Wednesday 23 September 2020

ምክሐ ዘመድነ: ሃይማኖተ አበው ቀደምት

እመቤታችን ድንግል ማርያምን ምክሐ ዘመድነ (የባሕርያችን መመኪያ) ብሎ ማመስገን ቃለ ሊቃውንት ከመሆኑም በላይ የነገረ ድኅነትን ምስጢር የሚያስረዳ የቀደሙ አባቶቻችን ርትዕት ሃይማኖት መገለጫ መሆኑን በሃይማኖተ አበው ክታባቸው የተደጎሰላቸው ቅዱሳን አባቶች ትምህርት ያስረዳናል። ለማሳያ እንዲሆነን ጥቂቶቹን ብቻ እንመልከት።

ቅዱስ ጎርጎርዮስ

ሰማዕት ዘእንበለ ደም (ያለ ደም ሰማዕት የሆነ) የአርማንያ ኤጲስ ቆጶሳት አለቃ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ጌታ ከእመቤታችን በመወለዱ ሰዎች መለኮትን ለማየት መብቃታቸውን አንስቶ ባመሰገነበት ድርሳኑ እንዲህ ብሏል። “ኮነ በአርያም ሰብእ እስከ ኮኑ ሰብአ ድልዋነ ይርአይዎ ለመለኮት እስመ ሶበ ርኢነ ዘመደ ሥጋነ ንሴብሖ ለመለኮተ ወልድ በኂሩቱ ለአብ/ሰዎች መለኮትን ያዩት ዘንድ የበቁ እስኪሆኑ ድረስ በሰው ባሕርይ ተገለጠ፣ በሥጋ ዘመዳችን ሆኖ ባየነው ጊዜ በአብ ቸርነት የወልድን ጌትነት እናመሰግነዋለንና።” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘአርማንያ 15:11)

ቅዱስ አትናቴዎስ

ሐዋርያዊ አትናቴዎስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ሥጋን ነፍስን ነስቶ መወለዱን ክደው “ቃል ሥጋ ለመሆን ተለወጠ” በሚል ክህደት የጠፉ መናፍቃንን በገሰጸበት ድርሳኑ ጌታ ከእመቤታችን የእኛን ባሕርይ መንሳቱ የድኅነታችን መሠረት መሆኑን ገልፆ አስተምሯቸዋል። ጌታ በተዋሕዶ ባሕርያችንን ባሕርይው ከማድረጉ በላይ ለሰው ልጅ የተሰጠ ክብርና መመኪያ የለምና። “ለብው ኦ አብዳን ሰሚዐክሙ ቃለ መጻሕፍት ወእመኑ እስመ ሥጋሁ ለእግዚእነ እማርያም እምቅድስት ድንግል ውእቱ ወአኮ እም ካልእ/እናንት አላዋቆች የመጻሕፍትን ቃል ሰምታችሁ ዕወቁ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተዋሐደው ሥጋ ከቅድስት ድንግል ማርያም እንደሆነ ከሌላ እንዳይደለ እመኑ።” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ 30:9)። “ደካማ ባሕርያችንን ለማዳን ወደዚህ ዓለም ስለመጣ” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ባስልዮስ 33:35) ከባሕርያችን መመኪያ ከእመቤታችን ሥጋን ነፍስን ነስቶ ተገለጠ።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ፍጡር ለሆነ ለሰው ባሕርይ ከእግዚአብሔር ጋር መዛመድን (በተዋሕዶ መክበርን) የመሰለ ምን ሞገስ አለ? ይህን ክብር ያገኘነው ተስፋ ቅዱሳን አበው በተፈፀመባት በባሕርያችን መመኪያ በድንግል ማርያም ነው። የተወደደ መምህር ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ አለ: “ለቡ ዘተብህለ ወኢተኀሊ ከመ ንስቲት ክብር ይእቲ ዘነሥአ እግዚአብሔር እምኔነ እስመ ኢወሀበ ዘንተ ለመላእክት ወኢህላዌ መላእክት እንተ ተወክፈቶ አላ ህላዌ ዚአነ። …ለዝንቱ ሶበ እዜከሮ ብዙኃ ጊዜያተ አነክር እምኔሁ ወእዴመም ወእኔጽር ብዙኃ ክብራተ ዘአልቦቱ ወሰን ዘረክበ እጓለ እመሕያው ወፍቅረ ዐቢየ ዘኢይትነገር ዘረከበ ህላዌነ ዘእምእግዚአብሔር/ የተነገረውን አስተውል እግዚአብሔር ከእኛ ባሕርይ የተዋሐደው ተዋሕዶ ጥቂት ክብር አይምሰልህ ይህንን ለመላእክት አላደረገውምና፣ የመላእክት ባሕርይም አልተዋሐደችውምና፣ የተዋሐደችው የኛ ባሕርይ ናት እንጂ።…ይህን መላልሼ ባሰብኩት ጊዜ  ሰው ያገኘውን ልክ መጠን የሌለውን ፍጹም ክብር ከእግዚአብሔር የተደረገውን ባሕርያችን ያገኘውን ታላቅ ፍቅር አይቼ ከዚህ የተነሣ አደንቃለሁ።” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ 62:4-7)

እስራኤል ዘሥጋ ሙሴ ስለ እነርሱ ከእግዚአብሔር ጋር ደጋግሞ በመነጋገሩ የሚመኩበት ከሆነ እኛማ በዘመነ ሐዲስ የምንገኝ፣ በሐዲስ ተፈጥሮ የእግዚአብሔር ልጆች የመባልን ጸጋ ያስገኘችልንን የባሕርያችን መመኪያ እመቤታችን ድንግል ማርያምን የቱን ያህል ማክበር ይገባን ይሆን?! የዘመነ ብሉይ ቅዱሳት አንስት (ሴቶች) እንደ ሐና እመ ሳሙኤል ምድራውያን ካህናትን ስለወለዱ እስራኤል ያከበሯቸው ከሆነ እኛማ መፈታትን ያገኘንበት ልዩ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ያዛመደችንን ድንግል ማርያምን ምን ብለን ብናመሰግናት ይበቃን ይሆን?! በሥጋ ማርያም በመገለጡ፣ ፍጹም እግዚአብሔር፣ ፍጹም ሰው (አብሲዳማኮስ፣ የሐዲስ ኪዳን መካከለኛ) በመሆኑ ማለፍ መለወጥ የሌለበት የዘለዓለም ሊቀ ካህናት ሆኗልና።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን ሲያስረዳ እንዲህ አለ: “ወአኮ ይኩነነ እኅወ ባሕቲቶ አላ ተሣሃለነ ፈድፋደ ወፈቀደ ዓዲ ይኩነነ ሊቀ ካህናት ለኀበ አብ ከመ ይስረይ ኃጢአተነ፣ ወበእንተ ዝንቱ ወሰከ በዲበ ነገሩ ወይቤ ከመ ይኩኖሙ መሐሬ በኵሉ ምእመን ሊቀ ካህናት ለመንገለ እግዚአብሔር ከመ ይስረይ ኃጢአተ ሕዝብ።/ሰው የሆነም ዘመድ ሊሆነን ብቻ አይደለም፣ ፈጽሞ ይቅር አለን። ኃጢአታችንን ለማስተስረይ ከአብ ጋር ለማስታረቅ ሊቀ ካህናትም ይሆነን ዘንድ ወደደ እንጂ። ስለዚህም ሰዎችን ሊመስላቸው ይገባል ባለው ነገሩ ላይ ጨምሮ በሁሉ አዛኝ የሕዝቡንም ኃጢአት ለማስተስረይ በእግዚአብሔር ዘንድ የታመነ አስታራቂ ይሆናቸው ዘንድ ነው።” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ 62:13)

ቅዱስ ኤራቅሊስ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ከባሕርያችን መመኪያ ከድንግል ማርያም ሥጋና ነፍስን ስለነሳ አማኑኤል (እግዚአብሔር ከእኛ ጋር) ተባለ። ፍጹም ሰው በመሆኑም የወደቀ ባሕርያችንን ወደቀደመ ክብሩ መለሰልን። ይህን አምላካዊ ምስጢር ለማድነቅ ቃላት ያጠረው ቅዱስ ኤራቅሊስ እንዲህ አለ: “ኦ ከርሥ ዘተጽሕፈ በውስቴታ መጽሐፈ ግዕዛን እምግብርናት ለኩሉ ሰብእ!?…ኦ መቅደስ ዘኮነ ባቲ እግዚአብሔር ካህነ/ ለሰው ሁሉ ከመገዛት የነፃነት መጽሐፍ የተጻፈባት ማኅፀን ወዮ እንደምን ያለች ናት!?…እግዚአብሔር ያገለገለባት መቅደስ ወዮ እንደምን ያለች ናት?!” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤራቅሊስ 48:15-17) ስለሆነም ዕለት ዕለት በጸሎተ ቅዳሴ በካህኑ መሪነት “የባሕርያችን መመኪያ ሆይ ደስ ይበልሽ” እያልን እናመሰግናታለን።

የባሕርያችን መመኪያ ሲባል ምን ማለት ነው?

ባሕርይ የምንነት መገለጫ ነው። የሰው ልጅ ከአራት ባሕርያተ ሥጋና ከሦስት ባሕርያተ ነፍስ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” እንዲል፡፡ (ዘፍ. 1፡26) ሰው በሥጋ ባሕርይ ውኀነትን፣ እሳትነትን፣ ነፋስነትንና መሬትነትን ሲይዝ በነፍስ ባሕርይ ደግሞ ልባዊነትን (ማስተዋልን)፣ ነባቢነትንና (መናገርን) ሕያውነትን (ለዘላለም መኖርን) ይዟል፡፡ የእነዚህ ባሕርያት ፍጹም ተዋሕዶ ሰብአዊ ባሕርይ ይባላል፡፡ ይህ የሰውነት ባሕርይ በውጫዊ ነገር መለዋወጥ በኑሮ ጉስቁልና ወይም ምቾት አይቀየርም።

ሰው በባሕርይው ባለ ነፃ ፈቃድ ተመሥርቶ ጽድቅንም ኃጢአትንም ማድረግ ይችላል። በአባታችን አዳምና በእናታችን ሔዋን ምክንያት የመጣው ሕገ እግዚአብሔርን መተላለፍም ይህን እውነታ በግልጥ ያስረዳናል። አዳምና ሔዋንም በነፃ ፈቃዳቸው ተመርተው በፈጸሙት መተላለፍ የሰው ባሕርይ (ሰውነት) ከነበረበት የቅድስናና የንጽሕና አኗኗር ተለይቶ ነበር፡፡ ባሕርይው ጎስቁሎ፣ ልጅነቱን አጥቶ ነፃነቱንና ሕያውነቱን አጥቶ በሞት መዳፍ ተይዞ ነበር። ይህ በአዳምና በሔዋን መተላለፍ ምክንያት ወደ ዓለም የገባው ኀጢአትና ውጤቱ ከእነርሱ በባሕርይ ለሚወለድ ሁሉ ተላለፈ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “…ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ…ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነውና” እንዳለ፡፡ ሮሜ. 5፡ 12-14። ይህ የአዳምና የሔዋን በደልም ጥነተ አብሶ ይባላል። ከእነርሱ የሚወለዱ ሁሉ በጥንተ አብሶ የሚያዙ ሆኑ።

እግዚአብሔር ከዚህ ያድናቸው ዘንድ አዳምና ልጆቹ በዘመናት ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልዩ ኖሩ። እግዚአብሔርም ቃል ገባላቸው። ቃል ኪዳኑ እስኪፈፀም ድረስም ላደፈው ባሕርይና ለጎሰቆለው ሕይወት መታደስ ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኛቸውን ድልድይ ሲጠባበቁ ኖሩ። ይህች ድልድይ ወይም መሰላል የኾነችም እመቤታችን ድንግል ማርያም ነች፡፡ ለዚያም ነው ‘የባሕርያችን መመኪያ’ የምንላት። እርስዋ በቅድስና ተጠብቃ በውስጥ በአፍኣ በነፍስ በሥጋ በንጽሕና ተሸልማ የሰውን ባሕርይ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ከባሕርያችን የተገኘች ምክንያተ ድኅነት ናትና፡፡

ይህ የእመቤታችን ድልድይነት ከዘመነ ብሉይ እስከ ዘመነ ሐዲስ በብዙ ሕብረ አምሳል የተገለጠ፣ ትንቢት የተነገረለት ሱባኤ የተቆጠረለት ነው፡፡ አባታችን ያዕቆብ ሰው ከእግዚአብሔር በተለየበት፣ እግዚአብሔርም ከሰው በረድኤት በራቀበት ዘመን መጭውን የድኅነት ብሥራት በሕልም አየ። በሕልሙ የወርቅ መሰላል ከምድር እስከ ሰማይ ተተክሎ እግዚአብሔር በላዩ ቆሞበት መላእክት በመሰላሉ ሲውጡ ሲወርዱ አየ። “ሕልምንም አለመ፤ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፣ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፣ እነሆም የእግዚአብሔር መላዕክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር፤ እነሆም እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር” እንዲል (ዘፍ. 28፡12-13)፡፡ ይህች አባታችን ያዕቆብ በሕልሙ ያያት መሰላል የድንግል ማርያም ምሳሌ ነበረች፡፡ ይህም ጌታ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በማኅፀኗ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን አድሮ ከእመቤታችን በቤተልሔም በተወለደ ዕለት መላዕክት ከእረኞች ጋር በአንድነት ባመሰገኑበት ጊዜ ተፈጽሟል፡፡ (ሉቃስ 2፡ 8-14)።

የብህንሳው ኤጲስ ቆጶስ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ “ወዮ ይህ ነገር ዕጹብ ድንቅ ነው የቀደሙ አባቶች ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገሩብሽ ድልድይ ሆይ፣ ከምድር እስከ ሰማይ የምትደርሽ መሰላል ሆይ፣ የፍጥረት ሁሉ መጀመሪያ በአንቺ ታደሰ፡፡ ከገነት በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው አንቺ ነሽ” በማለት አመስግኗታል፡፡ (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 30)። ስለዚህም እመቤታችንን የባሕርያችን መመኪያ እንላታለን፡፡

እመቤታችንን የባሕርያችን መመኪያ ያስባሏት ዋና ዋና ነጥቦች

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ክብር ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን ሁሉ በላይ ስለሆነ ሙሉ ምስጋናዋን አንሥተን መፈጸም አይቻለንም፡፡ ነገር ግን የባሕርያችን መመኪያ ከሚያስብሏት መጽሐፋዊ ምክንያቶች የተወሰኑትን እናያለን፡፡

አምላክ የሰውን ባሕርይ በእርሷ ስለተዋሐደ

እግዚአብሔር የወሰነው ዘመን ደርሶ የገባውን የምሕረት ቃል ኪዳን ሊፈጽም በወደደበት ወቅት ማደርያው ትሆነው ዘንድ የመረጣት ድንግል ማርያም ነች፡፡ እርሷም ዓለም ሳይፈጠር ለዓለም ድኅነት ምክንያት ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር የቀደሳት በውስጥ በአፍኣ፣ በነፍስ በሥጋ ፍጽምት ቅድስት ሆና የተገኘች ናት። ይህችውም ከአዳም ዘር የተወለደች እግዚአብሔር ለድኅነተ ዓለም ያዘጋጃት ሰዋሰወ ብርሃን (የብርሃን መሠላል) ናት። እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን የሰውን ባሕርይ እንጅ የመላእክትን ባሕርይ አልፈለገምና፡፡ ለዚያም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመዳናችን ራስና ፈጻሚ ስለሆነው ስለ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረበት አንቀጽ “የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጅ የያዘው የመላእክትን አይደለም” ያለው፡፡ (ዕብራ. 2፡16)

ስለዚህ የባሕርይ አምላክ የሰውን ባሕርይ ተዋሕዶ ከነፍስዋ ነፍስ፣ ከሥጋዋም ሥጋ ነስቶ ተወለደ። በተዋሐደው የሰው ባሕርይም እንደ ሕፃን አደገ። ወደ ግብፅ ተሰደደ። በዮርዳኖስ ተጠመቀ። ሦስት ዓመት ከሦስት ወር በምድር ላይ ተመላልሶ ወንጌልን አስተማረ። በተዋሐደው ሥጋ መከራን ተቀበለ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ፣ ተቀበረ። በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሳ። በአርባኛውም ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ። በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ። ከእንዲህ እናስተውል በአባቱ ቀኝ የተቀመጠው ወልድ ዋሕድ እየሱስ ክርስቶስ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ፣ ከሁለት አካል አንድ አካል የሆነው በተዋሕዶ የከበረው ከእርሷ ተወልዶ ነው። በእትሷ የተፈፀመው የተዋሕዶ ምሥጢር ሰው (የሰው ባሕርይ) አምላክ አምላክም (መለኮት) በተዋሕዶ ሰው የሆነበት ነውና በእውነት የባሕርያችን መመኪያ ናት።

በባሕርያችን ያደረ እርግማን በእርሷ ስለራቀልን

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ “ስለ ሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ፤ ዳግመኛም ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን” (የሐሙስ ውዳሴ ማርያም) በማለት የእመቤታችንን ምክንያተ ድኅነትነት አስረድቷል፡፡ የውዳሴ ማርያም መተርጉማንም ሲያስተምሩ እናታችን ሔዋን የሞት ምክንያት ስለ ተባለች ወቀሳ፣ ከሰሳ ይበዛባት ነበር፡፡ በሔዋን አንፃርም ሴቶች ሁሉ የስሕተት ምክንያት እንደ ሆኑ አድርገው የሚያስቡ ብዙዎች ነበሩ፡፡ ወንዶችም ይህን እየጠቀሱ በሴቶች ላይ ይመኩባቸው ነበር፡፡ አሁን ግን ድኅነት በእመቤታችን በኩል ሆኗልና የወንዶች ትምክህት ቀርቷል፡፡ እመቤታችንም ቅዱስ ገብርኤል የድኅነት ምክንያት መሆኗን ባበሰራት ሰዓት የሔዋንን ጸሎትና ልመና በማስታወስ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች….የባርያይቱን መዋረድ ተመልክቷልና” (ሉቃ. 1፡47-48) በማለት የሔዋን ምክንያተ ሞት መሆን በእርሷ ምክንያተ ድኂን መሆን መታደሱን ተናግራለች፡፡

በንጽሐ ባሕርይዋ የሰውን ንጽሐ ባሕርይ ስለምታሳይ

የሰው ልጅ ሕግን ተላልፎ በመበደሉ (ጥንተ አብሶ) እግዚአብሔር ተለየው፣ ከእግዚአብሔርም ተለየ፡፡ በራሱ ትሩፋትም ወደ እግዚአብሔር መመለስና መዳን አልተቻለውም። ስለዚህ ድካሙን ያግዝለትና ድኅነቱን ይፈጽምለት ዘንድ ጌታ ለአዳም ቃል ኪዳን ገባለት። ቃል ኪዳኑም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመስቀል ተሰቅዬ ሞቼ አድንሃለሁ የሚል ነበር። ለዚህ ቃል ኪዳን ፍጻሜም ምክንያት ትሆን ዘንድ እመቤታችንን በንጽሕና ፈጥሮ፣ ከጥንተ አብሶ ጠበቃት። በዘመነ ብሉይ የነበሩ ሁሉ በዚህ በደል የተያዙ ነበሩና (ሮሜ. 5፡12-14)። ሁሉም ከኃጢአት በታች እንደነበሩም ተጠቅሷል፡፡ ለምሳሌ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፣ ጽድቃችንም እንደ መርገም ጨርቅ ነው” ብሏል፡፡ (ኢሳ. 64፡ 6)

ነቢዩ ኢሳይያስ ከላይ የተጠቀሰውን የተናገረው ከሕግ በታች ይኖርበት ከነበረው ዘመነ ብሉይ ወደ ዘመነ ሐዲስ ለመሸጋገር የጌታን መወለድ (አስተርዕዮ) በተማጸነበት የትንቢቱ ክፍል ነው፡፡ ምዕራፉን ሲጀምርም “ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ!” (ኢሳ. 64፡1) ብሏል፡፡ ይህን የተናገረ ኢሳይያስ በዘመነ ብሉይ ከነበሩ ሰዎች ሁሉ ለይቶ እመቤታችን ድንግል ማርያም በጥበበ እግዚአብሔር ከመጀመሪያው በደል (ጥንተ አብሶ) ተጠብቃ መቀመጧን በትንቢት መነጽር ተመልክቶ ነበር፡፡ ይህንንም ሲያስረዳ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፣ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር” (ኢሳ. 1፡9) ብሏል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም በመዝሙሩ “ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውርም የለብሽም” (መኃልይ. 4፡7) በማለት በምሳሌ የእመቤታችንን ፍጹም ንጽሕና ተናግሯል፡፡ እንደ ሰዶምና ገሞራ ሰዎች ጠፍተን፣ በኃጢአት ተይዘን እንዳንኖር የድኅነት ምክንያት የሆነች፣ ንጹሕ ዘር የተባለች፣ የባሕርያችን መመኪያ የሆነች እመቤታችንን ከአዳም ጀምሮ እስከ ኢያቄም አብራክ ያስቀረልን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡

ይህን የእመቤታችንን ፍጹም ንጽሕና ባሰብን ጊዜ እርሷ እንደ እኛ ከሰው ባሕርይ ተፈጥራ ንጽሐ ሥጋና ንጽሐ ልቦናን አስተባብራ የያዘች በመሆኗ ከአዳም ልጆች ከአንስተ ዓለም እርሷን መርጦ የሰጠንን አምላክ እናመሰግናለን። እርሷንም በቅድስናዋ መዓዛ ከርኵሰታችን ሽታ ታነጻን ዘንድ እንለምናታለን። እርሷን ምሳሌ አድርገን ሰውነታችንን ለእግዚአብሔር ቅዱስ ማደርያው ይኾን ዘንድ በንጽሕና እንጠብቀዋለን። እርስዋ የንጽሕናና የቅድስና አብነት ሆናልናለችና፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ኤፍሬም በቀዳሚት ሰንበት ምስጋናው “ከዳዊት ዘር የተገኘሽ ባሕርይ /ዘር/ አንቺ ነሽ፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ ወልደሽልናልና” በማለት ያወደሳት፡፡

በትንሣኤዋ ለሰው ልጆች የክብር ትንሣኤ ማሳያ ስለሆነች

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ ባስረዳበት መልእክቱ “አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል” (1ኛ ቆሮ. 15፡20) ብሏል፡፡ የጌታ ትንሣኤ ሞት የተሸነፈበት ትንሣኤ ስለሆነ የሰው ልጆች በሙሉ በዳግም ምጽአት እርሱን አብነት አድርገን የማይፈርስ የማይበሰብስ አካል ይዘን እንነሣለን፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶች ይህን የትንሣኤያችን በኩር የሆነው የክርስቶስ ትንሣኤ ሲነገራቸው “እርሱ በገዛ ሥልጣኑ ስለ ተነሣ እኛ ግን እንዴት እንነሣለን?” በማለት ታላቁ የእምነታችን መሠረት የሆነውን ትንሣኤ ሙታንን የሚጠራጠሩ በየዘመናቱ አሉ። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ ለእነዚህ ወገኖች በእውነት ትንሣኤ ሙታን እንዳለ አንድ ማሳያ ነው።

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚታወቀው፣ ሁሉም ቀደምት አብያተ ክርስቲያናት እንደሚስማሙበት፣ በሊቃውንት አበው እንደተጻፈው እመቤታችን ድንግል ማርያም በሥጋ ባረፈች ጊዜ ጌታ ሥጋዋን ለመፍረስ ለመበስበስ አልተወውም፡፡ ይልቁንም የከበረ ሥጋዋን ለማቃጠል ከተሰበሰቡ ሰቃልያነ እግዚእ አይሁድ በጥበብ አስጥሎ ቅዱሳን ሐዋርያት ከቀበሯት በኋላ ጌታ የከበረ ሥጋዋን በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው እንጅ፡፡ የእውነተኛው ዕፀ ሕይወት (የሕይወት ፍሬ) መገኛ የሆነች የባሕርያችን መመኪያ የድንግል ማርያም የከበረ ሥጋ በሕይወት ዛፍ ስር ተቀመጠ፡፡ ትንሣኤና ዕርገቷንም በሱባኤ ይማጸኑ ለነበሩ ለቅዱሳን ሐዋርያት በልዩ ልዩ ተአምራት ገለጠላቸው፡፡ ድንግል ማርያም በተፈጥሮ እንደ እኛው ምድራዊት ስትሆን በልጅዋ ሥልጣን ሞትን ድል አድርጋ በመነሣት ወደ ሰማይ ዐረገች። ስለሆነም ትንሣኤዋ ለምድራውያን ሰዎች የማይቀር ትንሣኤ ማሳያ ሆነልን፡፡

የሰው ባሕርይ በሔዋን የሞት ምክንያትነት ሞት፣ ጉስቁልና እና መፍረስ መበስበስ አግኝቶት ነበር። አማኑኤል የተባለ የተወደደ ልጇን በወለደችልን በድንግል ማርያም የሕይወት ምክንያትነት ደግሞ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ። ሔዋን ለሞት፣ ድንግል ማርያም መፍረስ መበስበስ ለሌለበት ሕይወት ከሰው ልጆች ሁሉ የመጀመሪያ ሆኑ። ሔዋን በበደሏ፣ በትዕቢት ባለመታዘዟ ለሰይጣን መገዛትን ወደ ሰው ባሕርይ ለማምጣት የመጀመሪያዋ እንደነበረች ንጽሕት ድንግል ማርያም እግዚአብሔርን ባስደሰተ ቅድስናዋ፣ በፍጹም ትህትና በመታዘዟ በልጇ ሥልጣን ሞትን፣ መፍረስ መበስበስን አሸንፈው ለዘለዓለም በሕይወት ሊኖሩ የክብር ትንሣኤን ከሚነሱ ሁሉ ቀድማ በመነሣቷ የባሕርያችን መመኪያ መሆኗ ታወቀ።

የባሕርያችን መመኪያ ስለሆነች በጸሎታችን እንማጸንባታለን

እስራኤል ዘሥጋ ከእግዚአብሔር ምሕረትን ሲፈልጉ የሚመኩባቸውን ቅዱሳን አበው የአብርሃምን፣ የይስሐቅን፣ እስራኤል የተባለ የያዕቆብን ስም ይጠሩ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ይራራላቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ ሊቀ ነቢያት ሙሴ አግዚአብሔር በእስራኤላውያን ተቆጥቶ ሊያጠፋቸው ባለ ጊዜ ለሕዝበ እስራኤል ምሕረትን የለመነው የእነዚህን ቅዱሳን አበው ስም በአማላጅነት ጠርቶ ነበር፡፡ “ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፤ አለም፡፡…ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፣ ይኽችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፣ ለዘላለምም ይወርሷታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባርያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ”። ዘጸ. 32፡11-13።

የዘመነ ብሉይ ምዕመናን በታላላቅ አርዕስተ አበው ቅዱሳን በአብርሃም፣ በይስሐቅና በያዕቆብ ቃል ኪዳን ተመክተው እግዚአብሔርን ይለምኑት እንደነበር እኛም የባሕርያችን መመኪያ በሆነች በድንግል ማርያም ጸሎትና ቃል ኪዳን እንታመናለን። በምርኮ የነበሩ አይሁድ በምድራዊ ንጉሥ ቤተ መንግስት ባለሟልነት ባላት በወገናቸው በደካማዋ በአስቴር ተመክተው ከሞት ፍርድ ካመለጡ (መጽሐፈ አስቴር ምዕራፍ 4-ምዕራፍ 8) እኛማ አምላክን በወለደች፣ በንጽሕና በቅድስና ባጌጠች፣ የሰማያዊ ንጉሥ የክርስቶስ ምድራዊት ቤተ መቅደስ በሆነች በባሕርያችን መመኪያ በእመቤታችን ድንግል ማርያም የመመካታችን ዋጋ ምን ይሆን!? ስለሆነም እስራኤል ዘነፍስ የምንባል የሐዲስ ኪዳን ምእመናን ከቅዱሳን ሁሉ በምትበልጥ፣ የባሕርያችን መመኪያ በሆነች በድንግል ማርያም ስም ልጇ ወዳጇን ኢየሱስ ክርስቶስን እንማጸነዋለን፡፡ ዘወትርም በቅዳሴና በጸሎት “በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ/ ክርስቶስ ሆይ ስለ እናትህ ስለ ማርያም ብለህ ይቅር በለን” እያልን እንለምነዋለን፡፡ እርሱም ይታረቀናል፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍትን ባለማወቅ ትስታላችሁ!

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥራዝ ነጠቅ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባብ ተነሥተው ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያንን ሲገስፅ “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ባለማወቅ ትስታላችሁ” (ማቴ 22:29) ብሏቸው ነበር። ቅዱሳት መጻሕፍትና ቅዱሳን ሊቃውንት በአንድነት ተስማምተው ድንግል ማርያምን “ወላዲተ አምላክ ማእምንት/የታመነች አምላክን የወለደች”፣ “ምክሐ ዘመድነ/የባሕርያችን መመኪያ” በማለት ያመሰግኗታል። የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ለሚረዳ ሰው እነዚህ ምስጋናዎች ጌታ እኛን ያዳነበትን አምላካዊ ጥበብ የሚያስረዱ መሆናቸውን ይገነዘባል።

ስለ ድንግል ማርያም ክብር፣ አማላጅነት፣ ትንሣኤና ዕርገት ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ንጹሕ ሐዋርያዊ ወንጌልም ከውድቀት የተነሣ የሰው ባሕርይን የሚመለከት፣ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ ለሰው ልጅ የሰጠው መጠንና መመርመር የማይቻል ጸጋ ማሳያ መሆኑን ይረዳል። ይሁንና የነገረ ድኅነትን ትምህርት ባለማወቅ የሚቆነጻጽሉ፣ የድንግል ማርያምን ክብር የማይረዱ ሰዎች ምክንያተ ድኂን (የድኅነት ምክንያት) መሆኗን መረዳት ሲከብዳቸው እናስተውላለን። ባለማወቅና በድፍረት ተሞልተውም የባሕርያችን መመኪያ የእመቤታችንን የድኅነት ምክንያትነት ያቃልላሉ። በአንፃሩ ደግሞ የሔዋንን የሞት ምክንያትነት ግን መረዳት አይከብዳቸውም። ቅዱሳት መጻሕፍትን ባለማወቅ ስተዋል፣ ይስታሉ።

ከቅዱሳን ሐዋርያት ርትዕት ሃይማኖትን የተቀበለች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ግን የእመቤታችንን የድኅነት ምክንያት መሆን ዘወትር ታስባለች፣ በጸሎቷም ታሳስባለች። በሔዋን አለመታዘዝ፣ ሕግን መተላለፍ ሞት ወደ ዓለም እንደመጣ በእመቤታችን መታዘዝ፣ ሕግን መፈጸም ሕይወት ክርስቶስ ወደ ዓለም መጥቷልና እመቤታችንን “የባሕርያችን መመኪያ” ብለን እናመሰግናታለን።

ከጥሩ ምንጭ ቀድቶ ቃለ እግዚአብሔርን መረዳት የከበዳቸው ወገኖቻችን “የባሕርያችን መመኪያ” የሚለውን የቅዱሳት መጻሕፍትን ትኩረት (theme) መረዳት ቢችሉ ወደ ርትዕት ሃይማኖት በተመለሱ ነበር። ይሁንና አንዳንዶቹ ባለማወቅና በትዕቢት በማያውቁት ጉዳይ ራሳቸውን “መምህራን” እያሉ ጠማማ ትምህርትን ያስተምራሉ። ይህን የሚያደርጉት ጥሩ ምንጭ በሌለበት የሚኖሩት ብቻ አይደሉም። የሕይወት ውኃ ምንጭ በሚፈልቅባቸው የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረቶች ራሳቸውን ሾመው፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓት በሚያናንቅ፣ የምዕራባውያንና ሌሎች ምስራቃውያን ሴሚናሪዎችን ልማድ በመከተል ጌታ በወንጌል (ማቴ 23) የገሰፃቸውን ፈሪሳውያንን በሚያስንቅ ግብዝነት፣ በተገዛ ቀሚስና ሀብል፣ ማዕረግ አልባ በሆኑ በሐሰትና በማጭበርበር በተሰበሰቡ የማዕረግ ስሞች ተከልለው ኦርቶዶክሳዊውን ዐውደ ምሕረት ከአባቶቻችን ከተረከብነው ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት፣ ትውፊትና ላህይ ለይተው ርካሽ የጭብጨባና የእንቶ ፈንቶ ዐውድ የሚያደርጉትንም ይመለከታል።

እነዚህ ከምንጩ የተለዩ ሰዎች የቤተ ክርስቲያን ምልክት ተደርገው “ዕንቁ፣ ብርቅዬ” መባላቸው በእውነተኛው የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ላይ በአላዋቂ ልብስ ሰፊ እንደተደረተ መጋረጃ ይመስላሉ። ቤተ ክርስቲያን ልትመዘንበት በሚገባው በእውነተኛ አስተምህሮዋ ሳይሆን በምንፍቅና ወይም ለመወደድና ለንግድ ተብለው በሚቀርቡ ሰዎች የለብ ለብ (simplistic) አስተምህሮ እንድትታይ ያደርጋሉና። በዚህም ምክንያት ብዙዎች የቤተ ክርስቲያንን ዕንቍ ትምህርት ሳያገኙ ይቀራሉ። ስለሆነም ቀላል የማይባል ምዕመን ከቤተ ክርስቲያን ጥልቅ አስተምህሮ ባለማወቅ እየተለየ፣ ልቡናውን ከፍ ከፍ አድርጎ ስለ “ባሕርያችን መመኪያ” ከማሰላሰል ይልቅ ዲያብሎስ ትንንሾችን ለመጣል ባጠመደው እንቅፋት እየተጠለፈ ስለ ምልጃ፣ ስለ ትንሣኤና ዕርገት “ሀ” ብሎ የሚነታረክ ሆኗል። ለዚህ መሰል ትውልድ የአባታችን ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ተግሳፅ የሚጠቅም ይመስለናል።

ተግሳፅ ዘአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ሳይረዱ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ምንታዌ (ከተዋሕዶ በኋላ የሥጋና የመለኮት ባሕርይ ሳይነጣጠሉ፣ ሳይከፋፈሉ) ባሕርያችንን ባሕርይው ማደረጉን በመካዳቸው፣ እመቤታችን ድንግል ማርያምም የባሕርያችን መመኪያ መሆኗን በማቃላላቸው ንስጥሮሳውያንን በገሰፀበት የመጽሐፈ ምሥጢር ንባብ ያስተማረው ትምህርት በዘመናችን ላሉ የድንግል ማርያምን ክብር ባለማወቅ ለሚያሳንሱ ሰዎች የሚስማማ ነው።

አባ ጊዮርጊስ እንዲህ አለ: “በተከማቸ መጽሐፍ ውስጥ የተሸሸገ ዕንቍን ልቡ የታወረ አያየውም። በነቢያትና በሐዋርያት አፍ የመለኮት ድምፅ ይጮሀል ኅሊናው በደነቈረ ሰው ጆሮ ግን አይገባም። የብረት መዝጊያ ቢበረታም በብረት ሰሪው እጅ ይከፈታል፣ የናስም መቀርቀሪያዎች በማንጠሪያ እሳት ይቀልጣሉ፣ የዝንጉዎችን ልብ ግን በጥበብ ቃልም ቢሆን፣ በመጻሕፍትም ቃል ቢሆን ሊከፍተው የሚችል የለም። መጻሕፍትን ማንበብ በሰነፍ አፍ ውስጥ እንደ ነፋስ መንቀሳቀስ ነው፣ ስላነበባት ይመካል፣ በውስጧ ያለውን ግን አያውቅም። የተዘጋን የንጉሥ ቤት ሳጥኖችን የሚያድን ወደ ውስጧ ግን ያልገባን ሰው ይመስላል። ስለነገሥታት ገንዘብ ለሚጠይቀው ሰው ምን ይመልስለታል?።” (መጽሐፈ ምሥጢር የጌና ምንባብ ቁጥር 33)

እንግዲህ እኛስ ምን እንላለን? የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር መረዳት አቅቷቸው በስህተት ጎዳና በድፍረት የሚራመዱትን አላዋቂዎች ምን እንላቸዋለን? ተማሪዎች ነን ቢሉ የቅዱሳት መጻሕፍትን በር ከፍተው እንዲገቡ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም እንዲመራቸው፣ ማስተዋልን እንዲያድላቸው እንለምንላቸዋለን። የሚያሳዝነው አላዋቂነታቸው በግልጽ እየታየ ራሳቸውን “መምህራን” የሚሉት ይበዛሉ። እነዚህን ለመገሰፅ አሁንም ከአባታችን ጊዮርጊስ ዘጋሰሥጫ ቃል ተውሰን እንወቅሳቸዋለን፣ እንዲመለሱ እናሳስባቸዋለን።

“መጻሕፍትን ከማወቅ የተራቆቱ ሲሆኑ መምህራን የሚባሉ በከበረ ደንጊያ ካጌጡ በወርቅም ቅጠል ከተለበጡ፣ ቀለም በተነከሩ ልብሶች ከተሸፈኑ፣ በሐር ምንጣፍም ላይ ከተቀመጡ ውስጣቸው ግን ከተቆረጡ እንጨቶች፣ ከረከሱም የእንስሳ አጥንቶች ከተሠሩ ዕጣንና ሽቱ ከሚያጥኑአቸው፣ ነገር ግን የዕጣኑ መዓዛ በአፍንጫቸው ከማይገባ፣ ከመሥዋዕታቸው ስብ ከማይበሉ፣ ከወይን ጭማቂአቸውም ከማይጠጡ፣ የሚያምንባቸውን ከማይረዱት፣ በሚገፉአቸውም ላይ ክፉ ከማያደርጉ፣ በከንቱም አማልክት ከሚባሉ የአሕዛብ ነገሥታት ጣዖታት ከአዛጦን ሰዎች ዳጎንና አጵሎን ያልተሻሉ ናቸው። እነርሱ የእግዚአብሔርን ቃል የተጠሙ ሲሆኑ በከንቱ መምህራን የሚባሉ እኒህም እንዲሁ ናቸው፣ ወደነርሱ የመጣውን እንግዲህ እንዴት ያረኩታል? ቢያጠጡትም የደፈረሰውን ውኃ ከነቢያትና ከሐዋርያትም ምንጭ ያልተቀዳውን የተበላሸ ውኃ ያጠጡታል።” (መጽሐፈ ምሥጢር የጌና ምንባብ ቁጥር 34-35)

እንግዲህ እኛም እያንዳንዳችን ራሳችንን እንመርምር። ከእውነተኛ መምህራን ተምረን የባሕርያችንን መመኪያ እንወቅ እንጂ በሐሰተኛ መምህራን ማደናገሪያ ተታለን ከርትዕት ሃይማኖት የተለየን አንሁን። የንጽሕና አብነት የምትሆን፣ በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች፣ የባሕርያችን መመኪያ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አብነት አድርገን በመንፈሳዊ ተጋድሎ ለጽድቅ ሥራ የተጋን እንሁን፡፡

ኦ ማርያም አንቲ ውእቱ ወላዲተ አምላክ በአማን ወምክሐ ዘመድነ ለኩልነ ሕዝበ ክርስቲያን፣ አዕርጊ ጸሎተነ ቅድመ ገጸ ፍቁር ወልድኪ፣ ለዓለመ ዓለም አሜን።

እመቤታችን ማርያም ሆይ አንቺ በእውነት የአምላክ እናት፣ የባሕርያችን መመኪያ ነሽና ጸሎታችንን በተወደደ ልጅሽ ፊት አሳርጊልን፣ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ስብሃት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር።

ፍልሰታ ለማርያም፡ ሰአ(ዐ)ሊ ለነ ቅድስት!

“ፍልሰታ” የሚለው ቃል ፈለሰ፣ ተሰደደ(ተገለጠ)፣መከፈት፣ መገለጥ፣ የመዝጊያ የመጋረጃ ከሚለው የግእዝ ስርወ ቃል የተገኘ ሲሆን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤ ይመለከታል፡፡ “ፍልሰት” የሚለው ቃል ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መሔድን ያመለክታል፡፡ “ፍልሰታ ለማርያም” ሲባልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን (ማረጓን)፣ በኋላም ሥጋዋ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊትና ቀኖና መሠረት ከሰባቱ የአዋጅ አጿማት መካከል አንደኛው ጾመ ፍልሰታ ለማርያም ሲሆን ከህጻናት ጀምሮ እስከ አረጋውያን የሚጾም ታላቅ ጾም ነው፡፡

እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት በእናት በአባቷ ቤት፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ፣ ዘጠኝ ወር በዮሴፍ ቤት፣ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር፣ ዐሥራ አራት ዓመት በወንጌላዊው በዮሐንስ ቤት ከኖረች በኋላ በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩  ቀን ዐርፋለች፡፡ በሐዋርያት ውዳሴ፣ ዝማሬና ማኅሌት ነሐሴ ፲፬ ቀን ከተቀበረች በኋላ እንደሌሎቻችን ትንሣኤ ዘጉባኤን መጠበቅ ሳያስፈልጋት ነሐሴ ፲፮ በልጇ ስልጣን ተነሥታ በይባቤ መላእክት ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ “ተለዐለት እምድር ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገች፡፡ በሰማይም ከልጅዋ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች” በማለት ወደ ሰማይ ማረጓንና በክብር መቀመጧን ተናግሯል፡፡ ከሺሕ ዓመት በፊትም አባቷ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” ሲል የተናገረው ትንቢት ይህንኑ የእመቤታችንን ክብር የሚመለከት ነው (መዝ. ፵፬፥፱)፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማርም ነገረ ፍልሰቷን እንዳስሳለን፡፡

“እንደ ልጇ ‹ተነሣች፤ ዐረገች› እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” (አይሁድ)

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓ.ም በ፷፬ ዓመቷ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድና ድካም ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሔዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችንን የሰቀሉት አይሁድ “እንደ ልጇ ‹ተነሣች፤ ዐረገች› እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” ብለው ሥጋዋን ሊያጠፉ በዓመፃ ተነሡ፡፡ ከእነርሱም መካከል ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ የአልጋውን አጎበር ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀጣው፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወደ ገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም እመቤታችን ያለችበት ቦታ እንዲገለጥላቸው ባረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ፡፡

Filseta2

“ተንሥአት እሙታን፡ ማርያም ድንግል ከመ ትንሣኤ ወልዳ ዘልዑል/ እንደ ልጇ ትንሣኤ ባለ ትንሣኤ ተነሳች/” (ቅዱስ ኤፍሬም)

ሐዋርያት እመቤታችን ካረፈችበት ቀን ከጥር ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ ድረስ ጥያቄያቸውንና ጸሎታቸውን ባያቋርጡም ከሰው ተለይተው ሱባዔ ገብተው ጾም ጸሎት የጀመሩት ግን ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ነው፡፡ ቀድሞስ የክብር ባለቤት የጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኾነው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ተሰውራባቸው እንዴት ዝም ብለው ይቀመጣሉ? ቅዱሳን ሐዋርያት ሁለት ሱባዔ (ዐሥራ አራት ቀናት) ካደረሱ በኋላም የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታቸውን ሰምቶ ነሐሴ ፲፬ ቀን የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀንም በልጇ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስልጣን፣ እንደ ልጇ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤያችን በኩር ሆኖ በሞተ በሦስተኛው  ቀን ሙስና መቃብርን (የመቃብርን ሥልጣን) አጥፍቶ ሞትን ድል አድርጎ በገዛ ሥልጣኑ ተነሥቷል፡፡ እናቱ እመቤታችንም በልጇ ሥልጣን፤  እንደ ልጇ ትንሣኤ (ከመ ትንሳኤ ወልዳ ) በሦስተኛው ቀን ተነሥታ ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳትጠብቅ በክብር ዐርጋለች፡፡ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ የክብርና የሕይወት ትንሣኤ ሲሆን ሁለተኛ ሞትን አያስከትልም ትንሣኤ ዘጉባኤንም አይጠብቅም፡፡

“አይዞህ! አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃልና ደስ ይበልህ!” (ድንግል ማርያም)

ይህ ቃል እመቤታችን ለሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የተናገረችው ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ወንጌለ መንግስትን ሲሰብክ ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ ጠፈር ላይ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?›› ብሎ ትንሣኤዋን ባለማየቱ ኀዘን ስለ ተሰማው ከደመናው ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” እንዲል፡፡ እመቤታችንም ‹‹አይዞህ! አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃልና ደስ ይበልህ!›› ብላ ከሙታን ተለይታ መነሣቷንና ማረጓን ለሐዋርያት እንዲነግራቸው አዝዛ የያዘቸውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ ከዚያም እርሷ ወደ ሰማይ ዐረገች፤ እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም ወረደ፡፡ ቅዱስ ቶማስ ትእዛዟን ተቀብሎ በክብር ከተሰናበታት በኋላ ወደ ሐዋርያት ሔዶ እንዳልሰማ እንዳላየ መስሎ ‹‹የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ?›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አግኝተን ቀበርናት›› ሲሉት “አይደረግም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንደምን ይሆናል?” አላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የክርስቶስን ትንሣኤ መጠራጠሩን ጠቅሶ እየገሠፀ መከራከሩንና መጠራጠሩን ትቶ ስለ እመቤታችን መቀበር እነርሱ የሚነግሩትን ዅሉ አምኖ መቀበል እንደሚገባው ለቅዱስ ቶማስ አስረዳው፡፡

“ወንድሞቼ! አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ” (ቅዱስ ቶማስ)

ቅዱስ ቶማስም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ የቅዱስ ጴጥሮስን ተግሳጽ ሲሰማ ቆየ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ተቈጥቶ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለቅዱስ ቶማስ ለማሳየት ሔዶ መቃብሯን ቢከፍት የእመቤታችንን ሥጋ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ደንግጦ ቆመ፡፡ ቅዱስ ቶማስም ‹‹ወንድሞቼ! አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ›› ብሎ እመቤታችን የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ ሰበንም ሊቁ በመልክዓ ማርያም ድርሰቱ “ሰላም ለግንዘተ ሥጋኪ በእደ ሐዋርያት አርጋብ፣ በአፈወ ዕፍረት ቅድው ዘአሣበ ሤጡ ዕፁብ…እመቤቴ ማርያም ሆይ ዋጋው እጅግ ብዙ በሆነና መዓዛው በሚጣፍጥ ሽቱ በሐዋርያት እጅ ለተገነዘው ንጹሕ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡” እንዳለው ቅዱሳን ሐዋርያት ሞገሳቸውን እመቤታችንን ለመቅበር የገነዙበት ነበር፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ በየሀገረ ስበከታቸውም ሕሙማንን ሲፈውሱበትና ገቢረ ተአምርሲያደርጉበት ኖረዋል፡፡ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤ እንደዚሁም አባቶች ካህናት በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ቀጭን ልብስና በራሳቸው ላይ የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፤ቅዱሳን ሐዋርያት ለበረከት ተካፍለውታልና፡፡

“ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” (ቅዱሳን ሐዋርያት)

ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የእመቤታችንን ዕርገት ባየ በዓመቱ ቅዱሳን ሐዋርያት “ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” ብለው ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰባስበው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዋን ይሰጣቸው (ዕርገቷን ያሳያቸው) ዘንድ ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ይዘው ጌታችንን ጠየቁት፡፡ እርሱም ልመናቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፤ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ እመቤታችንንም ሐዋርያትንም አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን ተቀብለዋል፡፡

ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ይሁን፡፡ (ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን)

የእመቤታችንን የትንሣኤና የዕርገት ትምህርት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ኾኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው ሥርዓት ሠርተውልናል (ፍት.ነገ.አን.፲፭)፡፡ ይህ ጾምም ‹‹ጾመ ማርያም (የማርያም ጾም)›› ወይም ‹‹ጾመ ፍልሰታ ለማርያም (የማርያም የፍልሰቷ ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ በጾሙም መጨረሻ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ ይከበራል፡፡ በእመቤታችን የትንሣኤ በዓል ላይ ተንሥአት እሙታን ማርያም ድንግል! ከመ ትንሣኤ ወልዳ ዘልዑል” ማለትም “ድንግል ማርያም ከሙታን ተለይታ ተነሣች! ይህውም ልዑል አምላክ ልጇ እንደተነሳው ትንሳኤ ነው!” የሚለውን የምስራች ቃል ምእመናን ይለዋወጣሉ። ይህ የደስታ መንፈስና ስርአት እንደልጇ ዘመነ ትንሳኤ እስከ ነሓሤ 21 ቀን ድረስ ይቀጥላል። የመልክአ ማርያም ደራሲም ‹‹ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ ደባትረ ብርሃን ኀበ ተተክሉ፤ ለገነተ ጽባሕ በማዕከሉ (እመቤቴ ማርያም ሆይ በምስራቃዊ ተክለ ገነት መካከል የብርሃን ድንኳኖች ወደተተከሉበት ለዐረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል)›› ያለውም ይህንን ያመለክታል፡፡

በጾመ ፍልሰታ  የእመቤታችን ከፅንሰቷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ ይነበባል (ሰዓሊ ለነ ቅድስት/ሰአሊ ለነ ቅድስት)፡፡

በጾመ ፍልሰታ ወቅት በቤተክርስቲያናችን በየቀኑ በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም ማለትም የእመቤታችን ከመፀነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣ ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡ እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ሥጋዌ (ከነገረ ክርስቶስ) እና ከነገረ ማርያም ጋር በማመሣጠር የሚያትተው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤ ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ለተዋሕዶ መመረጧን፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡ የእመቤታችን ንጽህና የነገረ ድህነት፣ የጌታችን ቤዛነት መነሻ፣ መሰረት ነውና፡፡

በጾመ ፍልሰታ ገዳማውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም ሱባዔ ይገባሉ፡፡

በጾመ ፍልሰታ ገዳማውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን አማላጅነት የሰይጣንን ፈተና ድል ለማድረግ እንዲቻላቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፡፡ እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ይህ ጾም ለእመቤታችን ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት በአብዛኛው ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ጌታችን በስሙ ሁለትም ሦስትም ኾነን ለጸሎትና ለመልካም ሥራ ብንሰባሰብ እርሱ በመካከላችን እንደሚገኝ የገባልንን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ (ማቴ. ፲፰፥፳)፣ ሁላችንም በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት በጌታችን፣ በእመቤታችንና በቅዱሳን ሐዋርያት ስም በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመማር ባሻገር ብንጾም፣ ብንጸልይ፣ ብናስቀድስ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ደሙን ብንቀበል በበረከት ላይ በረከትን፤ በጸጋ ላይ ጸጋን እናገኛለን፡፡ በኋላም ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንችላለን፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው በቤተክርስቲያናችን በፆመ ፍልሰታ በተለየ መልኩ ከሚነበቡ፣ ከሚተረጎሙ ቅዱሳት መጻሕፍት አንዱ ውዳሴ ማርያም ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ከደግነቱ የተነሳ እመቤታችን ተገልጣለት ውዳሴ ማርያምን ደርሶ አመስግኗታል፡፡ ምስጋናውም በሰባቱ ዕለታት የተከፈለ ፷፬ ምዕራፎች ያሉት ነው፡፡ ፷፬ መሆኑም እመቤታችን በዚህ ምድር በሥጋ የኖረችበትን ዘመን ያጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ደግሞ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ “ሰዐሊ ለነ ቅድስት/ሰአሊ ለነ ቅድስት” (ቅድስት ሆይ ለምኝልን) የሚለውን ጨምሮበታል፡፡ ሰዐሊ ለነ ቅድስት ተብሎ በዐይኑ ‘ዐ’ ሲጻፍ አዕምሮውን ለብዎውን (ማስተዋሉን) ሳይብን አሳድሪብን ማለት ነው፡፡ ሰአሊ ለነ ቅድስት ተብሎ በአልፋው ‘አ’ ሲጻፍ ለምኝልን ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከታወቁ የሕግ ምንጮች ከቅዱሳን አባቶቻችን በተማረችው መሰረት “ሰዐሊ ለነ ቅድስት/ሰአሊ ለነ ቅድስት” እያለች እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ትለምንልን ዘንድ በጸሎትና በምልጃ ታሳስባለች፡፡

እኛም የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ በማሰብ ከልጇ ከወዳጇ የሚገኘውን ጸጋና በረከት ተስፋ በማድረግ የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን ፈለግ ተከትለን በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን፤ የምንችል ደግሞ ንስሐ ገብተን አስቀድሰን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንቀበላለን፡፡ ነገር ግን በሕግ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ በዚህ ወቅትም ኾነ በሌላ ጊዜ ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉ ወጣቶች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም አረጋውያንና ሕፃናት ብቻ ሳይኾኑ ወጣቶችም ጭምር የመቍረብና የመዳን ክርስቲያናዊ ተስፋ እንዳለን በመረዳት ራሳችንን ገዝተን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ አምላካችን በማይታበል ቃሉ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ፤ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው›› በማለት ተናግሯልና (ዮሐ. ፮፥፶፬)፡፡የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን፡፡ ጽንዕት በድንግልና፣ ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን፣ አዕምሮውን ለብዎውን ሳይብን አሳድሪብን፡፡

ምንጭ፡- ነገረ ማርያም፣ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ መልክአ ማርያም፣ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገፅ

 

 

መባ ስለሚያገቡ ሰዎች ጸልዩ: ጸሎት በገንዘብ አይሸጥም!

ምክንያተ ጽሕፈት

በዕለተ ሰንበት በአንዲት ቤተ ክርስቲያን አንድ ቅን ካህን ከቅዳሴና ትምህርት በኋላ መልእክት ለማስተላለፍ ተነሱ። ካህኑ በሚያገለግሉበት ደብር ያለውን የገንዘብ እጥረት በሚመለከት ከተናገሩ በኋላ ሰበካ ጉባኤውንና የደብሩን ካህናት ለማሳሰብ እንዲህ አሉ “ሁሉም ደብር ገቢውን የሚያሳድገው ምዕመናን በቅዳሴ ጊዜ ስማቸው እንዲጠራ የተወሰነ ገንዘብ እንዲከፍሉ በማድረግ ነው።” የእኒህ ካህን ንግግር በዘመናችን ጸሎትን እንደሸቀጥ የማየት አስተሳሰብና ተግባር የወለደው ነው። በተለይም ነውር በሚንቆለጳጰስባቸው፣ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ከምዕመናን መንፈሳዊ ሕይወት ይልቅ በቤተ ክርስቲያን ስም ለሚገነቧቸው ገቢ ማስገኛ ፎቆችም ሆነ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኖች በሚጨነቁባቸው ቦታዎች የተጀመረና በብዛት እየተዛመተ የመጣ ወፍ ዘራሽ ልማድ ነው።

ከዚህም ጋር በሚመሳሰል መልኩ  “አባቶች እንዲጸልዩላችሁ ስመ ክርስትናችሁን ስጡን” በማለት ከምዕመናን ገንዘብ ለመቀበል ጸሎትን መደለያ የሚያደርጉ አካላት ብዙዎች ናቸው። ይህ ጸሎትን በገንዘብ የሚተምን ሲሞናዊ ልማድ በቅዱሳት መጻሕፍት የተወገዘ ነው። ይሁንና በጥቅም ሰንሰለት የተያዙ ወይም “ስንት ችግር እያለ ስለዚህ ለምን እንጨነቃለን?” በሚል ስንኩል አመክንዮ ይህን ክፉ ልማድ የሚያበረታቱ፣ በተዛባ አስተምህሮ የሚደግፉ፣ እንዲሁም በዝምታ የሚያልፉ ካህናትና መምህራን ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። ስለሆነም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር በቅዳሴ ጊዜ በሕይወት ያሉ ሰዎችን “ስም ለማስጠራት” ስለሚከፈል ክፍያ፣ “አባቶች እንዲጸልዩላችሁ ስመ ክርስትናችሁንና መባችሁን ስጡን” ስለሚሉት ሰዎችና ከእነዚህ አዳዲስ ልማዶች የተነሳ ጸሎትን ለውዳሴ ከንቱ ማስገዛት የሚፈጥረውን የአስተምህሮ መፋለስና የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ድቀት እንዳስሳለን። ምዕመናንም እውነተኛውን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ብቻ እንዲከተሉ ለማስገንዘብ እንሞክራለን።

ጸሎት የጽድቅ መሰላል ናት!

ጸሎት የእምነት መገለጫ፣ የልጅነት ማረጋገጫ፣ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝባትና ጸጋ እግዚአብሔር የሚገኝባት የጽድቅ መሰላል ናት። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ ብፁዓን ትምህርቱ ስለ ጸሎት ሲያስተምር “በምትጸልዩበትም ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ፣ እነርሱ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በአደባባይ ማዕዘን መቆምንና መጸለይን ይወዳሉና፣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።” (ማቴ 6:5) በማለት የተናገረው ጸሎት ለታይታ መደረግ እንደሌለበት ያስረዳናል። ከቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት መጻሕፍት አንዱ ፍትሐ ነገሥት አንቀጸ ጸሎትን የሚጀምረው የጸሎትን መንፈሳዊ ትርጉም በግልፅ በማስቀመጥ ነው። “ጸሎትሰ ይእቲ ተናግሮተ ሰብእ ኀበ እግዚአብሔር ልዑል።/ጸሎትስ ሰው ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የሚነጋገራት ነገር ናት።” (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 14)

ጸሎት በግልም በማኅበርም (በኅብረትም) ሊፈጸም ይችላል። ከግል ጸሎት ይልቅ የማኅበር ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ነው። በኃጢአት የተመሰለ ቅጽረ ኢያሪኮን (የኢያሪኮን ግንብ) ያፈረሰው በእምነት የቀረበ የማኅበር ጸሎት ነው (መጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ 6)፣ ቅዱሳን ሐዋርያትም የሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የከበረችበትን የበዓለ ጰራቅሊጦስ በረከት የተቀበሉት በኅብረት ጸሎታቸው ዝግጁ ሆነው በመጠበቃቸው ነበር።  (የሐዋርያት ሥራ 1:14 እና 2:1-4)። ከማኅበር ጸሎቶች ሁሉ የከበረው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ለምዕመናን የሚታደልበት ጸሎተ ቅዳሴ መሆኑን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ያስረዳናል። ጸሎተ ቅዳሴ ዋነኛ ዓላማው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በስሙ ላመኑ ካህናትና ምዕመናን ለማደል ነው። ጸሎተ ቅዳሴ የማይነካው  ጸሎት የለም ማለት ይቀላል። በጸሎተ ቅዳሴ ከሚጸለዩ ጸሎቶች አንዱ “ጸሎት በእንተ እለ ያበውኡ መብአ/ መባ ስለሚያስገቡ ሰዎች የሚጸለይ ጸሎት” ነው። ለዚህ ጽሁፍ ዓላማ  “መባ” የሚለው ቃል በልዩ ልዩ መልክ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምዕመናን የሚሰጧቸውን ንዋየ ቅድሳት፣ ገንዘብና ሌሎች ቁሳቁሶች ያጠቃልላል።

ትክክለኛ የመባ ጸሎት

በጸሎተ ቅዳሴ ንፍቁ ዲያቆን “ጸልዩ በእንተ እለ ያበውኡ መባአ” (መባ ስለሚያገቡ ሰዎች ጸልዩ) በማለት ካህናትና ምዕመናን በአንድነት ለቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ መባ ስለሚሰጡ ሰዎች እግዚአብሔር መባቸውን ይቀበል ዘንድ እንዲጸልዩ ያሳስባል። ካህናትና ምዕመናንም በአንድነት “ተወከፍ መባኦሙ ለአኃው፣ ወተወከፍ መባኦን ለአኃት፣ ለነኒ ተወከፍ መባአነ ወቁርባነነ” (የወንድሞችን መባ ተቀበል፣ የእህቶቻችንንም መባ ተቀበል፣ የእኛንም መባችንንና ቁርባናችንን ተቀበል) ብለው በዜማ ይጸልያሉ። በዚህም ጊዜ መባ ስለሚያገቡ ሁሉ በኅብረት፣ በአንድነት ይጸለይላቸዋል። በየስማቸው ለይቶ የሚያውቃቸው እግዚአብሔርም የጸሎቱን ፍሬ ያደርግላቸዋል። ለማንም በስም ተለይቶ የሚጸለይ ጸሎት አይደለም።

እንደ ንፍቁ ዲያቆን፣ ንፍቁ ካህንም በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ ጸሎተ ቡራኬን በሚጸልዩበት ጊዜ “አምላካችን ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ዋጋቸውን ይከፍላቸው ዘንድ እጣንና ቍርባን ወይንና ሜሮን ዘይትም መጋረጃም የንባብ መጻሕፍቶችን የቤተ መቅደስንም ንዋያት በመስጠት የሚያገለግሉትንም ባርክ።” ይላሉ። በተጨማሪም ካህናት በሐዋርያት የመባ ጸሎት “ሁሉን የሚይዝ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን እንማልዳለን። ከሁሉ በላይ በምትሆን በከበረች በአንዲት ቤተ ክርስቲያን መባ ስለሚያገቡ፣ መስዋዕቱን፣ ቀዳምያቱን፣ ከአሥር አንዱን የመታሰቢያ ምስጋና ብዙውንና ጥቂቱን የተሰወረውንና የተገለጠውን ይሰጡ ዘንድ ሲወዱ የሚሰጡት ከሌላቸው ላይ ፈቃዳቸውን ተቀብሎ መንግስተ ሰማያትን ይሰጥ ዘንድ ለሁሉ በረከትን የሚያድልበት ስልጣን ገንዘቡ የሚሆን አምላካችን እግዚአብሔር።” በማለት ይጸልያሉ። በተመሳሳይ መልኩ በቅዳሴ ባስልዮስ ካህኑ “አቤቱ ይህን ቍርባን (መባ) ያመጡልህን ስለነርሱ ያቀረቡላቸውንም አስብ…ከነርሱ ዘንድ ላቀረቡትም ሁሉ በሰማይ ያለ ዋጋቸውን ስጣቸው ያንድ ልጅህ ትእዛዝ ይህ ነውና፣ ከጥንት ጀምሮ ያገለገሉህ ቅዱሳንህን እናስብ ዘንድ።” (ቅዳሴ ባስልዮስ ቁጥር 68-70)

በእነዚህና በመሳሰሉት የጸሎተ ቅዳሴ ክፍሎች መባ ስለሚያገቡ ሁሉ ይጸለያል እንጅ በስም ተለይቶ እንዲጸለይ የሚያዝ ሥርዓት የለም።  ለቤተ ክርስቲያን መባ ማቅረብ ሁሉም ወደ ቤተ እግዚአብሔር የሚመጣ ምዕመን የሚያደርገው (ሊያደርገው የሚገባ) ምግባር፣ ትሩፋት እንጂ “ስማቸው እንዲጠራ ለሚፈልጉ ሰዎች” ብቻ የሚተው አይደለም። መባ ማቅረብን “ስምን ለማስጠራት የሚከፈል ስጦታ” አስመስሎ የሚያቀርብ አሰራር ጌታችን በወንጌል “እውነት እላችኋለሁ፣ ዋጋቸውን ተቀብለዋል” (ማቴ 6:2) በማለት ያወገዘውን ግብር መድገም ይሆንብናል።

የማይገባ የመባ ጸሎት

የጸሎት ዓላማ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ማገናኘት እንጂ እወደድ ባይ “ስማቸው በሰዎች ፊት እንዲጠራላቸው” የሚፈልጉ ሰዎችን ፈቃድ መፈፀም አይደለም። “እንደ ግብዞች ለሰው ይታዩ ዘንድ” (ማቴ 6:5) የሚደረግ ጸሎትም ሆነ መባ የተወገዘ ነው። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጸሎተ ቅዳሴና መሰል የማኅበር ጸሎቶች “ስማችሁ በጸሎት እንዲጠራ ይህንና ያንን ክፈሉ” የሚሉና ለዚያም ገንዘብ የሚተምኑ ካህናት እየታዩ ነው። ይህ ለጸሎት ገንዘብ የመተመን ክፉ ልማድ በሌሎች የእምነት ድርጅቶች የተለመደና ምንደኞች ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እያስገቡት ያለ ዘመን አመጣሽ እንክርዳድ ነው።

ቤተ ክርስቲያን በጸሎተ ቅዳሴ በስም ለይታ መታሰቢያ የምታደርግላቸው በሞተ ሥጋ የተለዩትን ነው። ንፍቁ ካህን በጸሎተ ቅዳሴ ጸሎተ ቡራኬን ሲጸልይ “አምላካችን ሆይ በቀናች ሃይማኖት ሆነው ያንቀላፉትንና ያረፉትን ያባቶቻችንንና የወንድሞቻችንን የእኅቶቻችንንም ነፍስ አሳርፍ።” ይላል። መጽሐፈ ቅዳሴም “እዚህ ላይ የሞቱትን ስም ያንሳ” ይላል። በሞተ ሥጋ የተለዩንን ወገኖቻችንን መታሰቢያ (ተዝካር) ስናደርግላቸው ካህኑ ስማቸውን ያነሳል። ስማቸው የሚነሳውም በሞተ ሥጋ ቢለዩም በክርስትና ኅብረት አንድ ላይ መሆናችንን ለማሳየት “መዋዕያነ ዓለም አንትሙ፣ ሰዓሉ ቅድመ ፈጣሪ/ዓለምን ያሸነፋችሁ (ከዚህ በኋላ ለዘለዓለም በሕይወት የምትኖሩ፣ ሞት የማያገኛችሁ) እናንተ ስለ እኛ ጸልዩ” እያልን በጸሎታቸው እንማጸናለን። በሕይወተ ሥጋ ላሉ ሰዎች ግን ስለ መባቸው በጸሎተ ቅዳሴ የኅብረት ጸሎት ይደረግላቸዋል እንጂ “ስማቸውን አንሱ” የሚል ሥርዓት የለንም።

መባ የሚያገቡትን በጸሎተ ቅዳሴ በስም ለይቶ መጥራት በቆየው የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያልነበረ የቅርብ ጊዜ ልማድ መሆኑን ከልምድም ከመጽሐፈ ቅዳሴ ንባብም መረዳት እንችላለን። ይህ ከሆነ ገንዘብ እየተመኑ “በጸሎት ስምን ማስጠራት” ምን አመክንዮአዊ መሰረት አለው? ይህን ልማድ የሚያስፋፉ ሰዎች ሊያነሷቸው ከሚችሉ መከራከሪያዎች አንዱ “መባ ስለሚያገቡ ሰዎች መጸለይ የሚገባ ከሆነ ስማቸው መጠራቱ ምን ችግር አለው?” የሚለው ነው። “የሚጠራውም ዓለማዊ ስማቸው ሳይሆን ስመ ክርስትናቸው ስለሆነ ለውዳሴ ከንቱ አያጋልጥም” ሊባል ይችላል። እውነትም ስመ ክርስትና ውዳሴ ከንቱን ይቀንሳል። ይሁንና በአንዳንድ ቦታዎች “እነ እገሌኮ ማሰቀደሻ እየከፈሉ ስማቸውን ያስጠራሉ” የሚል ሽንገላን የሚጠቀሙ አሉ። በግልፅም በስውርም መባ ስለሚያገቡት ሁሉ  በአንድነት የሚጸለየውን ጸሎት አቃለው በልዩ ክፍያ ስም ለመጥራትም ለማስጠራትም የሚባክኑ ሰዎች “ጸሎት በእንተ እለ ያበውኡ መባአ/መባ ስለሚያገቡ ሰዎች የሚጸለየውን ጸሎት” ባለማወቅ ያቃልሉታል። እምነት እንደሌለው ሰው ሆነው ለራሳቸው ማጽናኛ በመፈለግ ከምዕመናን አንድነት ሳይታወቃቸው ይለያሉ።

ቤተ ክርስቲያንን መነገጃ አድርገው የሚያስቡ፣ አገልግሎቷም ግንብ መገንባትና የምንደኛ ካህናትንና ምዕመናንን የማይጠግብ ኪስ መሙላት የሚመስላቸው ሰዎች ከገንዘብ ስብሰባ ጋር የተገናኘ ማምታቻቸውን የሚሞግት ማንኛውንም አስተያየት መስማት እንደማይፈልጉ የታወቀ ነው። ስለሆነም ጸሎትን በገንዘብ የሚተምኑበትን “ወፍ ዘራሽ ልማድ” ለመከላከል (ትክክል ለማስመሰል) የማይሄዱበት ርቀት የለም። ለዚያ ሲሉ ቅዱስ ወንጌልን ያጣምማሉ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በልካቸው ይሰፋሉ፣ ውዳሴ ከንቱን ለገቢ ማስገኛ በሚል ያስፋፋሉ። ለማሳመኛ የሚነሱት ነጥቦች ግን ከቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ ጋር በግልፅ ይጋጫሉ፣ አመክንዮአዊ መሠረታቸውም በጣም የደከመ ነው። ከሚቀርቡት ማሳመኛዎች የሚበዙት በራሳቸው አዲሱን ክፉ ልማድ የሚመለከቱ ሳይሆኑ ለማደናገር በማሰብ ከሌሎች የተለየ አፈፃፀም ካላቸው የመባም ሆነ በችግር ላይ ላሉ ምዕመናን ከሚደረግ ጸሎት ጋር ያምታቱታል። ለዚህም ማሳያ እንዲሆነን የሚከተሉትን የሚገቡ ጸሎቶች ከገንዘብ መሰብሰቢያው ጸሎትን ሸቀጥ የማድረግ ልማድ ለይተን ለማሳየት እንሞክራለን።

መባ ለሚያገቡ ሰዎች መባውን በሚቀበለው ካህን የሚደረግላቸው ጸሎት

ለቤተ ክርስቲያን መባን መስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው። መባ በመስጠታችንም ውዳሴና ሙገሳ መጠበቅ የለብንም። ምዕመናን ለቤተ እግዚአብሔር የሚሆነውን ልዩ ልዩ መባ በስውርም በግልፅም መስጠታቸው የሚገባ ነው። በቤተ ክርስቲያናችን የቆየ ክርስቲያናዊ ትውፊት መባ የሚሰጥ ሰው ቤተ ክርስቲያንን ወክሎ መባውን በሚቀበለው ካህን ፊት በትህትና ራሱን ዝቅ አድርጎ እግዚአብሔር መባውን እንዲቀበልለት ይጸለይለታል። ያለ ከንቱ ውዳሴ በቅንነት የሚቀርብ መባ ኃጢአትን የሚያስተሰርይ፣ ቤተ ክርስቲያን በተሰጣት ጸጋ ከምታቀርበው ሰማያዊ አምሃ ከቅዱስ ቁርባን ጋር ቅድመ እግዚአብሔር የሚደርስ ስለሆነ መባውን የሚሰጠው ምዕመን በካህኑ ጸሎት ተማጽኖ “አቡነ ዘበሰማያት” ይቀበላል/ይጸልያል። ይህ ጸሎት ምንም ከንቱ ውዳሴ የለበትም። የሚጸለየውም በግል ካህኑና መባ አቅራቢው ባሉበት እንጂ በአዋጅ፣ በጭብጨባ አይደለም። ስለሆነም ገንዘብ ተምነው “ስም ለማስጠራት” ከሚያደርጉት ክፉ ልማድ ጋር መምታታት የለበትም።

በተለይም ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የክህነትና የወንጌል ሰባኪነት አገልግሎት ከድለላና ምዕመናንን በማጭበርበር ገንዘብ ከመሰብሰብ “ችሎታ” ጋር የተምታታባቸው ብዙዎች ናቸው። “ጨረታ እናጫርታለን፣ በማነቃቃት ምዕመናን ገንዘብ እንዲሰጡ እናደርጋለን፣ ምርቃት እንመርቃለን” እያሉ በየዐውደ ምሕረቱ፣ በየማኅበራዊ ሚዲያው ለተለያዩ በጎም ሆነ በግልፅ የማይታወቁ ዓላማዎች ገንዘብ መሰብሰብ የተለመደ ነው። ምዕመናን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በልግስና ቢሰጡ መልካም ነው። ይህንንም የሚያስተባብሩ ግልፅ አሰራርና ተጠያቂነት ያላቸው ካህናትም ሆኑ ምዕመናን መኖራቸው መደበኛ የሆኑትን የቤተ ክርስቲያን አካላት ማገዝ እንደሚችሉ ይታወቃል። ይሁንና ምዕመናን ልዩ ልዩ መባ የሚሰጡት አምነውበት፣ ለጽድቅ በሚበጅ ግልፅ አሰራር እንጂ ኮሚሽን በሚቆረጥለት፣ የግለሰቦች “ገንዘብ የመሰብሰብ ጸጋ” እየተባለ ደርዝ የሌለው ከንቱ ውዳሴ በሚዘንብበት፣ “ምርቃት” በገንዘብ የሚሸጥ በሚመስልበት የአጭበርባሪዎች መንገድ አይደለም። መባ ስለሚያገቡ ሰዎች በካህን የሚደረግ ጸሎት ኢያቄምና ሐና የተወደደች ልጃቸውን ድንግል ማርያምን እንደ ስዕለታቸው ለቤተ መቅደስ በሰጡበት ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ ያደረገውን ዓይነት ከንቱ ውዳሴ የሌለበት ጸሎት እንጂ “ለማነቃቃትና” ለማጭበርበር የሚግተለተል የአስመሳዮች የሽንገላ ምርቃት መሆን የለበትም። ስለሆነም ምዕመናን መባቸውን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ለማግኘት በቅንነት ሊሰጡ ይገባል እንጂ “ታዋቂ፣ ብዙ ተከታይ ያላቸው” በሚባሉ የዐውደ ምሕረት ደላሎችን ፊት የሽንገላ ውዳሴና ምርቃትን ሊናፍቁ አይገባም።

በልዩ ልዩ ችግር ላሉ ምዕመናን የሚደረግ ጸሎት

ቤተ ክርስቲያን የምዕመናን እናት ናት። እናት ለልጆችዋ እንደምትጨነቅ ቤተ ክርስቲያንም በልዩ ልዩ ችግር ውስጥ ላሉ ልጆቿ ትጸልያለች። እናት ልጆቿን በእናትነት በሰጠቻቸው በቁልምጫ ስማቸው እንደምትጠራቸው ቤተ ክርስቲያንም በጸሎት የምታስባቸውን ልጆቿን በስመ ጥምቀታቸው (በክርስትና ስማቸው) እየጠራች በችግራቸው ጊዜ ሁሉ ትጸልይላቸዋለች። የመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ሃይማኖቱ በታሠረ ጊዜ እንደጸለየችለት (ሐዋ 12:5)፣ ጸሎቷም ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ የቅዱስ ጴጥሮስን የእሥር ሰንሰለት የሚፈታ መልአክ እንደተላከለት ዛሬም በቤተ ክርስቲያን የሚደረግ ጸሎት ቅድመ እግዚአብሔር ይደርሳል፣ የተቸገሩትን ይረዳል።  ነገር ግን የተቀደሰውን ጸሎት እንደ ሸቀጥ በገንዘብ መተመንና “በችግራችሁ ጊዜ ስማችሁን እየጠራን እንድንፀልይላችሁ ይህንና ያን ክፈሉ” እያሉ ማምታታት የቤተ ክርስቲያንን ቅን አገልግሎት ጥላሸት የሚቀባ ነውር እንጂ ሌላ ስም የለውም። ለተቸገረው ያለ ዋጋ የምትጸልይ እንጂ ጸሎትን መደራደሪያ የምታደርግ ቤተ ክርስቲያን ከአባቶቻችን አልተቀበልንም።

በ2002 ዓ.ም. በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በወቅቱ አዲስ ከተቋቋመች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ጋር ሲወያዩ የተናገሩት አባታዊ መልዕክት ከእውነተኛ አባቶቻችን የተቀበልናትን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የምታጸና ናት። ይቅርና በውጭ ሀገር በሀገር ቤትም ቢሆን አዲስ ደብር መትከል ከባድ የገንዘብ ወጭ እንደሚጠይቅ ይታወቃል። ሰይጣንም በገንዘብ እጥረት እያሳበበ አብያተ ክርስቲያናትን ከሚያስተምሩት ወንጌል እንደሚለያቸው ከልምዳችን ተረድተናል። ያላቸውን ሁሉ ሰጥተው አዲስ ደብር ለመትከል የሚፋጠኑ አገልጋዮችም ወደ አባታችን ቀርበው ለክርስትናና ለፍትሃት ምን ያክል ማስከፈል እንዳለባቸው ለማማከር ጠየቋቸው። አባታችን አቡነ ጴጥሮስ ሲመልሱ እንዲህ አሏቸው “አይ ልጆቼ! አሁን በዚህ ቦታ ክርስትና ከሚነሳና ፍትሃት ከሚያስደርስ ምዕመን ገንዘብን መሰብሰብ ትፈልጋላችሁ? ብንችልስ እኛ እየከፈልን የጠፋው ሁሉ እንዲመለስ፣ በሥጋ የተወለደው ሁሉ ድጋሚ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያለ ዋጋ እንዲወለድ፣ የሞቱት ምዕመናን ሁሉ በጸሎተ ፍትሃት እንዲታሰቡ ማድረግ አለብን።” አሏቸው። ይህም አባታዊ ትዕዛዝ ብዙዎችን አሳምኖ አቡነ ጴጥሮስ ይህን ትምህርት ባስተማሩበት ቦታ ገንዘብ ተምኖ “ይህን ካልከፈላችሁ ክርስትና ማስነሳት፣ ፍትሃት ማስፈታት አትችሉም” የሚል ሲሞናዊ እንዳይኖር፣ ቢኖርም እንዳያድግ አደረገ። ይህን መሰል መልካም ዘር በተዘራባት እርሻ፣ በቅድስት ቤተክርስቲያን ጸሎትን በገንዘብ ተምኖ “የሚሸጥ”፣ ምዕመናንንም ሳይረዱት ከጽድቅ ጎዳና አውጥቶ በውዳሴ ከንቱ ጠልፎ የሚጥል እንክርዳድ ከየት መጣ? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት እንደተናገረው “ጠላት ሰው ይህን አደረገ”። (ማቴ. 13:28)

በረከት በማስመሰል አይገኝም!

“የክርስትና ስማችሁ በቅዳሴ እንዲጠራ መባ ስጡ” የሚሉት ሰዎች በምዕመናን ደካማ ጎን በመግባት የመባ ጸሎትንም ሲያሻሽሉ ታዝበናል። ከዚህም የተነሳ በአንዳንድ አጥቢያዎች “ስም ለማስጠራት የሚከፈለውን ዓመታዊ ወጭ” ከፍለው ስማቸውን በምድር እያስጠሩ ከሰማይ መዝገብ የሚያስፍቁ የዋሀን ይታያሉ። አንዳንዶቹም ከፍለው ያገኙት “ስምን የማስጠራት መብት” ምድራዊ ገንዘባቸውን የሚጠብቁበት መድኅን ይመስላቸዋል።  ከላይ እንደተገለጸው የቤተ ክርስቲያን ትክክለኛ የመባ ጸሎት መባ ያቀረበውን ምዕመን ከቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አንድነት የሚደምር እንጂ ምድራዊ በረከትን የሚለምን አይደለም። ይሁንና የጸሎትን ይዘት ለጥቅማቸው የሚቀይሩ ሰዎች በፈጠሩት ልማድ ስማቸውን ለሚጠሩላቸው ባለጸጎች የሚፀልዩት መጤ ጸሎት “ቤታቸውን በበረከት ሙላላቸው፣ ባለጸግነታቸውን ጠብቅ” የሚል ይዘት ያለው ነው። እግዚአብሔር ቸር መጋቢ ነው። ለደሃውም ለባለጸጋውም ያለመከልከል የሚሰጥ የማያልቅበት ሰጭ ነው። መባ ለሚሰጡም  በረከትን እንደሚሰጥ የታመነ ነው። ነገር ግን በማስመሰል ጸሎት ከንቱ ውዳሴ የሚፈልጉ ባለጸጎችን እንጂ እግዚአብሔርን ማታለል አይቻልም። በረከት በማስመሰል አይገኝምና።

መባ ስለሰጠን ይጸለይልናል እንጂ እንዲጸለይልን መባ አንሰጥም!

መባ ስለሰጡት ቤተ ክርስቲያን እንደምትጸልይ፣ ጸሎቱም ውዳሴ ከንቱን ከሚያመጣ ልማድ የተለየ መሆኑን አይተናል። በሌላ በኩል ደግሞ “አባቶች በጸሎት እንዲያስቧችሁ ስመ ክርስትናችሁን አምጡ” የሚል ልማድ እየተስፋፋ ነው። ከላይ እንደተገለጠው ቤተ ክርስቲያን ከጸሎት የከበረ ስጦታ የላትም። መባ ስለሚያገቡት ሁሉ የምታደርገው ጸሎትም በረከትን ያሰጣል። ምዕመናንንም የምታውቃቸው በስመ ጥምቀታቸው ስለሆነ መባ ስለሚያገቡት ለመጸለይ ስመ ክርስትናቸውን መያዝ ክርስቲያናዊ ትውፊት ነው። ይሁንና በጸሎት የሚነግዱ “አገልጋዮች” በማስመሰል የሚሄዱበት አካሄድ ምዕመናን እንዲጸለይላቸው መባ እንዲሰጡ በመገፋፋት የበረከትን በር ይዘጋል። በቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ፣ በቤተ ክርስቲያንም ትውፊት መባ ስለሰጠን ይጸለይልናል እንጂ ጸሎት እንዲጸለይልን መባ አንሰጥም። እንዲጸለይልኝ ብሎ መባ መስጠት “የእግዚአብሔርን ጸጋ በገንዘብ ለመግዛት” በማሰቡ ቅዱስ ጴጥሮስ “ገንዘብህ ከአንተ ጋር ይጥፋ።” ብሎ የረገመውን ሲሞን የተባለውን ጠንቋይ መምሰል ነው። (ሐዋ. 8:8-25)

ምዕመናን መባ በመስጠታችን የምንጠቀመው በእግዚአብሔር ፊት የቀና ልብ ይዘን ስንቀርብ እንጂ በስሌት አስተሳሰብ ጸሎትን በመባ ለመግዛት በሚያስብ ሲሞናዊ አካሄድ መሆን የለበትም። እንዲጸለይላችሁ “ስመ ክርስትናችሁን ስጡን” በሚል ማነቃቂያ ገንዘብ ከሚሰበስቡ ሰዎች እንኳ ምን ያህሉ ገንዘብ ለመሰብሰብ ሲሉ ቃል የገቡትን ጸሎት እንደሚያደርጉ እግዚአብሔር ይወቅ! ይበልጥ የሚያሳዝነው በጎ ያደረጉ መስሏቸው ይህንን ልማድ ያስፋፉ ሰዎች ምዕመናንን እንደሚሸለቱ በጎች ለሚቀራመቱ ሀሰተኛ ካህናትና መምህራን አጋልጠው መስጠታቸው ነው። ዛሬ ጸሎትን በገንዘብ የሚተምኑ፣ የማይራሩ ሰዎች ራሳቸውን “ሰባኬ ወንጌል፣ ባህታዊ፣ አጥማቂ፣ የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጅ” እያሉ የሚጠሩና የሚያስጠሩ በየቦታው በምዕመናን ላይ የሚያደርሱትን በደል ማየት ያሳምማል። በሐሰተኞች ወይም አርቀው በማያዩ ቅን አገልጋዮች ጉትጎታ እንዲጸለይለት መባ መስጠትን የተለማመደ ምዕመን የጨካኞች መረብ ውስጥ መውደቁ የሚደነቅ አይደለም።

ማጠቃለያ

ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መባን መስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው። በቅንነት የምናቀርበውን መባችንን በምድር ካህናት፣ በሰማይ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ይቀበሉናል። ቤተ ክርስቲያንም መባ ስለሚያገቡ ሰዎች ትጸልያለች። ይሁንና መባ መስጠት ከቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚደምረን፣ ከሚያርገው መሥዋዕተ እግዚአብሔር የሚያሳትፈን የትህትና አገልግሎት እንጂ በዘመናችን እየተለመደ እንደመጣው ክፉ ልማድ “በቅዳሴ ጊዜ ስማችንን ለማስጠራት” ወይም “አባቶች እንዲጸልዩልን” የምንሰጠው ቀብድ አይደለም። በቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ መጻሕፍት ከምዕመናን መካከል በስም ተለይተው የሚጸለይላቸው በዕለቱ መታሰቢያ የሚደረግላቸው በሞተ ሥጋ የተለዩት ናቸው። ይህም የሚደረገው በሞተ ሥጋ ቢለዩንም በአካለ ሥጋና በአካለ ነፍስ ያሉ ምዕመናን አንድነት ከሆነች ኦርቶዶክሳዊት ማኅበር እንዳልተለዩ ለማሳየት ነው። ከዚያ ባሻገር የተለየ ችግር የደረሰባቸውን ምዕመናን በክርስቲያናዊ ልማድ በጸሎት ስማቸውን እያነሱ ማሳሰብ ይገባል እንጂ ገንዘብ ተምኖ “ስማችሁ እንዲጠራ መባ ስጡ” ማለት የለየለት ክህደት ነው። ስለሆነም መባ ስለሰጠን ይጸለይልናል እንጂ እንዲጸለይልን መባ በመስጠት ጸሎትን በገንዘብ በሚተምን ሲሞናዊ ክፋት መተባበር የለብንም። ጸሎት በገንዘብ አይሸጥምና።

ተወከፍ መባኦሙ ለአኃው፣ ወተወከፍ መባኦን ለአኃት፣ ለነኒ ተወከፍ መባአነ ወቁርባነነ። አሜን።

ስብሃት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር።

No comments:

Post a Comment