር ግን በመደበኛው መጽሐፍ ቅዱስ በዝርዝር ያልተገለጹ ኃጢአቶች በቃየልና በሴት ልጆች መፈጸማቸውን ነው፡፡
(8) ዘፍጥ 6 ቁ.5-6 ‹‹እግዚአብሔርም የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ። እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ። እግዚአብሔርም። የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ከሰው እስከ እንስሳ እስከ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና አለ›› ከማለት በቀር እግዚአብሔርን ያስቀየሙ የሰው ልጅ ዝርዝር የርኵሰት ተግባራትን አይገልጽም፡፡ይሕን ክፍተት ለመሙላት የኛዎቹን አንድምታዎች፣ትውፊታውያኑን መጻሕፍት፣ኩፋሌንና ሄኖክን ነጭ ደባትር ሳይቀሩ ይጠቀሙባቸዋል–መልሰው ለማጣጣል ቢፋጠኑም!
(9) ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹ረዓይት›› የሚለውን ቃል በመጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ገጽ 845 ሲያብራሩ፤‹‹ሰብአ ትካት፤እኩያን ዐርበኞች፣ርስ በርሳቸው የሚባሉ፣ኃይላቸውና መጠናቸው ከሰው ልክ ያለፈ(ና) የተረፈ፤እንደ ጥድና ዝግባ ያሉ፤ከጥድ ከዝግባም የሚበልጡ፡፡ከፍ ከፍ የሚሉ ገናኖች፣ረዣዥሞች፡፡ደቂቀ ሴት ያባታቸውን ሕግ አፍርሰው፣ርግማኑን ጥሰው ከቃየል ልጆች ቢጋቡ እንደዚህ ያሉ ሕዝብ ተወልደዋል፡፡ዘፍ.6 ቁ1.-7›› ሲሉ በመጽሐፈ ኄኖክ፣በምሳሌና በጥበብ የሚገኙ ግእዝ ኃይለ ቃላትን በማስረጃነት ጠቅሰዋል፡፡
(10) አንዳንድ ኦርቶዶክስን ለማደስ ‹‹የኃላፊነት ሹመት›› ለራሳቸው የሰጡ ቆናጽል ዘመዶቻችን ደግሞ የዘፍጥረት ምዕራፍ 6፣የይሑዳ ቁ.7፣የ2ኛ ጴጥ ምዕራፍ 2 የመሳሰሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ካነሱት ውጭ ኩፋሌና ሄኖክ የተለየ ቃል እንዳመጡ አድርገው ለተዛወሩበት ቡድን ማሊያ ማስተዋወቂያ ኩፋሌንና ሄኖክን ይሰዋሉ!ነውር!!!ያውም እኮ በ190ዎቹ መጀመሪያ በዘመቻ ፊልጶስ ፀረ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ያሰለጠነንን፣በመጽሐፈ ሄኖክ ትርጓሜ ዙሪያ ተጠያቂ የነበረውን፣የኩፋሌንና የሄኖክን ትርጓሜ በመቅረጸ ደምጽ አኑሮልን ያለፈውን፣በ2000 ዓ.ም ከግእዙ ተስማምቶ ከኩፋሌና ሄኖክ ጋር ባንድ ላይ ተጠርዞ የወጣውን 81ዱ መጽሐፍ ቅዱስ በመሪነት ያዘጋጀውን፣ወዲህ በኢትዮጵያዊነቱ እንዲያም ሲል ቤተሰቦቼ ከፈለቁባት ከማኅፀነ ግዮን በመፍለቁ የምኮራበትን ሊቅ መጋቤ ብሉይ ሠይፈሥላሴ ዮሐንስን ‹‹አባታችን›› እያሉ ነው ‹‹የኢኦተቤክ መላእክትና ሰው ተጋቡ የሚል ቅዱስ መጽሐፍ አላት›› እያሉ የሚፈላሰፉት፡፡ድንቄም ተፈላስፈዋል አያ!ተፈላስፈው ሞተዋል፡፡ይልቅስ ይህን በዚሁ አሳድረን ስለ ነገረ ሩካቤ ፈላስፎች የሚሉትን እንይ፤ከዚያ በፊት አንዲት ስርዋጽ….
ቀዳሚት ስርዋጽ፡- ሰው በቅድስት ሥላሴ አምሳል ተፈጥሯል ካልን ሥላሴ ጾታ አላቸውን?
ኦሪት ‹‹እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ ፈጠረው›› ትላለች፡፡ስለዚህ የሰው አካላዊ መዋቅርና ገጽታ የእግዚአብሔርን ይመስላል ማለት ነው፡፡እንደሱ ከሆነ ለቅድስት ሥላሴ እንደ ሰው የመራቢያ አካል አላቸው ማለት ይቻላልን?ጥያቄው ኅሊናችንን ሸምቀቅ ያደርጋል፡፡ቢሆንም ጥያቄው አዲስ አይደለም፡፡አበው አንስተውት የራሳቸውን አተያይ አኑረውልናል፡፡ከነጥያቄና መልሳቸው በራሳቸው ቋንቋ እንስማቸው! ‹‹የሥላሴ አባለ ዘርእ የላቸውም ካሉ ‹ንግበር ሰብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ› ብለው የፈጠሩት አዳም አባለ ዘርእ ይዞ ተገኘሳ?! ‹ለሥላሴ (አባለ ዘርእ) የላቸውም ማለት አካል ማጉደል አይሆንምን?!› ቢሉ ይህስ አካል ማጉደል አይባልም፡፡የማንኛቸው አለባቸው ይሏላ?!የአዳም አለባቸው እንዳንል ሔዋንን ፈጥረዋታል፡፡የሁለቱም አለባቸው ማለት ስድብ ነውና (ለሥም አጠራራቸው ምስጋና ይሑንና ‹ፍናፍንት› ያሰኝብናል)፡፡ስለዚህ ነገር ለሥላሴ አባለ ዘርእ የወንድም የሴትም የላቸውም ብሎ ያምኑ ዘንድ ይገባል፡፡የወንድም የላቸውም ካልን ‹አዳምን በማን አምሳል ፈጠሩታ?!› ቢሉ አዳምንስ መዋቲ ስለሆነ እንዲዋለድ ዘር እንዳይጠፋ አባለ ዘርእ ያለው አድርገው ፈጥረውታል፡፡…ለሥላሴ አባለ ዘርእ የሴትም የወንድም የላቸውም ካሉ ስለምን መጽሐፍ በሴትም በወንድም ይመስላቸዋል?!ቢሉ ይህስ የመጽሐፍ ልማድ ነው፡፡አባለ ዘርእ የሌለውን ሁሉ በሴትም በወንድም ይጠራል…››ይላል የቆጋዎች መጽሐፍ (ወልደ አብ፡ገ.77-78)፡፡
አባለ ዘርእ ሳይኖራቸው በወንድና ሴት አንቀጽ እየተለዋወጠ ከተጠሩት ውስጥ ነፍስን እናገኛለን፡፡ነፍስ በወንድ አንቀጽ ሲጠራ ‹‹መንፈስ እምከመ ወጽአ ኢይገብእ–ወጥቶ የማይመለስ መንፈስ ሥጋም እንደሆነ አስቦ…›› ይላል መዝ 77 ቁ.39፡፡‹‹እምከመ ወጽአ/ወጥቶ የማይመለስ›› የሚለው ሐረግ ነፍስን በተባእታይ ጾታ ይገልጻል፡፡ነፍስ በሴት አንቀጽ ስትቀርብ ‹‹አኀሥሥ ዘአፍቀረቶ ነፍስየ–ነፍሴ የወደደችውን…እፈልጋለሁ›› ትባላለች(መኃ.3ቁ2)፡፡ወንድነትና ሴትነት የሌላት ረቂቋ ነፍስ በአነጋገር በ2ቱም ፆታ ትጠራለች ማለት ነው፡፡ምሳሌው ለፀሐይም ይሠራል፡፡መጽሐፍ ፀሐይን ‹‹ፀሐይኒ አእመረ ምዕራቢኁ–ፀሐይ መግቢያውን ያውቃል›› ብሎ በመዝ 103 ቁ. 9 በወንድ አንቀጽ ይጠራዋል፤በሴት አንቀጽ እንዲሁ‹‹ ወድቀት እሳት ወኢርኢክዋ ለፀሐይ–እሳት ወደቀች ፀሐይንም አላዩአትም›› ይላታል ፀሐይን(መዝ.57 ቁ. 8)፡፡
ነፍስና ፀሐይ የተጠቀሱት ሥላሴን በሴትና ወንድ መጥራት ፆታ እንዳላቸው ለማመልከት ሳይሆን አጠራሩ የመጽሐፍ ልማድ ነው ለሚለው መከራከሪያ አስረጂ እንዲሆኑ ነው፡፡ሥላሴ በወንድ አምሳል ‹‹ቅዱስ!ቅዱስ!ቅዱስ!አሐዱ አምላክ›› ይባላሉ፡፡‹‹ቅዱስ›› የሚለው ቃል ለተባእት ነው የሚነገር፤አሐዱም እንዲሁ፡፡ለሴት ሲሆን አሐዱ ሳይሆን ‹‹አሐቲ›› ነው የምንል፡፡በዘፍጥረት 18 ቁ. 2 ያለው ‹‹ወናሁ ሠለስቱ ዕደው ይቀውሙ መልዕልቲሁ–እነሆ ሦስት ሰዎች ከበላዩ ባለ ተራራ ቁመው አያቸው›› የሚል ቃል ውስጥ የግእዙ ‹‹ዕደው›› ትርጉም ‹‹ወንዶች/ጎልማሶች›› ማለት ነው፡፡ስለዚህ ሥላሴ በወንድ አንቀጽም ይጠራሉ፡፡በሌላ በኩል ስለ ርኅራኄያቸው፣ስለ መጋቢነታቸው፣አርግዛ የምትወልድ እናት እናትነቷ እንደማይጠረጠር የፍጥረት አስገኝነታቸው ለማይጠረጠር ፈጣሪነታቸው በሴት አንጽ ‹‹ቅድስት ሥላሴ›› ይባላሉ፡፡‹‹ቅድስት›› ለሴት ብቻ የሚነገር የቅድስና ቃል ነው፡፡አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ይህን ለመግለጽ ‹‹ኀበ ርኅራኄክሙ በዝኀ ወኀበ አልቦቱ መስፈርት፣እለ ትሰመዩ በሥመ ብእሲት፣ሥላሴ ዕደወ ምሕረት›› ሲል ርኅራኄያቸውን በሴት ከመጠራታቸው ጋር አያይዞ ተርኮታል፡፡በዚህ ርእስ ይብቃን፤ከዚህ በላይ ማለት አንችልም፡፡ሥሉስ ቅዱስን በሰጊድ እጅ ነስተን በእልባት ወደታጠፈው ርእሳችን እንመለስ…
3. ሩካቤ ሥጋ ከፍልስፍና አንጻር (ቁንጽል ንጻሬ)!
ነጮቹ ፈላስፎች በነገረ-ሩካቤ (Sexuality) ዙሪያ Metaphysical Sexual Pessimisim እና Metaphysical Sexual Optimisim በሚል እንደሚከፈሉ በዚህ http://www.iep.utm.edu/sexualit/ ተነግሮናል፡፡Metaphysical የሚለው ቃል በደርግ ዘመን በወጣው ሌኒኒስት ማርክሲስት መዝገበ ቃላት ‹‹ዲበ አካል›› ተብሎ ተተርጉሟል፤ከአካል በላይ የሆነ፣መንፈሳዊ ማለት ነው፡፡ሩካቤ ከሥጋዊም ባለፈ መንፈሳዊ ተመስጦ እንዳለው ለማመልከት ይመስላል የቃሉ ጠቋሚነት፡፡Pessimisim የሚለውን ‹‹ሕርመት/ትሕርምት›› ብለን ብንተረጉመው ያስኬዳል፡፡Optimisimን ‹‹ፍቅድ/መፍቅድ›› ብንለው ለቃሉ ትርጓሜ ይቀርባል፡፡ስናገጣጥማቸው 2ቱ ፍልስፍናዎች ‹‹ትሕርምተ-ሩካቤ- Sexual Pessimisim-›› እና ‹‹መፍቅደ-ሩካቤ–Sexual Optimisim›› ሊባሉ ይችላሉ፡፡ፈላስፎቹንም ‹‹ኅሩማነ-ሩካቤ››(ሩካቤን እንደ እርም የሚመለከቱ) እና ‹‹መፍቅድያነ-ሩካቤ››(ሩካቤን በበጎ የሚመለከቱ) ልንላቸው እንችላለን፡፡ፍልስፍናዎቹን በቁንጽል እጅግ በቁንጽል የድኩም ደብተራ ንባብ እንያቸው፡፡
3.1 ኅሩማነ-ሩካቤ (Pessimists) የተባሉት ፈላስፎች ሩካቤ ሥጋ አንድ ሰው ሌላውን ለፍትወት ማብረጃ የሚፈልግበት ሥርዓት በመሆኑ ከሩካቤ በፊትና በኋላ ሰውን እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ቁስ ወይም እንደ ዐላማ ማስፈጸሚያ መሳሪያ (Object of appetite) እንድናይ ያደርጋሉ ሲሉ ይተቹታል፡፡ከሩካቤ በፊት ተቃራኒ ጾታን ያልሆኑትን ሆኖ ለማሳመን አካላዊ (physical) ፣ ውሳጣዊ (psychological) ፣ ስሜታዊ (emotional) እና አእምሮአዊ (intellectual) ብልሃቶች ሁሉ ስለሚተገብሩ ሂደቱ ሰውን ከክቡር ተፈጥሮው ያወርዳል ይሉታል፡፡በሩካቤ ውስጥ ያለው ፍትወት (ፍላጎት) ትኩረቱ የተጓዳኙ ሰብእና ሳይሆን የተነሳሳው አባለ ዘርእ ተጣማጅ የሆነውና በዚያኛው ወገን ያለው የምኞት ማረፊያ የሆነ የተቃራኒ(?) ጾታ አባለ ዘርእ ነው፡፡በግብር መተዋወቅ ጊዜ 2ቱም አንዱ ባንዱ ልባቸው ተሰውሮ ራሳቸውንም ተጓዳኛቸውንም ይረሳሉ፤ይኸውም አንዱ ሌላውን እንደ መገልገያ (የእርካታ መሳርያ) ስለሚመለከት ነው፡፡
3.2 ስለሆነም ሩካቤ ለራስም ሆነ ለተጓዳኝ ክብረ-ሰብእና የኀሳር እንጂ የክብር ተግባር አይደለም ይላሉ እነ ኢማኑኤል ካንትና ቅዱስ ኦገስቲን፡፡በራሳቸው አማርኛ ‹‹…with its uncontrollable arousal, involuntary jerkings, and its yearning to master and consume the other person’s body. During the act, a person both loses control of himself and loses regard for the humanity of the other. Our sexuality is a threat to the other’s personhood; but the one who is in the grip of desire is also on the verge of losing his or her personhood.››. በእነ ካንት አመለካከት በ1ኛ ቆሮ 7 እንደተጻፈው ከሩካቤ መታቀብ ቀዳሚው የሕወት ምርጫ ነው፡፡ያ!ካልተቻለ ሩካቤ መደረግ ያለበት ሁለት የተለያየ ጾታ ያላቸው ተጋቢዎች አንድ ለአንድ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ለመዝለቅ ተስማምተው ጋብቻ ከመሰረቱ በኋላ ሆኖ እሱም ቢሆን ዘር ከመተካት ያለፈ ተራክቦ መሆን የለበትም፡፡ዘር ከመተካት ባለፈ ለፈቃደ-ሥጋ ብቻ የሚደረግ ሩካቤን አይደገፉም፡፡‹‹pessimistic metaphysicians of sexuality conclude that sexual activity is morally permissible only within marriage (of the lifelong, monogamous, heterosexual sort) and only for the purpose of procreation>>. ዘር ከመተካት የተለየ ዐላማ ያለው ለደስታና ለፈቃደ ሥጋ ማሳተገሻ የሚደረግን ተራክቦ ነውር ነው በእነሱ፤‹‹seeking pleasure is an impediment to morally virtuous sexuality, and is something that should not be undertaken deliberately or for its own sake. >>
3.3 መፍቅድያነ-ሩካቤ(Metaphysical sexual optimists) የተባሉት ፕላቶ፣ራስልና በመጠኑ ፍሮይድ መሆናቸውን ከላይ የቀረበው አድራሻ ነግሮናል፡፡በዚህ በኩል ያሉት፡- ‹ሩካቤ ሥጋ ሰዎች በገቢረ-ፈቃድና ያለገቢረ-ፈቃድ የሚተሳሰሩበት ተፈጥሮአዊ የደስታ ምንጭ ነው፤ሂደቱ ራስንም ሌላውንም ሐሴት ማላበስ ስላለበት የስሜት ቅብብሎሹ አንዱ ለአንዱ መሰጠትን ፈጥሮ ሰብአዊ ትስስርን የጠበቀና የጠለቀ ያደርጋል›› ይላሉ፡፡እነዚህ እንደሚሉት፡- ሩካቤ በራሱ መጥፎም ደግም አይደለም፤እንደ ገቢሩ ዓላማ ግብረ ገብነት የሌለበት (“vulgar” eros) እና ግብረ ገብነት ያለበት(“heavenly” eros) ሊኖር ይችላል፡፡ግብረ ገብነት የሌለበት ሩካቤ በማንኛውም መንገድ ለፍትወተ-ሥጋ እርካታን(ቃሉ ጸያፍ ሆነ እንጂ ‹‹ማብረጃ›› ቢባል ይሻል ነበር) ማግኘት ብቻ መፈልግና ስለ ተጣማጅ ደንታ ሳይኖር በራስ ወዳድነት ሩካቤን መሻት ነው፡፡(እዚህም ቃሉ ባያውከን ‹‹መቀንዘር›› የሚለው ቃል ነው ገላጩ፤((በቅንፍ-ቅንፍ ተሸሽገን ‹‹የቆመበት የቆመ አያይም!›› የሚለውን የገበና ተረት ብንተርተው ለ”vulgar” eros ልከኛ አማርኛ ተገኘ ማለት ነው))፡፡በሌላ በኩል ግብረ ገብነት ያለበት ሩካቤ (“heavenly” eros) ከማንኛውም ተጣማጅ ጋር ፍተወትን ለማርካት መጣደፍ ሳይሆን ከአንድ ተወዳጅ የሕይወት አጋር ተጎዳኝቶ የአጋሩን ማንነት፣ሰብእና፣ደኅንነትና ስሜት እንደ ራስ ወዶና ፈቅዶ የሚደረግ አእምሮአዊ፣አካላዊና መንፈሳዊ ተራክቦ ነው፡፡ይህች የተቀደሰች የሩካቤ መንገድ ሰው አእምሮና ለብዎ ያለውና ፍትወቱን የሌላውን ስሜት ባገናዘበ መልኩ በተፋቅሮ የሚገልጽ ክቡር ፍጡር መሆኑን ታሳያለች፡፡”Animals have sex and human beings have eros” መባሉም ለዚህ ነው ብለውናል ፈረንጆቻችን፡፡በአንዲት ቁንጽል መረጃ ፈረንጆቹን ከዳሰስን ወዲህ እንመለስ፡፡
3.4 ባገራችን የፈላስፎች በኩር ተደርጎ በስፋት የተነገረለት ዘርዐያዕቆብ (ጠቢቡ/ፈላስፋው) ከተመጠነች ድርሰቱ አንጻር ከታየ ቀላል የማይባል ቦታ ለጋብቻና ለተራክቦ ሰጥቷል (ለነገሩ ስለተራክቦና ስለ ፈጣሪ ባይሞግት ኖሮ በኛ አገር አመለካከት ፈላስፋ የሚለው አይገኝም ነበር!)፡፡ፈላስፋው የሙሴን ተከታዮች በሙሴ መጻሕፍት ውስጥ ከጥበበ-ፈጣሪና እና ከሕገ-ተፈጥሮ ያልተስማማ ስርዋጽ ጨምረዋል ሲል ይከስሳል፡፡ሙሴ ስለርኩሰትና መንጻት በዘሌዋውያን 12 የጻፈውን ዘርዐያዕቆብ የተቀበለው አይመስልም፡፡ይናገራል፤‹‹…የሰው ፍጥረት እንዳይጠፋ ልጆች ለመውለድ በፈጣሪ ፈቃድና በተፈጥሮ ሥርዓት ወንድና ሴት በሥጋዊ ግንኙነት ይገናኙ ዘንድ ታዟል፡፡እግዚአብሔር በሰው የተፈጥሮ ሕግ ውስጥ ያቆመው ይኽ የሥጋ ግንኙነት ርኵስ ሊሆን አይችልም፤ምክንያቱም እግዚአብሔር የእጁን ሥራ አያረክስም›› (ሐተታ ዘርዓያዕቆብ፣ትርጉም በፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፡ገ.21)፡፡ቅ/ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ 7 ቁ. 1 ‹‹ይኄይሶ ለብእሲ ኢቀሪበ አንስት–ከሴት አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው›› ሲል የራሱን ድንግላዊ ሕይወት አብነት አድርጎ ጽፏል፡፡ይኽን ሐዋርያዊ ቃል ፈላስፋው ዘርዐያዕቆብ ‹‹…ጋብቻ ፈጣሪ ካቆማቸው ሥርዓቶች ውስጥ እንደሆነ ልቡናችን ይነግረናል፤ያስረዳናልም፡፡ምንኵስና ታዲያ የፈጣሪን ጥበብ ይሽራል፤ምክንያቱም ልጆች መውለድን ይከለክላል፤የሰውንም ፍጥረት ያጠፋል፡፡የክርስቲያን ሕግ ‹ምንኵስና ከጋብቻ ይሻላል› ስትል ውሸት ተናግራለች፡፡ከእግዚአብሔር አይደለችም፤ምክንያቱም የፈጣሪን ሕግ የሚያፈርስ ሥርዓት እንዴት ከእሱ ጥበብ ይሻላል?የሰው ሐሳብ የእግዚአብሄርን ሥራ ሊያሻሽለው ይችላልን?›› ሲል ይሞግታል(ዝኒ ከማሁ፡ገ.23)፡፡
3.5 ቅ/ያሬድ ጾም ፍትወታተ-ሥጋን ለመግታት ያላትን ኃይል ‹‹ጾም ትፌውስ ቁስለ ነፍስ፣ወታጸምም ለኵሎ ፍትወታተ ዘሥጋ›› ሲል ያዜመውን ዜማ ዘርዐያዕቆብ ነጠቅ አድርጎ ‹‹የጾም ሕግ የተሠራው የሥጋን ፍትወት ለመግደል ነው የሚሉኝ ካሉ እንዲህ እላቸዋለሁ፤‹በሰው ላይ ያለ የሥጋ ፍትወት ወንድ ወደ ሴት የሚሳብበት ፣ሴትም ወደ ወንድ የምትሳብበት የፈጣሪ ጥበብ ነው፡፡ይኸንን ብታውቀው እሱ ፈጣሪ ባቆመው ሥርዓት፣በሥጋዊ መገናኘት ካልሆነ በቀር በሌላ መንገድ ማብረድ አይገባም፤ምክያቱም ፈጣሪያችን ይኸንን ፍትወት በሰውና በእንስሳት ሥጋ ሁሉ በከንቱ አላስቀመጠውም፡፡ይኸንን ፍትወት በሰው ሥጋ ላይ የተከለው ለዚች ዓለም ሕይወቱ መሠረት እንዲሆንና ፍጥረትን ሁሉ በአቆመለት ሥርዓት መንገድ እንዲያፀናው ነው›› ይላል(ዝኒ ከማሁ፡ገ.24)፡፡በዘርዐያዕቆብ ፍልስፍና ፍትወታችን ከወሰን እንዳያልፍ መፍትሄው ተፈጥሮአዊውን ሩካቤ ሥጋ መገደብ ሳይሆን የሚያስፈልገንን ብቻ እየተመገብን ራሳችንን ወዳላስፈላጊ ሩካቤ ከሚመራ ስካርና ጥጋብ መጠበቅ ነው፡፡እዚህ ላይ የሚገርመው በሐተታው መግቢያ ስለሰው ነጻ ፈቃድ የሚሰብከው ዘርዐያዕቆብ የምንኵስና ሕይወት በምርጫ ሊገባበት የሚችል የሕይወት መንገድ መሆኑን ባለመቀበል መልሶ ነጻ ፈቃድን (free will) መጻረሩ ነው፡፡ክርስትናን ከጋብቻና ምንኵስና አንጻር ያየበት መንገድ ምሬት የተሞላበት መሆኑ እውነታውን ለማየት ቀን ልቡና ሳያሳጣው አልቀረም ብዬ እፈራለሁ፡፡ስለሁሉም ስለሩካቤና ጋብቻ የኦርቶዶክሳዊውን ትውፊት አቋም ባቅማችን እንፈትሽ!ከዚያ በፊት ሚጢጢ ስርዋጽ እናስገባ…
ዳግሚት ስርዋጽ፡- ተመዝግበው ካገኘናቸው ፈንገጥ ያሉ የሩካቤ ገጠመኞች በጥቂቱ!
(ሀ). ለባሕልና ሃይማኖታችን ከበድ ካለው እንጀምር፡፡2 ሴቶች ጎንደር ውስጥ በጾታዊ ግንኙነት (ዛሬ ‹‹ሌዚቢያን›› የሚባለው) ተጎዳኝተው ይኖሩ ነበር፡፡አንዷ እንደ ባል ሌላዋ እንደ ሚስት እየሆነች ኖሩ፡፡በደንብ ኖሩ፡፡ሚስት የተባለችው አረገዘች፤ወለደች፡፡ባልዬዋ ጠፋች፡፡ሚስትዬዋ ‹ወ/ሮ ባል እንደ ልጅ አባትነቷ ተቆራጭ ታድርግልኝ› አለች፡፡ወ/ሮ ባል ጥያቄውን አልተቀበለችም፡፡ጉዳዩ ከንጉሡ ደረሰ፡፡ወ/ሮ ሚስት ከነልጇ በችሎት ቆመች፡፡ሊቃውንት ተጠሩ፡፡ተገረሙ፡፡ሆኖም ወ/ሮ ባልና ወ/ሮ ሚስት ጉድኝታቸውን አልካዱም፡፡በሌላ በኩል ሴትና ሴት በሚያደርጉት ግንኙነት ልጅ ሊወለድ እንደማይችል መጽሐፍም ተፈጥሮም ያስረዳሉ፡፡አንድ ሊቅ ተነሣ፡፡ወ/ሮ ባል ከወ/ሮ ሚስት ጋር ከመተኛቷ በፊት ከወንድ ጋር ግንኙነት አድርጋ እንደሆን ጠየቀ፡፡አመነች፤አድርጌያለሁ አለች፡፡አድራጊዋ (ወንዱ) ተጠራ፡፡መልኩ ለቀለብ ይቆረጥልኝ ክሱ ምክንያት ከሆነው አራስ ሕጻን ጋር ቁጭ!ሆነ፡፡ወ/ሮ ባል የወንዱን ዘር በአፈ ማኅፀኗ ይዛ ለተጎዳኘቻት ወላድ ማቀበሏ ታመነበት፡፡የቀለብ ወጪው ዳኝነት ተጠርቶ በመጣው ወንድ ላይ አረፈ፡፡ይህ ፍርድ የተሰጠው በንጉሥ አጼ ተክለ ሃይማኖት ዘመን (1762-1769) በአቃቤ ሰዓት ከብቴ ስለመሆኑ ፕ/ር ጌታቸው ኃይል ጽፈዋል(አንዳፍታ ላውጋችሁ፣ገ.177-178)፡፡መልአከ ምክር ከፍያለው መራሂ በበኩላቸው ፍርዱ የተሰጠው በአጼ ዮስጦስ ዘመን በነበሩት ቀዳማዊ አራት ዓይና ጎሹ የተባሉ ሊቅ መሆኑን አመልክተዋል(ዝክረ ሊቃውንት፡ገ.26-29)፡፡‹‹ገርመና’ሎ›› አሉ ኤርትራውያን!ምን ይሄ ብቻ!በሄኖክ ምዕራፍ 2 አንድምታ የቃየል ልጆች ለሴት ልጆች ‹‹ያንዱን ጽንስ ባንዱ፣ያንዱን ጽንስ ባንዱ ማሳደር፤አንድም ሰውን ፈረስ፣በቅሎውን ፈረስ፣በቅሎውን ሰው ማድረግ›› ማሳየታቸው ተጽፏል(መጽሐፈ ሄኖክ አንድምታ፡ገ.14)፡፡ጄኔቲክ ምህንድና፣የማኅፀን ኪራይ፣ክሎኒንግ…ወዘተርፈ…(የማላውቃቸውን) የሕክም ቃላት የሚያጠኑ ሰዎች የሄኖክ 2ን አንድምታ ቢመለከቱ ቢያንስ በታሪክ ደረጃ ብሔራዊ የትረካ መነሻ ሳያገኙ አይቀሩም፡፡
(ለ). ወደ ሴቶቹ ታሪክ እንመለስ!የነዚህ ሴቶች ታሪክ በአንዳንድ ነጮች ጆሮ ሳይደርስ አልቀረም፡፡መድረሱ ክፋት የለውም፡፡ነገር ግን ታሪኩን ከኢትዮጵያዊቷ ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ጋር አያይዘው ያልሆነ-ያልሆነ ቁንጸል ጥናት ተብዬ ሳያራቡ አልቀሩም፡፡ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ትውልዷ ጎንደር ነው፤ስማዳ፡፡26 ዓመት በትዳር ቆይታ 3 ልጆችን ካፈራች በኋላ መነነች፡፡በሱስንዮስ ዘመን በገነኑት ካቶሊካውያን ተጋድሎ ከፈጸሙ ወገን ነው ቁጥሯ፡፡በምናኔ 36 ዓመት ኖራ በ80 ዓመቷ ኅዳር 18 ቀን አርፋለች፡፡ቅድስናዋ በኢኦተቤክ የታወቀ ነው፡፡በስሟ ጎንደር ውስጥ 2፣ጎጃም 5 አብያተ ክርስቲያናት አሉ–የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም የሚለው መጽሐፍ በገጽ 254 እንዳስነበበን፡፡ምናልባት የታሪኳ ቁንፀላ ከካቶሊካውያኑ ጋር በተያያዘ የተፈጸመባት ሥም ማጥፋት ሊሆን ይችላል–ሴራ(conspiracy) ፈጣሪ ካላሰኘን!አጼ ፋሲል የሱስንዮስን አዋጅ ለውጦ በካቶሊካዊት ሃይማኖት ምትክ የቀደመችው ተዋሕዶ ትመለስ የሚል አዋጅ በማሰማቱ ‹‹ሴቶችን ተገናኝቶ ሲያበቃ ባሕር ይጥላል›› የሚል ሐሜት የካቶሊክ መነኰሳት አስወሩበት፤አስጻፉበት እንደሚባለው ነው፡፡ባገራችን የካቶሊክ፣ቅብዐት፣ፀጋና ተዋሕዶ የምዕተ-ዓመታት ክርክሮች አንዱ ላንዱ ጸያፍ ሥምና ብሂል መስጠት፣መፈራረጅ አዲስ አይደለም፡፡የወለተ ጴጥሮስን የተዋሕዶ ብሂል ተቆርቋሪነት ለማጠልሸት ከተቃራኒ ብሂል የሆኑ ደባትር ጠልስመውና ከላይ የተገለጹትን ሴቶች ታሪክ ለወለተ ጴጥሮስ አስመስለው በጸያፍ አግብተው ለፈረንጆቹ አቀብለውም ሊሆን ይችላል፡፡ሆነም ቀረ ነጮቹ ደባትር ስተዋል!ይቦጭቃቸው!
(ሐ). መላ ምቱን ባለበት አቁመን ወደ ተመዘገቡልን የሩካቤ ታሪኮች እንለመስ፡፡በዚች ቅጽበት እያነበብኩት የሚገኘው የሞገደኛው ጋሞ፣የጨንቻው፣የኢጭአቱ ጓድ አሰፋ ጫቦ ‹‹የትዝታ ፈለግ›› መጽሐፍ አቶ አሰፋ ጫቦን ፊደል አስቆጥረው ለዲቁና ያበቁት መሪጌታ ብቅአለ ክበበው እና ወንድማቸው መሪጌታ ደመቀ ክበበው ‹‹ሂያጆች›› እንደነበሩ ያትታል(የትዝታ ፈለግ፡ገ.41)፡፡የሚገርመው ሁለቱም ዓይነ ስውር መሆናቸው፡፡መንገዱ ለዓይነ ስውርም አይጠፋ ጃል!ዓይነ ስውር ቢባል 4 ኪሎ የነበሩ ዓይነ ስውር ትዝ አሉኝ፡፡ተራክቦ ሲፈጽሙ መንገድ ሳቱ፡፡ተጓዳኛቸው ‹‹እረ የኔታ!እግዜር በፈጠረው›› ብላለች፡፡‹‹ውይ!ይቅርታ!ግን ይኽንንስ አንቺ ነሽ የፈጠርሺው?›› አሉ ተብሎ በሹክሹክታ ተሳስቀናል፡፡ከየኔታዎች ውስጥ አራት ዓይና ጎሹ፣አለቃ ገብረ ሃና እና የአለቃ ለማ ኃይሉ የዜማ መምህር (የአለቃ ለማን መጽሐፈ ታሪክ ገጽ 61 ተመልከት) የተመዘገበ ሂያጅነት ያላቸው ታላላቅ መምህራን ናቸው፡፡ሲራክ መምህራንን ሴትና መጠጥ እንደሚፈትናቸው መጻፉን አንብቤ ነበር፤ምዕራፍና ቁጥሩ ተዘነጋኝ!የመካከለኛው ዘመን ሰሎሞናዊ ገናና ነገሥታትና የገዳማውያኑ ትልቅ ያለመግባባት ምንጭ የነገሥታቱ መፍቀሬ-አንስት መሆን ነበር፡፡የሰሎሞን ዘር መሆናቸውን በምን ያሳዩ?!ዕቁባት መደርደርንና እንደ አቤሴሎም የአባቶቻቸውን ቅምጦች ሳይቀር መጎብኘት ይወዱ ነበር!ይህን ስርዋጽ በአለቃ ተክለኢየሱስ ዋቅጀራ እንዝጋው፡፡ሰሞኑን ድጋሚ በታተመ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› መጽሐፉ ገጽ 219 አለቃ ተክሌ አንድ አባ ወልደ ሥላሴ የተባሉ ቄስ የንስሐ ልጃቸውን ለምደው የተፈጠረውን አጋጣሚ ከነሥነቃሉ ጽፎልናል፡፡ቄሱ የንስሐ ልጃቸውን ለምደዋል፡፡የመጋኛ መድኃኒት አድርግላታላሁ እያሉ ባሏን አቁመው ሌላ ነገር ያደርጋሉ፡፡የዋሑ ባል ዘግይቶ ነቃ፡፡ከደጃች ተድላ ከሰሳቸው፡፡ደጃች ተድላ በባልየው ንዝህላልነት ተበሳጨ፡፡‹‹እንስሳ!አሰርረህ ትከስሳለህን?!›› ብሎ አባረረው፡፡የወገን እረኛ ሰማ፡፡እንዲህ አላገጠ፤
‹‹ጫንቃ ሰበር ይዞ፤ስረሩ ቢላቸው፣
አባ ወልደ ሥላሴ፤ምን ፍርድ አለባቸው፡፡
አባ ወልድ ሥላሴ፤ምናኔ ምናኔ፣
ቆብሁ ተግድግዳ፤አካላትሁ ተኔ፡፡›› እያለ ዘፈነባቸው፡፡አሁን ዘፈኑን ትተን ወደ ዓቢዩ ርእስ መቋጫ እንገሥግስ…
ይቀጥላል

No comments:

Post a Comment