Friday 2 October 2020

 በአብ ስም በወልድ ስም በመንፈስ ቅዱስ ስም አንድ አምላክ አሜን!

በእንተ ሰማንያ አሃዱ (ክፍል-2)
[የዲዩትሮካኖን/Deuterocanonical መጻሕፍት ምንጮች]
=>>>በኦርቶዶክስና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ በፕሮቴስታንቶች ዘንድ የማይገኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዲዩትሮካኖን(Deuterocanon) ተብለው ሲጠሩ ሁለተኛ የቀኖና መጻሕፍት ማለት ነው። በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ደግሞ ፕሮቶካኖን(Protocanon) ተብለው ሲጠሩ የመጀመሪያ ቀኖና መጻሕፍት ማለት ነው። ፕሮቶካኖን እና ዲዩትሮካኖን የሚለው ቃል ቅደም ተከተልን (Chronological Order) የሚያሳይ እንጂ በመጻሕፍቱ መካከል ለየቅል የደረጃ ልዩነት እንዳለ (Distinction in Status) የሚገልጽ አይደለም። [1] ይህም ማለት ዲዩትሮካኖኒካል የተባለቡት ዋናው መክንያት በቀኖና የተመዘገቡበትን የታሪክ ምእራፍ ለማመልከት ነው።
=>>>የመጀመሪያዎቹ የብሉይ ኪዳን ቀኖና መጻሕፍት(Protocanonical Books) በእስራኤል የመመለስ ዘመን ካህኑና ጸሀፊው ዕዝራ በሠራው ቤተ መጻሕፍት ውስጥ አስቀምጧቸዋል። በዚህ ወቅት የተሰበሰቡት መጻሕፍት በአይሁድ እጅ የተገኙት ብቻ ነበሩ። በሳምራውያን እና በኤሴያውያን እጅ የነበሩ መጻሕፍት በወቅቱ አልተሰበሰቡም። [2] በሁለተኛ መቃብያን እንደ ተጻፈው ነህምያ ቤተ መጻሕፍት ባቋቋመ ጊዜ የነገሥታትንና የነብያትን መጻሕፍት የዳዊት መዝሙራትና የነገሥታትን ደብዳቤዎች አሰባስቧል። ዕዝራና ነህምያ በሌሎች የአይሁድ ክፍሎች (ሳምራውያንና ኤሴያውያን) እጅ የነበሩትንና ከእነርሱ በኃላ የተጻፉትን መጽሐፍት አላሰባሰቧቸውም።
=>>>ሁለተኛዎቹ የብሉይ ኪዳን የቀኖና መጻሕፍት (Deuterocanonical Books) ከእዝራና ከነህምያ በኃላ የተጻፉ ወይም ቀድመው ቢጻፉም በኃላ ተሰባስበው ወደ ቀኖና የገቡ መጻሕፍት ናቸው። እስራኤላውያን በግብጽ በባቢሎንና በፋርስ በተደጋጋሚ በደረሰባቸው ስደት የተነሳ መጽሐፍት ተበታትነው ይገኙ ነበር። በተለይም ከ 2ኛው ክ/ዘመን በኃላ ወደ ቁምራን ዋሻ (ሙት ባሕር አካባቢ) መሰባሰብ የጀመሩት ኤሴያውያን የያዙዋቸው መጻሕፍት ለብዙ ዘመናት ተጠብቀው ቆይተዋል። ከዚያ በኃላ የተነሱ የአይሁድም የክርስቲያንም ሊቃውንት እየተፈለጉ ሲገኙ ለቀኖና በመብቃታቸው ሁለተኛ የቀኖና መጻሕፍት ለመባል ችለዋል። [3]
=>>>የዲዩትሮካኖኒካል መጻሕፍት ምንጮች እና ቀኖናዊ ማረጋገጫዎች:-
፩. መጽሐፍ ቅዱስ:- የሀዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጸሀፊዎች ከዲዩትሮካኖኒካል መጻሕፍት እየጠቀሱ ጽፈዋል። ይኸውም መጻሕፍቱ ተአማኒነት እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ነው። ለአብነት የሚከተሉትን ጥቅሶች መመለከት ይቻላል።
1. ይሁዳ ጌታን በሠላሳ ብር ከሸጠው በኃላ ተጸጽቶ ሠላሳውን ብር ለካህናት አለቆች መልሶላቸዋል። እነርሱም የሸክላ ሠሪን መሬት ገዝተውበታል። ይህ አስቀድሞ በነብዩ ኤርሚያስ የተነገረ ትንቢት ነው። ይህ ትንቢት አስቀድሞ ከዲዩትሮካኖኒካል መጻሕፍት አንዱ በሆነው በተረፈ ኤርያስ ተጽፏል።
"በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው። ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ፥
ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት። የሚል ተፈጸመ።" ማቴ27÷9-10
"የእስራኤል ልጆች የተስማሙበት የክርስቶስን ዋጋ ሠላሳውን ብር ይቀበሉታል። ያንንም ብር ለሸክላ ሠሪ ቦታ ዋጋ አድርገው ይሰጡታል" ተረፈ ኤርሚያስ 7÷3 (1980 እትም)
2. አይሁድ ጌታችንን መከራ እንዳደረሱበት፣ እንደ ዘለፉት እና ለሞት አሳልፈው እንደሰጡት በመጽሐፈ ጥበብ በትንቢት የተቀመጠውን እና በወንጌላት የተጻፈውን በማነጻጸር ማየት ይቻላል።
ትንቢት:- "የእግዚአብሔር እውነተኛ ልጅ እንደሆነ ያድነው ከሚቃወሙትም ሰዎች እጅ ያድነው" ጥበብ2÷18
ፍጻሜ:- " በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአልና ከወደደውስ አሁን ያድነው።"
ማቴ 27:43
ትንቢት:- "ቅንነቱን እናውቅ ዘንድ እየሰደብን በመከራ እንመርምረው እንደ ቃሉ ረዳት ይሆነው እንደሆነ የከፋ የተዋረደ ሞትን እንፍረድበት አሉ" ጥበብ2÷19-20
ፍጻሜ:- "ኢየሱስንም የያዙት ሰዎች ይዘብቱበትና ይደበድቡት ነበር፤ ሸፍነውም ፊቱን ይመቱት ነበርና። በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር እያሉ ይጠይቁት ነበር።ሌላም ብዙ ነገር እየተሳደቡ በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር።" ሉቃ22÷63-65
3. በወንጌል ላይ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመፈተን የቀረቡ ትንሳኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን እንደ ነበሩ ተጽፏል።
"ሰባት ወንድማማች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ሞተ፥ ዘርም ስለሌለው ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት....ሁሉ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀንስ፥ ከሰባቱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች? ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ከመጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ።" ማቴ22÷24-28
ሰዱቃውያ ይህን ታሪክ ከመጽሐፈ ጦቢት ነው የወሰዱት። እነርሱ እሱን ለመፈተን ታሪኩን ቢጠቅሱትም መጻሕፍትን አታውቁምና ትስታላቹ ብሎ መልስ ሰጥቷቸዋል።
"እንሆ ሰባት ሰዎች አገቡሽ ባሎችሽ እየታነቁ እንዲሞቱ አታውቂምን? አሏት። ከነርሳቸው አንዱ እንኳን አልቀረሽም። እነርሳቸውም ሞተዋልና..." ጣቢት3÷8
4. ከጌታ ሐዋርያት ከሆኑት አንዱ ይሁዳ ሄኖክ ስለ ተናገረው ትንቢት ጽፏል። የሄኖክ ትንቢት በመጽሐፈ ሄኖክ ላይ ተጽፎ ይገኛል።
" ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ። እነሆ፥ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ... ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ።"
ይሁ 1:14-15
"ለወዳጆቹ ይፈርድላቸው ዘንድ እንሆ ከብዙ መላእክት ጋራ ይመጣል። ሕገ እግዚአብሔርንም የዘነጉ ሰዎች ያጠፋቸዋል።"
መጽሐፈ ሄኖክ 1÷9
5. ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልእክቱ ከመጽሐፈ መቃብያን ጠቅሶ ጽፏል።
" ነገር ግን። ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን።"
1ኛቆሮ 2:9
"ለደጋግ ሰዎች የተዘጋጀች ደስ የምታሰኝ ዓይን ያለየውን ጆሮም ያልሰማውን በሰው ልብ ያልታሰበውን እግዚአብሔር ደስ ላሰኙት ያዘጋጀውን..." 1ኛመቃ14÷20
6. ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱም ከመጽሐፈ መቃብያን ጠቅሶ አስተምሯል።
" ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤"
(ወደ ዕብራውያን 11:35)
ይህ ታሪክ በቀጥታ ከመጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ ከምእራፍ 3 የተወሰደ ታሪክ ነው። 1ኛመቃ3÷1-38 ይመልከቱ።
7. በትንቢተ ኤርሚያስ ላይ የኤርሚያስ ደቀ መዝሙር የነበረው ባሮክ ጸሀፊ እንደ ነበር ተጽፏል። ደግሞም ከኤርሚያስ የሚሰማቸውን ነገሮች ይጽፍ እንደ ነበር ተጽፏል።
"ኤርሚያስም ሌላ ክርታስ ወሰደ ለኔርያም ልጅ ለጸሐፊው ለባሮክ ሰጠው እርሱም የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም በእሳት ያቃጠለውን የመጽሐፍ ቃል ሁሉ ከኤርሚያስ አፍ ጻፈበት ደግሞም እንደ ቀድሞ ያለ ቃል ብዙ ቃል ተጨመረበት" ኤር36÷32
ይህ ሀሳብ ለመጽሐፈ ባሮክ ፍንጭ የሚሰጥ ነው። ባሮክ ጸሀፊ ከነበረ ባሮክ የጻፋቸው መጽሐፍት ወዴት አሉ? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል።
በቀጣይ ክፍል የዲዩትሮካኖኒካል መጻሕፍት ሌሎች ምንጮችን እንመለከታለን።
ማጣቀሻ
[1] Catholic Encyclopedia, Canonof the Old Testament
[2]The Bible through the Ages p-127
[3]Pope Shenouda lll CD, Coptic Orthodox Church, Australia, 1988
ስብሐት ለእግዚአብሔር!
©ዕቅበተ እምነት ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ
No photo description available.
9
17 Shares
Like
Comment
Share

No comments:

Post a Comment