Friday 2 October 2020

 ዱስ ስም አንድ አምላክ አሜን!

በእንተ ሰማንያ አሃዱ (ክፍል-3)
የዲዩትሮካኖኒካል(Deuterocanonical) መጽሐፍት ምንጮች
=>>>በክፍል-2 ጽሁፍ የዲዩትሮካኖኒካል መጻሕፍት ምንጮች መካከል ዋነኛው መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ተመልከተን የሀዲስ ኪዳን መጽሐፍት ፀሀፊዎች ከመጻሕፍቱ እየጠቀሱ መጻፋቸውን ተመልክተናል። በዚህ ጽሁፍ የቀሩትን ሌሎች ምንጮች ለማየት እንሞክራለን።
፪. ግሪክ ሰባ ሊቃናት (Septuagint/LXX) ትርጉምና ስብስብ
የሰባው ሊቃውንት ትርጉም በባቢሎን ምርኮ ጊዜም ሆነ ከምርኮው በኃላ በተፈጠሩ ችግሮች ወደ ግብጽ ተሰደው በዚያ በመሰረቱት የእስክንድርያ አይሁድ በበጥሊሞስ 2ኛ ፒላደልዩስ/Ptolemy II Philadelphus (285-247 ቅ.ል.ክ) ትእዛዝ ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ የተተረጎመ ነው። ይህ የሰባ ሉቃውንት ትርጉምና ስብስብ በግሪክ አናጊግሶስኮመና
(anagignoskomena) ወይም ዲዩትሮካኖኒካል (deuterocanonical) መጽሐፍትን ይዘዋል። ይሄን በሚያጠናክር ሁኔታ በግሪክ ቋንቋ የተጻፉ ቀደምት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች(codices) መሆናቸው በሚታመነው የቫቲካን ጥራዝ (Codex Vaticans)፣ የሲናይ ጥራዝ(Codex Sinaiticus እና የአሌክሳንደርያ ጥራዝ (Codex Alexanderinus) ውስጥ የዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍት ከሌሎት አሥራው መጻሕፍት ጋር አብረው ይገኛሉ። [Meade, John D. (2018-03-23). "Was there a "Septuagint Canon"?" . Didaktikos: Journal of Theological Education. Retrieved
8 October 2019.]
=>>>Septuagint vs Masoretic Text
=>>>አይሁድ ከክርስቶስ ልደት በፊት የታወቀ እና የተወሰነ የመጽሐፍት ብዛት የላቸውም። ለመጀመሪያ ጊዜ ከክርስቶስ በኃላ በ 90ዓ.ም በጃሚና ጉባኤ(Council of Jamina) የተሰበሰቡት ሊቃውንት ፕሮቴስታንቶች የማይቀበሏቸውን የዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍት ላለመቀበል ወሰኑ። በመቀጠልም ማሶሬቲክስ( Masoretic Text/MT) በመባል የሚታወቀውን የአይሁድ የብሉይ ኪዳን 39 መጽሐፍት ያሉትን ከ600ዓ.ም ጀምሮ ፈሪሳውያን አይሁዶች በገሊላ በጥብርያዶስ ባህር አጠገብ ተሰብስበው ማዘጋጀት ጀመሩ። በጃሚና የተሰበሰቡ አይሁድ የዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍትን ያልተቀበሉበት ሁለት ዋና መክንያቶችን ማንሳት ይቻላል። [Canon of the Old Testament" .
Catholic Encyclopedia .]
1. የመጀመሪያው አይሁድ የራሳቸውን መጽሐፍ እየጠቀሱ መልስ ላሳጧቸው የክርስቲያን ሊቃውንት መልስ ለመስጠት ትኩረት የሰጡበት ጊዜ ነበር። የአይሁድ ጉባኤ የዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍት ስለ መሲሁ መምጣት፣ አለምን ለማዳን ስለ መሰቀሉ፣ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በግልጽ ይመሰክራሉ። ይህ ደግሞ አይሁድ ለክርስቶስ ከነበራቸው አመለካከት ጋር ይጋጫል። ለራሳቸው አመለካከት ሲሉ መጽሐፍቱን ላለመቀበል ወስነዋል። ስለ መሲሁ በግልጥ የሚናገሩ የዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍት ለአብነት ያህል የቀረቡ:-
መጽሐፈ ጥበብ:-
"እግዚአብሔርንም ማወቅ በእኔ አለ ይላል ራሱንም የእግዚአብሔር ልጅ ያደርጋል" ጥበብ2÷13
መጽሐፈ ባሮክ
"እርሱን የሚመስል ሌላ የለምና ወደ አንተ መጣን ይላሉ።የጥበብን ሥራ ሁሉ እርሱ አገኛት ለባለሟሉ ለያእቆብ ለወዳጁም ለእስራኤል ሰጠው። ከዚህ በኃላ በምድር ተገለጠ እንደ ሰውም ሆነ።" ባሮክ3÷38
2. የአይሁድ ዳግማዊ የነጻነት እንቅስቃሴ 70ዓ.ም ከፈነዳ በኃላ የብሔራዊነት ስሜት ያየለበት ጊዜ ነበር። ይህ በመሆኑ በ 90 ዓ.ም በጃሚና ጉባኤ የመጽሐፍትን ቀኖና ለመወሰን የተሰበሰቡ አይሁድ በነበራቸው ፀረ ግሪካዊ አቋም በግሪክ ቋንቋ ብቻ ይገኙ የነበሩትን መጽሐፍት ላለመቀበል ወስነዋል።
[ለምን የሰባ ሊቃውንት ትርጉምና ስብስብ ለዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍት ምንጭነት ተጠቀሰ?]
=>>>ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከነበረበት የቤተክርስቲያን ምሥረታ ጀምሮ በቤተክርስቲያን አባቶች ዘንድ (Early Church Fathers) ተቀባይነት የነበረው የሰባ ሊቃናት ትርጉም ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት እንደ ሚናገሩት አብዛኛዎቹ በሀዲስ ኪዳን መጽሐፍት የተጠቀሱት የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ከሳባ ሊቃውንት ትርጉም የተወሰዱ ናቸው።በተጨማሪም በጥንቷ ቤተክርስቲያን በአብዛኛው ለትርጉም ምንጭነት እና ለማሥተማሪያነት ያገለገለው የሰባው ሊቃውንት ትርጉም ነው። የዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍትን አካቶ የያዘው የሰባ ሊቃውንት ትርጉምና ስብስብ በመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን ዘንድ እውቅና ያለው መሆኑ ለመጽሐፍቱ ተአማኒነት ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው። [Nicole, Roger, New Testament Use of the Old Testament Revelation and the Bible , ed. Carl. F.H. Henry (Grand Rapids: Baker, 1958), pp. 137–51.]
[የአይሁድ ውሳኔ እና ፕሮቴስታንቶች]
=>>>አይሁድ መጽሐፍቱን ያልተቀበሉባቸው የራሳቸው መክንያት ያላቸው ሲሆን ፕሮቴስታንቶችም እነርሱ ካልተቀበሉ እኛም አንቀበለም ብለው አውጥተዋቸዋል። ይህ የስህተት ሀሳብ ነው።
1. ከክርስቶስ መምጣት በኃላ አይሁድነት በቀድሞው ማንነት የሚታወቅ አይደለም። አሁን በክርስትና ዘመን አይሁድ ስንል የይሁዳ ነገዶች ወይም የያእቆብ ዘሮች ወይም የአብርሃም የቃልኪዳን ልጆች ማለት አይደለም። ከክርስቶስ እርገት በኃላ ያለው አይሁድነት እውነተኛ ሳይሆን ሐሰተኞች የክርስቶስ ተቃዋሚ (Anti-Christ) እና የሰይጣን ማህበር መሆናቸውን ቅዱስ መጽሐፍ አስቀምጦታል።
" መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፥ ነገር ግን ባለ ጠጋ ነህ፤ የሰይጣንም ማኅበር ናቸው እንጂ አይሁድ ሳይሆኑ። አይሁድ ነን የሚሉት የሚሳደቡትን ስድብ አውቃለሁ።"
(የዮሐንስ ራእይ 2:9)
አይሁዶች እኛ ከአማኞች ወገን ነን ቢሉም የሚታመኑበት መንገድ ግን በጌታ በክርስቶስ ከሆነው የመዳን መንገድ የተለየ በመሆኑ የሰይጣን ማህበር ተብለዋል። ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ እንዲህ ይላል:-
"በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፥ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም።" ሮሜ2÷28-29
=>>>የጥንቷ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ከሐዋርያት በተማሩት መሰረት ይህንን የቅዱስ ጳውሎስ ጥቅስ አብራርተውታል። የሁሉም አረዳድ ከክርስቶስ መወለድ በኃላ ያሉት የአይሁድ ማህበር ሀሰተኛ እንደሆነና እና በፊደል ሳይሆን በመንፈስ የሚመላለሱ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ሕግ የሚፈጽሙ በስሙም የተሾሙ እስራኤል ዘነፍስ እነርሱም የክርስቲያኖች ማህበር የሆነችው ቤተክርስቲያን ባለ ሙሉ ስልጣን እንደሆነች ነው። ለዚህም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ (St. John Chrysostom)፣ ሊቁ አርጌንስ (Origen the Scholar)፣ ቅዱስ ጎርጎሪዮስ( St. Gregory the Theologian) ተጠቃሽ ናቸው። [The Epistle of St Paul to the Romans. Based on the interpretation & Meditations of the Early Fathers by:- Fr Tadros, Yacoub Malaty. Page 52-54] በተጨማሪም ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበሩት አይሁዶች ወጥ የሆነ የመጽሐፍት ብዛት አልነበራቸውም። ፈሪሳውያን አይሁድ፣ ሰዱቃውያን አይሁድ፣ ኤስንያን አይሁድ፣ ሳምራውያን እና ቤተ እሥራኤል በሚጠቀሙት ቅዱሳት መጽሐፍት ይለያያሉ። በሀዲስ ኪዳን ባለ ሙሉ ስልጣን የሆነችው ቤተክርስቲያን እንጂ የሀሰተኞች ማህበር የሆነው የአይሁድ ስብስብ አይደለም። ይህ በሆነበት ሁኔታ ከመሲሁ መገለጥ በኃላ የተወሰነን የአይሁድ ውሳኔ ትክክል ነው ብሎ የቤተክርስቲያን መጽሐፍትን አለመቀበል የአይሁድ ፀረ ክርስቶሳዊ ሀሳብ መደገፍ ነው። ለዚህ ነው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ያስጠነቀቀን:-
" ኢየሱስም። ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ አላቸው።"
(የማቴዎስ ወንጌል 16:6)
2. ፕሮቴስታንቶች የአይሁድ ውሳኔ ትክክል ነው ብለው መቀበላቸው ራሳቸውን ችግር ውስጥ ይከታቸዋል። መክንያቱም አይሁድ የዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍትን አንቀበልም ብለው ያበቁ ሳይሆን በ 66ቱ ውስጥ ከሚገኙት 39ኙ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍትም ብዙ ነገር ሰርዘዋል። ለአብነት የሚከተሉትን መመልከት ይቻላል:-
፩. " እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።"
(የማቴዎስ ወንጌል 1:23)
ይህ ትንቢት ከትንቢተ ኢሳይያስ 7÷14 የተወሰደ ነው። በአይሁድ Masoretic መጽሐፍ ድንግል የሚለውን ወጣት ሴት young woman ይለዋል።
፪. " ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ። መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤"
(ወደ ዕብራውያን 10:5) ይህ የትንቢት ቃል የተወሰደው ከመዝሙር 40÷6 ነው። በአይሁድ Masoretic ስጋን አዘጋጀህልኝ የሚለው የለም።
=>>>ከዚህ የምንረዳው አይሁድ የዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍትን አለመቀበል ብቻ ሳይሆን ከፕሮቶካኖኒካል መጽሐፍትም ብዙ ለውጥ ማድረጋቸውን ነው።
[መጽሐፈ ሄኖክና መጽሐፈ ኩፋሌ]
አንዳንድ ሰዎች መጽሐፈ ሄኖክና መጽሐፈ ኩፋሌ በኢትዮጵያ ብቻ ስለሚታወቁ ተቀባይነት የላቸውም ይላሉ። ይህ ግን የስህተት ሀሳብ ነው።
=>>>መጽሐፈ ሄኖክ(Book of Enoch) በሀዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ በሐዋርያው ይሁዳ ተጠቅሷል። ይሁዳ1÷14 እና ሄኖክ 1÷9 ተመልከቱ። በኢትዮጵያ ብቻ ይታወቃል የሚለውን ሀሳብ የሚያፈርስ አዲስ ግኝት ተገኝቷል። ይኸውም የሙት ባህር ጥቅል (Dead See Scrolls) በመባል የሚታወቁት በቁምራን ዋሻ ውስጥ የተገኙት የቅዱሳት መጻሕፍት ስብስብ ነው። መጽሐፈ በአርማይክ (Aramaic)፣ በኩይኔ ግሪክ( Koine Greek) እና በላቲን (Latin) ቋንቋዎች የተጻፉ የመጽሐፈ ሄኖክ ቁርጥራጮች ተገኝተዋል። በዚህም መጽሐፉ አስቀድሞ በአይሁድ ዘንድ የታወቀ እንደሆነ ማረጋገጫ የሰጠ ነው። በተጨማሪም በተለያዩ የ 1ኛና የ2ተኛ ክ/ዘመን ደራሲዎች እንደተጠቀሰ ይታወቃል። [Cheyne and Black, Encyclopaedia Biblica (1899), "Apocalyptic Literature" (column 220)]
ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት መጽሐፉን ስላላገኙት በቀኖና ውስጥ ባይከቱትም ኢትዮጵያ መጽሐፉ በእጇ ስላለ እና በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት ያለው ብሎም ከሌሎች ቅዱሳት መጽሐፍት ጋር የሚስማማ ስለሆነ በቀኖና ውስጥ ከታዋለች።
=>>> መጽሐፈ ኩፋሌ (Book of Jubilees) :- የዚህ መጽሐፍ ጸሀፊ ሙሴ እንደሆነ ይታመናል። ይህንንም በመጽሐፉ ይዘት ማረጋገጥ ይቻላል። ይህም መጽሐፍ ልክ እንደ መጽሐፈ ሄኖክ በሙት ባህር ጥቅሎች (Dead see scrolls) ተገኝቷል። ይህም ልክ እንደ መጽሐፈ ሄኖክ አስቀድሞ ይታወቅ እንደ ነበር የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም በቀደምት የቤተክርስቲያን አባቶች ለማስተማሪያነት እንደ ተጠቀሰ ይነገራል። ለአብነትም ኤጲፋኔዎስ (Epiphanius) ፣ ጀስቲን (Justin Martyr), አርጌንስ(Origen) , የታርሱሱ ዲዮዶሮስ(Diodorus of Tarsus) ይጠቀሳሉ። [Charles, R. H. (1902). The book of Jubilees or the Little Genesis . London: Adam and Charles Black. pp. lxxvii–lxxxvi.]
=>>>በተጨማሪም በሙሴ ኦሪት መጻሕፍት የማይገኙ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱ ጥቅሶች አሉ። ለምሣሌ:-
" ሙሴም። እጅግ እፈራለሁ እንቀጠቀጥማለሁ እስኪል ድረስ የሚታየው እጅግ የሚያስፈራ ነበር፤" (ወደ ዕብራውያን 12:21) መመልከት ይቻላል። ይህ በሆነበት ሁኔታ ከአምስቱ የሙሴ መጽሐፍት ውጪ የሆነ ተቀባይነት የለውም ብሎ መደምደም አይቻልም። ቅድስት ቤተክርስቲያን በትውፊት በደረሳት መሠረት መጽሐፉን በቀኖና ውስጥ ከታ ትጠቀምበታለች።
=>>>በተጨማሪም በ Dead See Scrolls መጽሐፈ ሲራክ፣ ተረፈ ኤርሚያስ ያሉ የዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍት ተገኝተዋል።
=>>በቀጣይ ጽሁፍ ተጨማሪ ሌሎች የዲዩትሮካኖኒካል መጽሐፍት ምንጮችን እንመለከታለን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር!
©ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ!
No photo description available.
8
1 Comment
15 Shares
Like
Comment
Share

No comments:

Post a Comment