Friday 2 October 2020

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን!

[በእንተ ሰማንያ አሃዱ]
ክፍል-፰ (ንዑስ ርእስ-፪)
[በመጽሐፈ ሲራክ ለሚነሱ ትችቶች የተሰጠ ምላሽ/ ስለ ሞተ ሰው ምጽዋት መስጠትን አትተው ስለ ሚለው]
=>>> ተቃዋሚዎች "ስጦታው በሕያው ሁሉ ፊት ጸጋ አለው ስለ ሞተ ሰውም መጽዋት መስጠትን አትተው" ተብሎ በሲራክ7÷33 ላይ የተጻፈውን ሀሳብ ያነሱና ስለ ሞተ ሰው ምጽዋት ምስጠት የሚሰጠው ጥቅም የለም ብለው መጽሐፈ ሲራክን ይተቻሉ።
[ምላሽ]
√ ስለ ምጽዋት በይበልጥ በመጽሐፈ ሲራክ ይብራራ እንጂ ለሞተ ሰው መፀለይ ወይም ደግሞ ፍትሐት ማድረግና መዘከር እንዳለብን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ። ለሞተ ሰው ለሚደረጉ ተግባራት ዋናው ምክንያት የእግዚአብሔር ቸርነትና መሐሪነት ነው። ይህ ቸርነቱ በሕይወተ ሥጋ ለሌሉ (ሙታንም) ጭምር ነው።
ሩት2÷20 " ቸርነቱን በሕያዋንና በሙታን ላይ አልተወምና "
[ስለ ሞቱ ሰዎች ስለ ሚደረጉ ተግባራት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?]
1. የያዕቆብ የበኩር ልጅ የነበረው ሮቤል በአባቱ አልጋ ላይ ወጥቶ ከባላን በመገናኘቱ አባቱ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ ነበር።
ዘፍ49÷4 " እንደ ውኃ የምትዋልል ነህ፤ አለቅነት ለአንተ አይሁን፤ ወደ አባትህ መኝታ ወጥተሃልና፤ አረከስኸውም፤ ወደ አልጋዬም ወጣ።"
ከዚህም የተነሣ ሮቤል ከሞተ ከአመታት በኃላ እስራኤላውያን ከግብጽ ሲወጡ የአበውን ዓጽምም አብረው ይዘው ስለ ነበር በኃጢአቱ ምክንያት ከሌሎቹ አበው ዓጽም ተለይቶ የሮቤል ዓጽም ጠቁሮ ነበር። ሮቤል ከሞቱ ከብዙ ዘመን በኃላ ሙሴ እንዲህ ብሎ ጸለየለት:-
ዘዳ33÷6 " ሮቤል በህይወት ይኑር፥ አይሙት"
ለሞቱ ሰዎች ጸሎት የሚደረግ ተግባር ተገቢ ባይሆን እና ጥቅም ባይኖረው ሙሴ ለምን "በሕይወት ይኑርልኝ" ብሎ ለሮቤል ጸለየለት? ይህንን እንደ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ያሉ የቤተክርስቲያን አባቶች ከሞት በኋላ የሚደረግ ጸሎት እንደሚጠቅም አስረድተውበታል።
2. ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን በሐዋርያዊ ተግባር ላይ ሳለ በመልካም ላገለገለውና በኋላ ግን በሞት ለተወሰደው ሄኔሲፎሩ ለተባለው ክርስቲያን እንዲህ ብሎ ጸልዮለታል:-
2ጢሞ1÷16-18 "ጌታ ልሄኔሲፎሩ ቤተ ሰዎች ምሕረትን ይስጥ፥ ብዙ ጊዜ አሳርፎኛልና በሰንሰለቴም አላፈረበትም፥ ነገር ግን በሮሜ ባደረ ጊዜ ፈልጎ ፈልጎ አገኘኝ በዚያን ቀን ከጌታ ምሕረትን እንዲያገኝ ጌታ ይስጠው፤ በኤፌሶንም እንዴት እንዳገለገለኝ አንተ በደኅና ታውቃለህ።"
ቅዱስ ጳውሎስ ሄኒሲፎሩ በሮሜ ታስሮ ሳለ እንዲሁም በኤፌሶን ያገለገለው እንደሆነው ይገልጽና "ጌታ ለሄኒሲፎሩ ቤተሰቦች ምሕረትን ይስጥ" ሲል ለመነ። ሄኒሲፎሩ ያል ሞተ ቢሆን ኖሮ ከቤሰቦቹ ለይቶ ለእርሱ ለብቻው "በዚያን ቀን ከጌታ ምሕረትን እንዲያገኝ ጌታ ይስጠው" ብሎ ለምን ጸለየለት? በተጨማሪም በሌላ ቦታ ለሄኒሲፎሩ ቤተሰቦች ሰላምታ አቅርቡልኝ ብሎ እሱ እንደ ሌለ ይገልጻል።
2ጢሞ4÷19 " ለጵርስቅላና ለአቂላ ለሄኔሲፎሩም ቤተ ሰዎች ሰላምታ አቅርብልኝ።"
"በዚያን ቀን" የተባለው ቀንስ የቱ ነው? ብንል በዳግም ምጽአቱ በፍርድ ቀን እግዚአብሔር ምሕረትን እንዲሰጠው በሕይወተ ሥጋ ለሌለው ለሄኒሲፎሩ ቅዱስ ጳውሎስ ጸለየለት።
3. ከሞት በኋላ ይቅር ሊባል የሚችል ኃጢአት አለ።
ማቴ12÷32 " በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም።"
1ዮሐ5÷16 " ማንም ወንድሙን ሞት የማይገባውን ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይለምን፥ ሞትም የማይገባውን ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል። ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ፤ ስለዚያ እንዲጠይቅ አልልም።"
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከሞት በኋላ ንስሐ ወይም መካነ ንስሐ (Purgatory) አለ ብላ አታምንም። ነገር ግን እግዚአብሔር ቸር ስለሆነ ፣ ከሞት በኋላ ሊሰረይ የሚችል ኃጢአት ስላለ እርሱ ባወቀ ይቅር ይላቸውና ቸርነቱን ያበዛላቸው ዘንድ እንጸልያለን።
√ ለሞተ ሰው መጸለይ ጠቃሚ ሆኖ ካኘነው በሞተ ሰው ስም ምጽዋትን ብንሰጥ ምን ያህል ይጠቅመው ይሆን? ይህንን የምናደርገው ግን አምላካችን መሀሪና ይቅርባይ መሆኑን ስለ ምናውቅና ስለ ምናምን ነው እንጂ በራሳችን በመተማመን አይደለም።
ለዚህም ነው በሐዋርያት ዘመን ለነበረችው ቤተክርስቲያን ቅርብ የነበሩት አባቶች ለሙቱ ሰዎች የሚደረጉ ተግባራትን የገለጹት።
=>>>ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
"ለሞቱ ወገኖቻችን ስንል ብዙ ምጽዋትን እንስጥላቸው፣ ለመንገዳቸው በጣም ጠቃሚና መልካም የሆነ ስንቅ እንላክላቸው" [ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ትርጓሜ ወንጌለ ዮሐንስ ትምህርት 85፣ 6]
=>>>ቅዱስ ጎርጎሪዮስ ዘእንዚናዙ ሴዛርዮስ በተባለው በታላቅ ወንድሙ ሞት ምክንያት ባስተማረው ትምህርት ላይ ስለ ወንድሙ ከተናገረ በኋላ ጸሎት ይጸልያል። ከዚያም በየዓመቱ መታሰቢያውን በማድረግ በሕይወት የቀሩት በሞት የተለየውን ለያዘክሩት እንደሚገባ ይናገራል። [ቅዱስ ጎርጎሪዮስ ዘእንዚናዙ፣ ትምህርት በእንተ ዕረፍት እኃው ቁ 17]
=>>>>በ2ኛ ክ/ዘመን የነበረው ሊቁ ጠርጡለስ እንዲህ ይላል:-
"ስለ ሞቱ ሰዎች ቁርባን እናቀርባለን፣ ይህንን አሰራር ከወዴት አመጣችሁት ተብለን ብንጠየቅ የቀድሞ አባቶች የደነገጉትን የተለመደውን አሰራር ሳናቋርጥ በታማኝነት ስለ ቀጠልን ነው ብለን መልስ እንሰጣለን]
√መጽሐፈ ሲራክ በሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈውን እውነት ይመሰክራል። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የነገሩን አባቶችም ስለ ሞቱ ሰዎች ስለ ሚደረግ ጸሎትና ምጽዋት ይነግሩናል።
ማጣቀሻ መጻሕፍት
1.መድሎተ ጽድቅ ቅጽ-1 (ገጽ 454-476)
2. በእንተ ሰማንያ አሃዱ (ገጽ 96-99)
3. ትምህርተ መለኮት (ገጽ 282-283)
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
©ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ




No comments:

Post a Comment