Friday 2 October 2020

 በአብ ስም በወልድ ስም በመንፈስ ቅዱስ ስም አንድ አምላክ አሜን!

በእንተ ሰማንያ አሃዱ (ክፍል-1)
መግቢያ
የቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ምንም እንኳን ኦርቶዶክሳዊው እስቤ መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛው የክርስትና አስተምህሮ መመሪያና ምንጭ ነው ባይልም መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተክርስቲያን መተኪያ የሌለው የጽሁፍ ሀብቷ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛው የክርስትና አስተምህሮ መመሪያና ምንጭ አይደለም ያልነው ትውፊት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጎን ለጎን አብሮ ስለሚያገለግል ነው። የጽሁፉ ሀሳብ መጽሐፍ ቅዱስን በሚመለከት ስለሆነ ትውፊትን በሚመለከት እራሱን በቻለ ርእስ እንመጣበታለን። መጽሐፍ ቅዱስ ለክርስትና አስተምህሮ መሠረት ነው የሚለው በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት ቢኖረውም በውስጡ ስላሉት የመጽሐፍት ብዛት ግን ልዩነት መኖሩ የታወቀ ነው። በተለይም ፕሮቴስታንታውያን ከሉተር የተሃድሶ እንቅስቃሴ በኃላ እንደ አዲስ የተሰራውን 66ት መጽሐፍት ያለውን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሚቀበሉ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ያሉ (እነርሱ ጋር የሌሉትን) መጽሐፍት ሲተቹ ይታያሉ። ለአብነትም በቴዎድሮስ ደመላሽ "ሰማንያ አሃዱ በእግዚአብሔር ቃል ሲመዘን" የሚለውን መጽሐፍና "ኦርቶዶክስ መልስ ካላት እኛም ጥያቄ አለን" በሚል የተዘጋጀውን ቪሲዲ መጥቀስ ይቻላል። ይህንን መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስላለው በተለምዶ ሰማንያ አሃዱ ስለሚባለው መጽሐፍ ቅዱስ ከስር ከመሠረቱ በመመልከት ለጠያቂዎች ምላሽ አዘጋጅተናል።
=>>>እንደ መንደርደሪያ (አጠቃላይ ጥያቄያዊ መልእክቶች ለፕሮቴስታንታውያን)
1. መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ ጊዜና ቦታ የተጻፈ መጽሐፍ እንደሆነ ይታወቃል። በተለይም የሀዲስ ኪዳን መጽሐፍት በተጻፉበት ወቅት ሌሎች ሀሰተኞች መጽሐፍት (ψευδεπγραφα/Peudepigraha) ስለነበሩ እውነተኞችን መጽሐፍት ከሀሰተኞች ለመለየት የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና (Biblical Canonization) መንገድ ተጠቅመዋል። በዚህ የቀኖና ሂደት ውስጥ የተሳተፍት የጥንቷ ቤተክርስቲያን አባቶች (Early Church Fathers) ነበሩ። እነዚህ አባቶች በክህነት የሚያምኑና እራሳቸውም እስከ ጵጵስና ደረጃ የደረሱ ነበሩ። ይህ ከሆነ ዛሬ ላይ ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ እናምናለን የሚሉ የተለያዩ በክርስትና ስም ያሉ የእምነት ድርጅቶች (ፕሮቴስታንታውያን፣ ጅሆቫ ዊትነስ፣ ኦንሊ ጂሰሶች) የጥንቷ ቤተክርስቲያን አባቶች ሰፍረው እና ለክተው የሰጧቸውን መጽሐፍት ነው የሚጠቀሙት ማለት ነው። እኛም የቤተክርስቲያን አባቶች በምሥጢራተ ቤተክርስቲያን፣ በነገረ ክርስቶስ፣ በምሥጢረ ሥላሴ፣ በነገረ ማርያም፣ በነገረ ድኅነት፣ በነገረ ቤተክርስቲያን ያስተማሩትን ትምህርቶች ለምን አትቀበሉም? ብለን እንጠይቃለን። እውነተኞችን መጽሐፍት ከሀሰተኞች ለይተው ቀንነው በአንድ ጥራዝ የሀይማኖት መመሪያ የሆነውን መጽሐፍ ከተቀበላቹ ሙሉ ትምህርታቸውን ለምን አትቀበሉም? ለማለት እንወዳለን።
2. ሉተር ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሲወጣ ከጀመራቸው "የብቻ ትምህርቶች" አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ (Scripture alone) ነው። ይህ አመለካከት ዛሬ ላይ ባሉ የፕሮቴስታንት ዲኖሚኔሽኖችም ዘንድ የሚንጸባረቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ ምን ያህል መጽሐፍት እንዳሉት አይዘረዝርም። ጸሀፊያቸው ማን መሆኑን እንኳ የማይናገሩት የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት ራሳቸውን በራሳቸው አያረጋግጡም። ለምሣሌ የማቴዎስ ወንጌልን እንውሰድ። የማቴዎስ ወንጌል የተጻፈው ከ 12ቱ ሐዋርያት አንዱ በሆነው በማቴዎስ ስለ መሆኑ አንድም ቦታ ላይ እንኳ አይናገርም። እንዲያውም በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዘመን በማቴዎስ ስም ይሰራጭ የነበረው መጽሐፍ የማቴዎስ ወንጌል ብቻ አልነበረም። ማቴዎስ ወንጌላዊ ጽፎታል ተብሎ ይሰራጭ የነበረ "የተከራካሪው የቶማስ መጽሐፍ- The book of the contender" የሚባል መጽሐፍም ነበር። የማቴዎስ ወንጌልን ከዚህ አይነቱና ሌሎች መጽሐፍት ቱውፊትን ካልተጠቀሙ እንዴት መለየት ቻሉ?
3. ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ላይ ፕሮቴስታንቶች በሚቀበሏቸው መልኩ 66ቱ መጽሐፍ ቅዱስ የተቀነነው(የተዘጋጀው) ከሉተር በኃላ ነው። ለአብነት ብንመለከት:-
=>>> ሶስቱ ሲኖዶሳውያት ቀኖና ፕሮቴስታንቶች የማይቀበሏቸውኝን መጽሐፍት ይዘዋል።
1. 85 ሐዋርያውያት ቀኖናት 85ኛ ቀኖና ( Canons of the apostles)[1]:- ፕሮቴስታንቶች የማይቀበሏቸውን ከብሉይ ኪዳን መቃብያን መጽሐፍትን፣ ከሀዲስ ኪዳን መልእክታተ ቀለሜንጦስን አካቶ ይዟል። በአንጻሩ ደግሞ የዮሐንስ ራእይን አያካትትም።
2. ቀኖናት ዘሎዶቅያ/Council of Laodicea [2]:- የሎዶቅያ 60ኛ ቀኖና ፕሮቴስታንቶች የማይቀበሏቸውን መጽሐፈ ባሮክ እና ተረፈ ኤርሚያስን ይዟል በአንጻሩ ደግሞ የዮሐንስ ራእይን አያካትትም።
3. ቀኖናት ዘቅርጣግ (Codex Canonum ecclesiae africanae) [3] በመባል ይታወቃል። ይህ ቀኖና ፕሮቴስታንቶች የማይቀበሏቸውን መጽሐፈ ጥበብና የመቃብያን መጽሐፍትን ይዟል።
=>>>በቤተክርስቲያን አባቶች በግል ደረጃ የተቀነኑ ቀኖናዎች ስንመለከትም ዛሬ ላይ ፕሮቴስታንት እጅ ካለው የተለዩ ሆነው እናገኛቸዋለን። ለምሣሌ ቅዱስ አትናቴዎስ በ 367ዓ.ም በላከው የፋሲካ መልእክቱ 39ኛ ላይ የመጽሐፍትን ዝርዝር በቀኖና መልክ አስቀምጧል። [4]ቅዱስ አትናቴዎስ በዘረዘራቸው ውስጥ መጽሐፈ ባሮክና ተረፈ ኤርሚያስ(ፕሮቴስታንቶች የማይቀበሏቸው) ተካተው ሲገኙ መጽሐፈ አስቴር (ፕሮቴስታንቶች የሚቀበሉት) አልተካተተም።
=>>>እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ዛሬ 66ቱ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው እውነተኛ፣ ሌሎች መጽሐፍት ሀሰተኞች/ተቀባይነት የሌላቸው የሚለው ሀሳብ እንዴት ተቀባይነት ይኖረዋል? ከየትኛው ታሪካዊ የቀኖና ሂደትስ አገኙት?በእርግጥም ከጥንት የቤተክርስቲያን አባቶች ሉተር በልጦባቸው ይህን አድርገዋል።
=>>>በቀጣይ ጽሁፍ የሰማንያ አሃዱ መጽሐፍት ምንጮችን ለመመልከት እንሞክራለን።
ማጣቀሻ
[1]Michael D. Marlowe. "The "Apostolic Canons" (about A.D. 380)" . Bible Research . Archived from the original on 29 August 2010. Retrieved 2 September 2010.
[2] Council of Laodicea at bible-researcher.com . Retrieved 2011-10-05.
[4]የሰማንያ አሃዱ መጽሐፍት ምንጮች እና ቀኖናት-ዲበኩሉ ዘውዴ ገጽ 52
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር!
©ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ
No photo description available.
19
1 Comment
23 Shares
Like
Comment
Share

No comments:

Post a Comment