Friday 2 October 2020

 በአብ ስም በወልድ ስም በመንፈስ ቅዱስ ስም አንድ አምላክ አሜን!

በእንተ ሰማንያ አሃዱ (ክፍል-፭)
የሐዲስ ኪዳን የሥርአት መጻሕፍት (Books of Church Orders) ምንጮች
የሥርአት መጻሕፍት የሚባሉት 27ቱን የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ወደ 35 የሚያደርሱት 8ቱ መጻሕፍተ ሐዲሳት ናቸው። አጠቃላይ መጠሪያቸው ስምንቱ ብሔረ ቀኖናት ዘቀለሜንጦስ ወይም ሲኖዶስ ዘቅዱሳን አበዊነ ሐዋርያት የሚል ነው። ሥርአቶቹን የሰሯቸውና የደነገጓቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ሲሆኑ በእነርሱ ትምህርትና ትእዛዛት ላይ ተመሥርተው በጽሁፍ የቀረጿቸውና ያቀነባበሯቸው ደግሞ ከአንደበታቸው የተማሩ በእጃቸው የተሾሙ በእግራቸው የተተኩ ሐዋርያዊያን አበው (Apostolic Fathers) ናቸው። የቅንብራቸው መነሻ ጊዜ (Terminus a Quo) የ 2ተኛው ምዕተ አመት አጋማሽ ሲሆን መፈጸሚያው ደግሞ (Terminus end Qucm) ሶስተኛው ምእተ አመት መጨረሻ ነው። ለስምንቱ መጻሕፍት ቅንብር መሠረት የኾኑት የሚከተሉት ናቸው።
1.የሐዋርያት ቀኖና (Apostolic Canon/Ecclesiastical Canons):- ይህ አብዛኛው ቀኖናው በሐዋርያት እንደ ተጻፈ የሚታመነው የሐዋርያት ቀኖና የቤተክርስቲያን አስተዳደርን እና ሥርአትን በሚመለከት 85 ቀኖናዎችን የያዘ ነው። ሐዋርያት እንደ ጻፉት እስከ አሁን በትክክል ማረጋገጥ ባይቻልም ከምሥራቅ ቤተ-ክርስቲያን ልምድ ስንነሳ 85 ሐዋርያውያት ቀኖናት የሐዋርያትን ትምህርትና ሥርአት ይዘው በመገኘታቸው ለሥርአተ አምልኮ ጥቅም ላይ ውለዋል። ይህን ሐዋርያውያት ቀኖና በ691 በትሩሎ በተጠራው በምስራቅ ሲኖዶስ ( Eastern Council in Trullo) ተቀባይነት አግኝቷል።[1]
2. ዲደኬ ትምህርተ ሐዋርያት(The Didache):- ሙሉ የመጽሐፉ ስም "በዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ለአሕዛብ የተሰጠ የጌታ ትምህርት/ Teaching of the Lord by the Twelve Apostles to the Gentiles" የሚል ነው። ኦደስት(Adust) የተባለ አጥኚ ዲዳኬ ከ50-70 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት እንደ ተጻፈ በጥናቱ አሳይቷል። [2] ከ 8ቱ የሥርአት መጻሕፍት አንዱ የሆነው እና ከ Apostolic Constitution ተወስዶ የተቀናበረው መጽሐፈ ዲድስቅልያ ከዲዳኬ ውስጥ የወሰዳቸው ንባቦችና ትምህርቶች አሉት።
3. ከትንሳኤው እስከ እርግቱ ድረስ ለ 40 ቀናት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማራቸው ትምህርቶች:- የሐዋርያት ሥራ ጸሀፊ ቅዱስ ሉቃስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኃላ ደቀ መዛሙርትን እንደ አስተማራቸው ጽፏል።
" ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው።"
(የሐዋርያት ሥራ 1:3)
የዚህ ትምህርት ስብስብ መጽሐፈ ኪዳን (Book of Covenant) በሚል በ 8ቱ የሥርአት መጽሐፍት ውስጥ ይገኛል።
4. መጽሐፈ ቀሌምንጦስ:- ቅዱስ ቀሌምንጦስ ዘሮም (St. Clement of Rome) ከሐዋርያት በኃላ ከተነሡትና በትምህርታቸውም ለቤተክርስቲያን ማኅቶት ከሆኑት አባቶች ውስጥ ቀዳሚው ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ መልእክቱ "ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከቀሌምንጦስና ደግሞ..." ሲል ስሙን የጠራው ይህንኑ የሮም ሊቀ ጳጳስ እንደ ሆነ ሊቁ አውሳብዮስ(Eusebius) ፣ ቅዱስ ይሩማሲስና (St. Jerome) ሊቁ ኦሪገን(Origen) ይገልጻሉ። [3] መጽሐፈ ቀለሜንጦስ ከስምንቱ የሐዲስ ኪዳን የሥርአት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኝ ነው።
ቅዱሳን ሐዋርያት በተሰበሰቡ ጊዜ ሁሉ ስለ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን፣ ስለ ካህናት አገልገሎት፣ ስለ ምእመናን ድርሻ፣ ስለ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ውሳኔዎችን አስቀምጠዋል። ይኸውም የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር በነበረው በቀለሜንጦስ እጅ ለካህናት እና ለምእመናን ትልከዋል።
=>>>በመጽሐፍ ቅዱስ ሐዋርያት በዘመናቸው የተለያዩ ሥርአትን እንደሰሩ ይናገራል። በ50ዓ.ም በእየሩሳሌም ተሰብስበው የሰሩት ሥርዓት በሐዋርያት ሥራ ተመዝግቦ ይገኛል። ሐዋ15÷1-29 ይህንን የሰሩትን ስርአት ምእመናን ይጠብቋቸው ዘንድ ሰተዋቸዋል።
" በከተማዎችም ሲዞሩ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የቈረጡትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ ሰጡአቸው።"
(የሐዋርያት ሥራ 16:4)
=>>>ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ በላከው መልእክቱ ቅዱስ ስጋውን እና ክቡር ደሙን ለመቀበል ስለ ሚገባ ጥንቃቄ ጽፎላቸው ነበር። የቀረውን ሥርአት ወደ ቆሮንቶስ ሲሄድ እንደ ሚሠራላቸው ነግሯቸዋል። የሰራላቸው ሥርአት በመጽሐፍ ቅዱስ አልተጻፈም። ነገር ግን በቤተክርስቲያን የስርአት መጻሕፍት ተጽፎ ይገኛል።
" ማንም የራበው ቢኖር ለፍርድ እንዳትሰበሰቡ በቤቱ ይብላ። የቀረውንም ነገር በመጣሁ ጊዜ እደነግጋለሁ።"1ኛቆሮ 11:34
=>>>በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቲዎስ በጻፈለት መልእክት ዲያቆናትና ኤጲስ ቆጶሳት አገልግሎት ለመታጨት ምን መሆን እንዳለባቸው እና ስለ አገልግሎት ድርሻቸው ጽፎለታል።
1ኛጢሞ3÷1-13
=>>>ከላይ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጹት ሥርአቶች በአራቱ መጻሕፍተ ሲኖዶስ ሰፍረው ይገኛሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ በትንሹ ተጽፈው የሚገኙት ሥርአቶች በእነዚህ መጻሕፍት ተብራርተው እና ተሟልተው ይገኛል። እነዚህ መጻሕፍት ሥርአተ ጽዮን ሲኖዶስ፣ አብጥሊስ ሲኖዶስ፣ ትእዛዝ ሲኖዶስ እና ግጽው ሲኖዶስ ይባላሉ።
=>>>የተቀሩት አራቱ ካላይ የተገለጹት 1ኛ መጽሐፈ ኪዳን፣ 2ኛ መጽሐፈ ኪዳን፣ መጽሐፈ ዲድስቅልያ እና መጽሐፈ ቀሌምንጦስ ናቸው። እነዚህ 8ቱ የስርአት መጻሕፍት ቱውፊታውያን በሆኑ አብያተ ክርስቲያናት (Eastern Orthodox, Oriental Orthodox እና Catholic ) ዘንድ በሥርአተ አምልኮ (Liturgy) ውስጥ አገልገሎት ላይ የሚውሉ ናቸው። [4]የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በቀኖና ተክርስቲያን ውስጥ አስገብታ ትገለገልባቸዋለች። በዚህም በአለም ደረጃ Broader Canon ያላት ቤተክርስቲያን እንደሆነች ይነገርለታል። በሌላ መርሃ ግብር የተሃድሶ መናፍቃን የ 80 አሃዱ መጻሕፍት በሆኑት የዲዩትሮካኖኒካል መጻሕፍት ላይ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ይዘን እንመጣለን።
ማጣቀሻዎች
[1] Canons, Apostolic , 1910 New Catholic Dictionary , accessed 16 April 2016.
[2] J-P Audst, LA Didache: Instruction des Apotres. (Paris: Etudes Bibliques, 1958)
[3] Eusebius, Hist. Eccl. 2.6.3 (Lake, LCL); Jerome, Dir. 1ll. 15(NPNF 2/3: 366); Origen , Fr. Jo. 1.29 (ANF 9:378)
[4] Samuel A.B. Merce. The Ethiopic Liturgy: Its Source l, Development and Present Form
ስብሐት ለእግዚአብሔር!
©ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ
Image may contain: text
10
7 Shares
Like
Comment
Share

No comments:

Post a Comment