Friday 2 October 2020

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን!

[በእንተ ሰማንያ አሃዱ]
ክፍል-፱
ንዑስ ርእስ-፩
[በመጽሐፈ ኩፋሌ ላይ ለሚነሱ ትችቶች የተሰጠ ምላሽ/ የእግዚአብሔር መላእክት ተጋቡ ስለ ሚለው]
=>>> መጽሐፈ ኩፋሌን የማይቀበሉ ሰዎች በመጽሐፉ ላይ ከሚያነሱት ትችቶች አንዱ ኩፋሌ4÷9 ላይ ያለውን ሀሳብ ነው።
ኩፋ4÷9 "የአዳም ልጆች በምድር ላይ ይበዙ ዘንድ በጀመሩ ጊዜ እንዲህ ሆነ፣ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው የእግዚአብሔር መላእክትም በዚህ ኢዩቤልዩና በአንዲቱ አመት እነዚህን አዩአቸው። እነዚህ ያዩአቸው መልከ መልካሞች ነበሩና ከመረጧቸው ሁሉ ሚስቶች ሊሆኗቸው ወሰዱአቸው ወንድ ልጆችንም ወለዱላቸው እነዚህም ረዓይት ናቸው"
√ ይህን የመጽሐፈ ኩፋሌ ሀሳብ ይወስዱና መላእክት እንዴት አገቡ ይባላል? መጽሐፍ ቅዱስ መላእክት መናፍስት እንደሆኑ ደግሞም እንደማያገቡ ይናገራል። ማቴ22÷30 ስለዚህ የመጽሐፈ ኩፋሌ ሀሳብ የተሳሳተ ነው ብለው ይሞግታሉ።
[ምላሽ]
√ ቴዎድሮስ ደመላሽ ና መሰሎቹ የተሃድሶ ፕሮቴስታንቶች እነርሱ የማይቀበሏቸውን መጻሕፍት ከመተቸታቸው በፊት 66ቱን መጽሐፍ ቅዱስ በሚገባ እንዲያውቁት እየጋበዝን ወደ ምላሻችን እንግባ። ከላይ በመጽሐፈ ኩፋሌ ላይ የቀረበው ታሪክ እና ሀሳብ በ 66ቱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገባ ተገልጿል። ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ይሁዳ ከመጽሐፈ ኩፋሌ ወስደው በመልእክቶቻቸው ላይ አስፍረዋል። በኦሪት ዘፍጥረት ላይ [የእግዚአብሔር ልጆች] ተብለው የተጠሩት በመጽሐፈ ኩፋሌ [የእግዚአብሔር መላእክት] ተብለው ተገልጸዋል። "መላእክት" ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ አስቀድመን እንመልከት።
=>>> መልአክ (Angel) የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ሁለት የተለያየ ተፈጥሯዊ ማንነት ያላቸውን አካላት ለመግለጽ ውሏል።
1. መናፍስት የሆኑትን መልእክተኞች (ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚላኩትን መልእክተኞች)
መዝ104÷4 " መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል።"
2. ከሰው ወገን ሆነው መልአካዊ አናኗርን ገንዘቡ ያደረጉ ሰዎች ( በምስጋና፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በንጽህና የሚኖሩ ሰዎች፣ አለቆች)
√ በዮሐንስ ራእይ ላይ እንደ ተጻፈው የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት አለቆች መልአክ ተብለው ተጠርተዋል።
ራእ2÷1 " በኤፌሶን ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ (angel) እንዲህ ብለህ ጻፍ።"
√ በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቲዎስ በላከለት መልእክቱ ከሰው ወገን የሆኑትን መልአክ ብሎ ይጠራቸዋል።
1ጢሞ5÷21 " አንድን እንኳ በአድልዎ ሳታደርግ፥ እነዚህን ያለ መዘንበል እንድትጠብቅ በእግዚአብሔርና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በተመረጡትም መላእክት ፊት እመክርሃለሁ።"
√ በመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎችም መልአክ ተብለው እንደተጠሩ ካየን ዘንዳ በመጽሐፈ ኩፋሌ ላይ የሰፈረው ሀሳብ ምን እንደሆነ እንመልከት። የእግዚአብሔር መላእክት (የእግዚአብሔር ልጆች) የተባሉት እነማን ናቸው ስንል በምናኔ ሕይውት ንጽህናን ጠብቀው ይኖሩ የነበሩት የሴት ልጆች (ዘሮች) ናቸው። በንጽህናቸው መላእክት ተብለው የተጠሩት የሴት ልጆች የተረገሙትን የቃየን ልጆችን ሲያዩ በዝሙት ጾር በመነደፋቸውና ከእነርሱ ጋር በመገናኘት ንጽህናቸውን በማጉደፋቸው ምክንያት የእግዚአብሔር መላእክት ከቃየን ልጆች ጋር ተጋቡ ብሎታል። በዚህም የቁጣ ምልክት የሆኑትን ኔፍሊሞች ወይም ረዓይታንን ወለዱ። ይህን ሀሳብ በመጽሐፈ ኩፋሌ፣ በኦሪት ዘፍጥረት፣ በቅዱስ ጴጥሮስ መልእክት እና በቅዱስ ይሁዳ መልእክት ከተጠቀሱት ሀሳቦች ጋር እያነጻጸርን እንመልከት።
=>>>መጽሐፈ ኩፋሌ
ኩፋ6÷9 "የእግዚአብሔር መላእክትም ያዩአቸው መልከ መልካሞች ነበሩና ከመረጡአቸው ሁሉ ሚስቶች ሊሆኗቸው ወሰዱአቸው ወንድ ልጆችችንም ወለዱላቸው እነዚህም ረዓይት ናቸው"
=>>> ኦሪት ዘፍጥረት
ዘፍ6÷2 " የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ።"
√ በኦሪት ዘፍጥረት እና በመጽሐፈ ኩፋሌ መካከል ያለው ልዩነት የእግዚአብሔር ልጆች የሚለውና የእግዚአብሔር መላእክት የሚለው ብቻ ሲሆን ሌላው ሀሳብ ሙሉ ለሙሉ አንድ ነው። ኦሪት ዘፍጥረት የእግዚአብሔር ልጆች የሚላቸውን በቅዱስ ጴጥሮስና በቅዱስ ይሁዳ መልእክታት ደግሞ እንደ መጽሐፈ ኩፋሌ መላእክት ተብለው እንደተጠሩ ከመጽሐፈ ኩፋሌ ጋር በማነጻጸር እንይ።
=>>>መጽሐፈ ኩፋሌ
ኩፋ6÷11-12 "እርሱም ሰውንና በምድር ላይ የፈጠረውን የሥጋ ወገንን ሁሉ አጠፋዋለው አለ፣ ኖኀ ብቻ በእግዚአብሔር ፊት ባለሟልነትን አገኘ"
ኩፋ6÷16 "ከዚህ በኋላ መንገዳቸውን ባፈለሱ መላእክት ሁሉ ላይ ፍርድ ሊሆን እስከ ታላቋ የፍርድ ቀን ድረስ በምድር ጥልቅ ውስጥ ተጋዙ"
=>>>ከቅዱስ ጴጥሮስ መልእክት
2ጴጥ2÷4-5 " እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ...."
=>>>ከቅዱስ ይሁዳ መልእክት
ይሁ1÷6-7 "መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል። እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል።"
√ እንግዲህ በጥቅሶቹ በግልጽ እንደ ተቀመጠው መላእክት ተብለው የተጠሩ ሰዎች በዝሙት ምክንያት ኃጢአት አድርገው እስከ ታላቋ የፍርድ ቀን ድረስ ለፍርድ ወደ ጨለማ ተግዘዋል። ኖኅ ብቻ ጻድቅ ሆኖ ተገኝቶ ተርፏል። ይህ ደግሞ መቶ በመቶ በመጽሐፈ ኩፋሌ ከተገለጸው ጋር አንድ ነው። መጽሐፈ ኩፋሌን የሚተቹ ሰዎች አስቀድመው 66ቱ መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ እንዲያጠኑ እንመክራለን። እንዲያውም ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ይሁዳ ከመጽሐፈ ኩፋሌ መጥቀሳቻው ለመጽሐፉ ተዓማኒነት የሚሰጥ ነው።
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር!
©ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ
Image may contain: text
6

No comments:

Post a Comment