Friday 2 October 2020

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን!

በእንተ ሰማንያ አሃዱ (ክፍል-፯)
ንዑስ ርእስ ፩
[በመጻሕፍተ መቃብያን ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች/ትችቶች የተሰጠ ምላሽ]
=>>>ቃየን አቤልን በሴት ቀንቶ ገደለው ስለ ሚለው
√ የሀገራችን ተሃድሶዎች በተለያየ መልኩ የዲዩትሮካኖኒካል መጻሕፍትን መተቸት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ከሌሎቹ የ 66ቱ መጻሕፍት ጋር ይጋጫሉ የሚል ስሁት ሙግት ያቀርባሉ። ለአብነትም ቴዎድሮስ ደመላሽ "ሰማንያ አሃዱ በእግዚአብሔር ቃል ሲመዘን" ብሎ ያዘጋጀውን መጽሐፍ እና በእነ ጽጌ ስጦታው "ኦርቶዶክስ መልስ ካላት እኛም ጥያቄ አለን" በማለት ያወጡትን VCD መመልከት ይቻላል። ይህ አይነቱ ሙግት ሙስሊሞች መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በራሱ ይጋጫል እንደሚሉት ያለ ነው። መጀመሪያም ስህተት ፍለጋ መጻሕፍቱን ስለሚያነቧቸው አጠቃላይ የመጽሐፉን ዳራ ሳያጠኑ እንደ ሙስሊሞች መጻሕፍቱን ለመጋጨት ይጥራሉ። በዚህ ጽሁፍ በ 1ኛ መጽሐፈ መቃብያን ላይ ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ ተሰቶበታል። ይከታተሉን!
√ "ወንድሙ የሚወድደው መስሎት በየዋህነት የተከተለውን ወንድሙን በገደለው በቃየን መንገድ አትሂድ እርሱም በሴት ቀንቶ ወንድሙን ገደለው::" 1ኛመቃ23:1-2 ተብሎ የተጻፈውን ይይዙና በኦሪት ዘፍጥረት ቃየን አቤልን የገደለው እግዚአብሔር የአቤል መሥዋእትን ተቀብሎ የእርሱን ስላልተቀበለው ቀንቶ ነው ተብሎ ከተጻፈው ጋር ይጋጫል ይላሉ። በተጨማሪም "ቃየን ስለምን ወንድሙን ገደለው? የእርሱ ስራ ክፉ የወንድሙ ጽድቅ ስለነበረ ነው::"1ኛዮሐ.3:12 በማለት በልቡ ክፋትና በአቤል መልካምነት የተነሳ እንጂ እንዴት በሴት ምክንያት ነው የገደለው ይባላል? ይላሉ።
[ምላሽ]
√ ወደ ዋናው ምላሻችን ከመግባታችን በፊት ጥቂት ጥያቄዎችን እናንሳ!
ቅዱስ ጳውሎስ ከመጽሐፈ መቃብያን ጠቅሶ ጽፏል።
" ነገር ግን። ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን።"
1ኛቆሮ 2:9
ይህ ጥቅስ ከወዴት ይገኛል? ብለን ብንጠይቅ የሚገኘው በመጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ ነው። "ለደጋግ ሰዎች የተዘጋጀች ደስ የምታሰኝ ዓይን ያላየውን ጆሮም ያልሰማውን በሰው ልብ ያልታሰበውን እግዚአብሔር ደስ ላሰኙት ያዘጋጀውን..." ተብሎ በ1ኛመቃ14÷20 ላይ ተጽፏል። መጽሐፈ መቃብያንን የማይቀበሉ ሰዎች ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው ከየት አምጥቶ ነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡን እንጠይቃለን።
√ ሙሴ ከጻፋቸው ከኦሪት መጻሕፍት ውጪ በዲዩትሮካኖኒካል መጻሕፍት እና በአዋልድ መጻሕፍት ያሉ ታሪኮችን አንቀበልም ካሉ በአምስቱ የኦሪት መጻሕፍት የሌሉ ነገር ግን የሀዲስ ኪዳን ጸሀፊዎች የጠቀሷቸው ታሪኮች ከየት መጡ?
1. ቅዱስ ጳውሎስ ሙሴን የተቃወሙትን ጠንቋዮች ስም ከየት አግኝቶ ጻፈ?
" ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ።"
2ኛጢሞ3:8
2. በድጋሚ ቅዱስ ጳውሎስ በኦሪት መጻሕፍት ያልተጻፈውን ሙሴ የተናገረውን ከየት አምጥቶ ጻፈው?
" ሙሴም። እጅግ እፈራለሁ እንቀጠቀጥማለሁ እስኪል ድረስ የሚታየው እጅግ የሚያስፈራ ነበር፤" ዕብ12:21
3. ሐዋርያው ይሁዳ ስለ ሙሴ ስጋ ቅዱስ ሚካኤል እና ዲያቢሎስ ያደረጉትን ክርክር ከየት አምጥቶ ጻፈው?
" የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር። ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም።"
ይሁ1:9
4. ከዚህ በታች የተጠቀሰው የበልአም ትምህርት ከየትኛው የኦሪት መጽሐፍ የተገኘ ነው?
" ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበልዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ፥ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ።"
ራእ 2:14
እነዚህን መሰል ሌሎችን መጥቀስ እንችላለን። ከዚህ የምንረዳው ሙሴ ከጻፋቸው 5ቱ መጻሕፍተ ኦሪት ውጪ በሌሎች አዋልድ መጻሕፍት የተጻፉ ታሪኮች እንዳሉ ነው።
√ አቤልና ቃየን ከአዳምና ከሔዋን ተለይተው ለምን ብቻቸውን መሥዋእት አቀረቡ? አቤልና ቃየን ከመሥዋእቱ በፊት የነበራቸው ግንኙነት እንዴት ነበር? በዘፍ4÷17 ላይ "ቃየንም ሚስቱን አወቀ ጸነሰችም ሄኖህንም
ወለደች" ይላል። ይህች ሴት ከየት መጣች? ቀድሞ አዳምና ሔዋን የወለዱት ቃየንና አቤል ብቻ መሆናቸውን ገልጾ አልነበረምን? ይህች ሴት ከእነርሱ ጋር ከነበረች እንደ አቤልና እንደ ቃየን ለምን መሥዋዕት አላቀረበችም?
√ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ስናገኝ በመጽሐፈ መቃብያን የተጻፈው ሀሳብ ግልጽ ይሆንልናል። በመጽሐፈ መቃብያን፣ በመጽሐፈ ኩፋሌ፣ በገድለ አዳም (First Book of Adam And Eve)፣ መጽሐፈ ቀሌምንጦስ (Book Of Clement) ተባብረው የእነዚህን ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጡናል። [First Book of Adam and Eve/ገድለ አዳም] እና [ Book Clement/ መጽሐፈ ቀሌምንጦስ] በጥንታዊያን ቱውፊታውያን አብያተ ክርስቲያናት ተቀባይነት ያላቸዎ እና የጥንቷ ቤተክርስቲያን አባቶች ለማስተማሪያነት የተጠቀሙባቸው ናቸው።
√ በመጀመሪያ መታወቅ ያለበት ቃየን አቤልን በመሥዋእት መክንያት ገደለው የሚለው ሀሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ አልተጻፈም። በመጽሐፈ መቃብያን እና በኦሪት ዘፍጥረት ላይ የተጻፈው ሀሳብ መክንያት እና ውጤትን (Cause and Effect) የሚያሳይ ነው። መጽሐፈ መቃብያን መሥዋእት ያቀረቡበትን መክንያት እና መነሻውን ሀሳብ ሲናገር ኦሪት ዘፍጥረት ደግሞ ውጤቱን (መሥዋእት ማቅረባቸውን) ጽፏል።
መጽሐፈ ኩፋሌ ሲገልጽ አባታቸው አዳም ከቃየንና ከአቤል ጋር ሌሎች ሁለት ሴቶች እንደ ተወለዱ ይናገራል።
"ሔዋንም በአምስተኛው ሱባኤ አዋንን ወለደቻትአዳምም በስድስተኛው ሱባኤ ልዋን ወለዳት" ኩፋ.5:8
ይላል። እነዚህ ሴቶች ልጆች ከወንዶች ጋር መንትዮች ሆነው
እንደተወለዱ ገድለ አዳምም|First Book of Adam and Eve Prologue; P.1|
ይገልጻል። መጽሐፈ ቀሌሜንጦስ (ቀለሜንጦስ ዘሮም) እንዲህ ይላል:- "አዳምና ሔዋን ከደብር ቅዱስ ወርደው ከሱ በታች ተቀመጡ።በዚሁ አዳም
ሔዋንን ተገናኛት፣ እሷም ፀነሰች። የመውለጃዋ ጊዜም ደረሰ።
ቃየልንና ሉድንም መንታዎች ወለደች።ዳግመኛም ሔዋን ፀነሰች። የመውለጃዋም ጊዜ ደረሰ፣ መንታዎቹን አቤልንና አቅሌምያንም ወለደች። እነዚህ ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶች የአዳም ልጆች አድገው፣ለጋብቻ ደረሱ። አዳም ይህን ተመልክቶ ሔዋንን እነሆ እግዚአብሔር እነዚህ ልጆቻችንን አሳደጋቸው። ስለዚህ ቃየል የአቤልን እህት አቅሌምያን ያግባት፣ አቤል ደግሞ የቃየልን እህት ሉድን ያግባት አላት።አዳምና ሔዋን በዚሁ ተስማሙ።" ይላል:: [መጽሐፈ ቀለሜንጦስ፣ምዕራፍ አንድ]
√በዚህም ምክንያት በአንድነት ያደጉት መንትያ የሆኑት ማለት ከቃየን ጋር አብራ የምትውል (የተወለደችና) ከአቤል ጋር አብራ የምትውል(የተወለደች) በአንድነት እንደማይጋቡ አዳም በልቦናው ስላወቀና እግዚአብሔርም ስለ ገለጸለት ሁለቱም ሴቶች ልጆች ተቀያይረው እንዲጋቡ ፈቀደ። ገድለ አዳምም ስለዚህ ሁናቴ ሲገልጽ:-
Then Adam said to her|Eve|, "We will join
Abel's sister in marriage to Cain, the Cain's sister to
Abel."|Second Book of Adam and Eve; Chapter L
XXVIII|. ይላል።
ነገር ግን ቃየን በአባቱ ሃሳብ ስላልተስማማና ስላዘነ አዳም ወዲያውኑ ያደረገው አቤልና ቃየን በእግዚአብሔር ፊት
መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ነገራቸው።ይህን ያደረገበት ምክንያት ከአቤል ጋር ያልተወለደችውን መንትያ እግዚአብሔር መሥዋዕቱን ከተቀበለው ከእርሷ ጋር እንዲጋባ ነበር::
"But when Adam saw that the older brother hated the younger, he endeavor f to
soften their hearts, and said to Cain, "O my son, take of the fruits of your sowing and make an offering to God, so that He might forgive you for your wickedness
and sin." He said also to Abel, "Take son of your
sowing and make an offering and bring it to God, so that He might forgive you for your wickedness and sin."
|Second Book of Adam and Eve; Chapter LXVII|.
ቃየን ግን ቀድሞውንም በዚህ ውሳኔ አዝኖ ነበርና ይበልጥ ክፋት ሠራ። ይህም ለእግዚአብሔር ከፍሬው እንክርዳድ ያለበትን መሥዋዕት ሊቃጠል ነው እንጂ። እግዚአብሔር ንስሐ እንዲገባ ምክር መከረው።
"ለምንስ ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ
የሚያበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅዋ
ታደባለች ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው።አንተ ግን በእርሷ ንገስባት።"
ዘፍ4÷6-7 ያለው።
ይህም ማለት የአባትህ ሃሳብ የእኔ ነውና ተቀበለው በአባትህ ሃሳብ አትናደድ; አትዘን; የአባትህ ሃሳብ የእኔ ነውና። ለዚህ ነው የአቤልን መሥዋዕት የተቀበልኩት ሲል ነው።
[God would accept Abel's offering. Then God looked at Abel and accepted his offering ... because of his good heart and pure body. [Second Book of Adam and Eve; Chapter LXVII].
√ቃየን ወንድሙን ለመግደል ያነሳሳው የመጀመሪያው ምክንያት በሴት መሆኑን እንረዳለን ማለት ነው:: ለዚህም ነው ገድለ አዳም
[Cain becomes jealous of Abel because of his sisters. |Chapter LXXVI| ያለው:: ምክንያቱም
እግዚአብሔር የአቤልን መሥዋዕት ከተቀበለ የአባቱ የአዳም ፈቃድ
በማራራቅ ሊያጋባቸው እንደወሰነ ስላወቀ ይህችን የሚፈልጋት ሴት
ለማግባት ደግሞ ወንድሙን ለመግደል በቅናት ተነሳ። ገድለ አዳምም
Jealousy overcomes Cain[Chapter LXXVIII| ይላል።]
ዘፍ4÷17 ፣ ኩፋ5÷8 በ1ኛዮሐ3÷12 ላይ የተገለጸውን
ከመቃብያንና ከዘፍጥረት ጋር ሃሳባቸው የተጋጨ አይደለም:: የአቤል
ሥራው ወይም ጽድቁ ምን ነበር? የቃየንስ ክፉ ሥራ ምን ነበር? ብለን ብንጠይቅ የመጀመሪያው ምክንያት መሥዋዕት ማቅረባቸው ሊሆን አይችልም። ነገር ግን ቃየን በአቤል በመቅናቱ ነው።የቀናበት
ምክንያት ስንመለከት ደግሞ የመጀመሪያው የሚወዳት ሴቷን አቤል እንደሚያገባት ሲያውቅና የእርሱ እንደማትሆን ሲረዳ በቅናት ወንድሙን ገድሎታል። ሐሰት በ 4 ደረጃዎች እንደሚሰራ ማለት ነው:: ይህም በመጀመሪያ ከልብ ይጸነሳል፣ ከዚያም በገጽታ፣ ከዚያም በቃላት ወይም
በአንደበት በመናገር በመጨረሻም በተግባር እንደምንፈጽመው ማለት
ነው።ልክ እንደዚህ ሁሉ መጽሐፈ መቃብያን የመጀመሪያውን ምክንያት የሆነውን በሴት እንደቀና ገለጸው፣ ቀጥሎ ያለው ደግሞ በኦሪት እንደተገለጸው በመሥዋዕቱ ምክንያት እንደሆነ ገልጾታል።ሐዋርያው
ዮሐንስ ደግሞ የሦስተኛው የሆነውን የገደለበትን ምክንያትና ውጤቱን ጽፎታል። ከዚህም የምንረዳው በተለያየ ክፍሎች የአቤልና የቃየንን ጉዳይ ተካፍለው እንደጻፉት ነው። እንዲህ ካልሆነማ ቃየን አቤልን የገደለበት ምክንያት በመሥዋዕቱ ነው? ወይስ ክፉ ስራ ስለሠራ ነው? ክፉ ሥራ ተብሎ የተገለጸው ምን ይሆን? ታዲያ መጽሐፈ መቃብያን
የመጀመሪያው ምክንያት ወስዶ ቢጽፈው ስህተቱ ምኑ ላይ ነው? የመጽሐፈ መቃብያንን ሀሳብ የማይቀበሉ ሰዎች ከላይ ያስቀመጥናቸውን ጥያቄዎች ሁሉ ሊመልሱ ግድ ይላቸዋል።
ማጠቃለያ
√ ቅዱስ ጳውሎስ ከመጽሐፈ መቃብያን ጠቅሶ መጻፉ ለመጻሕፉ ተአማኒነት ማረጋገጫ ይሰጣል።
√ ሙሴ በጻፋቸው በ 5ቱ የኦሪት መጻሕፍት የማይገኙ ግን በሐዲስ ኪዳን ጸሀፊዎች የተጠቀሱ ሀሳቦች መኖራቸው አዋልድ መጻሕፍትን እንደ ተጠቀሙ ያሳያል።
√ መጽሐፈ መቃብያን ከመሥዋእት በፊት የነበረውን ዋናውን ግጭት የሚናገር ሲሆን ኦሪት ዘፍጥረት ደግሞ ከመሥዋእቱ ጀምሮ ያለውን ታሪክ ያሳያል።
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር!
©ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ
Image may contain: text
17
16 Comments
9 Shares
Like
Comment
Share

No comments:

Post a Comment