Wednesday 23 September 2020

ትምክሕተ ዘመድነ: ቃለ ሊቃውንት ቅዱሳን

በሊቃውንት ዘንድ ቃላት ተመጥነው፣ ተለክተው ይነገራሉ እንጂ ያለቦታቸው አይነገሩም። በተለይም በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የሚናገሩ ቅዱሳን ሊቃውንት ቃላቸው፣ አገላለፃቸው የሚያነበውን ሰው ልቡና ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ የማድረግ ኃይል አለው። እመቤታችንን “ትምክሕተ ዘመድነ/ምክሐ ዘመድነ (የባሕርያችን መመኪያ)” ብለው ካመሰገኗት ቅዱሳን ሊቃውንት መካከል ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግን፣ የውዳሴ ማርያምን ደራሲ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊን፣ እንዲሁም ከቀደምት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ቅዱስ ያሬድን፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫንና አባ ጽጌ ድንግልን ለአብነት መጥቀስ እንችላለን፡፡

ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ


የሥሩግ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ያዕቆብ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በደረሰው አኮቴተ ቁርባን (የቁርባን ምስጋና) ቅዳሴው የኃዳፌ ነፍስ ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዳግም ምጽአቱ በፊቱ ለፍርድ ስንቆም ይራራልን ዘንድ በተማጸነበት አንቀጽ እንዲህ ብሏል፡ “አሜሃ ከመ ትምሐረነ ወትሣለነ… ተማኅፀነ በማርያም እምከ እንተ ይእቲ እግዝእትነ ወትምክህተ ዘመድነ/በዚያን ጊዜ ትምረን ይቅርም ትለን ዘንድ…በእናትህ በማርያም ተማጽነናል፤ ይህችውም አንተን በመውለድ እመቤታችንና የባሕርያችን መመኪያ ናት/” (የያዕቆብ ዘሥሩግ ቅዳሴ)፡፡ ይህንን አብነት በማድረግ ዛሬም የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅዳሴው “የባሕርያችን መመኪያ” እያለች ታመሰግናለች።


ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊም በውዳሴ ማርያም የሰንበተ ክርስቲያን ጸሎቱ “አንቲ በአማን ምክሐ ዘመድነ። ወሰአሊት ሕይወተ ለነፍሳቲነ /በእውነት የባሕርያችን መመኪያ አንቺ ነሽ። ለሰውነታችንም ሕይወትን የምትለምኝ ነሽ/” በማለት አመስግኗታል። በማክሰኞ ውዳሴ ማርያም ድርሰቱም “አክሊለ ምክሕነ፣ ወቀዳሚተ መድኃኒትነ፣ ወመሠረተ ንጽሕነ ኮነ በማርያም ድንግል እንተ ወለደት ለነ ዘእግዚአብሔር ቃለ ዘኮነ ሰብአ በእንተ መድኃኒትነ/የመመኪያችን ዘውድ፣ የድኅነታችን መጀመሪያ፣ የንጽሕናችንም መሠረት እኛን ለማዳን ሰው የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል በወለደችልን በድንግል ማርያም ተገኘልን” በማለት እመቤታችን የሰው ባሕርይ የከበረባት የማየ ሕይወት ምንጭ መሆኗን ተናግሯል፡፡

በተጨማሪም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም ላይ “ትምክህተ ኩልነ ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ዘበእንቲአሃ ተስዕረ ዘቀዳሚ መርገም እንተ ኅደረት ዲበ ዘመድነ በዕልወት ዘገብረት ብዕሲት በልዐት እምዕፅ/ሔዋን እንጨት ብልህ ባደረገችው ዓመፅ በባሕርያችን ያደረ እርግማን በእርስዋ የጠፋልን አምላክን የወለደች ድንግል ማርያም የሁላችን መመኪያ ናት/” በማለት መመኪያነቷን መስክሯል። በዓርብ ውዳሴ ማርያም ላይም “ቡርክት አንቲ ማርያም ወቡሩክ ፍሬ ከርሥኪ። ኦ ድንግል ወላዲተ አምላክ ምክሖን ለደናግል/ የደናግል መመኪያቸው አምላክን የወለድሽ ድንግል ማርያም ሆይ የተባረክሽ ነሽ፣ የማኅፀንሽ ፍሬም የተባረከ ነው።/” በማለትም አወድሷታል። እንዲሁም በቀዳሚት ሰንበት ውዳሴው “ግርማ ያለሽ ድንግል ሆይ ገናንነትሽን እናመሰግናለን እናደንቃለን። እንደ መልአኩ ገብርኤልም ምስጋና እናቀርብልሻለን የባሕርያችን መዳን በማህጸንሽ ፍሬ ተገኝቷልና፡፡ወደ አባቱ ወደ እግዚአብሔርም አቀረበን፡፡” በማለት አመስግኗታል፡፡ እኛም አባታችን ቅዱስ ኤፍሬምን አብነት አድርገን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ‘የባሕርያችን መመኪያ’ እንላታለን።

ቅዱስ ያሬድ

በምስጋና ቅዱሳን መላእክትን የመሰለ ኢትዮጵያዊው የዜማና የቅዱሳት መጻሕፍት ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ እመቤታችንን ሲያመሰግን “አንቲ በአማን ዘኮንኪ ምክሐ ለዘመደ ክርስቲያን/ለክርስቲያን ወገኖች በእውነት መመኪያ የሆንሽ አንቺ ነሽ/” ብሏታል። በተጨማሪም “ማርያም ድንግል ምክሖን ለደናግል፣ ይእቲኬ ቤተ ምስአል፣ ለኩሉ ፍጥረት ትተነብል/ድንግል ማርያም የደናግል መመኪያ፣ የጸሎት ቤት ናት፣ ለፍጥረታት ሁሉ የምትለምን አማላጅ ናት/” በማለት አመስግኗታል፡፡ ይህም መመኪያነቷ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ለሚያምኑ ክርስቲያን ወገኖች ሁሉ መሆኑን ያስረዳናል። ምክንያቱም የአምላክ ልጅ ከእርስዋ ሰው በመሆኑ በእርስዋ ከምድር ወደ አርያም የቀረብን ሆነናልና በእውነት መመኪያችን ናት። በጸሎቷ ለምናምን ሁሉ ምሕረትን የምታሰጥ ናትና ድንግል ማርያም ለክርስቲያን ወገኖች ሁሉ መመኪያችን ናት።

አባ ጽጌ ድንግል

የማኅሌተ ጽጌ ደራሲ ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል (ብርሃን) ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የባሕርያችን መመኪያ መሆኗን ሲናገር “እግዚአብሔር ጽጌ ትንቢት ለቢሶ ሥጋኪ ሥጋ ዚአነ፤ አመ አስተርአየ በምድር ወተአምረ ለነ፤ ንዌድሰኪ እንዘ ንብል ምክሐ ዘመድነ፤ ዮም በፍሥሓ ለማርያም እምነ፤ አስተርእዮ በሰማይ ኮነ/ የትንቢት አበባ እግዚአብሔር እኛን ሥጋ የሆነውን የአንቺን ሥጋ ለብሶ በምድር እንደተገለጠ ለእኛም እንዲታወቅ ድንግል ሆይ የባሕርያችን መመኪያ ዛሬ ለእናታችን ለቅድስት ማርያም በሰማይ ፍጹም በደስታ መገለጥ ሆነ እያልን እናመሰግንሻለን” ብሏል፡፡

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ

ኢትዮጵያዊ ቄርሎስ የተባለው ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት አርጋኖን በተባለው መጽሐፉ በብዙ ስፍራ “የደናግል መመኪያ የቅዱሳንም የመመረጣቸው አክሊል፣ ያልበደሉት የድንግልናቸው መመኪያ፣ ያላደፉትም የንጽሕናቸው አክሊል፣ ሥጋ የለበሰ ሁሉ መመኪያ፣ ነፍስ የተዋሐዳቸው ፍጥረት ሁሉ አክሊል፣ የነዳያን ሀብት የንጹሐን መመኪያ፣ ለባሕርያችንም መመኪያ ሆንሽ፣ የዓለም ሁሉ መድኃኒት በአንቺ ተደረገ” እያለ አመስግኗታል፡፡


No comments:

Post a Comment