Friday 2 October 2020

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን!

በእንተ ሰማንያ አሃዱ (ክፍል-፯)
ንዑስ ርእስ ፪
[በመጻሕፍተ መቃብያን ለሚነሱ ትችቶች ምላሽ / ሰይጣን ለአዳም አልሰግድም በማለት ወደቀ ስለሚለው]
√ ባለፈው ባቀረብነው ጽሁፍ "ቃየን አቤልን በሴት ቀንቶ ገደለው" ተብሎ ስለ ተጻፈው የ1ኛመቃብያን ሀሳብ ተመልክተናል። በዚህ ጽሁፍ ደግሞ በ 3ኛ መቃብያን ላይ ተሃድሶ ፕሮቴስታንቶች የሚያነሱትን ትችት እንመለከታለን።
"የሚጠፉ በእኔም የሚስቱ ሰዎች ፈጽመው ይበዙ ዘንድ የአዳም ልጆች ከእኔ ጋር ይጠፉ ዘንድ በተናገሩ ጊዜ እኔ ደስ ይለኛል ለበታቼ አልሰግድም በማለቴ ስለ አባታቸው ስለ አዳም ከክብሬ ተዋርጃለሁና" ተብሎ በ 3ኛመቃ1÷15 ላይ የተጻፈውን ሀሳብ ይጠቅሱና ሰይጣን የወደቀው ለአዳም አልሰግድም በማለቱ ነውን? ብለው ይጠይቃሉ። በተጨማሪም በኢሳ14÷13-15 ከተጠቀሰው ሀሳብ ጋር ይጋጫል ይላሉ።
"አንተን በልብህ። ወደ ሰምይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፤ ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ።ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጕድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ።" ኢሳ14÷13-15
በመጨረሻም ይህ ሀሳብ ከቁርአን የተወሰደ ነው ብለው ይደመድማሉ።
[ምላሽ]
√ የዚህ ጥያቄ ሀሳብ የመነጨው "ለአዳም አልሰግድም በማለቴ ከክብሬ ተዋርጃለው" ብሎ የተናገረውን አካል ማንነት ካለማወቅና ሙሉ የመጽሐፉን ክፍል ካላማንበብ ነው። "ለበታቼ አልሰግድም በማለቴ እግዚአብሔር ስለ አባታቸው ስለ አዳም ከክብሬ አዋርዶኛልና" ብሎ የተናገረው እራሱ ዲያቢሎስ እንጂ የመጽሐፈ መቃብያን ጸሀፊ አይደለም። ዲያቢሎስ ደግሞ ሀሰተኛ የሀሰት አባት ተብሎ የተገለጸ ነው። በትዕቢቱ መክንያት ወድቆ ሳለ ለአዳም አልሰግድም በማለቱ እግዚአብሔር እንደ ጣለው በውሸት የተናገረበት ክፍል ነው።
" እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።"
ዮሐ 8÷44
√ ይሄን ጥያቄ የሚጠይቁ ሰዎች ሙሉውን የመጽሐፈ መቃብያን ሣልስ ምእራፎች አላነበቡም ይሆንን? የሚገርመው መጽሐፈ መቃብን ሰይጣን ዲያቢሎስ የወደቀበትን እውነተኛ መክንያት ከአንድ ምእራፍ በኃላ እንዲህ በማለት ያስቀምጣል።
"ነቢዩም እንዲህ አለ አንተ ጥፉና አጥፊ በትቢትህና በልብህ ደንዳናነት ፈጣሪህን በማሳዘን ፈጣሪህንም ባላ ማመስገንህ....የፈጠረህን ፈጣሪ ነኝ በማለት በታበይህ ጊዜ በአንተ ፈንታ የሚያመሰግን አዳምን ፈጠረው" 3ኛመቃ2÷8-11
ልብ እንበል መጽሐፈ መቃብያን ሰይጣን የወደቀው በትዕቢቱ ፈጣሪ ነኝ በማለቱ እንደሆነ እና የወደቀውም አዳም ከመፈጠሩ አስቀድሞ እንደሆነ በግልጽ አስቀምጦታል።
√ በኢሳ14÷14 ላይ ዲያቢሎስ ተናገረው ተብሎ የተገለጸው ሀሳብም በዚው በመጽሐፈ መቃብያን ላይ ሰፍሮ ይገኛል። "እርሱም(ዲያቢሎስ) እንዲህ አለ:- ከእኔ በላይ ማነው? ወደ ባሕሩ ጥልቅ እገባለሁና፣ ወደ ሰማይም እወጣለሁ፣ ጥልቆችንም አያለው..." 3ኛመቃ1÷3 መጽሐፈ መቃብያንን በትንቢተ ኢሳይያስ የተጻፈውን ሀሳብ የበለጠ የሚያረጋግጥ እና የሚያብራራ ነው።
√ መጽሐፈ መቃብያን ከቁርአን ወስዶ ነው የጻፈው የሚለው ሀሳብ ያፈጠጠ ውሸት ነው። መጽሐፈ መቃብያን ከክርስቶስ ልደት በፊት የተጻፈ እንደሆነ የሚታወቅ እውነት ሆኖ ሳለ ከቁርአን ወሰደው ማለት ምን የሚሉት ነው? ቁርአን መጽሐፈ መቃብያን ከተጻፈ ከ 800 አመት በኃላ የመጣ ነው። ቁርአን በመጽሐፈ ቅዱስ የተጻፉትን እና ክርስቲያኖች የሚያምኑትን አዛብቶ በተሳሳተ መንገድ እንደሚያቀርበው በመጽሐፈ መቃብያንም ሰይጣን የተናገረውን እውነተኛ መክንያት አስመስሎ ከመጽሐፈ መቃብያን ወስዶ ጽፎ ይሆናል። ቴዎድሮስ ደመላሽ እና መሰሎቹ ግን መጽሐፈ መቃብያንን በግድ ከሌሎቹ መጻሕፍት ጋር ለማጋጨት ይጥራሉ።
እግዚአብሔር ቢፈቅድ በቀጣይ ክፍል በመጽሐፈ ሲራክ ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንሰጣለን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
©ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ
Image may contain: text
16
4 Comments
4 Shares
Like
Comment
Share

No comments:

Post a Comment