Friday 2 October 2020

 በአብ ስም በወልድ ስም በመንፈስ ቅዱስ ስም አንድ አምላክ አሜን!

በእንተ ሰማንያ አሃዱ (ክፍል-፬)
[የዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍት ምንጮች]
ባለፉት ሁለት ክፍሎች የዲዩትሮካኖኒካል ምንጮች የሆኑትን መጽሐፍ ቅዱስንና የሰባ ሊቃናት(Septuagint) ስብስብና ትርጉም ተመልክተናል። በዚህ ክፍል የቀሩ ሌሎች ምንጮችን እንመለከታልን።
፫. የሐዋርያት ቀኖና (Apostolic Canon/Ecclesiastical Canons):- ይህ አብዛኛው ቀኖናው በሐዋርያት እንደ ተጻፈ የሚታመነው የሐዋርያት ቀኖና የቤተክርስቲያን አስተዳደርን እና ሥርአትን በሚመለከት 85 ቀኖናዎችን የያዘ ነው። ሐዋርያት እንደ ጻፉት እስከ አሁን በትክክል ማረጋገጥ ባይቻልም ከምሥራቅ ቤተ-ክርስቲያን ልምድ ስንነሳ 85 ሐዋርያውያት ቀኖናት የሐዋርያትን ትምህርትና ሥርአት ይዘው በመገኘታቸው ለሥርአተ አምልኮ ጥቅም ላይ ውለዋል። ይህን ሐዋርያውያት ቀኖና በ691 በትሩሎ በተጠራው በምስራቅ ሲኖዶስ ( Eastern Council in Trullo) ተቀባይነት አግኝቷል። [Canons, Apostolic , 1910 New Catholic Dictionary , accessed 16 April 2016.] ሐዋርያውያት ቀኖናት በአሁኑ ቅርጻቸው ተቀነባብረው ሊገኙ የቻሉበት (ለአገልግሎት በሚመች መልኩ) የጊዜ መነሻቸው (Terminus a quo) ሁለተኛ ክ/ዘመን አጋማሽ ሲሆን የተጠናቀቁት ደግሞ (Terminus ad quem) በ 3ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ነው።
በዚህ ሐዋርያውያት ቀኖናት የቀኖና መጻሕፍት ዝርዝር (List of Canonical Books) ይገኛል። በዚህ በ 85ኛ ቀኖና የዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍት አካል የሆኑት የመቃብያን መጽሐፍት እና መጽሐፍተ ዕዝራ ይገኛሉ። መጽሐፈ ሲራክም በቤተክርስቲያን ሊነበቡ ከሚችሉ መጽሐፍት ዝርዝር ውስጥ ተካቷል። [El-satic El-Assal the Collection of canons Chapter 2]
፬. የተለያዩ የተደረጉ ሲኖዶሳውያት ጉባኤዎች
1. የሂፖ ጉባኤ (Synod of Hippo):- ይህ በሰሜን አፍሪካ በ 393 ዓ.ም የተጠራው ጉባኤ የቅዱሳት መጽሐፍትን ቀኖና ዝርዝር አስቀምጧል። ይህ ጉባኤ የዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍትን በመቀበል በቀኖና ውስጥ ከቷቸዋል። [Augustine of Hippo. On Christian Doctrine . Book II, Chapter 8.]
2.የካርቴጅ ጉባኤ ( Council Carthage):- በ 397 ዓ.ም የተካሄደው የካርቴጅ ጉባኤም የቅዱሳት መጻሕፍትን ቀኖናን አስቀምጧል። የዚህ ቀኖና የመጀመሪያ የመረጃ ምንጭ ስለ ጉባኤው የሚያትተው "Codex Canonum Ecclesiae Africanae" ነው። በዚህ ቀኖና ውስጥ መጽሐፈ ዮዲት፣ መጽሐፈ ጦቢት፣ መጽሐፍተ መቃብያን፣መጽሐፍተ እዝራ፣ መጽሐፈ ጥበብ ያሉ የዲዩትሮካኖኒካል መጻሕፍት ተካተዋል። [http://www.bible-researcher.com/canon8.html]
፭. በቤተክርስቲያን ታሪክ ቀደምት የሆኑት የቅድመ ኒቂያ (Anti Nicen Fathers) እና ድኀረ ኒቂያ (Post Nicen Fathers) የዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍትን ተቀብለው ለሃይማኖት ማስተማሪያ ለመሠረተ እምነት(ዶግማ) ማስረጃ፣ ለመናፍቃን መልስ መስጫ ተጠቅመውባቸዋል። ይህንንም በጻፏቸው መጻሕፍትና በላኳቸው መልእክቶች ማረጋገጥ ይቻላል። ለአብነት ያህል ጥቂቶችን እንመልከት:-
-ቅዱስ ቀለሜንጦስ ዘሮም (St. Clement of Rome), [To the Corinthians 27:5 (A.D 80)] ላይ ከመጽሐፈ ጥበብ 12÷12 ጠቅሶ ጽፏል።
- ቅዱስ ፖሊካርፐስ (St. Polycarp), [to the Philippians, 10 (A.D 135)] ላይ ከመጽሐፈ ጦቢት 4÷10 ጠቅሶ ጽፏል።
-ቅዱስ ሄሬኔዎስ (St. Irenaeus), [Against Heresies V:35:1( A.D 180)] ላይ ከመጽሐፈ ባሮክ 4÷36 ጠቅሶ ጽፏል።
-ሊቁ ጠርጡለስ (Tertullian), [ Prescription against the Heretics, 7 (A.D 200)] ላይ ከመጽሐፈ ጥበብ ጠቅሶ ጽፏል።
- ቅዱስ ሂፖሊተስ (St. Hippolytus), [ Commentary on Daniel, 6÷1 (A.D 204)] ላይ ከመጽሐፈ ሶስና ጠቅሶ ጽፏል።
- ሊቁ አርጌንስ (Origen), [Fundamental Principles, 2:2 (A.D 230)] ላይ ከ2ኛ መቃ ጠቅሶ ጽፏል።
- ቅዱስ ቄርሎስ ዘእየሩሳሌም (St. Cyril of Jerusalem), [Catechetial Lectures, 9÷23(A.D 350)] ላይ መዝሙር ዘሰለስቱ ደቂቅ ጠቅሶ ጽፏል።
- ቅዱስ ጎርጎሪዮስ ዘእንዚናዙ (St. Gregory of Nazianzen), [Orations 45, 2nd Oration of Easter 15 (A.D 383)] ላይ ከመጽሐፈ ዮዲት5÷6 ጠቅሶ ጽፏል።
- ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ (St John Chrysostom), [Homilies on John, 48 (A.D 391)] ላይ ከመጽሐፈ ሲራክ10÷9 ጠቅሶ ጽፏል።
-ቅዱስ ጄሮም( St. Jerome), [to Paulinus, Epistle 58 (A.D 395)] ላይ ከመጽሐፈ ጥበብ4÷9 ጠቅሶ ጽፏል።
- የአቁሊያው ሩፊኖስ (Rufinus of Aquileia), [The Apostolic Creed, 37-38(A.D 404)] ላይ ከባሮክ3÷36-38 ጥቅሶች
ጽፏል።
=>>>[ቅዱስ አትናቴዎስ ስላልተቀበላቸው እኛም አንቀበልም የሚለው የፕሮቴስታንቶች ሙግት ሲመዘን]
ፕሮቴስታንቶች ቅዱስ አትናቴዎስን በመጥቀስ የ Deutrocanonical መጽሐፍትን ስላልተቀበለ እኛም አንቀበልም የሚል ሀሳብ ያቀርባሉ። ኦርቶዶክሳዊውን አባት ለኦርቶዶክሳዊውን ለመንቀፍ ይጠቀሙበታል። ቅዱስ አትናቴዎስ በ 367ዓ.ም በላከው 39ኛ የፋሲካ በአል መልእክቱ አምላካውያት መንፈሰ እግዚአብሔር ያለባቸውን መጽሐፍ ዘርዝሯል። መጽሐፍቱንም ከዘረዘረ በኃላ " እነዚህ የተጠማ በውስጣቸው በሚገኙ ቃላት ይረካ ዘንድ የእውነተኛ የደኅንነት ምንጮች ናቸው። በእነዚህ ብቻ የቅድስና ትምህርት ይሰበካል።" በማለት ተናግሯል። [ዲበኩሉ ዘውዴ 81 ቅዱሳት መጻሕፍት ምንጮች-ቀኖናት ገጽ-51] ፕሮቴስታንቶች ይህንን ይዘው መጽሐፍቱን አንቀበልም የሚል ሙግት ያቀርባሉ። በዚህም ራሳቸውን ወጥመድ ውስጥ ይከታሉ።
1. ቅዱስ አትናቴዎስ በዘረዘራቸው ዝርዝር ውስጥ ፕሮቴስታንቶች የማይቀበሏቸውን መጽሐፈ ባሮክ እና ተረፈ ኤርሚያስ ይገኛሉ። እነርሱ ቅዱስ አትናቴዎስ የተቀበላቸውን እንቀበላለን ካሉ ለምን እነዚህን አልተቀበሏቸውም?
2. ቅዱስ አትናቴዎስ መጽሐፈ አስቴርን ከብሉይ ኪዳን የቀኖና መጽሐፍት ዝርዝር ውስጥ አላስገባውም። ፕሮቴስታንቶች መጽሐፈ አስቴርን ተቀብለው ከብሉይ ኪዳን ቀኖና ውስጥ ከተው ይጠቀሙበታል። ይህ ከሆነ ቅዱስ አትናቴዎስ ያልተቀበለውን ለምን ተቀብለው አስገቡ?
=>>>ቅዱስ አትናቴዎስ በቀኖና የሚካተቱትን መጽሐፍት ከዘረዘረ በኃላ እንዲህ ይላል "በእርግጥ ስለ በለጠ እርግጠኝነታቸው ከእነዚህ በስተቀር ከሚቀነኑት መጽሐፍት ጋር ያልሆኑ ነገር ግን ኢዲስ ለሚመጡትና ትምህርተ ቅድስናን ለሚፈለጉ ይነበቡ ዘንድ በአባቶች የታዘዙ ሌሎች መጽሐፍት እንዳሉ አስፈላጊ መሆኑን እጨምራለው። እነዚህም መጽሐፈ ሲራክ፣ መጽሐፈ ጥበብ፣ መጽሐፈ አስቴር፣ መጽሐፈ ዮዲት፣ መጽሐ ፈ ጦቢትና ትምህርተ ሐዋርያት ናቸው።" [Auwers, Jean-Marie; de Jonge, H. J., eds. (2003). The Biblical Canons . Peeters Publishers. p. 267. ISBN 978-90-4291154-3 ]
1. ቅዱስ አትናቴዎስ አስቀድሞ ስለ ቅድስና በእነዚህ ብቻ ይሰበካል ካለ በኃላ የዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍት ስለ ቅድስና ለመማር መነበብ እንደሚችሉ መናገሩ መጽሐፍቱ እውነተኞች እና የሚታመኑ እንደሆኑ ያሳያል።
2. ቅዱስ አትናቴዎስ ያቀረበው መነሻ ሀሳብ ሲሆን በወቅቱ ሙሉ ለሙሉ ቀኖናቸውን አልፈዋል ብሎ ያመነባቸውን መጽሐፍት (καvοvικα) በቀኖና መልክ አስቀምጧቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና በቅዱስ አትናቴዎስ ዝርዝር ብቻ ያልተመሠረተ ነው። ለዚህም ነው ከቅዱስ አትናቴዎስ ጋር ህብረት ያላቸው ከእሱ በፊት የነበሩ፣ በእሱ ዘመን የነበሩ፣ ከእሱ በኃላም የተነሱ ሌሎች የቤተክርስቲያን አባቶች መጽሐፍቱን ተቀብለው ለሃይማኖት ማሥተማሪያ የተጠቀሙባቸው። ከላይ የዘረዘርናቸው የቤተክርስቲያን አባቶች ተጠቃሽ ናቸው።
3. ፕሮቴስታንቶች መጽሐፍቱን የተለያየ መክንያት እያነሱ ይተቻሉ፣ ግን መጽሐፍቱን ቅዱስ አትናቴዎስ ስለ ቅድስና የሚሰብኩ በቤተክርስቲያን ሊነበቡ የሚገባቸው ብሎ ማስቀመጡን አላስተዋሉም።
በቀጣይ ጽሁፍ የሀዲስ ኪዳን የሥርአት መጽሐፍት (Books of Church Orders) ምንጮችን እንዳስሳለን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር!
©ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ
No photo description available.
13
1 Comment
14 Shares
Like
Comment
Share

No comments:

Post a Comment