Friday 4 August 2017

የኢየሱስ አማላጅነት ( ክፍል ስምንት ) የኢየሱስ አማላጅነት ( ክፍል ስምንት ) የተወደዳችሁ ወገኖች በኢየሱስ አማላጅነት ዙርያ በሚሰጠው ትምህርት ክፍል ስምንት ላይ ደርሰናል የረዳን አምላካችን የተመሰገነ ይሁን በክፍል ስምንት ትምህርታችን ላይ የምንመለከተው የኢየሱስ ክርስቶስን የቤዛነት ትምህርት ነው ቤዛነትን ጠቅለል አድርገን ከመጽሐፍቅዱሳችን ስናጠና ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዲስኪዳን ቤዛ ሆኖ ለሰው ልጆች በመስቀል ላይ በመሞት ተላልፎ የተሰጠና እኛንም ያዳነ ቢሆንም ከዚያ በፊት ግን 1ኛ) ቤዛነትን በተመለከተ በብሉይ ኪዳን ዘመን በነበሩ እስራኤላውያን አማካኝነት ለነፍስ ቤዛነት የማስተስረያ ገንዘብ ለመገናኛው ድንኳን ማገልገያ ይደረግ ነበር ይህም ለእስራኤል ልጆች መታሰብያ ይሁን ተባለ ዘጸአት 30 ፥ 12 ፤ ዘጸአት 30 ፥ 16 ዘኁልቁ 3 ፥ 46 ፤ መዝሙር 55 ፥ 19 2ኛ ) በሐዲስኪዳን ግን ኢየሱስ ቤዛ ሊሆንልን ከእግዚአብሔር ተዘጋጀ ( የሉቃስ ወንጌል 1 ፥ 68 ፤ የማቴዎስ ወንጌል 20 ፥ 28 ) 3ኛ ) ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ቤዛችን በመሆኑ ወንድም ወንድሙን አያድንም ሰውም አያድንም ቤዛውን ለእግዚአብሔር አይሰጥም ለዘላለም እንዲኖር ጥፋትንም እንዳያይ የነፍሳቸው ለውጥ ከብሮአልና ሲል መዝሙረኛው ተናገረን ( መዝሙር ( 49 ) ፥ 6 እና 7 ) 4ኛ ) ቤዛ ማለት ለሰው ልጆች በደል ምትክ ሆኖ የሞተ ማለት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ታዳጊ ማለትን የሚያመለክት ነው ( የማቴዎስ ወንጌል 20 ፥ 28 ፤ የሐዋርያት ሥራ 7 ፥ 35 ፤ የሉቃስ ወንጌል 4 ፥ 16 _ 30 ፤ የሐዋርያት ሥራ 10 ፥ 38 ) 5ኛ ) ኢየሩሳሌም ቤዛ እንደነበራት እኛም የተቤዠን ፣ የሚቤዠን የተጠባበቅነውና ወደፊትም የምንጠባበቀው ቤዛ ሊኖረን ይገባል ( የሉቃስ ወንጌል 2 ፥ 38 ፤ የሉቃስ ወንጌል 21 ፥ 28 ) 6ኛ ) ቤዛ ለኢየሩሳሌም ብቻ ሳይሆን ለሁሉ የተሰጠና በትክክለኛው ጊዜ የተመሰከረለት ነው ( 1ኛ ጢሞቴዎስ 2 ፥ 6 ) 7ኛ ) የቤዛ ቀንና ለቤዛም ቀን የታተምንበት መንፈስ ስላለ እንዳናሳዝነው ታዘናል ( ኤፌሶን 4 ፥ 30 ) ውድ ወገኖቼ ሆይ ቤዛነትን በተመለከተ እነዚህ ማብራርያዎችና መጽሐፍቅዱሳዊ ማስረጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው አሁንም የተሳሳተ ማብራርያ እንደሰጡት ዓይነት የዘመናችን አውጣኪዎች ቤዛነት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያሳየው ተምሳሊትነትን ወይም አርአያነትን ብቻ የሚያሳየን ነው ብለን የእግዚአብሔር ቃል ፍቺ በመስጠት እንድንደመድመው መጽሐፍቅዱሳችን በፍጹም አያስተምረንም እንዲህ ሲሉ መደምደም ደግሞ የክርስቶስን የማዳኑን ሥራ መካድና ማስተባበል የኪዳኑንም ደም የመርገጥ ያክል በመሆኑ ሰማያዊ ፍርድንና ቅጣትን የሚያመጣ ነው ዕብራውያን 10 ፥ 26 _ 31 በቤዛነት ውስጥ የአርአያነትና የተምሳሊትነትን ሕይወት ብንመለከትም ቤዛነት ግን ከዛ ያለፈ በመሆኑ ኢየሱስ እኛን ሁላችንን ለማዳን ሲል በመስቀል ላይ ሕይወቱን ለሞት አሳልፎ እንዲሰጠን ሆኖአል ለዚህም ነው እንግዲህ በመጽሐፍቅዱሳችን ላይ ነፍሱን ስለወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም ተብሎ የተጻፈልን የዮሐንስ ወንጌል 15 ፥ 13 የዘመናችን አውጣኪዎች ያልተረዱት እውነት እንግዲህ ይህንን ነው ቤዛነት ማለት እነርሱ እንደተረጎሙት ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ለሰው ልጆች ያሳየው ተምሳሊትነትና አርአያነትን የሚያመለክተን ነው ማለታቸው ነበር ይህንንም ያሉበት ምክንያት ቤዛ ሆነ ፣ አለቀሰ ፣ ቃተተ ፣ ማለደ አስታረቀ ብንል ከአባቱ ከአብ እያሳነስነው ነውና ልክ አይሆንም እርሱ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስቅዱስ ጋር እኩል ነውና ስለዚህ ማስታረቁም ሆነ መቃተትና መማለዱ ለእኛ ተምሳሊትና አርአያ ሊሆነን ነው ሲሉ አፋቸውን ሞልተው ይናገራሉ ነገር ግን አንድ ያልተረዱት ነገር ኢየሱስ በመለኮቱ ከአብና ከመንፈስቅዱስም ጋር እኩል ቢሆንም በትስብዕቱ ወይም በሰውነቱ ደግሞ እግዚአብሔር ለዘላለም የማለበት ካህን ፣ ንጉስና ነቢይ ስለሆነ ቤዛችንና ከአብ ጋር ያስታረቀን ነው ኢየሱስ አምላክ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ፍጹም ሰውም ስለሆነ እኮ ነው ቤዛችን የሆነው እኛም ቤዛችን ነህ ያልነው የእኛ ምትክ ሆኖ በእኛ ፈንታ የተገረፈልን የቆሰለልን የደማልንና የሞተልንም ስለሆነ ነው ስለዚህ ታድያ ይህ የቤዛነቱ ሥራ ካልገባንና ይህንንም እውነት ካልተቀበልን አልዳንም አንድንምም እንደገናም በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ የለንም በመሆኑም አውጣኪዎች ይህንን መጽሐፍቅዱሳዊ የሆነውን እውነት አውቀን መረዳታችንን ማስተካከል አለብን ኢየሱስ ቤዛችን ሲሆን በቤዛነቱ ምክንያት ያስገኘልን ውጤት አለ ይህንንም የቤዛነት ውጤት እንደሚከተለው በየተራ እንመለከተዋለንና ተከታተሉ 1ኛ ) ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ቤዛችን በመሆኑ የመዳንን ጸጋ አምጥቶልናል ( ሮሜ 3 ፥ 24 ) 2ኛ ) ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ቤዛችን በመሆኑ ልጅነትን አምጥቶልናል ( ዮሐንስ ወንጌል 1 ፥ 12 ፤ ሮሜ 8 ፥ 23 ) 3ኛ ) ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ቤዛችን በመሆኑ ከእርሱ ከእግዚአብሔር አድርጎናል ( 1ኛ ቆሮንቶስ 1 ፥ 30 እና 31 ) 4ኛ ) ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ቤዛችን በመሆኑ የበደልን ሥርየት አስገኝቶልናል ( ኤፌሶን 1 ፥ 7 ) 5ኛ ) ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ቤዛችን በመሆኑ የኃጢአትን ሥርየትና የራሱን መንግሥት አስገኝቶልናል ከጨለማውም ሥልጣን አድኖናል ( ቆላስያስ 1 ፥ 13 እና 14 ) 6ኛ ) ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ቤዛችን በመሆኑ አንድ ጊዜ በፈጸመው የዘላለምን መቤዠት አምጥቶልናል ( ዕብራውያን 9 ፥ 12 ) 7ኛ ) ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ቤዛችን በመሆኑ በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላዕክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን ይለናል ( ዕብራውያን 2 ፥ 5 _ 10 ) ውድ ወገኖቼ ሆይ ታድያ የቤዛነቱ ምስጢርና ያስገኘልንም ውጤት በእንዲህ መልኩ ተዘርዝሮና ተነግሮ እያለ እኔ አልሰማሁም አላየሁም ጆሮ ዳባ ልበስ ሲሉ በኃጢአት መቀጠል ግን ክርስቶስን የኃጢአት አገልጋይ ነው እያልነው ነውና መልካም አይደለም( ገላትያ 2 ፥ 17 ) ስለዚህ ወደድንም አልወደድንም ተቀበልንም አልተቀበልንም ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን የሞተና እኛንም ስለማጽደቅ የተነሣ ስለሆነ ከእርሱ ጋር ልንስማማ የግድ ይለናልና ከእርሱ ጋር በመስማማት ኃጢአታችንን በደሙ ታጥበን ልጆቹ ልንሆን መወሰን አለብን ጌታ እግዚአብሔርም ለዚህ ይርዳን ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን ከ Joshua Breakthrough Renewal Apostolic Ministry ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ነኝ God bless u all http://www.Facebook.com/yonas.asfaw.39 https://www.youtube.com/yF76GIi_rCQ yonasasfaw8@gmail.com

No comments:

Post a Comment