Wednesday 3 October 2018

Hail Gebrselassie vs. Paul Tergat Sydney 2000 ሀይሌ በ ፖል ቴርጋት ሲገፋ የመልዕክት ርዕስ : — የሚያስቀሩ የመሰሉ ሰዎች አያስቀሩህም 1ኛ ሳሙኤል 17 ፥ 1 — 58 የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቅዱሳን ሰላም ለእናንተ ይሁን :: ይህንን መልዕክት በፌስቡክ ላይቭ ላይ ሰርቼ ለቅቄዋለሁ ፣ በዩቲዩብ ፔጄም ላይ ተቀምጦላችኋልና መመልከት ትችላላችሁ :: ይሁን እንጂ መልዕክቱ ጠቀሜታነት ያለው ስለሆነ አሁንም በጽሑፌ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ :: ብዙ ጊዜ ሰዎችን በማስቀረት የሚታወቁ ሰዎች ከድልና ከማሸነፍ የቀሩ ፣ የማሸነፉም ሆነ የድሉ ተስፋ ያመለጣቸውና ሊሆንላቸውም ያልቻሉ ሰዎች ናቸው :: በዚህ ትምህርቴ ላይ የአትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴና የኬንያዊውን ሯጭ ፖልቴርጋትን ውዽድር አስመልክቶ ባለቀ ሰዓት ኃይሌ ኬንያዊውን ሯጭ አልፎት ሊያሸንፈው በሮጠ ጊዜ የደረሰበትን ቡጢ አስመልክቶ በዩቲዩብ የተለቀቀውን ቪዲዮ ለትምህርታችን እንዲሆን እነሆ ብያለሁ :: ለተጨማሪ መረጃ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴን መጠየቅ ይቻላል :: ታድያ እንግዲህ ከሩጫው ፍጻሜ መልስ ያለውን የኃይሌና የኬንያዊውን ሯጭ ግንኙነት ባላውቅም ፣ አንዳንዶች እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች በስንፍናቸው ምክንያት ካመለጣቸው ተደጋጋሚ ድል የተነሳ ሕይወታቸው በቊጭትና በንዴት ሳይቀር የተሞላ በመሆኑ ቀደመ ብለው ያሰቡትን ወንድማቸውን አይደለም ክርክር ፣ ጥል ፣ ድብድብ ጌታ አይፈቅድላቸውም እንጂ በሞት እንኳ ሳይቀር ሊያስቀሩ ወደኋላ የማይሉ ናቸው :: ይህንን ያልኩበትን ምክንያት ከመጽሐፍቅዱስ አስረጂ አቀርባለሁና ተከታተሉኝ :: ከክፍሉ ምንባብ እንደምንመለከተው ዳዊትን ታላቅ ወንድሙ ኤልያብ ከድሉ ሠፈር በጥል ነበር ሊያስቀረው የተነሳው :: ቊጣው በዳዊት ላይ ነዶ ለምን ወደዚህ ወረድህ ?እነዚያንስ ጥቂት በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው ? እኔ ኲራትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁና ሰልፉን ለማየት መጥተሃል አለው ይለናል :: ዳዊት ግን የነገሩን መንስዔ ወንድሙም ኤልያብ ይህንን የነደደ ቊጣ በላዩ ላይ ያወረደበትን መነሾ በትክክል የተረዳ በመሆኑ እኔ ምን አደረግሁ ይህ ታላቅ ነገር አይደለምን ? በማለት ከእርሱ ወደ ሌላ ዘወር አለ :: እንደዚህም ያለ ነገር ተናገረ :: ሕዝቡም እንደ ቀድሞ ያለ ነገር መለሱለት ይለናል :: ዳዊትስ በነደደበት ቊጣ ምክንያት በወንድሙ በኩል የመደመጥ ዕድሉን ባያገኝም ዘወር ብሎ ግን ሊሰሙትም ሆነ ሊያዳምጡት ከሚችሉ ጋር ተነጋገረ :: አንዳንድ ጊዜ እኮ ዘወር ልበል ቢባል እንኳ የማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ይገባል :: የሁለቱ ወንድማማቾች የያዕቆብና የኤሳው ሕይወት የሚያስተምረን ይህንን እውነት ነው :: ኤሳው ከቊጣና ከጥል ባለፈ ሁኔታ ያዕቆብን አባቱ ስለባረከው ብቻ በያዕቆብ ላይ ቂም ያዘበት :: ዔሳውም በልቡ አለ ለአባቴ የልቅሶ ቀን ቀርቦአል :: ከዚያም በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ አለ :: ታድያ ሁለቱ ወንድማማቾች ያዕቆብና ኤሳው በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ነው ለርብቃም ይህ የታላቁ ልጅዋ የዔሳው ቃል የደረሰላት :: ቃሉ እንደሚነግረን ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብንም አስጠርታ አስመጣችው ፣ አለችውም :: እነሆም ወንድምህ ዔሳው ሊገድልህ ይፈቅዳል አሁንም ልጄ ሆይ ቃሌን ስማ ፣ ተነሣና ወደ ካራን ምድር ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ሂድ ፣ በእርሱ ዘንድ ጥቂት ቀን ተቀመጥ ፣ የወንድምህ ቊጣ እስኪበርድ ድረስ ፣ የወንድምህ ቊጣ ከአንተ እስኪመለስ ድረስ ፣ ያደረግህበትንም እስኪረሳው ድረስ ከዚያም ልኬ አስመጣሃለሁ :: በአንድ ቀን ሁለታችሁን ለምን አጣለሁ ? በማለት ታናሹ ልጁዋን ስትማጸነው እንመለከታለን ዘፍጥረት 27 ፥ 41 _ 46 :: ውድ ወገኖቼ ሆይ ከዚህ ምንባብ እንደተመለከትነው ማስቀረትን በተመለከተ በተለይም በአንዳንዶች ዘንድ በአጭሩ ልንገታው አንችልም መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ካልመጣ በስተቀር እውነተኛ ፍቅር ፣ እውነተኛ እርቅና ስምምነት ጭምር አይመጣምና ፣ እውነተኛ ፍቅርና እውነተኛ እርቅ ትክክለኛም ስምምነት እናምጣ በማለት አንለውጠውም :: ከዚህ የተነሳ የሚያስቀሩ ሰዎች አይነኬ በመሆናቸው በልባቸው ከፍ ብለውና ቃላቸውንም አስረዝመው የሚናገሩ ናቸውና ወንድሞቻቸውን እስከመግደል ደርሰው በሞት ሊያስቀሩ የሚችሉበትን ሁኔታ ይፈጥራሉ :: ነገር ግን አሁንም መቅደም ያለባቸው ሰዎች መቅደም ያለባቸው ሆነው ከተገኙና ከእግዚአብሔር ከሆኑ በሞት ጥላ መካከል እንኳ ቢሄዱ አልፈው ይቀድማሉ እንጂ የትኛውም ኃይል አቅም አግኝቶ እነርሱን የሚስቀራቸው አይሆንም :: የሐማና የመርዶክዮስ ታሪክም የሚያስታውሰን አሁንም ይህንኑ እውነት ነው :: ሐማም መርዶክዮስ እንዳልተደፋለት እንዳልሰገደለትም ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣ ፣ የመርዶክዮስንም ወገን ነግረውት ነበርና በመርዶክዮስ ብቻ እጁን ይጭን ዘንድ በዓይኑ ተናቀ :: ሐማም በአርጤክሲስ መንግሥት ሁሉ የነበሩትን የመርዶክዮስን ሕዝብ አይሁድን ሊያጠፋ ፈለገ ይለናል ( አስቴር 3 ፥ 1 — 7 ) ይህ ብቻ አይደለም ከዚህም ሌላ ሐማ መርዶክዮስን መናቁ ሳያንሰው ፣ በዓይኑ እንኳ ሊያየው የማይፈልገውና የጠላው መሆኑን ለመናገር ፈልጎ አስቴር ለግብዣ የጠራችው መሆንዋን ለዘመዶቹ በኩራት ሆኖ በማውሳት ፣ ንግሥቲቱ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ ከእኔ በቀር ከንጉሡ ጋር ማንንም አልጠራችም ፤ ደግሞ ነገ ከንጉሡ ጋር ወደ እርስዋ ተጠርቻለሁ ፣ ነገር ግን አይሁዳዊው መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ካየሁ ይህ ሁሉ ለእኔ ምንም አይጠቅምም ሲል ተናገረ :: ሚስቱም ዞሳራና ወዳጆቹ ሁሉ፦ ቁመቱ አምሳ ክንድ የሆነ ግንድ ይደረግ፥ ነገም መርዶክዮስ ይሰቀልበት ዘንድ ለንጉሡ ተናገር፤ ደስም ብሎህ ከንጉሡ ጋር ወደ ግብዣው ግባ አሉት ነገራቸውም ሐማን ደስ አሰኘው፥ ግንዱንም አስደረገ ይለናል :: ይህንን ምንባብ ስናይ እንግዲህ ማስቀረት ክፉኛ በሆነ ጥላቻ ውስጥ ገብቶ ፣ ለዓይን እንኳ ሳይቀር ለማየት ባለመፍቀድና በመሣሠሉትም ጭምር የሚያባራ አለመሆኑንና እስከ ሞት ድረስ የሚሄድ መሆኑን ነው የምንመለከተው :: የሚያስቀሩ ሰዎች አይሆንላቸውም ፣ ጌታም አይፈቅድላቸውም እንጂ ልባቸው ትልቅ ነው :: ነገር ግን ሊያስቀሩ ባዘጋጁት በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ እነርሱ ይቀራሉ :: ከዚህ የተነሳ እናስቀራለን ሲሉ የተነሱ ሰዎች እናስቀራለን ሲሉ ያዘጋጁት ነገር ሁሉ ለእኛ የመሸጋገርያ ድልድይ ሲሆን ፣ ለእነርሱ ግን መቅሪያ ብቻ ሳይሆን መቀበርያቸውም ይሆናል :: ለዚህ ነው አንዳንዱ ሳያውቀው የራሱን መሞቻና የመቀበርያ ጉድጓድ የሚምሰው ( መጽሐፈ አስቴር ምዕራፍ 5 ፤ 6 እና 7 ን በሙሉ ተመልከቱ ) :: ወገኖቼ ሆይ መልዕክቴን ስጠቀልለው ቤተክርስቲያንንም ሆነ ሀገርን ለመጥቀም ለተነሱ ሰዎች በክፋታችን ምክንያት ሊደርሱ ካለው የራዕያቸው ፍጻሜ ደርሰው ለሕዝብ በረከት እንዳይሆኑ መንገዳቸው ላይ እየቆምን ተንኮል የምንሰራ ሰዎች ፣ የቱንም ያህል ተንኮል ብንሰራና ክፋትን ብንሸርብ ልናቆማቸው አንችልምና ፣ ሥራ ለሠሪው እሾክ ላጣሪው እንዲሉ ስለ ክፉ ሥራችን እግዚአብሔር ይቅር እንዲለን ንስሐ እየገባን ፣ የእግዚአብሔርንም ምሕረት እየጠየቅን ለቀጣዩ ጉዞ ቅኖችና መልካም ሰዎች ሆነን ብንችል የመልካም ሥራ ሁሉ ተባባሪዎች እንሁን :: አለበለዚያ ግን በዚሁ በክፋታችን ከቀጠልን ፣ ጊዜ ይቆያል እንጂ በሐማ ላይ የመጣች የእግዚአብሔር ፍርድ በእኛም ላይ ትሆናለች በማለት መልዕክቴን እጠቀልላለሁ :: እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለን :: ግልባጭ ለአትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ቀሲስ አባ ዮናስ ጌታነህ ከጸአተ ግብጽ ኦርቶዶክሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት

No comments:

Post a Comment